Print this page
Monday, 20 September 2021 17:17

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የራሄል ጌቱ “ኢትዮጵያዬ” (የኔ 1ኛ)
                             ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

                የፓብሎ ፒካሶን “ገርኒካ” ሥዕል የፈጠረው 2ኛው የዓለም ጦርነት ነው። ሕወሓት ባርኮ የጀመረው ጦርነትም እንዲሁ የብዙ የፈጠራ ስራዎች መነሻ መሆኑ እየታየ ነው። ኪነጥበብ ከምቾት ይልቅ መከራን የሚፈልግ ይመስለኛል። በቅርቡ ከ100 በላይ የጥበብ ሰዎች ተሰባስበው በ20 ቀናትና ሌሊቶች የሰሯቸው “ስለ ኢትዮጵያ” የተባሉ መንትያ አልበሞች የዘመናችን ሀገራዊ ሀውልቶች ሆነው ይጠቀሳሉ። ድምጻዊት ራሄል ጌቱ ሰሞኑን የለቀቀችው “እቴሜቴ” አልበሟ ውስጥ “ኢትዮጵያዬ” የተባለው ቁጥር 1 ወኔ ቀስቃሽ ዜማ በቅርብ ከተሰሩ ሀገራዊ ዜማዎች ሁሉ ለየት ያለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በአሚናዎች እንጉርጉሮ የሚጀምረው ይህ ዜማ፣ ድምጻዊቷ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን ተክላ እስኪጠናቀቅ ሙሉ ሆኖ ዓይንንም ጆሮንም ሰቅዞ የመያዝ ኃይሉን አሳይቶናል። ስራው ሲያልቅ ማን ነው ይህን ምትሀት የፈጠረው? የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል። የግጥሙ ደራሲ ናትናኤል ግርማቸው ነው? የኢዮኤል መሀሪ ዜማና ቅንብር ነው? የቅድስት ይልማ ዳይሬክተር መሆን ነው ወይስ የሰዳኪያል አየለ ሲኒማቶግራፈርነት? አንድ ቦታ ላይ ቆሞ ለይቶ ማመስገን የሚቻል አይመስለኝም። የአማርኛ ዘፈኖች የጀርባ አጥንት የሆነው “እናናዬ . . . እህም እናኑ” እንኳ የክብር ቦታ አግኝቷል።
“እናና እናና እናና
ይጥለፈኝ ቀሚሷ ጉበኗ
ጠብ እርግፍ ያርገኝ ለክብሯ
ሆዴ እንዳታጣላኝ ካድባሯ
እናና እንዬ እናት ዓለም
የደም የአለላ ሰበዝ ቀለም “ ትላለች።
ቀጥላም፤ “ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኧረ ሰው ጌጥ ሀብቱ
ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኩራቱ
እንደምን አይከፋው
አንገቱን አይደፋው
ሲከፋት እናቱ” እያለች የዛሬዋን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በአጭር መስመሮች ስላ ታሳየናለች፡፡
ራሄል የምታዜማት ገጸ ባህሪ የኢሕአዴግ ዘመን ልጅ፣ ብሔሯ አማራ ናት።
“በልጅነት ፍቅርሽ የሰቀልኩት ሰንደቅ የታቀፍኩት በጄ
የዜግነት ክብር ስል የዘመርኩት ከሰልፍ ማልጄ
ያቆመሽ ካድባርሽ የነጻነት ደጄ
እሱ ነው እሱ ነው ወዳጄ” ብላ እያዜመች ነው ራሷን የምትገልጸው። በአሚናዎቹ እንጉርጉሮ የጀመረው ሀዘንና ልበሙሉነት የተቀላቀለበት ዜማ፣ ከቅድስት ይልማ ዝግጅትና ከራሄል ጌቱ እንደ አዚያዜሟ ሁሉ የቆፍጣና ፋኖ ምስለ ትወና የገፀባህሪዋን ማንነት እንደ ፎቶ ታሳየናለች።
“ኧረ ጎራው ኧረ ዱሩ
ጃል እንዴት ነው ዳር ድንበሩ
የእሷን ክፉ ቆሜ ከማይ
ያሳደገኝ አፈር ይብላኝ” ስትል ለዚያች የልጅነት ህልሟ ራሷን የመስጠት ቁርጠኝነቷን ቆርጣ ታሳየናለች፡፡
“ኧረ ጎራው ኧረ ዱሩ “ እያለች ዱር ታስገባናለች።
“ኧረገኝ ኧረገኝ ንቢቷን
ቀፎዋን የነኩባት ቤቷን
ኧረገኝ ኧረገኝ ፍም እሳት
ተባይ ሀገሬን ሲንቃት
ባይ ካንገት በላይ በላይ
ሁሉ ካንገት በላይ በላይ
ያለ ሀገር ኑሮ ስቃይ
ማን ኢትዮጵያን መሳይ ሲሳይ
ሲሳይ ነች እሷ ሲሳይ"
እያለች የፍቅሯን ጥግ፣ የቁጭቷን ጠርዝ “ያለ ሀገር" እያለች ሲርባት እሸት፣ ሲጠማት ቅራሪ ያቀመሷትን፣ የእናቷን ቀሚስ ተከትላ የሄደችባትን የሀገሯን ስቃይዋን ታጋራናለች። “ብሞትለት ሞት አነሰኝ” ስትል ነው አፈር ገፍቶ ለፍቶ የሚያጎርሳት ቀን የጎደለበትን፣ ቤቱ የፈረሰበትን፣ የአጋንንቶች ሰይጣናዊ በትር ያረፈበትን ወገኗን ነው “ ብሞትለት ሞት አነሰኝ የምትለው።
ይህ ቃሉ ነው። ምስሉ ከዚህ በላይ ጮኾ የሚናገር ነው።
“እናናዬ እናናይ" ስትል አንገቷ የሚሆነውንና የሚያስተላልፈውን መግነጢሲዊ ምስል በማሳየት ካልሆነ በቃላት መግለጽ አይቻልም። ቅድስት ይልማ እንደ ምንጊዜውም በ “ኢትዮጵያዬ” የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ተጠብባለች። የሙዚቃ ቪዲዮ በራሱ ጥበብ ከመሆኑም ባሻገር ስራውን ከፍ የማድረግ ኃይል አለው። ቅድስት ተክናበታለች። ጥላሁን ገሠሠ ንጉሠ ነገሥቱ ፊት በቀረበ ጊዜ ያሉት፤ “ድምጽህን ጠብቀው" ነበር ። ለራሄልም ይህንኑ ነው የምደግምላት።
“ኢትዮጵያዬ”ን በ2 ቀናት ውስጥ ከ30 ጊዜ በላይ ሰምቼዋለሁ። ገና ብዙ ጊዜ እደጋግመዋለሁ። ሙያተኞቹ ሁሉ ክበሩልኝ፡፡

