Print this page
Sunday, 26 September 2021 00:00

ያልተነገሩ የሰሜን ወሎ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 1 ኩንታል ጤፍ እስከ 8 ሺ ብር ይሸጣል - 1 ለምለም እንጀራ በ50 ብር ይሸጣል - ጨቅላ ህፃናት ለቶርቸር አላማ ውለዋል
                    
            በአሸባሪነት የተፈረጀው ህውሓት  በወረራ በያዛቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች፣ እጅግ ዘግናኝ የሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎችን እየፈጸመ መሆኑን በአካባቢው ከላይ ጥናት ያደረገው የወሎ ህብረት ከሰሞኑ  ይፋ አድርጓል።
የወሎ ህብረት ሊቀ መንበር ያሲን መሐመድ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መረጃ፤ በተለይ የህወሃት ሃይሎች በወረራ በያዟቸው የራያ፣ ዋግህምራ ዞንና ሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ላይ 2 ወር ከሁለት ሳምንት በላይ ለሆነ ጊዜ መሰረታዊ የሚባል አገልግሎቶች ሙሉ  በሙሉ መቋረጣቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢው ህክምና፣ መብራት፣ ውሃ፣ አጠቃላይ የጤና ክብካቤና የንጽህና መጠበቂያዎች የሉም ያሉት አቶ ያሲን፤ ህብረተሰቡ ሻማ ገዝቶ እንኳ ለማብራት እንዳይጠቀም ዋጋው የሚቀመስ አይደለም ብለዋል።
የሕብረቱ ባለሙያዎች ባሰባሰቡት መረጃ፣ አንድ ሻማ ከ50 ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን፣  እህል ለማስፈጨት በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው በናፍጣ የሚሰሩ ወፍጮዎችን በማሰስ ጊዜ፣ ጉልበትና አቅማቸውን እንደሚያባክኑ፤ አንድ ኪሎ ጥሬ እህልም  26 ብር በሚገመት  ዋጋ ለሳምንታት ወረፋ ጠብቀው እንደሚያስፈጩ መረዳታቸውን ይገልጻሉ።
“የፋብሪካ እቃዎች ዋጋም በእነዚህ አካባቢዎች የሚቀመሱ አይደሉም፤ ገበሬው ራሱ የሚያመርተው ጤፍ በወራሪው ሃይል መዘረፉን ተከትሎ በገጠር አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 8 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው፤ በዚህያ ላይ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ስለሌለ ሰው በዚህ ዋጋ እንኳ ሸምቶ ለመብላት መቸገሩን ተገንዝበናል” ይላሉ፤ አቶ  ያሲን።
በተለይ በራያ ቆቦ ህዝብ ላይ ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በወራሪው ሃይል እየተፈጸመ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ያሲን፤ የህብረታቸው ባለሙያዎች ከአካባቢው ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት፤ የሸቀጦች ዋጋ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ባልታየ መጠን አሻቅቧል ብለዋል።
