Saturday, 18 September 2021 16:52

የኬሚካል እርግዝናና የክሊኒካል እርግዝና ልዩነት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  ከኢሶግ በሳይንሳዊ አጠራሩ ኬሚካል እርግዝና የሚባለው እና ክሲኒካል እርግዝና የሚባለው አጠራር ምን አይነት እርግዝናዎችን የሚመለከት ነው የሚለውን ሀሳብ እንድናለሳ ያስገደደን የአንድ አንባቢ መልእክት ነው፡፡ በእድሜዋ ወደ 32 አመት ገደማ የሆነች እና የአንድ ልጅ ናት፡፡ የገጠማትን ነገር እንደሚከተለው አስረድታናለች፡፡ ሀሳብዋን የገለጸችው በስልክ ነበር፡፡
‹‹…በጣም የሚገርም ነገር ነው የገጠመኝ፡፡ አንድ ቀን በሰላም ከቤቴ ወጥቼ ወደስራዬ ስሄድ በድንገት የወር አበባ ሲፈሰኝ ተሰማኝ፡፡ አዎ… ጊዜው ነው… እንዲያውም መምጣት ከነበረበት አንድ ሳምንት ገደማ አልፎታል ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ። የወር አበባ መሰሉ ፈሳሽ ግን ፋታ ሊሰጠኝ አልቻም። ቶሎ ወደ አንድ ካፌ ዘው አልኩ። ወንበር ሳልይዝ በቀጥታ ወደመታጠቢያ ቤት ገብቼ ንጽህናዬን ለመጠበቅ ስሞክር ከወትሮው ለየት ባለ መንገድ ወፈር ወፈር እና በዛ ያለ የደም ፍሳሽን አየሁ… ይሄ ነገር እርግዝና ነው እንዳልል እርግዝናን አውቀዋለሁ… የዚያ አይነት ስሜት የለኝም… ምንድነው? አልኩና ወደቤቴ ተመለስኩ፡፡ እንደገለጽኩትም በርከት፤ ወፈር እና ፈጠን ያለ ነገር ስለነበር ወደሐኪም ስሔድ ምናልባት እርግዝና ሊሆን ያሰበ ….ነገር ግን መሆኑ ያልተረጋገጠ የኬሚካል እርግዝና ነው አሉኝ፡፡ የኬሚካል እርግዝና ማለት ምን ማለት ነው…?.›› የሚል ነበር የወይንሸት ሳህሉ ጥያቄ፡፡  
የኬሚካል እርግዝና ማለት ምን ማለት እንደሆነ Colleen de Bellefonds ያዘጋጁት መረጃ በMark Payson, M.D. on ለንባብ እንዲበቃ በAugust 13, 2021 ይሁንታን አግኝቶአል፡፡
የኬሚካል እርግዝና፡-
የኬሚካል እርግዝና ማለት እርግዝናው ለመፈጠር ገና ሲያስብ አስቀድሞ የሚበላሽ እና በወር አበባ መልክ ነገር ግን የራሱን ባህርይ ይዞ የሚወገድ ነው፡፡ የኬሚካል እርግዝና የተከሰተባቸው ብዙዎቹ ሴቶች ምክንያቱ እርግዝና ይሁን አይሁን ገና ሳይለዩት ወይንም ምንም ስሜት ሳይኖራቸው በድንገት የሚቋረጥ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ግን ችግሩ የሚፈጠርባቸው ሴቶች ላይ የጤና ጉድለት መኖሩን የሚያሳይ ወይንም ወደፊትም የተስተካከለው እርግዝና አይገጥማቸውም ማለት አይደለም፡፡ የኬሚካል እርግዝና ማለት እርግዝናው ገና ሲያስብ መቋረጡ ሲሆን ሁኔታው የሚከሰተውም የሴትዋ እንቁላል ለእርግዝና ዝግጁ ሲሆን እና የወንድ የዘር ፍሬን አግኝቶ ገና ወደማህጸን ሲገባ ነገር ግን በማህጸን ቆይቶ ለማደግ እድሉን ሳያገኝ ሲቀር ነወ፡፡ ይህ የሚሆነው የወር አበባ መጥቶ በሄደ ከ4 እስከ 5 ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ ነው፡፡  
