Sunday, 12 September 2021 21:02

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በእውቀቱ ስዩም

አለማየሁ እሸቴ በአጸደ - ስጋ አብሮን በነበረበት ጊዜ በተረብም በቁም ነገርም ሳነሳው ቆይቻለሁ፤ እና የሚከተሉትን ቃላት የምጽፈው “የሞተ ሰው አንገቱ ረጅም ነው” የሚለውን ልማድ ለመከተል አይደለም፡፡  
አለማየሁ እሽቴ አባቴ ከሚወዳቸው ዘፋኞች እንዱ ነበር፡፡ “አይዘራፍ እያሉ” “ከሰው ቤት እንጀራ” የተባሉትን፤ የልጅነቴን ትዝታ ቀስቃሽ ዘፈኖች፥ በቅርቡ ዩቲዩብ ላይ ፈልጌ አጣሁዋቸው፡፡
አለማየሁ የፊልም አፍቃሪ እንደነበር ሰምተናል፤ የወጣትነት ህይወቱም ሲኒማ- መራሽ ነበር፤ የሆነ ጊዜ ላይ አሌክስ ሂልተን ሆቴል ገባ፤ በሚዘናፈለው ጠጉሩ ላይ የቴክሳስ ባርኔጣ ገድግዷል፤ ከወደ ቁርጭምጭሚቴ የሚሰፋ ቦላሌ ለብሷል፤ እግሩን የመመገቢያ ጠረቤዛ ላይ አንፈራጦ በመቀመጥ ሲጃራ ማጤስ ጀመረ፤ አስተናጋጁ እግሩን እንዲያወርድ ጠየቀው፤ እምቢ አለ፤ ዘበኛ ተጠርቶ መጣ፤ አሌክስ ፊሻሌ ሽጉጥ አወጣና ተኩሶ የዘበኛውን ኮፍያ አወለቀው፤ ብዙ ሳይቆይ ፈጥኖ ደራሽና የክቡር ዘበኛ ሂልተን ሆቴልን ከበበው፤ አሌክስ ካዛንቺስ አካባቢ ሲግጥ የቆየውን ፈረሱን በፉጨት ጠራው:: ከዚያ “እንዳሞራ" ኮርቻው ላይ ፊጥ ካለ በሁዋላ ጋልቦ አመለጠ፤ ፈረስ የጠራበትን ፉጨቱን ወደ እንጉርጉሮ አሳደገው፤ በለስ የቀናው ዘፋኝ ሆነ፡፡
አሁን ያወጋሁት እልም ያለ ፈጠራ መሆኑን ተማምነን ወደ ቁምነገሩ እንሂድ፡፡
አሌክስ ከሚጥም ድምጹ ባሻገር ዘናጭ፤ ከፍተኛ በራስ መተማመን ያለው ሰው ነበር፤ እጣፈንታ በብዙ ነገር አዳልታለታለች፡፡ ተቸግሮ አልለመነም፡፡ የሆነ ጊዜ ባለስልጣን ሆኖ ያቅሙን ያክል ህዝብ ነድቷል፡፡ አርባ ምናመን አመት በሞቅ ትዳር ቆይቷል፤ ይህንን ያክል ዘመን ባንዲት ወይዘሮ እቅፍ ተወስኖ መቆየት በዘፋኝ አለም ብርቅ ነው፤ አሌክስ በትዳር የቆየበትን ጊዜ ያክል ኬኔዲ መንገሻ በሕይወት አልቆየም፡፡
ሙሉቀን መለሰ የሚያደንቀው ብቸኛ ዘፋኝ የጋሽ እሸቴን ልጅ ነው:: አለማየሁ በዘመናችን ካሉ ዘፋኞች የጎሳዬ ተስፋዬ አድናቂ መሆኑን ነግሮኛል::
“የወይን አረጊቱ”፥ "አዲሳበባ ቤቴ"፥ “አምባሰል" "እንደ ጥንቱ መስሎኝ”፥ "አልተለየሽኝም" "ታሪክሽ ተጽፏል” የሚሉት ዘፈኖቹ ዘመን አልሻራቸውም፤ በጸጋየ ወይን ገብረመድህን (ደብተራው) የተደረሰው “ያ ጥቁር ግስላ” የተሰኘው ዘፈኑ ራሱን የቻለ አብዮት ነው ማለት ይቻላል:: “የአስር ሳንቲም ቆሎ፤ ቁርጥም አደርግና" እሚለው ዘፈኑ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከየት ወዴት እንደሄደ ያመላክታል፤ ለካ አስር ሳንቲም ሙዝየም ከመግባቱ በፊት ይሄን ያህል ሙያ ነበረው::
“ካጣን ምናባቱ እንብላ ሽንብራ
የሰው እጅን ብቻ እንዳናይ አደራ“ የሚለው ዘፈንስ እንዴት ይረሳል? በአሌክስ የጉርምስና ዘመን፥ ያጣ የነጣው ድሃ ሽምብራ ተመጋቢ ነበር፤ አንዳንዴ ዜጎች የድሮውን ቢናፍቁ ምክንያት አላቸው::
አሌክስ የተረፈው ሀብታም ልጅ ነበር፤ በጉርምስና ዘመኑ አንዴ ለመሰደድ የወሰነው እንጀራ ለማደን ሳይሆን የሆሊውድ አክተር የመሆን ምኞቱን ለማርካት ነበር:: ቢሆንም ስለ ድህነት አብዝቶ በመዝፈን ድሀ- አደግ ዘፋኞችን ሳይቀር ይቦንሳል:: በተለይ ኮለኔል ግርማ ሐይሌ ከተባለ ደራሲ የተቀበላቸው እንጉርጉሮዎች ከሙሾ በላይ ሆድ የሚያስብሱ ናቸው:: እዚህ ላይ “ስቀሽ አታስቂኝ" የሚለው ፒያኖውን የሚያስለቅስበት ዜማው ትዝ ይለኛል፤ የዘፈኑ ባለታሪክ የሙት ልጅ የሆነች ድሃ ናት:: ኑሮን ለማሸነፍ “ትፍጨረጨራለች”፤ በመከራዋ ላይም ትስቃለች:: ይህ በእንዲህ እያለ ወንድምየው ጣልቃ ገብቶ “ስቀሽ አታስቂኝ" ይላታል፤ “ትፍጨረጨርያለሽ ወጉ አይቀር ብለሽ" እያለ ያዳክማታል:: ጭራሽ “ውሃ ጉድጉዋድ ግቢ የምየ ልጅ ባክሽ" እያለ ይጎተጉታታል፡፡
የሰው ልጅ ሁኔታ በጠቅላላው፤ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተስፋ አስቆርጦኝ ያውቃል፤ “ስቀሽ አታስቂኝ”ን ስሰማ ግን እኔን ብሎ ተስፋ ቆራጭ እላለሁ፡፡ እንደዚህ ተስፋን ከጎድንና ከዳቢቱ እሚቆርጥ ዘፈን ገጥሞኝ አያውቅም::
ሰው ማለቂያ በሌለው ውድቀት መሀል እንኳን እየኖረ ተስፋና መጽናኛን የሚያማትር ፍጡር ነው፤ ከአለማየሁ እሸቴ “ስቀሽ አታስቂኝ" ይልቅ የአለማየሁ ሂርጶ ”አታቀርቅሪ ቀን ያልፋል" የሚለው  ዘፈን ይበልጥ የገነነው ለዚህ ይሆን?