________________________________________

                  
                   ‹‹ዋጋዬማ አትታረድም!››..
                          በድሉ ዋቅጅራ


              ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡፡
.ስነጥበብ በምጡቅ ምናብ (elivated imagintion) እና በውበት ስሱነት (sensitivity to beauty) ዳግም የሚፈጠር እውነት ነው፡፡ እቅጬ እውነት (fact) አይደለም፣ እውነት (truth) ነው፡፡ እውነት ከእቅጬ እውነት የሰፋ፣ የፋፋ፣ የተንሰራፋ ነው፡፡ ይህ መስፋት - መፋፋቱ ነው የምንኖርበትን ሁለንተናዊ መስተጋብር ውጤት (እቅጬ እውነታችንን) እንድናጠይቅ የሚጎነትለን፡፡ ስነጥበብ እቅጬ እውነታችንን እንድንቀበል ሳይሆን እንድንጠይቅ፣ እንድንመረምር ሲያደርግ ለግቡ በቅቷል፡፡
.የስነጥበብ ጉንተላ የማህበረሰብን ህሊናዊ ልእልና ይሞርዳል፤ የተሞረደ ህሊና ሳይቆርጥ - ሳያደማ በተወረወረለት ሀሳብ ላይ አይደላደልም፡፡
"ዋጋዬማ አትታረድም!" (እረኛዬ ተከታታይ ድራማ፣ ክፍል 4) ትላለች እናና፤ ከከብቶቿ ጋር ገደል የምትገባዋ እረኛ። ‹‹ሀገሬስ ለእኛ ለዜጎቿ እንዲህ አይነት እረኛ የምታቆመው መቼ ነው? በከተማ በገጠሩ፣ በየወንበሩ እንደ እናና ያሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያንስ አይሞቱም!›› የሚሉ፣ ከሚያስተዳድሯቸው ዜጎች ቀድመው ገደል የሚገቡ፣ በተተኮሰበት ጥይት ፊት የሚቆሙ እረኞች የምናገኘው መቼ ነው? . . . ይጎነትላል፡፡
የራሔል ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› የሚለው ዘፈን በዘነጋነው እቅጬ እውነት የገነነ ውበት ነው፡፡ ውበቱ ይቆጠቁጣል፤ እውነቱ ይሸነቁጣል፤ አይደለድልም፤ ይፈረፍራል።
እንደነዚህ ያሉ ስራዎች ዛሬያችንን አስጠይቀው ለነገ መልስ ያንደረድራሉ፣ የዛሬዬያችንን ጥቀርሻ ባንጠርገው መኖሩን አውቀን እንድንጸየፈው ያደርጋሉ፡፡ ... ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡፡


_________________________________________


                        Politicization of History... የአዲስነት ፀር!
                                ጌታሁን ሔራሞ



                 ለዩጎዝላቪያ መፈራረስ የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ከብሔር ፖለቲሳይዜሽን ያልተናነሰ ሚና ተጫውቷል። የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ፅንሰ ሐሳብ ፖለቲከኞች ላለፈው ዘመን ታሪክም ሆነ በወቅቱ ንቃተ ህሊና መመዘን ላለባቸው ታሪክ-ተኮር ስህተቶች ዛሬ ፖለቲካዊ ቅርፅ ሰጥቶ በብሔሮች መካከል መቃቀርን ለመፍጠር የሚጠቀሙበትን ጥረት የሚያመላክት ነው። ያለፈ ታሪክ ስንል አፍቅሮተ ትናንት (Nostalgia) አሊያም የትናንት ጭቆና በሌለበትም ጭቆናው ዛሬም እንዳለ መቁጠርንም (Internalized oppression) እንደሚያካትት ይሰመር። ለምሣሌ ቀደም ሲል የዩጎዝላቪያ ሪፐብሊክ በነበረችው ክሮሺያ ከድህረ ኮሚኒዝምም በኋላ ፖለቲካዋን ይዘውር የነበረው ያለፈው ታሪኳ ነበር። በአጭሩ የትናንት ታሪክ የክሮሺያን የየዕለት ፖለቲካዋን ይቀርፃል። ኮሶቮ ውስጥም ቁርሾ ለመቀስቀስ ሲባል በጦርነት የተሰው አርበኞች አፅም ተቆፍሮ እየወጣ እንደገና ይቀበር ነበር፣ በብሔር ብሔረሰቦች መካከልም ጠብን ለመዝራት ሲሉ የብሔር ፖለቲከኞች ሐውልት ያቆሙ ነበር።
የብሔር ፖለቲከኞች የቅስቀሳ ዘዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይነቱ አንዱ ገራሚ ነገር ነው። ከእግዚአብሔር ምህረት ለጥቆ ዕድሜ ለሕዝባችን ንቃተ ሕሊናና ነባር ማህበረሰባዊ ትስስር እንጂ የኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካም መተንፈሻ ሳንባው፣ የትናንት ቁርሾና ታሪክ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የትናንት ስህተቶች ለዛሬ ልምድና ትምህርት መቅሰሚያ አጋጣሚ ከመሆን ያለፈ ሚና ሊኖራቸው ዘንድ አይገባም። በቂም፣ በበቀልና በቁርሾ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ሀገርን አንድ ኢንች ወደ ፊት አያስኬድም። አዲስ ሐሳብን ለማፍለቅ አቅሙ የሌለው ፖለቲከኛ፣ በትናንት ትውስታ ዛሬን ለመኖር ይገደዳል። በአዲሱ ዓመት በአሉታዊ ትውስታ የተሰነገ አሮጌው ትናንቱ ይሰለጥንበታል።
መልካም አዲስ ዓመት!
በነገራችን ላይ ስለ ዩጎዝላቪያው የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ጠለቅ ያለ መረጃን ከሚቀጥለው መፅሐፍ ማግኘት ይቻላል፦
Nationalism and the Politicization of History in the Former Yugoslavia, Editors Gorana Ognjenovic and Jasna Jozelic, 1st ed. 2021.


_____________________________________



                       “የአዲሱን ዓመት ለምድ ለብሰው ከሚመጡ 2012ቶችና 2013ቶች ተጠበቁ”
                                    ረድኤትአሰፋ


