Sunday, 26 September 2021 00:00

“ቆፒና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ መተማመን ካለ ይበቃል አንድ ወዳጅ!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ሎሌ፣ ጌታው ፊት ይቆምና ቃል ይገባል። የሎሌው ስም ብርቄ ነው።
ቃሉም፤
“ጌታዬ ሆይ”
ጌታው፤    
“እህ ብርቄ ምን ፈልገህ ነው?”
“ጌታዬ፣ ቃል እንድገባ ይፈቅዱልኛል?”
ጌታው፤
“አዎን እፈቅድልሃለሁ። የምን ቃል ልትገባ ነው የፈለከው?”
ብርቄ፤
“ጌታዬ አሁን አይበለውና የእርሶ ህይወት ቢያልፍ፣ ያለ እርስዎ መኖር ስለማልሻ ዓለም በቃኝ ብዬ እመንናለሁ።”
ጌታውም፤
“ተው አታረገውም ብርቄ። መመነን ቀላል ነገር አይምሰልህ!”
ብርቄ፤
“ጌታዬ፤ በጭራሽ ቃሌን አላጥፍም”
ጌታው ወደ ሌላው አገልጋያቸው ዞረው፣ “ንሣ አንተ አሽከር፣ ለብርቄ አንድ ኩታ ሸልምልኝ!” ሲሉ በትፍስህት ተሞልተው አዘዙ።
ያም ሌላኛ አገልጋይ ሮጦ ወደ ቤት ገብቶ አንድ ኩታ ይዞ መጥቶ ለብርቄ ሸለመ!!
ጌትዬው አርጅተው አፍጅተው ሞቱ። ብርቄ ሳይመንን ቀጣዩን ጌታውን ለጥ ሰጥ ብሎ ማገልገሉን ጀመረ።
 አዲስ የመጡት ጌታም ድንኳን አስጥለው፣ ጠጅ በጋን አስሹመው፣ ሰንጋ አርደው የሰፈር ሰዎችንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም ዘመድ አዝማዱን ሁሉ ጠርተው ድል ያለ ግብዣ ደገሱ።
በድግሱ ላይ አንድ አዝማሪ ተገኝቷል። አዝማሪው ሟቹን ጌታም፣ አዲሱን ጌታም እያነሳ እንዲያወድስ አዲሱ ጌታ፤
“ንሳ አንተ አዝማሪ አጫውተና!” አሉት።
አዝማሪውም፣
“የኔማ ጌትዬ የሚበላው ጫማ
የኔማ ጌትዬ የሚጠጣው ጠጅ
እንዴት ዝም ይባላል ይሞገሳል እንጂ!” ብሎ ገና ሲጀምር፤
“ይበል! ይበል! ሠናይ! ሠናይ!” አሉ በደስታ እየተፍነከነኩ።
አዝማሪው ቀጠለና፤
“የኔማ ጌትዬ ዘረ መኳንንት
ሥጋ አልበላም አለ ትከሻው ከብዶት!” አለ።
አዲሱ ጌታም፤
“ንሣ አንተ አሽከር አንድ ኩታ ሸልምልኝ” አሉ።
አሽከር ፈጠን ብሎ ለአዝማሪው ኩታ ሸለመው።
ይሄኔ አዝማሪው ወዲያውኑ ቀልጠፍ ብሎ ቀጠለና፤
“ትላንትና ማታ…
የጥንቱን ጌታዬን መንገድ ላይ አግኝቼ፡-
ሚስቴ ደህና ናት ወይ?
ልጄስ አደገ ወይ?”
ብለው ቢጠይቁኝ፤
“ሚስትዎት ደህና ናቸው
ልጅዎትም አድጓል
ብርቄም አልመነነም!” ብዬ ብነግራቸው…
(ጣቱን እንደ ጌታው እያወናጨፈ ያሳያል)
“አዬ ጉድ!
 አዬ ጉድ!
አዬ ጉድ!...ያሉበት-
ረገፈ ጣታቸው!”
ሲል ገጠመ ይባላል።
*   *   *
ከነገር ሁሉ መጥፎ ቃልን አለመጠበቅ ወይም አለማክበር ነው።
 ጥንት፣ ገና በጠዋት፤
“ቆፒና ወረቀት፣ ቀሪ ነው ተቀዳጅ
መተማመን ካለ ይበቃል አንድ ወዳጅ!”
ተብሎ የተዘፈነው ለዚህ ነው።
በዘንድሮው አዲስ ዓመት አዲስ ራዕይ፣ አዲስ መንፈስ፣ አዲስ ተሐድሶ ይኖረን ዘንድ ልብና ልቡና ይስጠን! የተስፋችን ብርሃን የበለጠ ብሩህና ጋን የሚያጎናጽፈን ይሁን።
መልካም የ2014  አዲስ ዓመት ይሁንልን!
ከአዲስ አድማስ ጋር ወደፊት እንጓዝ!!

Read 12119 times