===============================
  የዓለማየሁ ዓለም
ከማዕረግ ጌታቸው (ይነገር ጌታቸው)

አሜሪካ ገብተው የሆሊውድ ፊልም ተዋናይ መሆን የፈለጉት ጓደኛሞች፣ አዲስ አበባን ተሰናብተው ምጽዋ ደርሰዋል። የያኔዎቹ ተስፈኞች ምጽዋ ገብተው ሳይጐበኟት ሊሰናበቷት አልፈለጉም፡፡ ያረፉበትን ቤት ለቀው ማምሻውን በቀይ ባህር ነፋሻማ አየር ታጅበው ቶሪኖ የምሽት ክበብ ገቡ፡፡ ቤቱ በሰዎች ተሞልቷል። የመርከባቸውን መልህቅ ጥለው አዳራቸውን በምሽት ቤቱ ያደረጉ የውጭ ሐገር ሰዎች እዚህም እዛም ከሙዚቃው ጋር ይወዛወዛሉ። ሆሊውድን ሊቀላቀሉ ለሸገር ጀርባ የሰጡት ወጣቶችም ለባህር ዳርቻዋ ከተማ አዲስ አይመስሉም፡፡ በመጣው የውጭ ሙዚቃ ሁሉ አብረው ይደንሳሉ፡፡
የኤልቪስ ፕሪስሊ ሙዚቃ ከፍ ብሎ እየተደመጠ ነው፡፡ የዳንስ ሰገነቱ ላይ ያለው ታዳጊ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል:: ዳንሱም ግጥሙንም እኩል ያስኬደዋል። ይህ የገረማቸው የምሽት ክበቧ ታዳሚዎች በዚህ ሰው ተገርመው ሲመለከቱት ቢቆዩም ግብፃዊያኑ ግን አይተውት ዝም ሊሉ አልፈለጉም፡፡ ከሙዚቃው በኋላ ጠርተው አናገሩት፡፡ የምጽዋ ልጅ አለመሆኑን ነገራቸው:: ሆሊውድ ውስጥ የፊልም ተዋናይ ለመሆን ፈልጐ ከአዲስ አበባ ጠፍቶ መምጣቱን ገለፀላቸው፡፡
ግብፃዊያኑ መርከበኞች የሱን ምኞት የራሳቸው አደረጉት፡፡ ከጓደኛህ ጋር ሎሳንጀለስ  ድረስ እንወስድሀለን አሉት። ሩቅ የመሰለው ምኞት ከንጋቱ ወገግታ ጋር አብሮ ሊፈካ ተቃረበ:: በቀጣይ ቀን ከግብፃዊያኑ ካፒቴኖች ጋር የሚገናኝበትን ሰዓት ወስኖ ከስደት ወዳጁ ጋር ወደ ክፍሉ ተመለሰ፡፡ :
የዓለማየሁ እሸቴን ህልም የምትፈታው ዕቃ ጫኟ መርከብ “ሳሂካ” ትባላለች።  የጉዞ ሰዓቷ ደርሷል:: ካፒቴኗ ባልደረቦቹን አሁንም አሁንም ይጠይቃል:: ፀጉረ ሉጫ የጠይም መለሎ ወጣት ተሳፈረ? ይላቸዋል:: ምላሻቸው አልመጣም የሚል ነው:: “ሳሂካ” መልህቋን አንስታ የአሜሪካ ጉዞዋን አንድ አለች፡፡ እነዚያ ሆሊውድን ናፍቀው ምጽዋ የደረሱ ወጣቶች ግን በፖሊስ እጅ ነበሩ፡፡
ነገሩን ለማጣራት ሲሞክሩ ዓለማየሁን የሚያውቅ ዘመድ ወደ አሜሪካ ከማያውቀው ሰው ጋር ሊጓዝ መሆኑን ሰምቶ ለፖሊስ አመልክቶ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ ብዙ አልቆዩም :: የልጅነት አምሮታቸውን እርም ብለው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ::
1934 ዓ.ም ሰኔ 10 ቀን ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢ የተወለደው ዓለማየሁ እሸቴ፤ ገና በልጅነት ዘመኑ እናትና አባቱ ፍች በመፈፀማቸው ያደገው አባቱ ቤት ነው፡፡ ለዚሀ ደግሞ ምክንያቱ አባት ልጃቸውን በወይዘሮ በላይነሽ ዮሴፍ እጅ እንዲያድግ አለመፈለጋቸው ነበር።  በ1940ዎች መባቻ እንዳብዛኛው የዘመኑ ሕፃናት የአብነት ትምህርትን አሀዱ ብሎ የጀመረው ዓለማየሁ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ ዘመናዊ ትምህርት እንዲከታተል በመፈለጋቸው የፈረንሳይኛ ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ ተመዘገበ፡፡
