Saturday, 18 September 2021 17:04

ችግራቸውን ወደ መልካም አጋጣሚ የለወጡ ወላጆች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “ፓሽን አካዳሚ” ትልቅ ሆኖ እንዲቀጥል እንሰራለን

            ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም የዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ  ተማሪዎች (ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል) አንድ የታሸገ ፖስታ ለወላጆቻቸው እንዲያደርሱ ከአካዳሚው አስተዳደር ተሰጣቸው  ፖስታውን እንዳይከፍቱ ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋር፡፡ ተማሪዎቹ እንደተባሉት አደረጉ፡፡ ፓስታው ግን ለወላጆች መልካም ዜና አልነበረም ያደረሳቸው፡፡ ዱብዳዕዳ ነበር፤ ፈፅሞ ያልጠበቁት አስደንጋጭ ዜና፡፡ “የ2014 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት በዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ ቅርንጫ ስለማይቀጥል፣ለልጆቻችሁ ት/ቤት ፈልጉ” የሚል ነበር፤ በማስጠንቀቂያ ታጅቦ ለቤተሰብ የደረሰው ፖስታ፡፡ የልጆቻቸውን የትምህርት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ትልቅ ተቋም ወላጆችን ሳያማክር በቁራጭ ወረቀት ፅፎ መላኩ በእጅጉ አሳዝኖአቸው እንደነበር ያስታውሳሉ የተማሪዎቹ ወላጆች፡፡ ይህን ተከትሎ ወላጆች ልጆቻቸውን ላለመበታተንና በለመዱት ት/ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ የበርካታ የመንግስት መ/ቤቶች በርን አንኳኩተዋል፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችንም አልፈዋል፡፡ ጥቂት ወላጆችም በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው ልጆቻቸውን በሌሎች ት/ቤቶች አስመዝግበዋል፡፡ በጽናት የቆሙትና የቻሉት ወላጆች ግን የማታ ማታ ያልጠበቁትን ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ቸግራቸውን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረዋል፡፡ ወላጆቹ ባለፉት 3 ወራት ያሳለፉት ውጣ ውረድ ምን ይመስላል? በመጨረሻስ ያገኙት ድል ምንድን ነው? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የወላጅ ኮሚቴ አባል፣ አዲስ የተመሰረተው አክስዮን ማህበር የቦርድ አባልና የሚዲያ ዘርፍ አስተባባሪ  ከሆኑት ወ/ሮ ሳባ ሀይለማሪያም ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡


            አስኪ ስለ እርስዎ ትንሽ ያጫውቱኝ ስንት ልጆች ነበር በዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ያስተምሩ የነበረው?
የአራት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ሶስቱ ልጆቼ በአካዳሚው ለሁለት ዓመታት ሲማሩ ነበር። አራተኛውም ልጄ በጀመርነው ዓመት ፕሪኬጂ ሊገባ በዝግጅት ላይ ነበርን። ከዚህ ቀደምም ስንጮህ እንደነበረው ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ምንም ባልጠበቅነውና ባላሰብነው መልኩ ደብዳቤ ደረሰን፡፡
ደብዳቤው በትክክል ምንድን ነው የሚለው?
