Tuesday, 28 September 2021 00:00

መቀለድ የማላገጥ ጎረቤት ነው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

• የቀልድ መንታ ገፅታና “ፎርሙላ” - አርተር ኮስለር ይናገራል።
              
          “GC” ማለት ምንድነው? ድምፅ መቅረጫውን ቀስሮ፣ የምረቃ ግቢ ውስጥ እየዞረ ይጠይቃል። የዋህ ተመራቂ ወጣቶች፣ ምንም ሳይጠረጥሩ፣ መልስ ይሰጣሉ። ለነገሩ፣ በየዋህነት አይደለም። የምረቃ ቀን ማለት፣ መልካም መንፈስን የሚያላብስና የቅንነት ስሜትን የሚያበዛ ብሩህ ቀን አይደል! በምረቃ እለት፣ ሁሉም ነገር በጎ ነው። ተመራቂ ወጣቶች፣ ማንኛውንም ነገር፣ ወፍ ዘራሽ የዘፈቀደ ጥያቄንም ጭምር፣ በቀና መንፈስ ይቀበላሉ። በይሉኝታም፣ በፌሽታ ስሜትም ያስተናግዳሉ። በየተራ ይመልሳሉ።
ጂሲ… ማለት ጉድ ኮንግራጁሌሽን…
እ… ግራጁዌሽ ኮንግላሉሽን…
ወንዶች ብቻ አይደሉም ተጠያቂዎቹ። የፆታ ተዋጽኦ አልተጓደለም። ሴት ተመራቂዎችም አሉ። ጂሲ ማለት፣
እ… አንደር ግራጅዌሽን…
እ… ግራጅዌሽን ኮንግራጁሌሽን።
ጠያቂው፣ ተመራቂዎችን ያበረታታል። የሙከራ እድል እንደገና ለወንድ ተመራቂዎች ይሰጣል። ጂሲ ማለት፣…
እ… ግራጅዌሽን ኮንዲሽን፣…
በየመሃሉ፣ ነገሩን የሚያዳምቁ፣ የተለያዩ የመሳለቂያና የማላገጫ አባባሎች ገብተዋል። “አላውቅም ማለት ማንን ገደለ?” እያለ ያሾፋል። ለዚያ ለዚያማ፣ “መሞከርስ ማን ገደለ?” የሚል አባባል ቢጨመርበት ምን ችግር አለው?
ለማንኛውም፣ ብዙዎች ተመራቂዎች፣ በፍንደቃና በጨዋታ ስሜት የሰጡት መልስ፣ ተመሳሳይ ነው - የሚያሸማቅቅ፣ የሚያሳቅቅ።
አንዳንዶቹ፣ አንድ ፊደል፣ አንድ ድምጽ ቀንሰው ወይም ጨምረው ተናግረዋል። አንዱን ቃል አስቀርተው ወይም አስቀድመው፤ ሌላኛውን ለመተካት ወይም ለማስከተል የመረጡም ነበሩ። ሁለት ቃላት ውስጥ ወይም ሁለት ቃላት መሰል ድምጾች ውስጥ ነው የሚሽከረከሩት።
ትንሽ ትንሽ ያስቃልም፤ ብዙ ብዙ ያሳቅቃል። ጥያቄ  አቅራቢው ይዝናናል፤ ያላግጣል።
ግን ከምር፣ “GC” ማለት ምን ማለት እንደሆነ መናገር፣  አላዋቂነትን ይመሰክራል? አዋቂነትን ያጋልጣል? ደግሞም፣ በተመራቂዎቹ ላይ ለመፍረድ ያስቸግራል። እለቱ፣ የምረቃ ቀን ነው። ጥያቄውን ከምረቃ ጋር አዛምደው መልስ መስጠታቸው፤ ከምረቃ ስነ-ስርዓት ጋር የተቀራረበ ሃሳብ መናገራቸው ይገርማል? እሱንስ መች በወጉ ተናገሩ? ትሉ ይሆናል። አዎ፤ ቃላትን እየጎረዱ እየደረቱ የሚናገሩ ተመራቂዎችን ማየት፣ ያሳቅቃል። “ከተመራቂዎች የማይጠበቅና የማይመጥን” ነው - ነገሩ።
ግን፤ ከማሳቁ ይልቅ ማሳቀቁ ይበልጣል። ማሳቅ የማሳቀቅ ዘመድ አይደል! መቀለድ የማላገጥ ጎረቤት አይደል!
