Print this page
Monday, 10 September 2012 13:43

የፕሬስ ወዳጆች!

Written by  ሰለሞን ከበደ
Rate this item
(0 votes)

በአንዳንድ የዲሞክራሲ መብቶች በተጠበቀባቸውና ህጎች ለሁሉም እኩል በሚተገበሩባቸው ሀገሮች ከታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር መነጋገርና ቃለ - ምልልስ ማካሄድ ለአንድ መሪም ሆነ ፖለቲከኛ እንደመታደል ይቆጠራል ይባላል፡፡መሪዎችና ፖለቲከኞች ጋዜጠኞችን ይፈልጓቸዋል፡ሁሉም ነገር ህግና ስርአቱን ጠብቆ ይከናወናል፡፡ ባለስልጣኖችም የስልጣኑን የገደቡን ልክ፣ ጋዜጠኛውም የጨዋታው ሜዳ የት ድረስ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ሁሉም ከመስመሩ ከወጡና ህጉን ከተላለፉ ምን እንደሚጠብቃቸው ያውቁታል፡፡ ህጉ የጋራ ነው፡፡ አያዳላም፡፡

በአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ መሪዎችና ባለስልጣኖች ከጋዜጠኞች ጋር አይጥና ድመት ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ መብቶችና የህጐች ልዕልና ያልተረጋገጠ በመሆኑ፣ ህጉና የጨዋታው ሜዳ ለመሪዎችና ለባለስልጣኖች ብቻ ያጋደለ ነው፡፡ በህግ መተላለፍ የሚጠየቀው ጋዜጠኛው ብቻ ይሆናል፡፡ በመሪዎችና በባለስልጣኖች የተፈፀመን ወንጀል ቢያጋልጥ የጉዳት ሰለባ የሚሆነው ወንጀሉን የፈፀመው ባለስልጣን ወይም መሪው ሳይሆን ወንጀሉን ያጋለጠው ጋዜጠኛ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ወንጀል ሆኖ የሚያስቀጣው ዘረፋው ሳይሆን ዘረፋውን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ እነኝህ ጋዜጠኞችን በውሃ ቀጠነ የሚያንገላቱ፣ አሳር መከራቸውን የሚያሳዩ መሪዎች እንዲህ አይነት ድርጊት ለምን እንደሚፈጽሙ ሲጠየቁ ታዲያ አንድ አስገራሚ መልስ ይሰጣሉ፡፡

“እኛ የፕሬስ ወዳጅ ነን” የሚል፡፡ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም CPJ የተባለው የጋዜጠኞች ጥበቃ ተሟጋች ድርጅት፣ የፕሬስ ጠላቶች ብሎ ካወጣቸው አስር የሀገራት መሪዎች፣ ለሶስት ተከታታይ አመታት ከተከሰሱት አንዱ የሆኑት የቱኒዚያው መሪ ዚን አልአብዲን ቤን አሊ፤ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ “ስለፕሬስ መታፈንና ስለጋዜጠኞች መጉላላት የምትሰሙት ሁሉ ውሸት ነው፡፡ የዚህ ሀገር ህግና መንግስታችንም ለዲሞክራሲ መብቶች መከበር ዘብ የቆመ ነው፡፡ እኛ የፕሬስ ጠላቶች ሳንሆን ይልቁንም ዋነኛ ወዳጆች ነን” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

ለዛሬ እንግዲህ እነኝህ የዲሞክራሲ ጠበቆችና የፕሬስ ወዳጆች የሀገሮቻቸውን ጋዜጠኞች እንዴት እንደሚያደርጓቸው የጥቂቶቹን መርጬ ላጫውታችሁ፡፡

ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተመረጡ ገና የቃለ-መሀላ ፊርማቸው ሳይደርቅ፣ የሀገር ሀብት ለመዝረፍና በጉቦ ለመበልፀግ ተጣድፈዋል፤ እየተባለ ባገሬው አፍ ውስጥ የገቡትና ይሄው ሀሜት እውነት ሆኖ በቅሌት ከስልጣናቸው ተባረው፣ ለዘብጥያ የተዳረጉት የቀድሞው የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ስትራዳ፤ ስልጣን በያዙ በሁለተኛ ሳምንታቸው የሀገሪቱን ጋዜጠኞች ሰብስበው በነፃነት እንዲሰሩና ሙስናንና ህገ-ወጥ የሆነን ነገር ሁሉ በንቃት እንዲያጋልጡ፤ ለዚህም መንግስታቸው ሙሉ ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ነገሯቸው፡፡ “በእኔ የስልጣን ዘመን” አሉ ፕሬዚዳንቱ “በእኔ የስልጣን ዘመን አንገቱን የሚደፋ የፕሬስና የሚዲያ ሰው ጨርሶ አይኖርም፡፡ የእኔ ዘመን አዲስ ዘመን ነው፡፡” በማለት አበሰሩ፡፡ የተሰበሰበው ጋዜጠኛ ሁሉ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ልቡ ተነክቶ በስሜት አጨበጨበላቸው፡፡ ከአምስት ወራት በኋላ በሀገሪቱ አሉ ከሚባሉ ከበርቴዎች ጋር በአንድ የምሽት የመዝናኛ ክበብ ጥንብዝ ብለው ሰክረው ከቆነጃጅት ጋር አጓጉል ሲዳሩ ያያቸው ጋዜጠኛ፤ ትዕይንቱን በካሜራው በድብቅ ቀርጾ ያስቀርና ለአለቃው ያቀርባል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያኔ ሰብስበው የነገሯቸውን ንግግር እውነት ነው ብሎ ያመነው አዘጋጅም፣ የሰውዬውን ሴሰኝነትና መጠጥ ደፋሪነት በManila Review የፊጽ ገጽ ላይ አወጣው፡፡ ህዝቡ ጋዜጣ ላይ ባየው ነገር አፍሮም ይሁን ደንግጦ ዝም ሲል ከምርጫው ዘመቻ ጀምሮ “ይህ ሰው ሰካራምና የለየለት ሴሰኛ ነው” እያለች ስትናገር የቆየችው የፊሊፒንስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን “ይሄው ያልኩት ደረሰ፤ ይህ ሰው የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ሳይሆን ማፈሪያዋ ነው” በማለት ነገሩን አጠነከረችው፡፡ በሁዋላ የቤተ-መንግስቱ ቃል አቀባይ በኮምፒውተር የተቀነባበረ ነው የተባለና ሙሽሮች የተጨመሩበት ያንኑ ፎቶ በመበተን “ፕሬዚዳንቱ እንደተባለው ሲዝናኑ ሳይሆን በጓደኛቸው ልጅ ሠርግ ላይ ተገኝተው ነው፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ለአንድ የሀገር መሪ መልካም አባትነትንና አርአያን ማሳየት ነው” በማለት አስተባበለ፡፡ ይህ በሆነ በአራት ቀናት ውስጥ የዚያ ጋዜጣ አዘጋጅ (ከተፈቀደው በታች መኪና ሲያሽከረክር በሌላ መኪና ተገጨ) ተባለና ሁለት እግሮቹንና የግራ እጁን አጥቶ በማኒላ ሉፓንግ ሆስፒታል በተሽከርካሪ ወንበር ታየ፡፡ ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችም ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡ ይህም ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በፊሊፒንስ የተገደሉትን ጋዜጠኞች ቁጥር 34 አደረሰው፡፡

በዮርዳኖስ የጆርዳን ታይምስ ጋዜጠኛ ስለ አየር ሁኔታ መግለጫ ለማውጣት ከውሀ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ እየተመላለሰ መረጃ ቢጠይቅ መልስ እያጣ፣ የወቅቱን የዝናብና አየር ሁኔታ መግለጫውን ጋዜጣው ላይ ማተም ያቆማል፡፡ አንባቢው ደግሞ “ምነው ይሄን መረጃ መስጠት አቆምክ?” እያለ ወጥሮ ይይዘዋል፡፡ የህዝቡ ውትወታ ፋታ የነሳው ጋዜጠኛም፤ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሄዶ ሲጠይቅ “ይህን መረጃ የሚሰጡትና የሚያውቁትም ሚኒስቴሩ ስለሆኑና እሳቸውም እስከ ቅዳሜ ድረስ ስለማይመጡ ታገስ” ይባላል፡፡ ሁኔታው ያስገረመው ጋዜጠኛም፤ የውሀ ባለስልጣኖች ቅዳሜ እለት እንዳሉት፤ “በሊቢያ በጉብኝት ላይ የሚገኙት ሚኒስትሩ ብቻ ናቸው፤ ባለፈው ሳምንት ምን ያህል ዝናብ እንደዘነበ የሚያውቁትና ለፕሬስ የሚናገሩት፡፡” በማለት ዘገበ፡፡ ሚኒስትሩ ከሊቢያ ሲመጡ ዘገባው ቀረበላቸው፡፡ ወዲያው ለአቃቤ ህጉ ደውለው ይህን ዘገባ ያወጣውን ጋዜጠኛ “ያለ ሚኒስትሩ ፈቃድ የሚኒስቴሩን መረጃ በማውጣትና በተከበረው የዮርዳኖስ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ በማላገጥ በሚሉ ክሶች ተከሶ በሶስት ወር እስራትና በአስር ሺ ዶላር እንዲቀጣ አስደረጉት፡፡