ነገር ግን በዚህ ትምህርት ቤት የቆየው ለወራት ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ፈረንሳይኛ ከማወቅ ይልቅ አረብኛ መማር የተሻለ ነው የሚል ምክርን የሰሙት አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ፤ ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንስ አስወጥተው ዑመር ስመተር ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡
የኢትዮጵያዊው ኤልቪስ የማይደበዝዝ ትዝታ አንዱ መገኛም ዑመር ስማትር ትምህርት ቤት ነው:: ትምህርት ቤት ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ቤታቸው በሰዎች ተጨናንቆ ይመለከታል፡፡ የያኔው ብላቴና ነገሩ ባይገባውም እንደ ሁልጊዜው ሁሉ በቤቱ የተገኙትን እንግዶች ሰላምታ እየሰጠ አለፈ፡:
ከእነዚህ መኃል ግን አንደኛዋ ሴት በአፍታ ሰላምታ የምትለየው አልሆነችም:: ዓይኖቿ እምባ አዝለው ደጋግማ አቀፈችው:: እንግዶቹ ዓለማየሁን እናትህ እኮ ናት በደንብ ሰላም በላት እንጂ አሉት:: ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቱ ጋር ተዋወቀ፡፡ ይህ ትውውቅ ግን ብዙ የዘለቀ አልነበረም፡፡ ወይዘሮ በላይነሽ ተመልሳ ወደ ቤቷ አቀናች፡፡ ብላቴናውም ዳግሞ እናቱን መናፈቅ ጀመረ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት የተከታተለው ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ፤ የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን የወሰደው በአርበኞች ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ታዳጊው ከአንድ የትምህርት ምእራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ የተላለፈበት ብቻ ሳይሆን ከያኒው ዓለማየሁ እሸቴ እየመጣ መሆኑንም ያበሰረ ነው:: በ1951 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ የወላጆች በዓል ላይ ኢትዮጵያዊው ኤሊቪስና ጓደኞቹ የእንጨት ጊታር ይዘው መሬት ላይ እየተንፈራፈሩ በቴሌቭዥን እንዳዩዋቸው ሙዚቀኞች የተዘጋጁበትን ዜማ አቀረቡ፡፡
ዓለማየሁ በአብዮት ቅርጽ የወደቀ እንጨትን ጊታር ባደረጉ እኩዮቹ ታጅቦ መደረክ ላይ ይሰየም እንጅ የእሱ ታዋቂነት ምንጭ ግን ተዋናይነቱ ነበር “ኪንግ ሪቻርድስ ኤንድ ዘ አኖውን ኪንግ” የተባለው በትምህርት ቤት ቆይታው የተወነበት ቴአትርም ዓለማየሁን ብዙ እንዲያስብ አድርጐታል፡፡ በዚህ የተነሳም ከትምህርት እየቀረ ዘመነኞቹን ፊልሞች መመልከት አዘወተረ፡፡ .....
(በቅርቡ ለንባብ ከሚበቃው “ጠመንጃና ሙዚቃ-የወርቃማው ዘመን ታዝታዎች “መጽሐፍ የተቀነጨበ )
ጋሼ፤ ሕይወትህን አንብቤ ታሪክህን ላወራ ስዘጋጅ ሞት ቀደመኝ!! በሰላም እረፍ