“ኤልፎራ ግቢውን ለሌላ ጉዳይ እፈልገዋለሁ ስላለ በ2014 ዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ ቅርንጫፍ ማስተማር አይቀጥልም” ነው የሚለው፡፡ ከዚያም በኋላ በማግስቱ ት/ቤት ሄደን፣ ምንድን ነው የተፈጠረው ብለን ለመጠየቅ ስንሞክር፣ የት/ቤቱን በር ዘግተው ማንም ሊያናግረን አልፈለገም፡፡ ወላጅ ተንጫጫ፡፡ ወላጅ ተጠርቶ ውይይት ሳይደረግ እንዴት በልጆች ይላካል ብለን ብንጮህ የሚሰማን ጠፋ፡፡ ልጆቻችን እቤት መጥተው “አባዬ እማዬ ይህን ደብዳቤ በፍፁም  እንዳትከፍቱ ለቤተሰቦቻችሁ ስጡ ተባልን፤ ምንድነው ደብዳቤው” ብለው ጠየቁን፡፡ ነገር ግን “ቦንብህን ይዘህ ሂድ ተባብለው ነው ልጆቹ ከት/ቤት የወጡት፤ ከkg -12ኛ ክፍል ያሉ የተለያየ እድሜ ላይ ያሉ ልጆች ናቸው በዚያ ት/ቤት ውስጥ ያሉት፤ “ቦንብህን ይዘህ ሂድ” ሲባባሉ ግራ የተጋቡም ነበሩ፡፡ በጣም በሚያሣዝን ሁኔታ ደብዳቤው ፕሪኬጂ ለነበሩ ህፃናትም ነበር የተሠጠው፡፡ እኔ በተማሪዎችና በወላጆች ላይ የተፈፀመብን ግፍና መገፋት ከዚህ በፊት ተፈጥሮ ሰምቼ አላውቅም፤ በጣም አስቆጥቶንም አሳዝኖንም ነው ያለፈው፡፡
ከዚያ በኋላ ህጉ ምን ይመስላል? መንግስት ጉዳዩን እንዴት ነው የሚያየው? ብለን መታገል ጀመርን፡፡ ብዙ የመንግስት መስሪያ ቤት በሮችን አንኳኩተናል፤ ብዙ ወጥተናል ወርደናል፡፡ በዚህ ሂደት አዲስ አድማስን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች ከጎናችን ነበሩ፡፡ ጉዳዩን ከጅምሩ አንስቶ ያውቁታል፡፡ ሆኖም መልስ ማግኘት አልቻልንም፡፡ በተለይ በዩኒቲ አካዳሚ አመራሮች በእነ ዶ/ር አረጋ በኩል ሁሉም ነገር ዝግና ድፍን ነበር፡፡ በሬዲዮም  በቴሌቪዥንም ቀርበው መልስ እንዲሰጡን ጥረት አደረግን፡፡ ዶ/ር አረጋ ጭራሽ ስልካቸውን አጥፍተው አሜሪካ ገቡ። የእርሳቸውን ተወካዮች እነ ዶ/ር ብርሃኑን ጠየቅን፤ ፈፅሞ ምላሽ ሊሰጡን አልፈለጉም፡፡
ት/ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ያቆመበት ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?
እንግዲህ ከዩኒቲ መልስ ስናጣ ፊታችንን ወደ ኤልፎራ ነው ያዞርነው፡፡ ለኤልፎራ በምን ምክንያት ነው ልጆቻችን እንዳይማሩ የተደረጉት ብለን ስንጠይቅ፣ ከኤልፎራ ያገኘነው ምላሽ፣ ዩኒቲ አካዳሚ ያንን የሚያክል የተንጣለለ ግቢ ላለፉት አምስት ዓመታት በወር 50 ሺህ ብር እየከፈለ፤ ነበር የቀጠለው፡፡ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድና የኤልፎራ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ እነሱ ወደ አመራርነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ኦዲተር መጥቶ ጉዳዩ ሲታይ ያንን የሚያክል ወደ 22 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በ50 ሺህ ብር ለዩኒቲ አካዳሚ ማከራየታችን ተዓማኒነት አላገኘም ነው ያሉን፡፡ እናም ይህ ቦታ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኪራይ ስንት ያወጣል የሚለውን አስጠንተው 2.3 ሚ ብር በወር መከራየት ይችላል የሚለውን ውጤት ካገኙ በኋላ ቦታው ይሄን ያህል እንደሚከራይ በባለሙያ ተጠንቷል፤ ሆኖም ይህንን ያህል አንጠይቃችሁም፤ ባይሆን 1.3 ሚ ብር በወር ክፈሉ” ተብለው ዶ/ር አረጋ ሲጠየቁ፤ “በፍጹም አልሞክረውም” ብለው ማስተማር ማቆማቸውን ነው ከኤልፎራ የሰማነው፡፡ ወደ ዘጠኝ ጊዜ ደብዳቤ ፅፈውላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ዶ/ር አረጋ ይህንን አልቀበልም ማለታቸውንም ነው ጨምረው የነገሩን፡፡ በዚህ ሂደት ዶ/ሩ የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን የካቲት አካባቢ ሌላ ህንጻ ተከራይተው አስወጡና እኛን ሰኔ 3 ቀን በደብዳቤ አሰናበቱን ማለት ነው፡፡
ወቅቱን አስቢው፤ ተማሪዎች ፈተና የሚፈተኑበት ወቅት ነበር፡፡ ለምሳሌ እኔ 8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ የምትፈተን ልጅ አለችኝ፤  ፈፅሞ በተሰበረና ባዘነ ልብ ውስጥ ሆና ነው የተፈተነችው፡፡ ይሄ ሁሌም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው፡፡  በውጤቷም ላይ ተፅዕኖ አሳድሮባታል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከሁሉም የሚሳዝነው 1 ሺህ 420 ተማሪ፣ ያለ ወላጅ ውይይት በንቀት በቁራጭ ደብዳቤ መበተኑ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ወደ በርካቶቹ የመንግስት ሚዲያዎች ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ጉዳያችንን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ አልሆኑም ይሄም ከምናዝንባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ እስከሚገባን ድረስ የሚዲያ ተግባር የህዝብን እሮሮና ድምፅ ማሰማት ነው፡፡ ብዙዎቹ ይህንን አላደረጉም፤ እናዝናለን፡፡ የቀደሙት የወላጅ ኮሚቴዎች አስፈላጊውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ፅፈዋል፤ ነገር ግን መልስ አላገኙም፡፡
እናንተ አዳዲስ የኮሚቴ አባላት ናችሁ ማለት ነው?
እኛ በጎ ፈቃደኛ የወላጅ ኮሚቴዎች ነን፡፡ የበፊቶቹ ኮሚቴዎች ጉዳዩ ተስፋ  አስቆራጭና ያልተሳካ በሆነበት ሰዓት እኛ በበጎ ፈቃደኝነት ተሰብስበን እኛ ስራችንንም ትተን ጥግ ድረስ እስከ መጨረሻው ሄድን፤ መብታችንን እናስከብራለን እንጂ መብታችንን ከሰው አንለምንም በማለት እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ ለሶስት ወራት ያህል መራር የሆነ ጊዜ ነው ያሳለፍነው፡፡  ጉዳዩን አንቺም ስትከታተይው ስለነበር በደንብ ታውቂዋለሽ ብዬ አስባለሁ፡፡
እስኪ መፍትሔ ለማግኘት የት የት ሄዳችሁ? ምንስ አደረጋችሁ?
በጣም ብዙ ቦታ ነው የረገጥነው፡፡ እርግጥ ጉዳዩ የሚመለከተው አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ነው፤ እዚያ አመለከትን፡፡ ትምህርት ቢሮ “አግባብ አይደለም፤ ተማሪ መበተን የለበትም” አለ፡፡ ከዚያ ትምህርት ጥራትና ምዘና ሄድን፡፡ ክብርት ከንቲባ ቢሮ ሄደናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ ፓርላማ አመልክተናል፡፡ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ደብዳቤ ፅፈናል፡፡ “እርስዎ በየክፍለ ሀገሩ ት/ቤት እያስገነቡ እዚህ መሃል ከተማ ልጆቻችን ትምህርት ቤታቸው ተዘጋ” ብለን ማለት ነው፡፡  ብቻ ያልሄድንበት ያላንኳኳነው በር የለም፡፡
