Sunday, 26 September 2021 00:00

ግልፅ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሊ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ጉዳዩ፡- ኪራይ ቤቶችን ይመለከታል

              ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ ባሳዩን መጠነ ሰፊ ትዕግስትና አርቆ አስተዋይነት ያለኝን አድናቆት መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ በ2013 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት በነበሩት ሁለት አመታት በመላ ኢትዮጵያ ሞት፣ መፈናቀልና ውድመት በቀጠለበት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ የፖለቲካ ትኩሳት በሆነበት፣ ስድስተኛው ሀገራዊ መርጫ እንዲደናቀፍ የሻገቱ ፖለቲከኞች የሸረቡትን ሴራ ማክሸፍ፣ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የአራዊቶች ስብስብ የሆነው ሕወኃት ከቻለ  አራት ኪሎ ለመግባት ካልቻለ ኢትዮጵያን ለመበተን በከፈተው ጦርነት፣ በወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋና ያወደመው ንብረት፣ በገቡበት ሁሉ ሽንፈትና ውርደት እየተከናነቡ የሚወጡት አሜሪካኖችና አጋሮቻቸው ያደረሱብንን ጫና ተቋቁመው፣ ለድል መቃረብዎ የአድናቆቴ መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የዚያኑ ያህል ባይሆንም ስህተቶችን እየሰሩ እንደሆነ ስገልፅልዎ ከፍ ባለ ትህትና መሆኑን እወቁልኝ፡፡ ለምሳሌ ወያኔን በአሽከርነት ሲያገለግሉ የነበሩና ዜጎችን ከማሳሰርና ከማስገረፍ ጀምሮ በመዝረፍና በማዘረፍ የምናውቃቸውን ግለሰቦች በአማካሪነት፣ በቦርድ ሰብሳቢነትና በአምባሳደርነት መድበው ሲያሰሩ በማየታችን አዝነናል፡፡
በመሰረቱ አንድ ካድሬ ሁለት ጊዜ ሚኒስትር፣ እንድ ጊዜ አፈጉባኤ፣ አምስት ጊዜ አምባሳደር ሆኖ በሚሾምበት ጊዜ በየሙያው (Field of Study) የሰለጠኑ ምሁራን በአገራቸውን ጉዳይ ከመሳተፍ ይልቅ ገለልተኛ አቋም እንዲወስዱ ይገደዳሉ። በነገራችን ላይ ምሁራን ስንል ለወፍራም እንጀራ ደፋ ቀና የሚለውን አድር ባይና አስመሳይ ማለታችን አይደለም፡፡ ባጭሩ በሕይወት ካሉትና ከሌሉት እንደነ ሎሬንሶ ትዕዛዝ (ዶ/ር)፣ አክሊሉ ሀብተወልድ (ፀሀፊ ትዕዛዝ)፣  ተስፋዬ ዲንቃ (አቶ)፣ ጎሹ ወልዴ (ኮሎኔል)፣ ሀይሉ ይመኑ (አቶ)፣ ሀይሉ ሻወል (እንጅነር)፣ መርስኤ እጅጉ (አቶ)፣ ሚካኤል እምሩ (ልጅ)  እና የመሳሰሉት ልሂቃን  (intellect) ከነበራቸው መልካም ተሞክሮ ልምድ የተጋሩ አይመስለንም፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፡- ከላይ የጠቀስኳቸው ምስጋናዎችና ነቀፌታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ለዛሬው በዋናነት የማነሳልዎ በቀድሞ ስሙ ኪራይ ቤቶች ስለሚባለው ተቋም  ይሆናል፡፡ ይህ ተቋም በደርግ መንግስት ከተቋቋመ አርባ አምስት አመት ያስቆጠረ ሲሆን አላማና ግቡም በአቅም ውስነት የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ወገኖች ዝቅተኛ ኪራይ እየከፈሉ እንዲኖሩ ለማስቻል ነበር፡፡
ዛሬ ግን ተቋሙ ከሚያስተዳድራቸው 18,000  ስምንት ሺህ) ቤቶች  ሶስት አራተኛው ወይም 13,500 (አስራ ሶስት ሺህ አምስት መቶ) ከሚሆኑት ውስጥ 702 (ሰባት መቶ ሁለት) ቤቶች በቁልፍ ሰበራና በቁልፍ ግዢ የተያዙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 12,798 (አስራ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት) ቤቶች በእከክኝና ልክክልህ ቲያትር ውስጥ በተወኑ ቤት ፈላጊዎችና በኪቤአድ የስራ ሀላፊዎች መካከል በተደረገ ድርድር የተከራዩ ናቸው፡፡
በተለይ ከ702 (ሰባት መቶ ሁለት) ተከራዮች ውስጥ ቁልፍ ሰባሪዎቹ በወንጀል መጠየቅ ሲገባቸው ውል እንዲዋዋሉ መደረጉ ኪራይ ቤቶች የቱን ያህል የነቀዘ ተቋም መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ ቀሪዎቹ አንድ አራተኛ ወይም 4,500 (አራት ሺህ አምስት መቶ) ቤቶች ከአስር አመት በላይ በወሰደ ደጅ ጥናት በህጋዊ መንገድ የተሰጡ ናቸው፡፡ ተቋሙ ከኋላ ታሪኩ ጀምሮ በሙስና የተጨማለቁ አመራሮች እየተፈራረቁ የድርሻቸውን የወሰዱበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ተከስተ እና ተስፋሁን የተባሉትን ሙሰኞች፣ የፖሊስ መኮንን የነበረና በሙያው ዶ/ር የሆነ ሰው ቢሮአቸው ውስጥ ከገደላቸው በኋላ  እጁን ሰጥቷል፡፡
ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ የተደናገጡት የስራ ሀላፊዎች፣ ሽር ጉድ እያሉ ደንበኞችን ማስተናገድ ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ ወደነበሩበት ለመመለስ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን በአከራይና ተከራይ መካከል ያለው ግንኙነት ግልፅነትንና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ አመራሮቹ የመንግስትን ቤት እንደፈለጉ ቆምረውበት፡፡
ኬቤአድ በአርባ አምስት አመት እድሜው አንድም ጊዜ  ከተከራዮች ጋር የሚያገናኘው መድረክ ባለመፍጠሩ እራሱን መፈተሽ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ምንም እንኳ ሚኒስትሮች በሚገኙበት ቦርድ የሚመራ ተቋም ቢሆንም ቦርዱ በተሰበሰበ ቁጥር ቃለጉባኤዎችን ተፈራርሞ ይበተናል እንጂ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ አላመጣም፡፡ ለምሳሌ ቤት እንዴት እንደሚሰጥና እንደሚከለከል ግልፅ የሆነ መመሪያ የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት የጀግና ሚስቶች ከእነ ልጆቻቸው፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አስተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የግለሠብ ኩሽናዎችን እየተከራዩ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ሕገወጦች ደግሞ የራሳቸውን ሁለትና ሶስት ቪላ ቤቶቻቸውን እያከራዩ በመንግስት ቤት ይኖራሉ፡፡ ወይም ለሶስተኛ ወገን ያከራያሉ፡፡ ወይም ውስጥ ለውስጥ ይሸጣሉ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ኬቤአድ (ሻለቃ)፣ (ኮሎኔል)፣ (ወ/ሮ)፣ (አቶ)፣ እና ተጋዳላይ የነበሩ ሰዎች ስራ አስፈፃሚ፣ ዋና ዳይሬክተርና ሥራ አስኪያጅ እየተባሉ ተፈራርቀውበታል። ከአንዲት እንስት በስተቀር የሁሉም እጆች ረጃጅሞች ነበሩ። አሁንም ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት ያለ ሥራው ገብቶ ጥቃቅን ሳንቲሞች እሰበስባለሁ ካላለ በስተቀር ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት መስራት ያለበት ሲሆን ለዚህም ሂደት ይረዳ ዘንድ ሁለት አማራጮችን አቀርባለሁ፡፡
1ኛ. ቤቶቹ ለረጅም ጊዜ እድሳትና ጥገና ያለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ድምፅ ስለሚያስተላልፉ የአንድ አባወራ ሬድዮ ወይም ቴሌቪዥን፣ ለስምንት አባወራ ከነቤተሰቡ ፀጥታ ይነሳል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃም ስለሌላቸው መጥፎ ሽታው ከተከራዮቹ አልፎ ለአካባቢውም ህብረተሰብ   ለስርዐቱ በነበራቸው ታማኝነት ያለ አግባብ ቤት የታደላቸውን ሳይጨምር፣ ተቋሙ ሲቋቋም በነበረው አላማና ግብ መሰረት ተከራይተው ለሚኖሩ ግለሰቦች ቢሸጡ የአገልግሎት እድሜያቸውን ማራዘም ከማስቻሉም በላይ መንግስት ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ ካለው ፍላጎት በተጨማሪ፣ እየተከተለ ላለው ፖሊሲና ለነደፈው ስትራቴጂ ተግባራዊነት አንዱን ምዕራፍ እንደጀመረ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የተወሳሰቡና  አሰልቺ አሰራሮችን ያመክናል። ኪራይ በመሰብሰብ የሚያጠፋውን ጊዜ ያስቀራል፡፡ በአ.አ መስተዳደር እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለውን የአሰራር ክፍተት ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን በውጭ ምንዛሬ የሚከራዩ ቤቶችን ያስቀጥላል፡፡
2ኛ. መንግስት ቤቶቹን የመሸጥ ፍላጎት ከሌለው ኬቤአድን በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በመበተን ተከራዮች በአካባቢያቸው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን ጉዳያቸውን ለማስፈፀም የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞና ለትራንስፖርት የሚያባክኑትን ገንዘብ ያስቀራል፡፡ ይህ ያልተማከለ (Decentralized) አሰራር ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ያስቀራል ተብሎ ባይገመትም፣ ህዝቡ በቅርበት ስለሚከታተልና አዲስ በሚመሰረተውም መንግስት የተሻሉ አመራሮች ይመጣሉ ተብሎ   ስለሚጠበቅ መፍትሄ ይኖራል ብለን እንጠብቃለን፡፡     
ኢትዮጵያ ከወንበዴዎች፣ ዘራፊዎችና ሙሰኞች ተጠብቃ ለዘላለም ትኑር!
         ከውብሸት ተክሌ ፍትህአወቅ  (ገርጂ ቡናና ሻይ)

Read 1323 times