Monday, 13 September 2021 00:00

2013 በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዓይን (የአዲስ ዓመት ምኞትና ተስፋ)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ያለፈውን ዓመት በብዙ መከራዎችና ፈተናዎች ነው ያሳለፈችው፡፡ ጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፣የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀል ወዘተ… የመከራና ፈተና ዓመት ብቻ ግን አይደለም፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅን ጨምሮ መልካም ውጤቶችም ተመዝግበዋል፡፡ የአገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዛሬ የሚጠናቀቅውን የ2013 ዓ.ም እንዴት ይገመግሙታል፡፡ ለአዲስ ዓመትስ ምን ይመኛሉ-ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮችን አነጋግራ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡- እነሆ


“ኢትዮጵያ በታሪኳ ትልቁ ፈተና ነው የገጠማት
አቶ የሺዋስ አሰፋ የኢዜማ ሊቀመንበር)

 2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያ በጣም ፈታኝ የሆነ ዓመት ነበር። በታሪካችንም በጣም ከባድና ፈታኝ ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ነው። ምንም እንኳ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ያላለፈ ቢሆንም፣ ይህ አመት ኢትዮጵያ ካለፈችባቸው የጥንታዊም የዘመናዊም የታሪክ ጊዜያት በጣም ከባዱ ነው። በተለይ በእኛ እድሜ ከተከሰቱ ችግሮችና ፈተናዎች በጣም አስከፊው ነው ማለት ይቻላል።
ከአባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ በህዳሴ ግድብ አጠቃቀም የመጣብንን ችግር እናውቀዋለን፣ የጎረቤት አገር የመሬት ወረራ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የበረሃ አንበጣው፣ የእርስ በእርስ ግጭቱ ሁሉ በዚህ ዓመት የተከሰቱና በዓመቱ የሆነው መልካሙ ነገር የቱ ነው የሚለውን መለየት እስኪያቅተን ድረስ የተፈተንንበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልሽ፤ ኢትዮጵያ ስትፈተን ይሄ የመጀመሪያዋ አይደለም። በጣም ለረጅም ጊዜ በውጪ ወረራም በውስጥ ችግርም ተፈትና ያለፈች ጥንታዊት አገር እንደመሆኗ አሁንም በዚያ  ሂደት ውስጥ ናት። ይህ ሁሉ ፈተና የደረሰው በደካማ አገር ወይም ደግሞ በቅኝ ግዛት ተጠፍጥፎ በተሰራ አገር ቢሆን፣ የዚህን ችግር ግማሹን መቋቋም የሚችል አይመስለኝም። አገሩ ጠንካራ መሆኑ (ሲስተም እንኳን ባይኖር) የማህበረሰቡ አብሮ የመኖር ስርዓት በሽታውን ለመቋቋም፣ የውስጥና የውጭ ችግሩን ለመቋቋም፣ እንደ አገር ለመቀጠል አስችሎናል ብዬ ነው የማምነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከገጠማት  ፈተናዎች ሁሉ ከባዱን የተጋፈጠችበት የሚወስደው ፈተና የተከሰተበት ዓመት ነው።