ክብርት ከንቲባ አዳነች አበቤ ጋር ልጆቻችንን ይዘን ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ነበር ያሰብነው አገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ሰልፉን ማድረጉ አግባብ እንዳልሆነ ገልፀው መለሱን፡፡ ከከንቲባ ፅ/ቤት አስቀድመን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ቢሮ ሄደን ነበር፡፡
ዩኒቲዎች ወላጆችን ሰብስበው  ሳያነጋገሩ ሲቀሩ፣ ራሳችን ስብሰባ አዘጋጅተን የሚድሮክ ሀላፊዎችንም የዩኒቲ አካዳሚ  ሀላፊዎችንም ጠርተን ነበር፡፡ ሃላፊዎቹ አልተገኙም፤ ግን እኛ ቀጥሎ ምን እናድርግ የሚለውን ለመወሰን ከሁሉም ወላጆች ጋር መጀመሪያ የተገናኘነው በአዳራሽ ስብሰባ ነው፡፡ በአዳራሹ ስንወያይ ተጨማሪ ክፍያም ከሆነ ጨምረን ከፍለን ልጆቻችን ትምህርታቸውን ከለመዷቸው  ጓደኞቻቸውና በለመዱት ት/ቤት እናስቀጥል ወይስ ምን እናድርግ በሚል ተወያየን፡፡ ከዚያ በኋላ “ስብሰባ ላይ ጠርተናችሁ ቀራችሁ፤ ችግሩ ገንዘብ ከሆነ ንገሩንና መጨመር ያለብንን እንጨምር፤ ካልሆነ ዩኒቲ አካዳሚ ት/ቤቱን የማይፈልገው ከሆነ ወላጅ ተከራይቶ ይዞ ልጆቹን የሚያስቀጥልበት እድል ይመቻችልን” አልን፡፡ ከእነ አቶ ጀማልም መልስ አላገኘንም፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ክብርት ከንቲባ ቢሮ የሄድነው። እዛ መመላለስ ጀመርን፤ በየቀኑ ማለት ነው፡፡ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ የከንቲባ ፅ/ቤት ችግራችንን ተረድተው ወደ መደራደር ተገባ ማለት ነው።
ድርድሩ ምን ይመስላል? ማን ከማን ጋር ነው የተደራደረው?
መጀመሪያ የትምህርት ቢሮ ምን አለ? “ዩኒቲ አካዳሚ  መቀጠል አለበት፤ ይሔ ከኤልፎራ  የማይጠበቅ ነው፡፡ ዩኒቲ ልጆቹን በትኖ ባለቀ ሰዓት መሄድ የለበትም” የሚል ደብዳቤ ፃፈልን፡፡ በዚህ ወላጅ ሁሉ ተደስቶ ነበር፡፡ እኛ በየሚዲያው ትምህርት ቢሮንና እነ አቶ ዘላለምን አመስግነን ልንረጋጋ ስንል፣ የልጆቻችንን ውጤት በአግባቡ ሳይሰጥና ሳያጠቃልል ዩኒቲ አካዳሚ እቃውን ጭኖ ወጥቷል፡፡ ያን ጊዜ የተፈጠረው ቀውስና የወላጅ ብስጭት በጣም ከባድ ነበር፡፡ ልጆቻችን ላይ የፈጠረው ስነ ልቦናዊ ጫና በእጅጉ አሳዛኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ተመልከቺ፤ ዩኒቲ አካዳሚዎች ለመንግስትም የሚታዘዙ አልሆኑም፡፡
ከዚህ በኋላ ነው በድጋሚ ከፍተኛ ትግል የጀመርነው፡፡ የክብርት ከንቲባ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ጋ ስንሄድ፣ “ይህ ጉዳይ የሚመለከተው አዲስ አበባ ት/ቢሮን ነው፤ እንዴት ወደኛ መጣችሁ” አሉን፡፡ ትምህርት ቢሮ የፃፈውን ደብዳቤና  የዩኒቲን እንቢተኝነት አስረዳን፡፡ ከዚያም ትምህርት ቢሮ ይህንን የማይችል ከሆነ ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን በደብዳቤ ይግለፅልን አሉ፡፡ትምህርት ቢሮ ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ነው የሚል