በ1990 ዓ.ም ኢራቅ ኩዌትን ከመውረሯ አስቀድሞ ሱሌማን አልዳኪልና ሙሐመድ ኦልአዋዲ ቤሲሶ የተባሉ የኦልኒዳ ጋዜጣ አዘጋጆች የኢራቅ ነገረ-ስራ አላምር ብሏቸው ሀገራቸው ኩዌት መዘጋጀት እንዳለባት በጋዜጣቸው ሲወተውቱ፣ ራሳቸው የኩዌት ኤሚር አልሳባህ ጠርተው “ይህን በሬ ወለደ ወሬ ስለ አላህ ብላችሁ ተውኝ” ሲሉ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ ኋላም ኢራቅ ኩዌትን ስትወር እነኝህ ሁለት ጋዜጠኞች በኢራቅ ወታደሮች እጅ ወደቁ፡፡ ወደ ኢራቅ ባግዳድ ተወስደው ለሁለት ወራት አሰቃቂ መከራ ከተቀበሉ በኋላ፣ እንደገና ወደ ኩዌት ተወስደው በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተቆልፎባቸው፣ ከባግዳድ ከባዝ ፓርቲ የሚመጣላቸውን ጽሁፍ በግድ እንዲያትሙ ተደረጉ፡፡ ያን ጊዜ የእነኝህ ሁለት ያልታደሉ ጋዜጠኞች ስራ፣ የመጣላቸውን ጽሁፍ የጋዜጣ ፅሁፍ መልክ መስጠት እንጂ አንዲት ቅንጣት ፊደል መጨመርም ሆነ መቀነስ አይችሉም ነበር፡፡

የኢራቅ ኃይል በአሜሪካ መራሹ የህብረት ጦር አሸንፎ ኩዌት ነፃ ስትወጣ፣ ከኋላ ተቆልፎባቸው የነበረውን የክፍላቸውን በር ሰብረው እንደወጡ ወደተቀረው የኩዌት ዜጋ መውጣታቸው በፈጠረባቸው ብርቱ ስሜት የደስታ እንባ አንብተዋል፡፡

ታዲያ ምን ያደርጋል፤ በደስታ ያነቡት እንባ ከፊታቸው ሳይደርቅ የኩዌትን ኤሚር ተከትሎ አብሮ ሸሽቶ በነበረውና ከኤሚሩ ኡዲ ጀት ጋር “በድል አድራጊነት” የገባው የደህንነት ኃይል “ከወራሪው የኢራቅ ጦርና መንግስት ጋር አብራችኋል፤ ሀገራችሁን በጽኑ ከድታችኋል” ተብለው ታሰሩ፡፡

በእስር ቤት ከሰው ተራ እስኪወጡ ድረስ በደልና ስቃይ ከተቀበሉ በኋላ፣ በጥድፊያ በተቋቋመ ፍርድ ቤት በሞት እንዲቀጡ ተበየነባቸው፡፡ ከፍርዱ በኋላ ምን እንደተሰማው በሌላ ጋዜጠኛ የተጠየቀው ሱሌማን አልዳኪል፤ ጥያቄውን በዝምታ በማለፉ እንደ ሌላ ወንጀል ተቆጥሮበት 15 ጅራፍ በተጨማሪ እንዲገረፍ ተፈርዶበት ነበር፡፡

እርሱ ግን የቀኝ መንጋጭላው አጥንቶች ሶስት ቦታ ላይ ተሰባብረው፣ አፉን መክፈት እንኳን አይችልም ነበር፡፡ በእነኝህ መከረኛ ጋዜጠኞች ላይ የተሰጠው የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት የተቀየረው በአለም አቀፉ ህብረተሰብ ግፊትና በአሜሪካ ውትወታ ነበር፡፡ ለመሆኑ እንደነሱ ያለ ክፉ እጣ የደረሰበት ሰው ሁኔታውን እንዴት ሊያሳልፈው ይችል ነበር?