የኬሚካል እርግዝና የሚለው ስያሜ የተሰጠው ሴቶች የወር አበባቸው መምጣት ከነበረበት አንድ ሳምንት አልፎ  ያልጠበቁት አይነት የደም መፍሰስ ሲገጥማቸው እና ወደሕክምና ሲቀርቡ የገጠማቸው ምን እንደሆነ መርምሮ ማግኘት የሚቻለው ኬሚካልን በመጠቀም በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የእርግዝና አይነት ክሊኒካል እርግዝና ከሚባለው የሚለየውም ክሊኒካል የሚባለው እርግዝና እድገትና ያለበት ሁኔታ ሐኪሞች በአልትራሳውንድ እና መሰል ምርመራዎች የሚያገኙት ሲሆን የኬሚካል እርግዝና ግን በኬሚካል በመታገዝ በሚደረግ ምርመራ ብቻ የሚታወቅ ስለሆነ ነው፡፡
በአለም ላይ ከሚከሰቱ እርግዝናዎች ግማሽ ያህሉ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ የሚቋረጡ ሲሆን አብዛኞቹም የኬሚካል እርዝናዎች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህንን ያህል የኬሚካል እርግዝናዎች ተቋርጠዋል ለማለት የማይቻልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምክንያቶችም ብዙዎቹ ሴቶች ምንም አይነት የእርግዝና ስሜት ሳይኖራቸው ስለሚቋረጥ እና ወደህክምና መሄድ ሳያስፈልጋቸው እራሳቸው ስለሚያስተናግዱት ነው፡፡
የኬሚካል እርግዝና ምክንያቱ ምንድነው?
የኬሚካል እርግዝናን ጨምሮ አብዛኞቹ ጊዜያቸው ሳይራዘም የሚቋረጡ ጽንሶች ምክንያታቸው በሰውነት ውስጥ የሚገኝ የክሮሞዞም መዛባት ነው ይላል ጽሁፉ፡፡ የእርግዝና ምርመራ በሚደረግበት ወቅት የሴትዋ እንቁላልና የወንዱ የዘር ፍሬ እያንዳንዳቸው 23 ክሮሞዞምን በማዋጠት ሽሉን ለመፍጠር በድምሩ 46 ክሮሞ ዞም እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሲሟላ ሽሉ ተፈጥሮአዊ ሁኔታው በሚፈቅደው መሰረት በማህጸን ውስጥ ማደጉን ይቀጥላል፡፡ የኬሚካል እርግዝና ግን የእነዚህ ሁኔታዎች መጉዋደል ይታይበታል፡፡
በኬሚካል እርግዝና፤-
የወንድ የዘር ፍሬ ወይንም የሴትዋ እንቁላል በጣም ብዙ ወይንም ደግሞ በቂ ያልሆነ ክሮሞዞም ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡
እርግዝናው በመፈጠር ላይ እያለ ሽሉ ወይንም ጽንሱ በበኩሉ ቁጥሩ ትክክል ያልሆነ ክሮሞዞም ሊኖረው ይችላል፡፡
ይህ የክሮሞዞም ቁጥር መብዛት ወይንም ማነስ ጽንሱ እንዳይቀጥል ምክንያት ይሆናል፡፡
የክሮሞዞም ቁጥር መዛባት በማንኛውም ሰው ላይ ባልታወቀ ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ በአብዛኛው ግን በእ ድሜ ምክንያት ሊያጋጥም ይችላል፡፡  ነገር ግን የኬሚካል እርግዝና ማለት ሁሉም ሊረዳው የሚገባው ወደ ፊት እርግዝና ይከሰታል ወይንም አይከሰትም የሚለውን ድምዳሜ ለመስጠት በፍጹም ምክንያት አይሆንም። የኬሚካል እርግዝና ከተከሰተ በሁዋላም እርግዝናው ከዚያ በሁዋላ ይዘገያል፤አይከሰትም ማለትም አይደለም፡፡
ለኬሚካል እርግዝና ምክንያት ከሚሆኑት መካከል፡-
በእድሜ ከ35 አመት በላይ መሆን፤
ሕክምና ያልተደረገለት የደም መርጋት ሁኔታ መዛባት፤
ህክምና ያልተደረገለት የታይሮይድ ሁኔታ፤
ሌሎች ሕክምና ያልተደረገላቸው ህመሞች…ለምሳሌም እንደስኩዋር ሕመም ወዘተ…