ደብዳቤ ለከንቲባ ፅ/ቤት ፃፈልን፤ ያንን ደብዳቤ  ይዘን ወደ ከንቲባ ፅ/ቤት መጣን ማለት ነው፡፡ ከንቲባ ፅ/ቤቱ ምን አለ? “ይሄ የተከራይና  የአከራይ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን የአንድ ሺ አራት መቶ ሀያ ተማሪ መበተንና የቤተሰብ ቀውስ የከተማ አስተዳደሩም ይመለከተዋል” አሉና ለክብርት ከንቲባ አዳነች አበቤ አማካሪ ለአቶ ዮሀንስ ምትኩ መሩን፡፡ አማካሪው ይህን ውጣ ውረድ ሲሰሙ በጣም አዘኑ፡፡ በዚህ በኮቪድ ወቅት ይህ ሁሉ ተማሪ እንዴት ይበተናል አሉ፡፡ በመጨረሻም የሚድሮክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል፣ የዩኒቲ ሀላፊዎችና የወላጅ ኮሚቴዎች  ተጠርተን አንድ ላይ ፊት ለፊት ልንነጋገር ቀጠሮ ተያዘ፡፡ በቀጠሮአችን ስንቀርብ አሁንም የዩኒቲ ሀላፊዎች ሊገኙ አልቻሉም፡፡
አቶ ጀማል በቀጠሮው ተገኙ?
አቶ ጀማል የዩኒቲ ኃላፊዎች በተገኙ ሰዓት ጥሩኝ እመጣለሁ አሉ፡፡ ነገር ግን የዩኒቲ ሀላፊዎች አልተገኙም፡፡ ሌላ ቀጠሮ ተሰጠን፡፡ ዩኒቲዎች እንዲገኙልን እኛ በአካል ሄድን፤ የዶ/ር አረጋን ምክትል ዶ/ር ብርሀኑን ተማፀንን፤ በፅሁፍም ጠየቅን፤ እንገኛለን ብለው ቃል ገቡ፤ ግን አሁንም በቃላቸው አልተገኙም፡፡ ስልካቸውንም አጥፍተዋል፡፡ ይሄ ከሃላፊነት  ያፈነገጠና የማይጠበቅ ምግባር ነው በጣም ነው፤ የምናዝነው፡፡ በዚህ ጊዜ እኛ ለከንቲባው ፅ/ቤት ሌላ አማራጭ አቀረብን፡፡ ዩኒቲ ፍቃደኛ ካልሆነና ሀላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ “ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ  የነበረውን እንከራይና በወላጅ የሚተዳደር ት/ቤት እንፍጠር፤ አክሲዮን ተመስርቶ በቦርድ ይተዳደር” የሚል ሀሳብ አቀረብን፡፡ “ከንቲባ ፅ/ቤት ለዚህ ጥያቄያችሁ መልስ ሊሰጥ አይችልም፤ ነገር ግን ለሚድሮክ የትብብር ደብዳቤ ይፅፍላችኋል” አሉን፡፡ ይህን ያሉን የከንቲባ ፅ/ቤት ሃላፊው አቶ ጥላሁን ወርቁ ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በወላጅና በልጆቻችን ስም ይህን ቅንና የህዝብ አገልጋይ ሰው ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ሌላ ስራ ላይ ተጠምደው ቆይተው ደብዳቤውን ሳንይዝ እንዳንወጣ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አምሽተው ነው የፃፉልን፡፡ ምከንያቱም በዚያን ቀን ልጆቻችን የደንብ ልብስ ለብሰው ወላጆችም  ተሰብስበው “እባካችሁ መልስ ስጡን” እያሉ ሲማጸኑ ነበር የዋሉት፡፡ ይህ ነገር በጣም ስለተሰማቸው ተነጋግረውበት ወደ ማታ መጥታችሁ ደብዳቤ ውሰዱ ብለውን ነበር። 11፡30 አመሻሽ ላይ ስንሄድ እርሳቸው ስብሰባ ላይ ነበሩ፤ እና ጠብቀን ጠብቀን ወጡ፤ እስከ 2፡30  ፀሃፊያቸው ሳትቀር አምሽታ ደብዳቤውን ሰጡን፤ በዚህ እጅጉን ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡ በመንግስት መ/ቤት እንኳን እስከ 2፡30 እስከ 12፡00 ያመሻሉ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ከከንቲባ ፅ/ቤት የተደረገልን ነገር ትልቅ ነው፡፡ ለህዝብ መቆማቸውንም በሚገባ ተረድተናል፤ እናመሰግናለን፡፡
ከዚያስ?
