Print this page
Monday, 20 September 2021 16:03

መሠንበት

Written by  ደሳለኝሥዩም
Rate this item
(6 votes)

 ጠባቧ ክፍል በሲጋራ ጭስ ታፍናለች፡፡ አንገቱን ወደ ኮርኒሱ ቀና አድርጓል፡፡ ዐይኖቹ በኮርኒሱ ርብራብ ሥር ይመላለሳሉ፡፡ ጥልቅ ሐሳብ ይዟል፡፡
ጫፍ ላይ የደረሰውን ሲጋራ በኃይል ሲስበው እሳቱ የእጁን ጣቶች መለብለብ ጀምሮ ነበር፡፡ የጽሕፈት ጠረጴዛውን መሳቢያ መዘዘና የሲጋራ ፓኬት አወጣ። ከሲጋራ ሳንዱቁ አንድ ዘንግ መዘዘና በጨረሰው ሲጋራ ትርኳሽ አቀጣጠለው፡፡ ዐይኖቹ ተመልሰው ወደ ላይ ወደለመደበት ሥፍራ ተቀሰሩ፡፡ ወደ ኮርኒሱ፡፡
ሁሌም ሊጽፍ ሲል እንዲህ ነው፡፡ ያንቀዠቅዠዋል፡፡ አለዚያም ጭልጥ ያለ ሐሳብ ይወስደዋል፡፡ ስሜቱን መግራት እስኪጀምር ድረስ ደጋግሞ ቡና ይጠጣል። ወይም ሲጋራ በላይ በላዩ ያጨሳል። አእምሮው ውስጥ የሚመላለሰው ሐሳብ መስመር ሲይዝለት በፍጥነት እስክርቢቶውን ይጨብጣል፡፡ ወረቀቶችን ይመዝዛል፡፡
ዛሬ ግን ለየት ያለ፣ ጫን ያለ፣ የከበደ ሐሳብ ሰቅዞ ይዞታል፡፡ አሁን እየተወዛገበ ያለው የዚችን ልጅ ታሪክ ልጻፈው ወይስ አልጻፈው በሚል ነው፡፡ ስሜቱ ውኃ ላይ እንደ ተጣለ ኩበት ሲዋልልበት ነው የዋለው፡፡
እንደ ደራሲነቱ ታሪኳን ሊጽፈው ይገባል፡፡ ቢያንስ ነገ ለሚታተመው ጋዜጣ መላክ ይችላል፡፡ ይህንን በማድረጉ ኅሊናው ዕረፍት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ኪሱም ገንዘብ ያገኛል፡፡ ገንዘብ ደግሞ ያስፈልገዋል። ስለዚህ መጻፍ አለበት፡፡ የዚች ሴት ታሪክ ደግሞ ይበልጥ ያጓጓል፡፡ ለመጻፍ ሲወስን ደግሞ ሌላኛው ልቡ አሻፈረኝ ይላል፡፡ መጻፍ አይፈልግም፡፡ የአንዲትን ድሃ ብሶት ጽፎ ገንዘብ የሚቀበለው እሱ ማን ስለሆነ ነው? ከኪሱ ስለጎደለበት ብቻ የአንዲትን ምስኪን ሕይወት ጽፎ አይሸጥም፡፡ ስለዚህ መጻፍ የለበትም፡፡
ሌሊቱ እየተጋመሰ ይመሥላል፡፡ መጻፍ ካለበት ጊዜው እየባከነ ነው፡፡ ከሌላኛው ክፍል ረዥም የሴት ልጅ ሳል ተሰማ። አንገቱን ቀና አድርጎ የበሽተኛዋን ሳል ማዳመጥ ጀመረ፡፡ በኃይለኛው ያስላታል። ‹ሲነሣብኝ ለትንፋሽ ጊዜ አይሰጠኝም፤ በጣም ያስለኛል›  ብላዋለች፡፡
አዘነላት፡፡
በጠዋት ቡና ሊጠጣ ነበር ወደ ደንበኛው የሄደው፡፡ ይህን ቡና ቤት የሚወደው ቡናቸው ስለሚስማማውና ቤቱ ጫጫታ ስለሌለበት ነው፡፡ ያዘዘውን ቡና ከመጎንጨቱ በፊት ነው ታማሚዋ ከአጠገቡ መጥታ የተቀመጠችው፡፡
‹‹እባክህ ቡና አጠጣኝ›› አለችውና እሽና እምቢታውን ሳታረጋግጥ ለአስተናጋጁ የአምጣልኝ ምልክት አሳየችው፡፡