በእኛ እምነት ይህንን ፈተና ለማለፍ ሶስት ነገሮች መደረግ ነበረባቸው። ምርጫ መደረግ ነበረበት፣ ግድቡ መሞላት ነበረበት፣ ሀገረ መንግስት መመስረት ነበረበት። ምርጫው ምንም ይሁን በምርጫው የነበረው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገረ-መንግስቱ መቀጠል ስላለበት፣ መንግስት መመስረት አለበት። ከዚያ በኋላ ግን በመሰረታዊ የሀገር መቆሚያ አምዶች ላይ ልዩነት አለኝ የሚልም የሚያነሳበት፣ ልዩነቱ በዚህ መልኩ ይታረቃል የሚልም የሚናገርበት የሀገራዊ መግባባት መድረክ  መፈጠር አለበት። ታዲያ መድረኩ የይስሙላ ሳይሆን የእውነት ንግግር መደረግ አለበት። ይሄ ብዙ ችግር ይፈታል የሚል እምነት አለኝ።
እንደ ኢዜማ በፖለቲካው መስክ ሀገረ መንግስቱን ለማስቀጠል፣ ከዚያ አልፎ በሀገሪቱ ውስጥ የተሻለ ስርዓት እንዲኖር ጉልህ ሚና ይኖረናል። እንደሚታወቀው ሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት  ናት ስንል፣ አገዛዙ ንጉሳዊ ሊሆን ይችላል ብቻ ሀገረ መንግስቱ የቀጠለ ነው።
ሀገረ መንግስት ስናስቀጥል ግን፣ የውስጥ ዴሞክራሲውን የምናሻሽልበትን ስርዓት እስካሁን ድረስ አልሰራንም። ስለዚህ እሱን ለመስራት የሚያስችል ሀሳብ ይዘን እንቀርባለን። ለምሳሌ በእኛ እምነት፣ የበሽታዎቹ ሁሉ መነሻ ህገ-መንግስቱ ነው። የፌደራል አወቃቀሩ፣ ልዩ ሀይል የሚባለው፣ የመሬት ፖሊሲውና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች እኛ ባልነው ይሁን ሳይሆን ለውይይት ቀርበው በውይይትና በፓርቲዎች የጋራ ስምምነት የሚፈታውን በጋራ ስምምነቱ፣ ከዚያ ያለፈውን ለህዝበ ውሳኔ አቅርበን ህዝብ የተቀበለውንና ያመነበትን ገዢ ሀሳብ አድርገን እንወስዳለን ማለት ነው። ምክንያቱም የሀገር መቀጠል ከፖለቲካ በላይ ነው።
እኛም የመፍትሔ ሀሳብ ያስፈልጋቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች በማስረጃና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሀሳብ ይዘን ለመቅረብ ዝግጁ ነን። ከዚያ በኋላ አብዛኛው ያመነበትን ለመቀበልም ዝግጁ ነን። ምክንቱያም የሀገሩና የስልጣኑ ባለቤት ህዝበ ነው የሚል እምነት ስላለን። ሁሉንም ሀሳብ በህዝብ ውሳኔ እንደ መፍታት እፎይ የሚያሰኝ ነገር የለም የሚል እምነት አለን። አሁን ደግሞ ወሳኝ ጊዜ ላይ ስላለን የዚህኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ የሚባል ነገር መኖር የለበትም። እንደ ሀገር በጣም በሰከነ መልኩ ተወያይተን መፍትሄ ልናበጅላቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በነዚህ ላይ እንደ ፓርቲ የመፍትሔ ሀሳብ ለማዋጣት ዝግጁ ነን።
በመጨረሻም የፈተና ወቅት በፅናት እያለፈ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት፣ ሚሊሺያና ልዩ ሃይሎች፣የግድቡን ስራ በዲፕሎማሲውም በግንባታውም  ለሚሰሩ ወገኖች እንዲሁም፣ ለመላው የኢዜማ አመራሮችና አባላት፣ ለሎቹም የፓርቲ አመራሮች በሙሉ አዲሱ አመት የምንስማማበት፣ አገራዊ መግባባት የምንፈጥርበት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ መከራ እፎይ የሚልበት፣ በሀገሩ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት እንዲሆን እመኛለሁ። መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን።