በነጋታው ደብዳቤውን ይዘን አቶ ጀማል ቢሮ ሄደን አገኘናቸው፡፡ በሚዲያ ይወራ በነበረው ያልተገባ ነገር፣ ሼህ መሀመድ አላሙዲም አዝነዋል አሉን፡፡
ያልተገባ ነገር የተባለው ምን ነበር?
እርግጥ እኛ የወላጅ ኮሚቴዎች በተገቢው መንገድ ነበር ስንጓዝና ጥያቄ ስናነሳ የነበረው። እያንዳንዱን እንቅስቃሴና ጥያቄ በደብዳቤ አስደግፈን ስንጠይቅ ነበር፤ ያስገባነው ደብዳቤ በፀሀፊያቸው ተፈርሞ ቀሪው ሁሉ አለን፡፡ እኛ አላማችን  ለልጆቻችን ፍትህ  ማስገኘት ብቻ ነበር  እንጂ ሌላ የተለየ አጀንዳ አልነበረንም፤ ነገር ግን በወላጅ ስም ከጀርባ እየሄዱ ያልተገባ  ነገር  ለሚዲያ ሲሰጡ የነበሩ ሰዎች ይሆናሉ ያሳዘኗቸው፤ ነገር ግን  ይቅርታ ጠይቀናቸዋል፡፡
ባካሄዳችሁት ዘመቻ በጣም መነጋገሪያ የነበረው “ደማችን ለሰራዊታችን፤ ፍትህ ለልጆቻችን” በማለት በቀድሞው ዩኒቲ አካዳሚ በር ላይ ያደረጋችሁት የደም ልገሳና የአልባሳት ድጋፍ ነበር፡፡
እውነት ነው፤ እኛ ለልጆቻችን ፍትህ ለማግኘት የግለሰቦችን በር በርካታ ጊዜ ስናንኳኳ፣ ምላሽ ሳናገኝ አክብሮ መልስ የሰጠን መንግስት ነው፡፡ ያውም አገሪቱ በዚህ ጭንቅ ላይ እያለች ጆሮ ሰጥተው ስላስተናገዱን፣ እኛስ ምን እናግዝ ስንል መከላከያችን ደሙን ለሀገር እያፈሰሰ ነው ህይወቱን እየሰጠን ነው፤  ደም በመለገስ የበኩላችንን እያደረግን ፍትህ መጠየቃችንን እንቀጥላለን በሚል፤ ቀይ መስቀሎችን ጠርተን በርካታ ዩኒት ደም  ለግሰናል፡፡ ልጆቻችን መስጠትና ማካፈልን እንዲለምዱና እንዲማሩ፣ የራሳችንንም የልጆቻችንንም  ልብሶችና ጫማዎች ለጎዳና ወገኖቻችን ለግሰናል፡፡ ቀሪውን በትልልቅ ማዳበሪያ ሞልተን ሰለሞን ለተባለ ልበ ቀና፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ገላ በማጠብ ፀጉር በመቁረጥና አልባሳትን በመለመን በጎ ለሚያደርግ ሰው አስረክበናል፡፡ ይሄ በእጅጉ የምንኮራበት ተግባራችን ነው፡፡ በዚህ በጎ አድራጎትም እንደምንቀጥል ቃል ገብተናል፡፡
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ታልፎ “ፓሽን አካዳሚ” ተወልዷል፤ ልጆቹም በቀድሞ ግቢ እንዲማሩ ስራ ተጀምሯል፡፡ ከኤልፎራ ጋር ያላችሁ ስምምነት ምን ይመስላል?