እየቀለዱ በጨዋታ የማሳቅ ለዛ፣ ብዙ ጊዜ ያሟልጫል። የቅሌት ገመናዎችን እየገለቡ፣ ወደ መሳለቅና ወደ ማላገጥ ይንሸራተታል። የማቅለልና የማዋረድ ክፉ አመል ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ የግድ ነው። መጠንቀቅ የማይፈልግ ሰው፤ ቀልድና ጨዋታ ባያበዛ ይሻለዋል።
ይሄ የጭካኔ ምክር ይመስላል። ብዙ ሰው፣ “የደስታ ጊዜ´ ማለት፣ “የቀልድና የጨዋታ ጊዜ” ማለት እንደሆነ ያስባል። እውነት ለመናገር፣ ሳቅና ጨዋታ፣ መዝናኛና መንፈስ ማደሻ ናቸው። ግን፣ ሰዎች በጣም ሲደሰቱ፣ በሳቅ አይንከተከቱም። በጣም የተደሰታችሁበትን ጊዜ አስታውሱ። ሳቅ አይመጣላችሁም።
ሳቅ ሌላ፤ ደስታ ሌላ።
ከሳቅ ይልቅ፣ ፈገግታ፣ ከስኬትና ከደስታ ጋር ይቀራረባል። የሚጨበጥ ስኬትና የምር ደስታ፣ ከሳቅ ጋር ግንኙነት የለውም። ጎል ያገባ ተጫዋች፣ በሳቅ አያስካካም። ሲያቀብጠው፣ እቀናጣለሁ ብሎ፣ ለታይታ ሲሽሞነሞን፣ ኳሱን ስቶ አዳልጦት ቢወድቅ ግን፣ ለተመልካች ያስቃል።
በእርግጥ፣ ሲወድቅ እጁ ከተሰበረ አያስቅም። አወዳደቁ አስፈሪ ሆኖ፣ ፊቱ በድንጋጤ ተለውጦ፣ ግን ደግሞ ክፉኛ ካልተጎዳ፣ ነገሩ አስቂኝ ሊሆን ይችላል።
ሳቅና ጨዋታ፣ ነገሮችን አምርሮ፣ አግንኖና እውነት አስመስሎ እያቀረበ፣ በዚያው ቅጽበት፣ ነገሩ ውሸት መሆኑን ገልጦ፣ አቅልሎና አረጋግቶ የማየት ወይም የማሳየት ጉዳይ ነው።
ካላመናችሁ Mr. Bean ይመስክር።
መጥፎነቱ፣ ብዙ የቀልድ ጥበበኞች፣ ቀልድ ለመፍጠርና ለማሳቅ እንጂ፣ ስለ ቀልድ ተመራምረው ለማሳወቅ አይደክሙም።
ሁለተኛ ነገር፣ መሳቅ እና ማሳቅ ይለያያሉ። ታዋቂው Seinfeld፣ መሳቅና መዝናናት ከፈለገ፣ ሌሎች ቀልደኞችን እንደሚመለከት ይገልጻል። ቀልድ እያደመጡ መጫወት እንጂ፣ ቀልድ መፍጠር አያዝናናም። የኮሜዲ ባለሙያ መሆን አያስቅም፤ አያዝናናም።
በእርግጥ፣ ጥበበኞቹ፣ ሙያው የሚማርካቸው፣ ስራው የሚመስጣቸው፣ ስኬቱም የሚያስደስታቸው ናቸው። ቀልድ መፍጠር፣ ቀልድ መስራት ከባድ ሥራ ነው። ሞርዶና ቀርጾ፣ አጣቶና አንጥሮ ፣… የቀልድ ቡቃያውን ለአቅመ ቀልድ ማብቃት፣… በርካታ  ሰዓትን ወይም ተከታታይ ቀናትን ሊፈጅ ይችላል። ትዕግስትን የሚፈታተንና የሚመስጥ ስራ እንጂ፣ የሚያስቅ ጨዋታ አይደለም - የቀልድ ሙያ።  ተግቶ ሲሰራ እንጂ፣ ተዝናንቶ ሲስቅ አይውልም - ጎበዝ ሙያተኛ።
ተሰርቶ ያለቀለት “ቀልድ”፣ ለአድማጭ ለተመልካች፣ በጣም አስቂኝ ሊሆን ይችላል። ገና ሲለቅሙትና ሲፈጩት፣ ሲያቦኩትና ሲጋግሩት ግን፣ አስቂኝ አይደለም - እንደ ሌሎች ስራዎች ነው። ለጎበዝ ባለሙያ፣ የየራሱ ስራ፣ አድካሚና ፈታኝ፣ መሳጭና አስደሳች ነው። ግን፣ አያስቅም።
