Saturday, 18 September 2021 16:48

አውራ - ዶሮ ፈረስን ረግጦ፤ “እርግጫ ከኔ ተማር!” አለው የኦሮምኛ ተረት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ የፈረንጆች ተረት አለ፡፡
በማፍቀር ዕድሜ ላይ ያሉ ጐረምሶች፤ “የት ሄደን ነው ራት የምንገባበዘው?” ሲባባሉ፤ አንደኛው፤
“ኦሽን-ቪው ሆቴል እንሂድ” አለ
“ለምን?” ሲሉት፤
“እዚያ ቆንጆ ቆንጆ፣ የሚታዩ ኮረዶች አሉ!” አለ፡፡
ሁሉም ተስማሙና ሄደው በርቸስቸስ ሲሉና ሴት ሲያጫውቱ አመሹ፡፡
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደዚሁ ተገናኙ፡፡ “የት እናምሽ?” የሚል ጥያቄ ተነሳ!
“ኦሽን-ቪው ሆቴል” አለ አንዱ፡፡
“ለምን?” አሉት፡፡
“ጥሩ ራትና ጥሩ መጠጥ አለ” ሲል መለሰ፡፡  
ይህ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ ዳግም ተገናኙ። አሁን ወደ ሰባ ዓመት ተጠግቷቸዋል። እንግዲህ “የት እንብላ ራት?” ተባለ፡፡
“ኦሽን- ቪው ሆቴል” አለ አንደኛው፡፡
“ለምን?” አሉት፡፡
“በጣም ፀጥ ያለ፣ የውቂያኖሱን ሰላምና ነፋሻ አየር የምናገኝበት ቦታ ነዋ!” አላቸው፡፡
ተያይዘው ነፋሻውንና ፀጥ ያለውን አየር ሲኮመኩሙ አመሹና ተለያዩ፡፡
ይሄ በሆነ ከአሥር ዓመት በኋላ እንደገና ተገናኙ፡፡ አሁን ጎብጠዋል፡፡ ከዘራ ይዘዋል። ባርኔጣ አድርገዋል፡፡ በጣም በዝግታ ነው የሚራመዱት፡፡ እየተደጋገፉ እየተቃቀፉ ነው የሚቆሙት፡፡
“ዛሬስ ለእራት የት እንሂድ?” አለ አንደኛው፡፡
“ኦሽን- ቪው ሆቴል” አለ ሌላው፡፡
“ለምን?” ብለው ጠየቁ ሌሎቹ፡፡
ሰውዬውም፤
“እዛ ሆቴል ሄደን አናውቅማ!”
“ብራቮ! አዲስ ሆቴል ማየት በጣም ደስ ይላል” አለ አንዱ፡፡
“ድንቅ ሀሳብ!”
“አስገራሚ ሀሳብ!”
“ጉደኛ ሀሳብ!” እየተባባሉ እየተጓተቱ፣ እየተገፋፉ፣ መሰሰሰስ እያሉ፤ ወደ ኦሽን ቪው ሆቴል አመሩ፡፡
*   *   *
የተፈጥሮን ሂደት ለማቆም አይቻልም፡፡ ይህን የተፈጥሮና የዕድሜ መሰላል፤ በየዕለቱ ከሚገጥመን አገራዊ ችግርና አፈታቱ ጋር ለማስተያየት ብንሞክር፤ አርጅተን ጃጅተን የሠራነውንና ያልሠራነውን፣ የሄድንበትንና ያልሄድንበትን ለመለየት የማንችልበት የመርሳት ዕድሜ እስከምንደርስ ንቅንቅ አልልም ብለን፤ በያዝነው ሥልጣንና ሹመት ሙጭጭ ካልን፤ በዚያውም ለተተኪው ትውልድ ቦታ ካልለቀቅን፤ የአገር- ለውጥ- ቀን እየራቀ ነው የሚሄደው፡፡ በእርግጥም ይሄ ቦታን በሰላም የመልቀቅ ባህል የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ-ገፅ አለው፡፡ የኢኮኖሚ-ገፅ አለው፡፡ የግል ጥቅም-ገፅ አለው። ከፓርቲ ጋር፣ከራስ ጥቅም ጋር፣ ከራስ ህሊና ጋር መሟገትንና መታገልን ይፈልጋል፡፡ ይህን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆነ በማይገኝበት ዘመን የአገር ምጧ ብዙ ነው፡፡ ያ ነው በትክክል ዛሬ አገራችንን የገጠማት፡፡  ለዚያም ነው ዛሬ አገራችን ምጧ የበዛው፡፡ ለዚያም ነው አገራችን ዛሬ የለየለት ጦርነት ውስጥ የገባችው፡፡ ጥቂቶች ከላይ የተጠቀሰውን  ዋጋ ለመክፈል አሻፈረኝ በማለታቸው ነው፣ ብዙዎች የህይወት ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙት፡፡ ጥቂቶች ከለመዱት ሥልጣንና ምቾት መነቅነቅ ባለመፈለጋቸው ነው፣ አገር እየታመሰች ያለችው፡፡ በእርግጥም የተፈጥሮን ሂደት ማቆም የማይቻል ነገር ነው፡፡ የተፈጥሮን ሂደት ለማቆም ሙከራ ሲደረግ ግን አገር ምስቅልቅል ውስጥ ትገባለች፡፡   