‹‹ሳይህ ጨካኝ አልመሰልከኝም፤ ሌሎች ሰዎች እንዳሉም ዐይቻለሁ፡፡ …. ሆን ብዬ ነው ወደ አንተ የመጣሁት … ስለማትከለክለኝ›› ህመም ባኮሰመነው ድምጽዋ ፋታ እየወሰደች አወራችው። መልስ አልሰጣትም፡፡ የቀረበለትን ቡና ጨለጠና ሌላ አዘዘ፡፡
‹‹መስከረም እባላለሁ፡፡ …. ደራሲ አባት ነበረኝ፤ እርግጠኛ ነኝ ታውቀዋለህ›› አለችው፡፡ ተመስገን ዐይኑ ፈጠጠ፡፡ ትኩር ብሎ ተመለከታት፡፡ መቸም እያሾፈች አይደለም፡፡
‹‹ደራሲ አይደለህ?  የእኔን አባት በትክክል ታውቀዋለህ … እርግጠኛ ነኝ! ብዙ መጽሐፎቹ ይኖሩሃል የአባቴ….›› ንግግሯን አቋርጣ ፈገግ አለች፡፡ አስተናጋጁ ቡናውን አምጥቶላት ስለነበር ስኳር መጨመሩ ላይ ተመሰጠች፡፡
‹‹የኔ አባት…›› ቀጠለች.. ‹‹አዝናኝ ሰው ነበረ፡፡ ታምናለህ ሰላሳ መጻሕፍት አሳትሟል፡፡ ግን ችስታ ነበር፡፡ ሊሞት ሲል መታከሚያ ተለምኖለታል፡፡ ግን አልተረፈም፡፡ ለምን መሰለህ? ከመሞቱ በፊት ችስታ ስለነበር ሰውነቱ ተጎድቷል። …. አባቴ ያናድደኛል፡፡ …. ሞኝ ነበር ታውቃለህ… የዋህ ነው  ያናድዳል››  ፋታ ወሰደች፡፡
ቡናዋን ቶሎ ቶሎ ጨለጠች፡፡ ፊቷ በቅጽበት ፍክት ሲል ይታይ ነበር። ‹‹ልድገም?›› ጠየቀችው፡፡ ተመስገን ፈገግ ብሎ አንገቱን በአዎንታ አወዛወዘ፡፡ አውቋታል፡፡ እንዳለችውም የአባቷን ብዙ መጽሐፎች አንብቧል፡፡ ስለ ድህነቱም ያውቃል፡፡
‹‹አባቴ ያስጠላኝ ነበር›› ቀጠለች መስከረም፡፡
‹‹ለነገሩ አባቴ አይደለም ሥራው…ሙያው ነው የሚያስጠላኝ፡፡ ደራሲ ነኝ ይላል። …..ብዙ መጻሕፍት ጽፏል፡፡ ግን እናቴ ሁልጊዜ ሳንቲም ያጥራት ነበር፡፡ ….ለእኔ ምን እንዳወረሰኝ ታውቃለህ፡ ‹አንብቢ› ን ብቻ! እና እየራበኝ ብዙ መጽሐፍ አነባለሁ፡፡ ቁርስ ምሳ እራቴን አነባለሁ፡፡ አባቴ ረዥም ቁመቱ ታጥፎ እስኪጎብጥ ድረስ ….ከዘራ እስኪመስል ድረስ ያነብ ነበር፡፡ ሊሞት ሰሞን ምን ይመስል እንደነበር ታስታውሳለህ?››
ሁለተኛ ቡናዋን ማማሰል ጀምራለች። ተመስገን ድጋሚ ያዘዘውን ቡና አጋምሶታል። ‹‹ላጭስ?›› አለችው ድንገት፡፡
ከኪሱ ውስጥ የሲጋራ ፓኬት አውጥቶ ወደ እሷ ገፋላት፡፡
‹‹ድንቅ ሰው ነህ …. ለነገሩ ደራሲ አይደለህ? .. ለአባቴ ለቅሶ መጥተሃል? ታምነኛለህ ……. እኔ አልሄድኩም …. መቃብር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ሁሉ ‹አንብቢ› የሚለኝ ይመስለኛል›› መሣቅ ጀመረች፡፡ ከሣቋ ጋር ረዥም ሳል ያጣድፋት ጀመር፡፡ ፊቷ ቲማቲም መሰለ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ፈልጋለች፡፡ አልቻለችም፡፡
