Saturday, 18 September 2021 16:43

ኢሰመጉ የግጭትና ጦርነት ተፈናቃዮች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየቦታው የሰፈሩ ዜጎች ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ያመለከተው ኢሰመጉ፤ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ዘላቂ መፍትሄዎች እንዲታለሙ ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ለአዲስ አድማስ ባደረሰው አስቸኳይ መግለጫው፤ እጅግ አሳሳቢ ለሆነው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች  ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያሻ አስታውቋል። በዚህም መንግስት፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የጋራ ንቅናቄ እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
የህወኃት ታጣቂ ሃይሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ የታጠቁ ሃይሎች በንጹሃን ላይ በሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት ከሰሜን ወሎ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ከደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከሶማሌ ክልልና ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ሁኔታ አሳሳቢ  መሆኑን ኢሰመጉ ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ነው ያመለከተው።
ታጣቂዎች ባደረጓቸው ጥቃቶች ምክንያት ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውንና ተፈናቃዮች ምግብ፣  ውሃ፣ መጠለያና የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ መሆኑን አስታውቋል።
ተፈናቃዮች በሚገኙበት አካባቢ ስልክና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ መንገዶች በሙሉ ዝግ በመሆናቸው በአሁን ወቀት ያሉበትን ሁኔታም ለማወቅ አዳጋች መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል። ኢሰመጉ በዚህ መግለጫው መሰረት፤ ሰፊ መፈናቀል ከመፈጠሩ በፊት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባራት በሚከናወኑበት ሁኔታ ላይ አዲስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ፤ የሚደረጉ ድጋፎች በቀጥታ ለተፈናቃዮች መድረሱን የሚያረጋግጥ ስራ በመንግስትና በባለድርሻዎች እንዲከናወን፤ ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበትና ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም ግጭትና ጦርነት በዘላቂነት ቆሞ በሃገሪቱ እርቅና ሰላም በሚሰፍንበት ሁኔታ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።

Read 13865 times