            ስልኬ የዛሬ ሳምንት አካባቢ መቀባዠር ጀመረች። ሁሉን ነገር በጸብ መፍታት አይገባኝም ብዬ ታገስኳት። በዚያ ላይ ደሞ ዓመቱ ነጃሳው 2013 ነው ብዬ፣ ያላበደ የለም ብዬ ታገስኩ። አዲስ ዓመት ይግባ ብዬ፣ መስከረም ይጥባ ብዬ ታገስኩ። <እንዳያልፉት የለ>ን ያለፖለቲካዊ ዘመኑ እያፏጨሁ፣ ዓዲሱን አመት ተቀበልኩ። ለካ መስከረም እንደ ክፉ ህጻን አባቱን ከልክሎ ለራሱ ብቻ ነው የሚጠባው! ትናንትና በ2014 ከእንቅልፌ ስነቃ ስልኬ ቴሌቭዥኔ ጋ ተመሳስላ አገኘኋት። የምትታይ ግን የማትነካ። ብትነካም እንዳኮረፈች ፍቅረኛ የማትሰማ የማትለማ። ጃንሆይ ወደ ቮልስ ዋገን በወረዱበት በመስከረም ሁለትስ አልዋረድም... ብዬ ባላየ አለፍኩት። ስልኬም ዶክተር አሸብርን በሚያስከነዳ ድርቅና ስታክ አድርጋ ዋለች።
ዛሬ በማለዳ ገላዬን ታጥቤ፣ የክት ልብሴን ለብሼ ካፌላቴ በአናቱ ከልሼ... ማህለኛውንና ሌባ ጣቴን በgoodluckኛ አቆላልፌ ... የቤትና የቢሮ ቁልፌን እያሽከረከርኩ ፉጨት አስቀድሜ... መገናኛ ካሉ ... ጉንዳን የወረራቸውን አጥንቶች... በሚያስቀና መልኩ በሰው ከተወረሩና የጾም ኬክ ከመሰሉ ህንጻዎች በአንደኛው ስር ከሚገኝ የስልክ ክሊኒክ ገባሁ።
እንደገባሁ አንድ ልጅ እግር አቀርቅሮ... እንደ ኢትዮ360 አናቷ ባጠረ ምላሷ በረዘመ መፍቻ የአንዲት ምስኪን ሞባይልን ሆድ እቃ ሲፈተፍት ደረስኩና < ደህና አደርክ?> አልኩት። በጎሪጥ ቀና ብሎ ፊቴን ሳያይ እጄ ላይ የያዝኳትን ስልክ አይቶ እና ለ “ደህና አደር”ኬ ሳይጨነቅ
“ምን ሆኖብህ ነው?” አለኝ
“ስነካት አልመልስ እያለች...” አላስጨረሰኝም
“ስክሪን ፌል አድርጎ ነው!... ሌላ ስልክ ግዛ...”
በሸቅኩ።
“እየመከርከኝ ነው? ምክር ፈልጌ ሳይሆን ሰሪ ፈልጌ ነው የመጣሁት ሰውዬ”
በንቀት የሽሙጥ ሳቅ ታጅቦ “የሱ ስልክ ስክሪን ውድ ነው” አለና ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቴን አየው። የመግዛት አቅሜን እየመዘነ መሆኑ ታውቆኝ በብሽቀት፤
“ስለ ገንዘብ ማን አወራ? ስንትስ ቢሆን ...” ቁልፌን እያሽከረከርኩ ፎከርኩበት
ሳቅ ብሎ “አስር ሺህ ብር ነው” አለኝ። ከዛ በኋላ የሆነውን አላስታውስም። የስልክ ክሊኒክ ወድቄ ጤና ጣቢያ አልጋ ላይ ነቃሁ። ቀና ስል ስልክ ሰሪው ከአንዲት ነርስ ጋር በሀዘኔታ እያዩኝ ነው። ስልክ ሰሪው ፈጠን ብሎ አጠገቤ መጣና “አስጠንቅቄህ ነበርኮ... አልሰማ አልከኝ “ አለኝ በሀዘኔታ። ከኪሱ የገዛ ስልኩን ላጥ አድርጎ አወጣና ወደኔ ዘረጋልኝ። ምን አይነት ምስኪን ሰው ነው ብዬ ተገርሜ እጄን ስዘረጋ መልሶ ወደራሱ ወሰደውና፤
“እኔ ሙስሊም ነኝ.... ግን ይቺን መዝሙር ሊሰራ ከመጣ ስልክ ውስጥ ነው ያገኘኋት አድምጥበት “ ብሎ  ከፈተልኝ... በጉጉት የተዘረጋ እጄን አጥፌ መስማት ጀመርኩ
“ማን አለን ጌታ ሆይ ካንተ በቀር...”
ስልክ ላሰራ ሄጄ ዋጋው መንፈሳዊ ሰው ሊያደርገኝ ለጥቂት....
ወገን ከመቼ ጀምሮ ነው የስክሪን ዋጋ ከሙሉ ስልክ ዋጋ የበለጠው? ወይስ የድሮ ሼባዎች “በጉን አንድ ብር ገዝቼ ቆዳውን ብር ከሀምሳ ሸጥኩት” ያሉን ታሪክ በዲጅታልኛ ሊደገምብን ነው? ወይኔ 2014... አምኜህ?
{ይህንን ፖስት እጽፍ ዘንድ.... ለመታደስ ከመጡ ስልኮች አንዷን በማዋስ የተባበረኝን... ስልክ ጠጋኝ ቶፊቅ ኢብራሂምን አመሰግናለሁ። ካሁን በኋላ ምንም ፖስት በኔ አካውንት ብታዩ የቶፊቅ ወይም ስልክ ሊያሳድስ የሰጠው የባለቤቱ አቋም መሆኑን እወቁልኝ። ነጃሳ 2014 ? መች ነው 2015 ደሞ የሚጠባው?

Read 2251 times
Administrator

Latest from Administrator