Tuesday, 28 September 2021 00:00

ቅዳሜ ሞት የተፈረደባቸው ትራምፕ፤ ማክሰኞ የወንድማቸውን ልጅ በ100 ሚ. ዶላር ከሰሱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ቅዳሜ በየመን የሁቲ ታጣቂዎች፣ ፍርድ ቤት በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ እሳቸው በወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ የወንድማቸውን ፍሬድ ትራምፕን ሴት ልጅና ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣን የከሰሱት ተንኮል በተሞላበት ሴራ የግል የፋይናንስ መረጃዎቼን ያለ አግባብ በመጎልጎል የታክስ ማጭበርበር እንደፈጸምኩ የሚያስመስልና በሃሰት የሚወነጅል ዘገባ ሰርተው ለንባብ አብቅተዋል፤ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊክሱኝ ይገባል በሚል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕ ባለፈው አመት ባሳተመቺው የግል ማስታወሻ መጽሃፍ ላይ የትራምፕ ቤተሰብ በምን መልኩ ሃብት እንዳፈራ የሚያጋልጡ መረጃዎችን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ የቤተሰቡን የግል የፋይናንስ መረጃዎች ለጋዜጣው አሳልፋ ሰጥታለች ተብላ በትራምፕ መከሰሷንና ይህም ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች ሰፊ የምርመራ ዘገባ ዋነኛ መነሻ መሆኑን ሮይተርስ አብራርቷል፡፡
የጋዜጣው ሪፖርተሮች ወራትን በፈጀ ምርመራ ያገኙትን ግላዊ መረጃ በማቀነባበር በሰሩት ሰፊ ዘገባ፣ ትራምፕ በተጭበረበረ መንገድ ከአባታቸው ግዙፍ የሪልስቴት ኩባንያ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በታክስ ተመላሽ መልኩ ተቀብለዋል ሲሉ ማጋለጣቸውን የጠቆመው ሮይተርስ፣ ዘገባውን የሰሩት የጋዜጣው ሶስት ሪፖርተሮች በዚህ ስራቸው በ2019 የታዋቂው ፑልቲዘር ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸውንም አስታውሷል፡፡
ትራምፕ ከ100 ሚሊዮን ዶላሩ በተጨማሪ የወንድማቸው ልጅ ካሳተመቺው መጽሃፍ የሚገኘው ገቢ በሙሉ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤት ባቀረቡት 27 ገጽ ክስ መጠየቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በ2018 በተፈጸመው የአየር ጥቃት ከተገደሉት የየመን ሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት ሃላፊ ሳልህ አል ሳማድ ግድያ ጋር በተያያዘ በሑቲ ታጣቂዎች ፍርድ ቤት በተመሰረተባቸው ክስ ባለፈው ቅዳሜ ከሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር  በሌሉበት ሞት እንደተፈረደባቸው ያስነበበው ቢቢሲ ሲሆን፣ ከእነ ትራምፕ ጋር የተከሰሱ 9 ሰዎች በአደባባይ የሞት ቅጣቱ እንደተፈጸመባቸውና ይህም ውሳኔ ተመድና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በበርካታ አገራት መንግስታት ክፉኛ መተቸቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2675 times