ወጣቱ ላይ ዕምነት ይኑረን፡፡ ያለ ጥርጥር አዲሱ ትውልድ  አሸናፊ ነው፡፡ The New is invincible ይሉ ነበር የጥንት ፖለቲከኞች፡፡ ዛሬም ይሄ ዕውነታ አይሻርም፡፡ አዲስ ኃይል መፍጠር የአገር አቅም መፍጠር ነው። ለወጣቱ ትውልድ ቦታ መልቀቅ ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ህግ ነውና፡፡
ከፖለቲካ ባህላችን ውስጥ እጅግ ሚዛን የሚደፋ አንድ ባህል አለ፡፡ ብዙ ሊጤን ይገባል! የይቅር መባባል ባህል!  ቂም፣ የወንጀለኝነት-ስሜት፣ ብድር-የመመለስ ፍላጎት፤ አጥፊ ናቸው፡፡ ዴቪድ ሀውኪንስ እንዲህ ይለናል፤ “የ2ኛው የዓለም ጦርነት አንጋፋ ተሳታፊዎች አሰቃቂውንና አንገፍጋውፊን ጦርነት ከተወጡ በኋላ አብዛኞቹ የጠላት ተፋላሚዎች በፍጥነት ይቅርታ ተደራረጉ፣ ይቅር ተባባሉ፡፡ ሰላምታ ተሰጣጡ፡፡ የፍልሚያውን ፍፃሜም በዓል አከበሩ፡፡ በአዲስ የመተሳሰብ መንፈስ ተጨባበጡ፡፡ አሜሪካኖች አቶሚክ ቦምብ የጣሉና በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን የቀጠፉ ነበሩ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ግን “በቃ ጦርነትኮ ይሄው ነው” ተባለ! የትላንት ተፋላሚዎች የዛሬ ጓደኛ ሆኑና ይጠያየቁ ጀመር፡፡ ይሄው እስካሁንም የተረፉት ታላቁን የጦርነት ቀን ያከብራሉ”
በአያሌ ሰዎች በተግባር እንደተረጋገጠው፤ አሉታዊ አመለካከትና የወንጀለኛነት ስሜት፤ በአዎንታዊ የመረዳት ስሜት፣ በመረዳዳትና በትውስታ ስሜት፤ ሊተካ ይችላል፡፡ … በዚህ ስሜት ሲታይ ከዚህ ቀደም በጠላትነት ይታዩ የነበሩ ሰዎች ይቅርታን ሊያገኙ ይችላሉ። ከዚህ ቀደም ያስፈሩ የነበሩ ሰዎችም አሁን ሰላማዊ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ራስን ለማየትና ጥፋትን ለመቀበል ዝግጁ የመሆን ጉዳይ ነው። እርግጥ በአንድ ጀምበር እውን የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ልምምድ ይፈልጋል፡፡ አዕምሮአችንንና ልቡናችንን ክፍት እናድርግ፡፡ ለዚህ ቁልፉ ነገር፤ አንዱ ከሌላው መማሩ ነው፡፡ ችግሩ ግን ያልተማረው የተማረውን ካላስተማርኩ፣ አላዋቂው አዋቂው ካላዳመጠኝ የሚልበት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአዕምሮም በአካልም ያልዳበረው ሰው፤ ልምድ ያለውንና የዳበረውን ሰው፤ ዘራፍ ሲልበት፣ ሲፎክርበት፣ ከእኔ ወዲያ ላሣር ሲለው የታየበት አገር መሆኑ ነው! “አውራ ዶሮ ፈረሱን ረግጦ፤ ‘እርግጫ ከእኔ ተማር!’” አለው፤ የሚለው የኦሮምኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!!


Read 15853 times