Monday, 10 September 2012 13:46

የብሔራዊ ሐዘን ሥርዓት ደንብ ያስፈልገናል

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሰማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ጠቅላላው የሐዘን ጊዜ እስከተፈፀመበት ጊዜ ድረስ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚፃፃፉባቸው ደብዳቤዎች፣ ኤንቨሎፖችና ወረቀቶች በጥቁር የተከፈፉ መሆን እንዳለባቸው ደንቡ ከማዘዙም በተጨማሪ የሙሉ ሀዘን ወቅት እስኪፈፀም ድረስ የመንግሥት ሬዲዮ ሙዚቃ እንደማያሰማ ያስረዳል፡፡ብሔራዊ የሐዘን ጊዜ፤ ርእሳነ ብሔራት በሞት ሲለዩ ወይም ከፍተኛ እልቂት ያስከተለ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ደንብ ወጥቶለት በየሐገሩ የሚፈፀም ወግና ሥርዓት ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃዘንን የምትፈፅምበት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ያለው ወግና ሥርዓት ነበራት፡፡ ይኼው ወግና ሥርዓት የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲወድቅ አብሮ በመጥፋቱ የተነሳ፣ ላለፉት 37 አመታት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሐዘንን የምታስተናግድበት ደንብና ሥርዓት አልነበራትም፡፡

የአቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም ማለፍ በኦፊሴል ከተሰማ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመላው ኢትዮጵያ የብሔራዊ ሀዘን ጊዜ እንዲሆን እና ሰንደቅ ዓላማችንም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መወሰኑን መንግሥት በመገናኛ ብዙሃን ገልጧል፡፡ ይሁን እንጂ የሀዘን ጊዜው ምን ያህል እንደሚቆይ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማው ለምን ያህል ጊዜ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ አለመታወቁ በዜጐች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል፡፡ ያለፈው የሀገራችን የሐዘን ልማድ ምን እንደሚመስል ለመረዳት እንዲያስችለን የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት የሐዘን ደንብ፣ ወግና ሥርዓት መመልከት ጠቃሚነት አለው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት፤ ብሔራዊ ሐዘን የሚደረግበትን አኳሃን የደነገገ ህገ መንግሥታዊ አንቀፅ የቀረፀ ሲሆን ይህንን የሚፈፅምበትም ደንብ፣ ወግና ሥርዓትም ነበረው፡፡ በ1948 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሕገ መንግሥት፣ በአንቀፅ 18 ላይ ብሔራዊ ሐዘን የሚደረግበትን ሥርዓት አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት የሚደረገው የሐዘን ሥርዓት ሙሉ እና ግማሽ የሐዘን ጊዜ ተብሎ ተወስኗል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በሞት በሚለይበት ጊዜ የሦስት ወር የሙሉ ሐዘን ጊዜ እና የስድስት ወር የግማሽ ሐዘን ጊዜ ይታወጃል፡፡ እቴጌይቱ በሞት በምትለይበት ጊዜ ደግሞ እስከ ሁለት ወር የሚቆይ የሙሉ ሐዘን ጊዜና አራት ወር የሚዘልቅ ግማሽ ሐዘን እንደሚኖር ተገልጧል፡፡ ይህ አንቀፅ በመቀጠልም ሌሎች የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ ዘመዶች በሞቱ ጊዜ ለነሱ የሚደረገውን ሐዘን ንጉሠ ነገሥቱ እንደሚያውጅ ጠቁሞ፤ አልጋ ወራሹ ዘውድ የሚጭንበት ጊዜ በሙሉ ወይም በግማሽ ሐዘን ወቅት የሆነ እንደሆነ ሐዘኑ ከንጉሡ በዓል ሰባት ቀን አስቀድሞ እንደሚቆም ይጠቁማል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ደንብ ወጥቶለት ሥራ ላይ ከዋለባቸው ጊዜያት መካከል በየካቲት ወር 1954 ዓ.ም እቴጌ መነን እንደሁም በሚያዝያ ወር 1954 ዓ.ም የንጉሳዊ ቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ልዑል ሳህለ ሥላሴ ያረፉ ጊዜ የነበረው የሐዘን ሥርዓት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የግቢ ሚኒስቴር በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 18 ላይ ተመስርቶ የሐዘን ደንብ አውጥቷል፡፡ በመሆኑም ለልዑል ሳህለ ሥላሴ የሚደረገው የሐዘን ጊዜ ከቀብሩ ሥነ ሥርዓት ጀምሮ 40 ቀን ድረስ ሙሉ ሐዘን እንደሚሆን፣ ከዚያም ቀጥሎ ሁለት ወር ግማሽ ሐዘን እንደሚኖር ተገልጦ ነበር፡፡ ልዑሉ ካረፉበት ቀን ጀምሮ እስከ ሦስት ቀን ድረስ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ፣ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማዎች በግማሽ ሰንደቅ እንደሚውለበለቡ ተጠቁሟል፡፡