በተሰባሰበው መረጃ መሰረት፤ ቀደም ሲል ከ10 ብር ባነሰ ዋጋ ይሸጥ ነበረ አንድ የእጅ ባትሪ ድንጋይ በ100 ብር፣ አንድ ሻማ 50 ብር፣ አንድ ደረቅ (ለምለም) እንጀራ 50 ብር፣ ወፍጮ ማስፈጫ ዋጋ በ1 ኪሎ 26 ብር (ያውም ለሳምንት ወረፋ ተጠብቆ እንዲሁም ከቆቦ ወደ ዋጃ በጋሪ ተጓጉዞ ነው የሚፈጨው)፣ ግማሽ ኪሎ ቡና 1200 ብር፣ 3 ሊትር ዘይት 950 ብር፣ 1 ኪሎ ስኳር 110 ብር፣  ክብሪት ፓኬቱ 50 ብር፣ በርበሬ በኪሎ  400 ብር፣ ሁለት ብር ይሸጥ የነበረው ዳቦ 10 ብር፣ ጥልፍልፍ ጫማ በፊት ከ100 ብር ባነሰ ዋጋ ይገዛ የነበረው 5 መቶ ብር፣ ውሃ አንድ ጀሪካን 20 ብር፣ በፕላስቲክ የታሸገ 1 ሊትር ውሃ 25 ብር፣ ሞባይል ቻርጅ ማስደረጊያ 25 ብር፣ ቤንዚን በሊትር 350 ብር፣ 5 ኪሎ ሩዝ 1800 ብር፣ ትንሿ የእጅ ባትሪ 160 ብር፣ ትራንስፖርት ከቆቦ ዞብል ወልዲያ-ከ150-200 ብር ፣ ከቆቦ -ሃራ 5መቶ ብር (ከአዲስ አበባ ባህር ዳር የነበረው ያህል ዋጋ ማለት ነው)
መሆኑን በመጥቀስ በዚህም የአካባቢው ህዝብ በህይወት የመኖር ህልውናው ፈተና ላይ መውደቁን ህብረቱ አስገንዝቧል።
ወራሪው ሃይል በህዝቡ ላይ እያደረሰ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በተጨማሪ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፈጸመ መሆኑንም አቶ ያሲን ይናገራሉ።
“ወላጆቻችሁ መሳሪያ ደብቀዋል፤ ከቤት አውጡ” በማለት ወላጆቻቸው ወደ ዘመቻ የሄዱባቸውን ታዳጊዎችና ህጸናት ከፍተኛ ስቃይ ፈጽመውባቸዋል። የ1 ዓመት ህፃናትን ከእናቶቻቸው እቅፍ በመንጠቅና ለረጅም ሰዓታት በባዶ ቤት በመደበቅ፣ እናቶቻቸውን “ባለቤታችሁ የደበቀውን መሳሪያ አምጡ” እያሉ ያስጨንቋቸዋል፤ እሳት በማቀጣጠል ጨቅላ ህፃናትን ሁለት እግራቸውን ይዘው ወደ እሳቱ ነበልባል በጭንቅላታቸው ቁልቁል በመያዝ፣ ቤተሰቦቻቸውን የማስጨነቅና የማሰቃየት ተግባር ሲፈፅሙ ቆይተዋል።
“መሳሪያችሁን አምጡ በሚል በተለይ ጉራ ወርቄ በሚባል አካባቢ በርካታ አዛውንቶችንና ትልልቅ ሰዎችን ቤታቸው ውስጥ  በር ዘግተው በእሳት አቃጥለዋቸዋል፤ አርሶ አደሮች በእርሻ ቦታቸው ላይ ሳሉ ቀጥታ ጥይት እየተተኮሰባቸው ተገድለዋል። ብለዋል አቶ ያሲን፡፡
የሕወሃት ወራሪ ቡድን ይህን ግፍ ማበራከቱን ተክትሎ፣ ከነሐሴ 22 ቀን 2013 በኋላ እስከ  ጳጉሜ 5 ድረስ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ወራሪውን ሃይል ባላቸው መሳሪያ መግጠማቸውን፣ በዚህም ወራሪው ሃይል መሸሽ መጀመሩን፣ በዚህ የሽሽቱ ወቅት መንገድ ላይ ያገኛቸውን ሁሉ መጨፍጨፉን የማህበሩ መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህ ሳያበቃ ወደ ከተማ በመግባትም መንገድ ላይ ያገኙትን ሰው በሙሉ በተለይ ጳጉሜ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ሲጨፈጭፉ አምሽተዋል፣ በበነጋው ጳገጉሜ 5 ግድያውንና ጭፍጨፋውን ቀጥለውበት ማንኛውንም በመንገድ ለይ ያገኙትን ሰው ሁሉ ገድለዋል።
በተለይ ዙ-23 የተሰኘውን መሳሪያ በመጠቀም የአርሶ አደሮችን መንደሮች አቃጥለዋል። “በዚህም ሳቢያ በበርካታ መንደሮች የነበሩ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የኔም ቤተሰቦች እድሜቸው ከ3 ዓመት ጀምሮ ያሉ ህፃናት ሳይቀር ተፈናቅለው አግኝቻቸዋለሁ” ይላሉ አቶ ያሲን።