አስደንግጦ መመለስ፣ ያጠበ አስመስሎ ማስተንፈስ - የቀልድ ቀመር።
“ፕራንክ” ተብለው ከሚቀርቡት የመዝናኛ ቪዲዮዎች መካከል፣ በጣም ምርጦቹን ተመልከቱ። “ፕራንክ” የተደረጉ ሰዎች፣ ነገሩ ሲያልቅና የውሸት ጨዋታ እንደሆነ ሲገለጥላቸው ነው፤ በእፎይታ የሚስቁት፤ የሚተነፍሱት። ከዚያ በፊትማ፣ ነገሩ ቀልድ አይደለም።  የውሸት እንደሆነ አያውቁም።
ነገሩ፣ የምር ግራ የሚያጋባ፣ ከምር የሚስፈራና  የሚያስደነግጥ፣ ከምር የሚያሳዝን፣ የሚያናድድ፣ የሚያስቆጣ፣ የሚረብሽ፣ የሚጎመዝዝ… ከወትሮው የባሰ የምር ጉዳይ ነው የሚሆንባቸው። የገጠማቸው ነገር፤ እውነትም የምር ከሆነ አያስቅም። ወይ የማይታመን ግራ የሚያጋባ ቅዠት ይሆናል። ወይ ይረብሻል፤ አደጋው ያስፈራል። ወይ ያሳዝናል፤ ያሰቆጣል።
ደግነቱ፤ የውሸት ነው፤ ለቀልድ ነው። ለማስመሰል ነው።
ግራ የሚያጋባ፣ የሚያሳዝን፣ የሚያስፈራ፣ የሚያስቆጣ የመሰለው ጉዳይ፣ ብዙ መቆየት መንዛዛት የለበትም። በተቃራኒው፤ ጉዳዩ የውሸት ጨዋታ ወይም ቀላልና ተራ ጉዳይ መሆኑ ወዲያው ሲገለጥ ነው፤ አስቂኝ ቀልድ የመሆን እድል የሚኖረው። አርተር ኮስለር፣ ይሄ የኮሜዲ ተፈጥሮ ነው ይላል።
ሁሉም አስቂኝ ቀልዶች ውስጥ፣ ተቃራኒ ነገሮች አሉ። አዋቂ መሳይ አላዋቂ፣ አስፈሪ መስሎ ቀላል ነገር፣… “ድንገት ፈነዳ” ብሎ የሚጀምር አስደንጋጭ ትረካ፣ “ፊኛው ተነፈሰ”፣ ወደሚል  ተቃራኒ ስሜት “ተከርብቶ” የሚቀየር ነው - የቀልድ ፎርሙላ።
ተቃርኖ ነው ገጽታው። አክሮባት ነው ቀመሩ።
እነዚህን ለመግለጽም “The Paradox of Laughter” እና “The Logic of Laughter”  የሚሉ ስያሜዎችን ይጠቀማል - ኮስለር። በ”ተቃርኖ” የሚሸመን ነው፤ የሳቅና የቀልድ መዋቅር። ተቃርኖ ይመስላል። ግን ደግሞ፣ ሥርዓት አለው።
አለበለዚያ ግን፣ ጉዳዩ ካልተከረበተ ግን፣ አምርሮ ከቀጠለ ግን፣ ወይ ትራጀዲ ወይ ሆረር ይሆናል።
ቀልድ ነኝ ካለስ?  ቅዠት፣ አደገኛ፣ መራራ፣ ገናና የመሰለውን ነገር፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ቀላልና ተራ ነገር መሆኑን ማሳየት አለበት። ታዲያ፣ አክሮባቱ በፍጥነትና በጥበብ ከሆነ ነው የሚሳካው። በጣም ማዝገምና መዘግየት የለበትም። ግራ የሚያጋባ፣ የሚያስፈራራ፣ የሚያስጠላ መስሎ ለበርካታ ደቂቃዎች ከተንዛዛ፣ ከምር አሳሳቢና አስጨናቂ ጉዳይ ሆኖ ያርፈዋል።