የኬሚካል እርግዝና ከሚያጋጥማቸው መካከል በተፈጥሮ እርግዝናው የማይሞክራቸው እና በላቦራቶሪ የሚታ ገዘው (in vitro fertiliz- ation  (IVF) አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በተፈጥሮ ማርገዝ ያልቻሉ እና በላቦራ ቶሪ እርዳታ እርግዝናውን ለማግኘት የሚሹ ሴቶች ይህ አጋጣሚ ሊያሳዝናቸው አይገባም፡፡ ምክንያቱም በ(IVF) እርግዝናን ለማግኘት የሚሞክሩ ሴቶች የኬሚካል እርግዝና ቢገጥማቸው (ለጊዜው ቢቋረጥም) ወደፊት እርግዝናው ሊከሰት እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡
ከኬሚካል እርግዝና በሁዋላ ልጅ የማግኘት ሙከራን በሚመለከት መረጃው እንደሚገልጸው እርግዝናው በተቋረጥ በቅርብ ጊዜ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል የሚል ነገር ባይኖርም የህክምና ባለሙያን ማነጋገር ጠቃሚነት ግን አይካድም፡፡ ምናልባትም ጅምር የሆነው እርግዝና የመቋረጡን ምክንያት ምን እንደሆነም ለመገመት የሚያስችሉ መላምቶችን ለማግኘት ሊረዳ ይችላል፡፡ ወደህክምና ባለሙያ ከመሄድ በፊት ግን የወር አበባ ኡደትን በሚመለከት ወይንም የሚመጣበት ወቅት መዛባ ቱን እና ከ35 ቀን በላይ መርዘሙን እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ አስፈላጊውን ምርመራ ካደረጉ በሁዋላ ምናልባትም ሁኔታው የተደጋገመ ከሆነ ዘር በማፍራት ዙሪያ እስፔሻ ሊስት ወደሆኑ ባለሙያዎች ሊመሩ ይችላሉ፡፡
ወደሕክምና ባለሙያ መሔድ የሚያስፈልገው፡-
ሴትዋና ባለቤትዋ በእድሜአቸው ከ35 አመት በታች ከሆኑ እና ዘር በማፍራቱ ጉዳይ ባለፉት 12 ወራት ጥረት ቢያደርጉም እርግዝናው ካልተከሰተ፤
በእድሜ ከ35 አመት በላይ ከሆኑና  ለስድስት ወር ለእርግዝና ጥረት አድርገው ካልተሳካ፤
በእድሜ ከ38 አመት በላይ ከሆኑና ለሶስት ወር ለእርግዝና ጥረት አድርገው ካልተሳካ፤
በእድሜ ከ40 አመት በላይ ከሆኑ እና በቤተሰብ ደረጃ ዘር ያለማፍራት (የመካንነት)ታሪክ ካለ፤ ሐኪምን ማማከር ይጠቅማል፡፡
የኬሚካል እርግዝና ማለትም እርግዝው ገና ከመጀመሩ መቋረጡ የሚደጋገም ከሆነ እርግዝና አይሳካም ማለት ባይሆንም ለሚገጥማቸው ሴቶች ልብን የሚሰብር መሆኑ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ለመካንነት ማስጠንቀቂያ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ችግሩ ሲገጥም በተለይም ተደጋጋሚ ከሆነ ሁኔታውን ለሕክምና ባለሙያዎች እንዲታወቅ ማድረግ ይገባል፡፡ መንፈስን አረጋግቶ በቀጣዮቹ ጊዜያት ለእርግዝናው መዘጋጀትም ይጠቅማል፡፡  
በኬሚካል እርግዝና እና በክሊኒካል እርግዝና መካከል ያለው ልዩነት፡-
ኬሚካል እርግዝና ገና ከጅምሩ የሚቋረጥ እና በኬሚካል በሚደረግ ምርመራ ካልሆነ በስተቀር እርግዝና ስለመከሰቱ ለማወቅ አስቸጋሪ የሚሆን ነው፡፡
ክሊኒካል እርግዝና የሚባለው ጽንሱ ተገቢውን እድገት እያደረገ በሕክምና ምርመራው በአልትራሳውንድ እና በመሳሰሉት ምርመራዎች የህክምና ባለሙያው የሚያገኘው ሲሆን ነው፡፡

Read 14310 times