ይሄ ወራሪ ሃይል ቤተ ክርስቲያናትን፣ መስጊዶችን አውድሟል፣ ቅዱሳን ድርሳናትን አቃጥለዋል፤ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ አካባቢውን አጥረው በመጠበቅ ለመመለስ የሚሞክረውን ሁሉ ይገድላሉ። በአጠቃላይ በራያ ቆቦ ህዝብ ላይ ወራሪዎቹ የፈጸሙት ግፍና በደል ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ነው ብለዋል የወሎ ህብረት ሊቀ መንበር።
የአካባቢው አርሶ አደሮች የነበሯቸውን የቤት እንስሳት ሁሉ ወራሪው ሃይል ወስዶባቸዋል፤ ከፊሎቹንም ገድሏል፤ በቀላል ቁጥር የማይገመቱም ከባለቤቶቻቸው  ተነጣጥለው በየጫካው የአውሬ ሲሳይ እንዲሆኑ አድርጓል።
ጳጉሜ 4 እና 5 ብቻ ቡድኑ በቆቦ ከተማ የጨፈጨፋቸውን ሰዎች ብዛት ለመገመት  አዳጋች ነው የሚሉት አቶ ያሲን፤ “አንዳንዶች  6 መቶ፣ 8 መቶ ሲሉ እሰማለሁ፤ ይህ ግን ከተፈጸመው ወንጀል ጋር ሲነጻጸር በጣም ያነሰ ቁጥር ነው። ወራሪው ሃይል ራሱ ጨፍጫፊ ራሱ ቀባሪ በሆነበት ሁኔታ የጭፍጨፋውን መጠን ለመገመት አስቸጋሪ ነው።” ሲሉ ይናገራሉ፡፡
“ከአንድ ቤት ውስጥ ከ5-7 የሚሆኑ የቤተሰብ አባላትን መንገድ ላይ እያወጡ በደካማ እናቶቻቸውና አባቶቻቸው  ፊት ረሽነዋል፤ ወንዶችን በሚስቶቻቸውና በህጻናት ልጆቻቸው ፊት አንበርክከው ረሽነዋል” ይላሉ - የወሎ ህብረት ያሰባሰበውን መረጃ ዋቢ አድርገው ለአዲስ አድማስ ያስረዱት አቶ ያሲን።
እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ህብረቱ የተደራጀ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ አሁንም በወራሪው ሃይል ስር ባሉ የአካባቢው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ ያለ ህዝብ  ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
መንግስት የቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ መሆኑን እንደሚረዱ ነገር ግን እርምጃው ፈጣን መሆን እንዳለበትና ህዝብን የመታደግ ተግባር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።
በራያ እና ሰሜን ወሎ ህዝብ ላይ ስልታዊ ብቻ ሳይሆን  ግልጽ ሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው እየተፈጸመ ያለው ያሉት አቶ ያሲን ይሄን የሰብአዊ መብት ጉዳይ የሚመለከታቸው  ተቋማት ሁሉ የአለም ህብረተሰብ ይህን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲያውቀው ማድረግና ተጨማሪ ህይወት እንዳይጠፋ አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ብለዋል።
የአማራ ክልልና የፌደራል መንግስት ለአካባቢው የሰጡት ትኩረት ቁርጠኝነት የጎደለው መሆኑ የአካባቢውን ህዝብ ቅሬታ ውስጥ እንዳስገባው የሚያወሱት አቶ ያሲን፤ ቢያንስ የተፈናቀሉ  ዜጎችን በመደገፍ ረገድ በቂ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
“ረሃብ ስንት ቀን ይሰጣል?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ያሲን፤ “መንግስት ለምንድን ነው ለዚህ አካባቢና ህዝብ ተገቢውን ትኩረት የነፈገው” በማለት ወሳኝ ጥያቄ ወደ መንግስት ይወረውራሉ። ምላሽ የሚሰጥ ይኖር ይሆን? አስረግጠው ተናግረዋል፡፡


Read 2451 times