ብዙም ሳይቆይ፣ ያበጠው መተንፈስ፤ የተሳከረው መገለጥ አለበት። እዚያው በዚያው፣ መምሰልና መገለጥ አብረው እየተፈራረቁ የሚቀርቡበት ሊሆንም ይችላል - እንደ Mr.Bean ኮሜዲ። እዚያው በዚያው በተቃርኖ የተሸመነ ነው - የሚስተር ቢን ኮሜዲ።
በአንድ በኩል፣ ነገረ ስራው ሁሉ እንደ ሸረኛ ሕፃን ነው።
እድሜው ግን የአዋቂ ነው።
እንደ ህፃን የመሰለው ባሕርይ፣ የምር የሰውዬው ባሕርይ ቢሆን አስቡት። ግራ የሚያጋባና አሳዛኝ የአእምሮ ህመም ሆኖ ይታያችኋል። ማንኛውም ጤናማ ሰው፤ እንዲህ አይነት የአእምሮ ጉዳቶችን ሲያይ ያዝናል፤ ወይም ይጨነቃል። ለቤተሰብ ደግሞ፣ ልብን የሚሰብር፣ እለት በእለትም ኑሮን የሚያከብድ ፈተና ይሆንበታል።
ደግነቱ፣ የምር የመሰለው የMr Bean ባሕርይ፣ እዚው በዚያው፣ የውሸት ጨዋታ እንደሆነ ይታያል። የቀልድ የውሸት መሆኑ ነው - ቀልድነቱ። ግራ አጋብቶ፣ አምርሮ፣ አስፈራርቶ፣ አስጨንቆ፣… እዚያው በዚያው፣ ወይም ወዲያው ሳይዘገይ፣ ወደ ዘወትሩ እውነታ በእፎይታ የሚመልስ ጥበብ ነው - የቀልድ ዋና ባሕርይ። እንግዲህ፣ አርተር ኮስለር ብሏል።
በቀልድ ላይ ደግሞ፣ እንደሱ የተመራመረ ሰው የለም ማለት ይቻላል። ስለ ቀልድ አሳምሮ ያውቃል። በእርግጥ፣ ስለ ቀልድ አሰራርና ባሕርይ ተመራምሮ ማስተማር፤ ቀልድ አይደለም፤ ቀልድ አይሆንም፤ አያስቅም። ቁምነገር ነው።
ስለ መኪና አሰራር መመራመርና መናገር፤ መኪና አይሆንም፤ የመኪና ሽርሽር አይደለም። ነገር ግን፣ የመኪና እውቀትና ትምህርት፣ ትልቅ ቁምነገር መሆኑ ምን ይጠራጠራል? በዚያው መጠን ስለድራማ ወይም ስለ ኮሜዲና ቀልድ ማወቅስ?
እንዲያውም፤ የመኪና አሰራር አብዛኛውን ሰው በቀጥታ የሚመለከት ጉዳይ  አይደለም። ድራማና ቀልድ ግን፣ የሁሉም ሰው፣ የግል የዘወትር ጉዳይ ነው - ከጥንት እስከ ዛሬ፤ ለወደፊትም ጭምር።
እንዲሁ ስታስስቡት፤ በአንድ ትወና ልባችን የሚንጠለጠለው፤ በሌላኛው ትወና የምንስቀው ለምን እንደሆነ፣ ሚስጥሩንና ምክንያቱን ማወቅ አያጓጓም?
ለዚህ ለዚህ፣ ጠራ ያለ፣ ፈካ በራ ያለ፣ የሚያጠግብ የሚያረካ እውቀት የፈለገ፤ የአርተር ኮስለር መጽሐፍ አለለት - “The Act of creation”። ሌሎችም ጽፈዋል። ብዙ ባይሆኑም፣ ስለቀልድና ስለ ኮሜዲ የተጻፉ ቁምነገሮች አሉ። አርተር ኮስለር ግን፣ ምርምሩን ወደ ከፍታ አመጠቀው።
እንግዲህ ተመልከቱ።
የተሳከረና ግራ የሚያጋባ፣ ከተለመደው  እውነታ የተለየ ወይም የተቃረነ፣ አንዳች የሚያስገርም ነገር ቢከሰት፣ ትርጉሙ ምንድን ነው?