ተመስገን አንጀቱ ተንሰፈሰፈ፡፡ ቶሎ ሒሳብ ከፈለ፡፡ ‹‹እባክሽ ወደ ቤት እንሂድ፤ ትንሽ አረፍ ብለሽ እናወራለን››
እቤት እንደደረሱ ዘፍ ብላ ተኛች። እስካሁን አልነቃችም ነበር፡፡ አሁን ሳሏ ተነሥቶባታል፡፡
የረባ ምግብ አለመብላታቸውን አስታወሰ፡፡ ኪሱን ፈተሸ፡፡ የሚረባ ገንዘብ ኪሱ ውስጥ አልነበረም፡፡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ አዛጋ፡፡ ጎንበስ ቀና ብሎ ሰውነቱን ለማፍታታት ሞከረ፡፡ መስከረም ወደ ተኛችበት ክፍል አመራ፡፡ ትራሷን ከፍ አድርጋ ተቀምጣለች፡፡ ረዥሙ ሳል ለቀቅ አድርጓት ስለነበር ከላይ ከላይ ትተነፍሳለች።
‹‹መስኪ ደኅና ነሽ?››
‹‹እንዳባቴ አንድ ቀን እስኪወስደኝ ድረስ… ስማ ዕድሜዬ ስንት እንደሆነ ትገምታለህ?›› ያልተዘጋጀበት ጥያቄ ስለጠየቀችው ግራ ተጋብቷል፡፡ ፈገግ አለ፡፡ የእውነት ግን ስንት አመት ይሆናታል? ፈገግ አለ፡፡
‹‹ገምት አልቀየምህም›› አደፋፈረችው
‹‹ሰላሳ ሁለት››
‹‹ተሳስተሃል፤ ሃያ አመት አልሞልኝም። ….አባቴ በድህነት ስላሳደገኝ ተጎሳቆልኩ፤ እናቴን ብታያት ደግሞ የተወቀጠ ጋቢ ነው የምትመስለው… ልጅ አለህ?››
የረሃብ ስሜት እየተሰማው ስለነበር የሆነ ነገር መብላት እንዳለባቸው አሰበ፡፡ ኪሱ ውስጥ ያለው ገንዘብ ሁለት ደኅና ምግብ እንኳ የሚገዛ አይደለም፡፡ የግድ ታሪኳን መጻፍ አለበት፡፡ በነገው ጋዜጣ ላይ ጽሑፉ ከታተመ ማገገሚያ ገንዘብ ያገኛል፡፡
‹‹መልስልኝ እንጅ?›› መስከረም ነበረች ጠያቂዋ
‹‹አዎ የ6 ዓመት ልጅ አለኝ..ከእናቱ ጋር ይኖራል፡፡ እናቱ የእኔን ሙያ አትወደውም፤ ለዚያ ነው የተለያየነው፡፡››
‹‹ደግ አደረገች፡፡ ልታደንቃት ይገባሃል፡፡ ….. ደራሲ ባለ ዛር ነው፡፡ ከዛሩ ጋር ያብዳል እንጅ ሚስት ልጅ ብሎ አይጨነቅም፡፡ ምግብ አታበላኝም እንዴ?”
ኪሱ ውስጥ ያሉትን ብሮች አወጣና አሳያት፡፡
‹‹በቻለው ሁሉ እንበላለን! ምን እንብላ?››
‹‹ሌላ ብር የለህም?››
‹‹ምናልባት ነገ … ደሞዝ ከወጣ ይኖረኛል››
የአባቷን ህይወት እያስታወሰች ሳቀችበት። ድንገት የተመስገን ስልክ ጮኸች፡፡ የልጁ እናት ናት፡፡ ጩኸቷን አስቀድሞ ፈራው። … ግን ስልኩን አነሣው፡፡ ደረቁ ድምጽዋ በጆሮው ውስጥ ሲሠርግ በቆመበት ደነዘዘ፡፡
‹‹ልጅህ ልቡን አሞታል፤ ሆስፒታል ላስተኛው ብዬ 14ሺ ብር አስይዥ ብለውኛል። ቶሎ ድረስ!››
መስከረም ነገሩ የገባት ይመስላል፤ በረዥሙ ሳቅች፡፡ ረዥሙ ሳሏ እስኪነሣባት ድረስ፡፡


Read 1837 times