በኩባ ያለው ሚዲያ በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑን መቼም ማንም አይስተውም፡፡ እንደኛ አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ አይነት ማለት ነው፡፡ “ካስትሮ እንዲህ አሉ፡፡” “እዚህ ሀገር ሄዱ፡፡” “ወደ ሀገራቸው መጡ፡፡” “የኩባ ኢኮኖሚ በ10 በመቶ አደገ፡፡” “አመራሩ የነጠረ ነው፡፡” “ኩባ ለኢምፔሪያሊዝም አትንበረከክም፡፡” “በዚህ ክፍለ ሀገር አንድ ድልድይ ተሰራ፡፡” “በዚህኛው ደግሞ አስር ምንጮች ጎለበቱ” … ወዘተ ዜና ያወጣሉ፡፡

እንዲህ አይነት የSociology Report ዜና ማውጣት የሰለቸውና የ2000 ዓ.ም የCPJ አለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ የሆነው ጂሰስ ጆል ዲያዝ ኸርናንዴዝና ጓደኛው የስርአቱንና የካስትሮን አመራር እንከኖች እየነቀሱ ለለውጥ መቀስቀስ ይጀምራሉ፡፡ ነገሩ አላምርህ ያለው መንግስት፤ ሁለቱን ጋዜጠኞች ያስርና ፍርድ ቤት ያቀርባቸዋል፡፡ አንደኛው ተከሳሽ ኸርናንዴዝ “ህገ-መንግስታዊውን ስርዓት ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ለመቀየር አሲረሀል” በሚል በአንድ አመት እስራት እንዲቀጣ ተፈረደበት፡፡

ሁለተኛው ተከሳሽ ጉለሆርም ሳቮን ግን የሚከሰስበት ምክንያት ቢጠፋ “በቤቱ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉን አሻንጉሊቶች አከማችቷል” በሚል ተከሰሰ፡፡

በፍርድ ቤቱ ይህ ክስ ሲነበብለት ነገሩ በጣም አስገርሞት ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ይሄኔ ጥሩ መክሰሻ ወንጀል ተገኘለት፡፡ “የተከበረውን የኩባ ፍርድ ቤት በመድፈርና በማዋረድ” በሚል እዚያው ተወንጅሎ በአንድ ወር እስራት ተቀጣ፡፡

በኢራቅ “አልታውራ” ጋዜጣ የአምድ አዘጋጅ የነበረው መሀመድ አልታይስ ጠሀ፤ ለስድስት ወራት እስራትና ከስራ ለመባረር የተዳረገው እርሱ በሚያዘጋጀው አምድ ላይ ያወጣው የፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ፎቶግራፍ “ትንሽና ኮስታራ ነው” በመባሉ ነበር፡፡

“ዩዴይ” የተባለው ጋዜጣ ፎቶግራፈር የነበረው ጀማል ሁሴን አቡበከር፤ የፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴንን የልደት በዓል አስመልክቶ ለሚታተመው ልዩ እትም ትልቅ ፎቶግራፍ ለማውጣት በጋዜጣው ስቱዲዮ ሲያዘጋጅ ያጨሰው የነበረው ሲጋራ አመድ፣ ተመርጦ ለህትመት ከተዘጋጀው የሳዳም ፎቶግራፍ ላይ ይራገፋል፡፡

በሁኔታው የደነገጠው አቡበከር እየተርበተበተ አመዱን በእጁ ከፎቶው ላይ ለማራገፍ ሲሞክር፣ እጁ ከድንጋጤው የተነሳ አልቦት ኖሮ አመዱ የበለጠ ይለቀለቃል፡፡

በዚህ መሀል ቀኑ ለአቡበከር ክፉና የተረገመ ነበርና በጭካኔው የሚታወቀውና የጋዜጣው ባለቤት የሳዳም የመጀመሪያ ልጅ ኡዴይ መጣና የሆነውን ሁሉ አየ፡፡ እንደ መልካም አለቃ ኡዴይ፤ አቡበከር ፎቶውን እንዲቀይረውና ሳይደናገጥ እንዲሰራ አበረታቶት ወጣ፡፡

ይሁን እንጂ ከሚቀጥለው ቀን ምሽት ወዲያ ያን ምስኪን ፎቶግራፈር ጀማል ሁሴን አቡበከርን አይኑን አየሁ፤ ድምፁንም ሰማሁ የሚል ሰው አልተገኘም፡፡

በኢራቅ የሚገኘውን የሚዲያ ተቋማት በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ኡዴይ ግን “ሀቀኛና ነፃ ንግግር እንዲከበር ላበረከቱት ቀልጣፋና የመጠቀ አገልግሎት” በሚል “የኢራቅ የሚዲያ ቤተሰብ ጋዜጠኛ” ተብሎ ተመረጠ፡፡ አጃኢብ ነው፡፡