ደንቡ ወታደሮች፣ ሲቪሎችና ወይዛዝርት በመላው የሐዘን ወቅት እንዴት መልበስ እንዳለባቸው በዝርዝር ተንትኗል፡፡

የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሲከናወን

የሚኖር አለባበስ

ሚሊተሪ - ጠይም ገበርዲን፣

በግራ ክንድ ላይ ጥቁር የሐዘን ምልክት፣ ጥቁር ክራቫት እና ሜዳይ

ሲቪል - ሞርኒንግ ኮት፣ ከጥቁር ክራቫት ጋር

ወይዛዝርት - ጥቁር ልብስ፣ ማናቸውም ጌጥ አይደረግም

በሙሉ ሐዘን ጊዜ የሚኖር አለባበስ

ሚሊተሪ - በግራ ክንድ ጥቁር የሐዘን ምልክት፣ ጥቁር ክራቫት

ሲቪል - ጥቁር ክራቫት

ወይዛዝርት - ጠቆር ያለ ልብስ

በግማሽ ሐዘን ጊዜ የሚኖር አለባበስ

ሚሊተሪ - ጥቁር ክራቫት

ሲቪል - ጥቁር ክራቫት

ወይዛዝርት - ጠቆር ያለ ልብስ

ይህ ከላይ የተዘረዘረው የሐዘን አለባበስ የሚመለከታቸው ሰዎች ማንነት በደንቡ በግልፅ የሰፈረ ሲሆን ንጉሳውያን ቤተሰብ፣ የቤተ መንግሥት ሹማምንት፣ ሚኒስትሮች፣ በውጪ አገር ያሉ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ እንደራሴዎች፣ ጠቅላይ አገረ ገዢዎች፣ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ሹማምንትና የጦር መኮንኖች እንደሆኑም ደንቡ ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪም ማናቸውም ሰው በቤተ መንግሥት በሚገኝበት ጊዜ ማዕረጉ በሚፈቅደው መሰረት ከላይ ከተዘረዘረው በአንዱ አይነት መልበስ እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡

ጠቅላላው የሐዘን ጊዜ እስከተፈፀመበት ጊዜ ድረስ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚፃፃፉባቸው ደብዳቤዎች፣ ኤንቨሎፖችና ወረቀቶች በጥቁር የተከፈፉ መሆን እንዳለባቸው ደንቡ ከማዘዙም በተጨማሪ የሙሉ ሀዘን ወቅት እስኪፈፀም ድረስ የመንግሥት ሬዲዮ ሙዚቃ እንደማያሰማ ያስረዳል፡፡

ደንቡ ከደነገጋቸው የሐዘን ሥርዓቶች ውስጥ መንግሥታዊ ግብዣ የሚደረግበት አኳኋን ይጠቀሳል፡፡ የሙሉ ሐዘን በሚደረግበት ጊዜ በቤተ መንግሥት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም በመንግሥት ሹማምንት ኦፊሴላዊ ግብዣ አይደረግም ሲል ደንቡ ያዝዛል፡፡

የሙሉ ሐዘን ከተፈፀመ በኋላ ኦፊሴላዊ ግብዣ ሊደረግ የሚችለው ግብዣው ለበጐ አድራጐት ሥራ፣ በቤተ መንግሥት አቀባበል ለተደረገላቸው እንግዶች ወይም ለሌሎች ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ክብር ብቻ መሆኑ ተገልጧል፡፡ የሙሉ ሐዘን ጊዜ ከተፈፀመ በኋላ የመንግሥት ሹማምንት ዘፈን ወይም ጭፈራ (ዳንስ) የማይደረግበት ግብዣ ለማድረግም ሆነ ለመቀበል እንደሚችሉ ደንቡ ፈቃድ ይሰጣል፡፡

ከልዑል ሳህለ ሥላሴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማግስት፣ ሚያዝያ 22 ቀን 1954 ዓ.ም በራስጌውና በግርጌው ወፍራም ጥቁር መስመር ተጋድሞበት ለንባብ የበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐዘኑን አስመልክቶ ከቤተ መንግሥት የተላከ መግለጫ ይዞ ወጥቷል፡ ጋዜጣው ባወጣው መግለጫም፤ በዚህ በሀዘን ወቅት ሊደረጉ አስቀድሞ የተዘጋጁ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች እንዳይስተጓጐሉ ሲባል በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት እንዲቀጥሉ መፈቀዱን የቤተ መንግሥቱን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ከአቶ መለስ ዜና እረፍት በኋላ ወደሆነው ነገር ስንመለስ፣ መንግሥት የወሰነው የሐዘን ጊዜ ዝርዝር የአፈፃፀም ሥርዓት የሌለው በመሆኑ ችግር ማስከተሉን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር ከተፈፀመ በኋላ ባሉት ሁለት ቀናት ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ መውለብለቡን መቀጠሉ የሐዘን ደንብ ያለመኖር ውጤት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው አይነት ያለ ዝርዝር የሐዘን አፈፃፀም ሲኖር ግን ሹሞችም ሆነ የጦር አለቆች ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ስለሚያውቁ ግር የሚያሰኝ ነገር አይኖርም፡፡ የሐዘን ደንብ ወጥቶ መደረግ ያለበት፣ የተከለከለውና የተፈቀደው ግልፅ ሲሆን ዜጐችም ግራ አይጋቡም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የቆየ ልማድን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሆኖም ዘመናዊ የሆነ የብሔራዊ ሐዘን ደንብ፣ ወግና ሥርዓትን በማበጀት ከዘፈቀደ አሰራር መውጣት ይገባል፡፡

 

 

 

 

Read 2520 times Last modified on Monday, 10 September 2012 13:51