Saturday, 18 September 2021 16:38

በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች መጠነ ሰፊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ግድያንና፣ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በርካታ አሰቃቂ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች አስታውቋል።
“በትግራይ ክልል በኤርትራ ስደተኞች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋ ግልፅ የጦር ወንጀሎች ናቸው” ብለዋል፤ የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲቫ ባዴር።
ባለፉት አስር ወራት በኤርትራውያኑ ላይ የሚደርሰው ጥቃትና ሰቆቃ መበራከቱን ተከትሎ በርካቶች ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እየወጡ መበታተንን አማራጭ ማድረጋቸውን የሚጠቁመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ኤርትራውያኑ ጥቃት የተፈጸመባቸው  ጥቃት በዋናነት በትግራይ ሃይሎች ቢሆንም በኤርትራ ወታደሮችም ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው አመልክቷል።
በስደተኛ ካምፕ ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ግልፅ አለማቀፍ የጦር ወንጀል መሆኑን የጠቆመው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ አጥፊዎች በህግ ይጠየቁ ዘንድ ለህግ ሂደት ግብአት የሚሆኑ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አስታውቋል።
ምርመራውን ሲያከናውን 28 ኤርትራውያን ስደተኞችን፣ ሁለት ስደተኞቹ ከተጠለሉባቸው ካምፖች አንዱ በሆነው ህፃፅ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የአይን እማኞችን እንዲሁም የረድኤት ድርጅት ሰራተኞችን ማነጋገሩን ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በምርመራ ግኝቱም በተለይ ሰፊ ቁጥር ያለውን ስደተኛ አስጠልለው የነበሩት የህፃፅና ሽመልባ የስደተኞች ጣቢያ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን፣ በዚህም በሁለቱም ጣቢያዎች በድምሩ 35 ያህል ስደተኞች በሁለት ቀን ጥቃት መገደላቸውንና፣ በመቶዎች መቁሰላቸውን አመልክቷል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ በህፃፅና ሽመልባ ካምፖች ውስጥ ተመዝግበው ይኖሩ ከነበሩ 20 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን መካከል 7 ሺህ 643 ያህሉ አሁን ላይ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ሪፖርቱ ጠቁሟል። ጥቃቱን ሽሽት በተለያየ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ስደተኞችም ያለ እርዳታ በችግር ላይ እንደሚገኙ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ስደተኞችም ታፍነው መወሰዳቸውንና እስካሁን የት እንደደረሱ እንደማይታወቅም ተገልጿል።
አሁንም በትግራይ ያሉ ስደተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት ግጭት በሚቆምበት ሁኔታ ላይ እንዲሰሩ፣ በትግራይ ያለው ሃይል በሃላፊነት ለስደተኞች ጥበቃ እንዲያደርግ፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኮሚሽን የት እንደገቡ ያልታወቁ ኤርትራውያን ስደተኞችን እንዲያፈላልጉ  እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት በጉዳዩ ላይ ልዩ መርማሪ ቡድን አቋቁሞ እንዲመረምር ሂውማን ራይትሰ ዎች ጥሪ አቅርቧል።

Read 1074 times