በአንድ በኩል፤ እንደ እምነት ወይም እንደ ሆረር ይሆናል። “የመዓት ወይም የምትሃት ተዓምር ነው” ብለን፣ ነገሩን በጭፍን ፍርሃትና በትህትና መቀበል እንችላለን።
በሌላ በኩል ግን፣ ለምርምር የሚያነሳሳም ይሆናል።  ግራ ያጋባን እንቆቅልሽ፣ በምርምር ፍቺ አግኝቶ፣ እውኑን ዓለም ከነስርዓቱ፣ ከቀድሞ በተሻለ ስፋትና ጥልቀት ለመገንዘብ እንበቃለን። ወደ ላቀ  ብርሃንና ከፍታ  እንደርሳለን።
ግራ የሚጋባና አሳሳቢ የመሰለን ነገር፣ “መምሰል ብቻ” ከሆነስ? ወይ ሰርከስ ነው። ወይ ቀልድ ነው።
በአንድ በኩል፤ “በአንዳች ዘዴ  የተፈጠረ አስደማሚ ክስተት ነው” ብለን እንደነቃለን- የሰርከስ የማጅክ ትርኢት እንደመመልከት ይሆናል። ዘዴውን ባናውቀውም፤ ነገሩ ማስመሰያ “Trick” እንጂ፣ የእውነት “Magic” እንዳልሆነ ይገባናል።
ነገርዬው ከነማስመሰያው ወዲያው የሚገለጥልን ከሆነ ነው- ኮሜዲ ወይም  ቀልድ ሊሆን የሚችለው።  የሚስተር ቢንን አይተን የለ! ነገረ ስራው የህጻን ነው፤ ግን የምር አይደለም፤  ሰውዬው አዋቂ ነው።
ይህንን ለማስረዳት ሌላ ምሳሌ ያቀርባል-ኮስለር።
ሰዎች፣ በኩርኮራ ለምን ይስቃሉ?
መልሱን የምናገኘው፣ ሌላ ተመሳሳይ ጥያቄ በማንሳት ነው። ሰዎች ለምን ኩርኮራ ያስፈራቸዋል? ለምን ያሸማቅቃቸዋል?
የኩርኮራ ተፈጥሮ፣ ሁለቱን ነገሮች ያጣምራል። ሰዎች፣ በተፈጥሮ፣ የተቀሰረ ነገር ሲመጣባቸው ያሰጋቸዋል። እንደጥቃት ያስፈራቸዋል። ድንገት ሳያውቁ፣ ሰው ቢጎነትላቸው አያስቃቸውም- ያስበረግጋቸዋል- እንደ ድንገተኛ ጥቃት።
እያወቁ፣ እያዩ፣ የማይጎዳቸው ሰው፣ እናት ወይም አባት፣ ቢሆንስ? አያስፈራም፤ አያሰጋም፤ ቢሆንም፤ ያስፈራቸዋል፤ ያሳቅቃቸዋል። ከዚያስ ከዚያስ? ያሸማቅቃል፤ ግን… አይጎዳም፤ አያስፈራም። አደገኛ ይመስላል፤ ግን መምሰል ብቻ ነው- ከዚህ ውጥረት ጋር በሚፈጠረው እፎይታ ነው ሳቅ የሚፈነዳው።
የቀልድና የኮሜዲ አይነቶች ሁሉ ዋና ቀመር ይሄው ነው ይላል - ኮስለር።
በነገራችን ላይ አንድ የተረሳ ነገር አለ። GC ምን ማለት ነው? ምን ማለት እንደሆነ ካላወቅን´ኮ፣ የቀልዱ ጣዕምና ቀለም ሊቀየር ይችላል። ቀልድነቱም ሊጠፋብን ይችላል እንጂ።
አበበ የከበደን አኳኋንና አነጋገር አስመስሎ ሲታይና ሲናገር፣ ሊያስቅ ይችላል።
“በጣም ይመስላል። ግን የእውነት አይደለም”… ይህ ነው የቀልድ መንታ ገፅታና ቀመር። ከበደን የማናውቀው ከሆነ ግን፤ ቀልዱ አይገባንም። አንድ በሉ። ራሱ ከበደ ሲናገር ብናይና ብንሰማስ?... ምንም አያስቅም። ሁለት በሉ።
ልክ እንደዚው፣ GC ምን ማለት እንደሆነ የማይታወቅ ከሆነ፣… ቀልዱ ይቀየራል። እና ጂሲ ማለት፣ ግሪጎሪያን ካሌንደር አልያም ግራጅዌሽን ሴርሞኒ፣ ግሎባል ኮሚሽን አልያም ግራንድ ካንየን መሆኑ፣ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተገልጿል?Read 9447 times