የትብብር ደብዳቤውን ይዘን ከአቶ ጀማል ጋር ከተገናኘን በኋላ እነዛ ከእኛ ጀርባ ሆነው የሚድሮክን፣ የአቶ ጀማልንም ሆነ የሼህ መሃመድን ስም ለማጥፋት የሚሯሯጡ አካላት እንደነበሩ ደረስንበት። ተግባባን። ህጋዊ  ንግድ ፈቃድ አወጣን። አክስዮን አቋቋምን ፓሽን አካዳሚን መሰረትን፡፡ ነ
ሀሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከኤልፎራ ጋር ተፈራረምን፡፡ አሁን  በቀድሞ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የማስተማሪያ  ቦታ ላይ ልጆቻችንን ለማስተማር  ምዝገባ ጀምረናል። ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ጎን ዳሽን ባንክ በር ላይ ምዝገባ እያካሄድን ብሩን ዳሽን ባንክ ያስገባሉ፡፡
እዛው ልጆቻቸውን ያስመዘግባሉ። በዚህ ላይ ነው ያለነው፡፡  ልጆቻችን ያደጉበት ግቢ፣ ዩኒቲ ኪራይ አልጨምርም ሲል ለሌላ ት/ቤት አከራይተውታል፡፡ ነገር ግን በዚያው ግቢ ኩዊይንስ ጎን ያለውን ወስደን ስራ ጀምረናል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ  ወላጆችን ስሜት  ያጋሩን እስኪ?
ወላጆች እጅግ ተደስተዋል፤ እጅግ ኮርተዋል፡፡ በኔ በኩል እንዲህ አይነት ፈተና ሲገጥመኝ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በጣም ከባድ ነበር፤ ነገር ግን የሆነ  ተግዳሮት ሲፈጠር  ማንም ቢሆን፣ በምንም ጉዳይ ቢሆን it is ok  ብሎ ማለፍ የለበትም። እስከመጨረሻው ለመብትና ለመፍትሔ ታግለን ያመጣነው ውጤት ለሌላው ምሳሌ ይሆናል በሚል ነው ይህን ለአዲስ አድማስ የምንገልጸው፡፡ ተስፋ ቆርጠው ልጆቻቸውን ሌላ ት/ቤት ያስመዘገቡ ወላጆች እኮ አሉ፡፡ አሁን ለእነሱም ጥሪ እያደረግን ነው “የከፈላችሁበትን  ደረሰኝ ይዛችሁ መጥታችሁ ወጪውን ተጋተርተን፣ ልጆቹ ከጓደኞቻቸው ጋር ትምህርታቸውን ይቀጥሉ” እያልን ጥሪ እያስተላለፍን ነው፡፡ በዚህ መሃል ትምህርት ከሸቀጥ እኩል  ፈቃድ የሚወጣበት ዘርፍ መሆኑን ተረድተናል፡፡ በሂደት ይህ ህግ እንዲሻሻል እንሰራለን፡፡ ህጉን ያወጣው ሰው ነው የተሻለ ሀሳብ ያለው ሰው ይህን ህግ ያስቀይረዋል ብለን እንምናለን፡፡ በመጨረሻም፤ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ አብረውን የነበሩትን ሚዲያዎች እንደ ኢሳት፣ አዲስ አድማስ፣ አሃዱ ሬዲዮ እና ሌሎችንም የኦን ላይን ሚዲያዎች እናመሰግናለን፡፡
የወረዳ የክ/ከተማና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን፣ የሚድሮክ እና የኤልፎራ ከፍተኛ ሀላፊዎችና የከንቲባ ፅ/ቤት አመራሮችን በህጻናት ተማሪ ልጆቻችን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ፓሽን አካዳሚም አላማው የትምህርት ጥራት እንጂ ትርፍ ሳይሆን የትውልድ መቅረጫ ሆኖ ይቀጥላል። ሀሳባችንና ዓላማችን ሰፊ ነው፡፡ በሂደት እንተገብረዋለን፤ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ።

Read 5807 times