 ============================================

  ሀገሪቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ብታልፍም ያገኘቸውም እድል አለ”
(ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፤ የህብር ኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነት)

እያገባደድነው ያለው 2013 ዓ.ም  ሀገሪቱ በእጅጉ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የገባችበት ነው። በተለይም ከህወሃት ጋር በተያያዘ መከላከያ ሰራዊታችን ያለ አግባብ ያለቀበት፣ በዚህም የተነሳ ወደ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ የገባንበትም ዓመት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ያገነችው እድልም ጥቅምም  አለ።
ባለፉት 27 ዓመታት ህወሃት ህዝቡን ከፋፍሎ በተለይ በብሄር ለያይቶ ሀገሪቱን ለመበታተን ብዙ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር በሀገራቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን ያሳዩበት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ጥላ ስር የተሰባሰቡት ዓመት ነው ብለን ማለት እንችላለን። ከዚያ ከአስፈሪ መነጣጠልና የጎሪጥ መተያየት ወጥቶ፣ በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ ለመሆን መብቃት በእኔ እምነት ትልቅ እድል ነው።
ሀገሪቱ  ከገባችበት መከራ  አንድትወጣ ከፈለገ ከጦርነት  አጠቃላይ የጦርነቱን ቀስቃሾች በቁጥጥር ስር በማዋልም ሆነ በመደምሰስ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ አለበት። ህወሃት እስካለ ድረስ ሀገርም ህዝብም ሰላም አይኖራቸውም። ህወሃቶች በባህሪያቸው ስታይው አገር አፍራሽና አሸባሪዎች ስለሆኑ በድርድር የማያልቅ ነገር የለም። በደርግ ጊዜ ስንመለከት፤ ህወሃቶች አውሮፓ ቁጭ ብለው ተደራድረው ነው እዚህ የገቡት። አሁን ላይ ግን ከነዚህ አገር አጥፊዎች ጋር እንደራደር ማለት፣ ጦርነቱ እድሜው ይርዘም፤ ህወሃት ያንሰራራ ማለት ነው። ከስር ተነቅለው መጥፋት ነው ያለባቸው። አገሪቱም ህዝቧም ሰላም  የሚያገኙት ይህንን ቡድን ጨርሶ በማጥፋትና በማጥፋት ብቻ ነው።
እንደሚታወቀው ቀደም ሲል እኛንም ጨምሮ  ብዙዎች ጉዳዩ በእርቅና በድርድር እንዲፈታ ብዙ ጥረን ደክመን ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከህወሃት ጋር በምን ጉዳይ ነው የምንደራደረው? ህወሃት´ኮ ሀገር የመከፋፈል አላማ ብቻ ነው ያለው፤ ያውም ከምዕራባዊያን ጋር በመሆን በባንዳነት  የአጥፊነት አላማ እንዳለው ፍላጎቱም እንደሆነ የምታውቂው የተኩስ አቁሙ ስምምነት ተደርጎ እንኳን ከመቀሌ ወጥቶ ሰሜን ወሎና ደቡብ ጎንደር ድረስ ሄዶ ያን ሁሉ ጥፋት ሲያደርስ ቤተ ክርስቲያንና ቅርስ ሲያቃጥል፤ ንፁሃንን በከባድ መሳሪያ ሲገድል ስታይ ነው። ስለዚህ ህወሃትን ማጥፋት ብቻ ነው ለሀገር ሰላምና መፍትሄ የሚሆነው።
ህወኃት ከዚህ በኋላ ብዙ አቅምና እድሜ ኖሮት ኢትዮጵያን ፈተና ውስጥ ይከታታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። አሁን ህወሃት መርዙን ተፍቶ ጨርሷል፡፡ ሁለተኛ የኢትዮጵያ የበላይነት እየመጣ ነው። በተለይም ኮሪደሮችን ማጣቱ ህልሙንና አቅሙን ቀምቶቷል። ጦርነቱን ሲጀምር እንዲህ  ኮሪደር አጥቼ ወጥመድ ውስጥ የገባች አይጥ እሆናለሁ ብሎም ያሰበ አይመስለኝም። ኮሪደር አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ምዕራባዊያን ሶሪያን፣ የመንንና ሌሎች ሀገራትን መሳሪያ በእርዳታ ስም እያስገቡ እንዳፈረሷቸው ሁሉ ኢትዮጵያንም ያንን ከማድረግ አይመለሱም ነበር።  የምዕራባዊያን ዋና አላማ መሳሪያ መሸጥና አቅም ያላቸውን ሀገራት ማዳከም ነው አልተሳካላቸውም፤ አይሳካላቸውምም።
ህወኃም ኮሪደር የማግኘት እድሉ ጨልሟል። በአፋር በኩል አክትሟል አይሞከርም፤ በወልቃይትም ያለው የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህ ህወኃት ከዚህ በኋላ አቅም አበጅቶ ችግር የሚሆንበት ጉዳይ ያበቃለት ነው። አሁን ላይ አምስት ሺህ ያህል ወታደር አንድ ቦታ ላይ ያፈሳል የሚተርፈው አምስት ሰው እንኳን አይሆንም።  የትግራይ ህዝብ እስከ ዛሬ ድረስ መንቃት ነበረበት። አሁንም መንቃትና ልጆቼን አልሰጥም፤ የሄዱትስ የት አሉ? ብሎ አምርሮ መቃወምና ከስቃይ መውጣት አለበት። በአጠቃላይ ህወኃት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠፋል፤ ሀገሪቱ ሰላም ታገኛለች። ለዚህ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ተጋግዞ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ።
በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2014 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ። አዲሱ ዓመት ጦርነት የማንሰማበት ሰላም የሰፈነበት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትበለጽግበት፣ ሁለንተናዊ እድገት የምናስመዘግብበትና የምንፋቀርበት  እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ።===========================