በእርስ በርሱ ጦርነት ጊዜ ቻርለስ ቴይለር እንዴት አይነት ሰው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ጋዜጠኞች፤ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ምንም ለውጥ እንደማያመጡ ገምተው፣ አፋቸውን ዘግተው ተቀምጠው ነበር፡፡ በህገ-ወጥ ጦር መሳሪያና አልማዝ ንግድ ሳቢያ አለም አቀፍ ጫና ሲበረታባቸው፣ ያኔ አድብተው የነበሩት ጋዜጠኞች የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመሩ፡፡

ደፈር ብለውም “ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዴት ሳይታሰብ በድንገት ሊሞቱ ቻሉ?” በማለት በጥያቄ መወጠር ያዙ፡፡ ፕሬዚዳንት ቴይለርም የአንዱን ታዋቂ ጋዜጣ አዘጋጆች በሙሉ በቤተ-መንግስታቸው ሰበሰቡና ቡና ጋብዘው “ጥረታችሁ ጥሩ ነው፡፡ ስለ ዲሞክራሲም ማንሳታችሁ ድንቅ ነው፡፡ ግን ከጳጳሱ የበለጥን ካቶሊክ ነን ማለታችሁን ተውኝ፡፡ እኔ አዲስ ዲሞክራት አልወድም ገባችሁ ልጆች?” አሏቸው፡፡

ከፊት ለፊታቸው የተሰቀለውና በጦርነቱ ጊዜ በረሀ እያሉ ከጀሌዎቻቸው ጋር ላውንቸር ይዘው የተነሱትን ትልቅ ፎቶግራፍ እያሳዩ፡፡ ጋዜጠኞቹ የፕሬዚዳንቱ መልዕክት በትክክል ገብቷቸዋል፡፡

በሚቀጥለው ወር ሁሉም እንዳሉ ነብሴ አውጪኝ ብለው ከአገር ኮበለሉ፡፡ በበርማ ደግሞ የወታደራዊ መንግስት የፕሬስ ጭቆና አያድርስ ነው፡፡ ዜና መቀበልም መላክም ክልክል ነው፡፡ የውጪ ሬዲዮ በግልጽ መስማት በእስር ያስቀጣል፡፡

አንድ የበርማ ፍርድ ቤት ቺንግ ፓህ የተባሉትን አዛውንት የ77 አመት ጽኑ እስራት ቀጣቸው፡፡ ቺንግ ፓህን ለዚህ የእስር ቅጣት ያበቃቸው ጥፋት ግን ከአንድ የምዕራብ ዲፕሎማት ያገኙትን ስለ ስኳር በሽታ የሚያወራ የሄራልድ ትሪቢውን ጋዜጣ ቁራጭ ፎቶ ኮፒ አድርገው፣ በስኳር በሽታ ለሚሰቃዩ ሶስት ጓደኞቻቸው በመላካቸው ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው “የዲሞክራሲ ጠበቃና የፕሬስ ወዳጅ ነን” እያሉ በሚምሉና በሚገዘቱ መሪዎች ነው፡፡

እኔ ይህን ያህል ስለ “ፕሬስ ወዳጆች ካወጋኋቸው የኛን ሀገርና የሌሎችንም የምታውቁ ደግሞ ጨምሩበት፡፡

በመጨረሻ ግን ከሁሉም በተለየ መልኩ ቁም ነገረኛ፤ ነገር ግን ቀልደኛና እጅግ ምርጥ የአፍሪካ ልጅ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ስለ ትዳራቸው በወፈ-ሰማይ ጋዜጠኞች ተጠይቀው የመለሱትን ልንገራችሁ፡፡

ማንዴላ ከግራሻ ማሼል ጋር ወጣ-ገባ ማለት ጀምረው “ሊጋቡ ነው” እየተባለ ይታሙ ነበርና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጋዜጠኛው ሁሉ ይጠይቃቸው ነበር፡፡ እናም አንድ ቀን ያገር ጋዜጠኛ ከበባቸውና “ግራሻ ማሼልን አግብተው ሊሞሸሩ ነው አሉ፤ እውነት ነው ወይ?” በማለት ይጠይቋቸዋል፡፡ እሳቸውም በተለመደው ለዛ ያለው ተረባቸው “መቸም ለእኔ እንዲህ መጨነቃችሁ የሚያስገርም ነው፤ ልጅነታችሁና ወጣትነታችሁ ደስ ይላል፡፡

ይሁን እንጂ እኔ ባደግሁበት ወግና ባህል መሠረት ጋብቻን ያህል ትልቅ ቁም ነገር ለልጆች አይነገርም” በማለት ጋዜጠኛውን ሁሉ በሳቅ ገደሉት፡፡ የእነማንዴላን ዓይነት መሪዎች ማግኘት እንችል ይሆን?

 

 

Read 1930 times Last modified on Monday, 10 September 2012 13:46