“ሀገር ሰላም እንድትሆን  ህወሃት የሚባል አሜኬላ ተጠራርጎ መጥፋት አለበት”
አረጋዊ በርሄ (ደ/ር)
ያለፈው ዓመት በጣም ጥሩ ጥሩ የሆኑ ነገሮች። አንዳንድ  ደስ የማይሉ አስከፊ ነገሮችም ተከስተውበታል። ደስ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ አድዋ በአንድነት ተነሳስቶ፣ ህዳሴ ግድባችንን ከ83 በመቶ በላይ በማድረስ በአሁኑ ወቅት በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።  የግድቡ ከባዱ ስራ የተጠናቀቀበት ዓመት ነበር። ይህ እንግዲህ መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሳተፈ በጣም ደስ የሚያሰኝ ስራ ነው።
በሌላ  አቅጣጫ፤ እነዚህ አንድነትና ለውጥ የማይወዱ፣ ስግብግብ የሆኑ የቀድሞ የህወሃት አመራሮች የፈጠሩት ጦርነት ደግሞ በህዝባችን ላይ የሞት የመፈናቀል፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ማውደም ያደረሰበት እያደረሰም ያለበት ዓመት ነው። እንግዲህ በዓመቱ ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ያጠናቀቅንበት፣ የህዳሴ ግድባችንን  ፍሬ ልናይ የተቃረብንበት፣ እንዳልኩት በህወሃት የቀድሞ አመራሮች አገር ወደ ጦርነት የገባችበት ነው፡፡  ከመጥፎው ይልቅ መልካሙ ነገር ያመዘነበት ዓመት ነበር እላለሁ።
ይህ ደግሞ ወደተሻለ እድገት ሊመራን የሚችል መሰረት ነው። ለዚህ ሁሉ ችግር መቀረፍ ዋናው ህዝቡ ነው። ህዝቡ በህዳሴ ግድብ ላይ ያሳየውን አንድነትና ተሳትፎ በተለያየ መንገድ ተደራጅቶ አንድነቱን እያጠናከረ፣ መንግስትን እየደገፈና መንግስትም ያልተገባ አካሄድ ሲሄድም እያረመ በንቃት ከተንቀሳቀሰ በመጪው ዓመት ህወሃት የፈጠረውን ችግር በቀላሉ መፍታት ይችላል። ምክንያቱም ህወኃት ጸረ ለውጥ ነው። ህዝቡ ደግሞ ለውጥ ነው የሚፈልገው። ስለዚህ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተባብሮ ከተንቀሳቀሰ በቀላሉ ችግሩን መፍታት፣ ህወሃት ከፈጠረው ቀውስና ስቃይ መውጣት ይችላል። የሚሻለውም ይሄው ነው።
ትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) እንደ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት እነዚህን ጦርነት የጀመሩና መከላከያ ሰራዊታችንን ከጀርባ የወጉ የቀድሞ የህወሃት አመራሮችን እነዚህን የሀገር አሜኬላዎች ከሀገር ጠራርጎ አጥፍቶ፣ በዚህች ሀገር ሰላም ማውረድ ያስፈልጋል ሰላም ወዳዱን የትግራይ ህዝብ   ከጦርነት ወዳዱና ህፃናትና ወጣቶችን  ወደ ጦርነት ከሚከተለው ወንበዴ ቡድን ለይተን በማየት ወገኑ ከሆነው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ  ጋር ሆኖ እነዚህን የጥፋት ሃይሎች አጥፍቶ ሰላማዊና ህዝባዊ የሆነ ስርዓት ተመስርቶ፣ እኛም እንደ ትዴፓ ትግራይ ገብተን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን የትግራይን ህዝብ ቀስቅሰንና አደራጅተን ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ በሚደረገው ትግል ለማሳተፍ ቃል የምንገባበት ቀድሞ የገባነውንም ቃል የምናድስበት ወቅት ነው የሚሆነው።
ሀገራችን ሰላም ትሆናለች። ምክንያቱም ህዝቡ ለውጥ ፈላጊ ነው። ከ27 ዓመታት ጭንቅና መከራ በኋላ ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ህዝቡ ተነቃቅቷል። ስለዚህ መጨው ዓመት የደስታ ፣ የሰላም፣ የመረጋጋትና የእድገት እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየተመኘሁ፣ መልካም ምኞቴን እንድገልጽ ስለጋበዛችሁኝ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።

Read 5996 times