=========================================================

  ና ገዳይ ያገር ልጅ!
አማን መዝሙር

አማን መዝሙር
የኢትዮጵያ ዘፈን ግጥሞችና ክሊፖቻቸው ውስጥ ያለ ተቃርኖ አያድርስ ነው። በተለይ የሰርግ ዘፈኖች ግርም ነው የሚሉኝ (ለነገሩ እንኳን የሰርግ ዘፈን ሰርግም አይገባኝም) እኔና የሆነች ልጅ ሁልግዜ አብረን ለመተኛት በወሰንነው እናቱ ወልዳ የጣለችውን ህዝብ የምቀልብበት አሳማኝ ምክኒያት አይታየኝም፡፡
አሁን አብዱ ኪያር ከሆነች ቆንጅዬ ልጅ ጋር የሰራውን “ ፍቅርዬ ወዬ ወዬ” ምናምን የሚል ክሊፕ አየሁ። አራዳው አብዱ አጠገቡ የቆመችውን ጠይም አጠር ያለች ማይክ ታጣቂ ልጅ «ፍቅርዬ» ይላታል። ልጅቷም እግዜር ወዬ ይበላትና «ወዬ ወዬ» ትለዋለች። (ወዬ የምትለውን ይስጣችሁ) አብዱ ኪያር ምን ሊላት ነው ብዬ ስጠብቅ፤ «እኔ ናፍቄሻለሁ አንገናኝም ወይ?» ብሏት አረፈው። በቃ ግጥም ዘጋኝ ዘጋኝ። አጠገቧ ቆሞ እቺን ጠይም ጨረቃ የመሰለች ልጅ በውዳሴ እንደማጨናነቅ በግማሽ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ “አንገናኝም ናፈቅሺኝ?” ይላል እንዴ? ነውርም አይደል እንዴ? አብዱ  ያን ቢሸነሸን ዘጠኝ እጀጠባብ የሚወጣውን ሰፊ ቲሸርት መልበስ ካቆመ በኋላ እርድና ቀንሷል፡፡
ቀልዱ እንዳለ ሆኖ የፀሃዬና የንዋይን «ዶሮ ውሃ ጠምቶት ተንጋሎ ይጠጣል» የሚለውን ዘፈን አስታወሳችሁት አይደል? በአለም ላይኮ ተንጋሎ የሚጠጣ ዶሮ ታይቶ አይታወቅም። ግን በቃ የዘፈኑ ገጣሚ ለዛሬ ዶሮ ውሃ ቢጠማውና በጀርባው ጋለል ብሎ ቢጠጣ ምን ይሆናል? አለና ፃፈው። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ የዘፈን ግጥሞች ተቃርኗቸው ብቻ ሳይሆን ሁለት በምንም የማይገናኙ ሃሳቦችን ማገናኘታቸውም ነው የሚገርመኝ።
“ዶሮ ውሃ ጠምቶት ተንጋሎ ይጠጣል” ሲሉ የምታስበው ዘፈኑ ስለ ዶሮ ወይም ስለ መጠጥ እንደሆነ ነው። ግን “ከዋሉ ካደሩ መረሳት ይመጣል” ብሎ ነው የሚጨርሰው። ታዲያ የዶሮው ተንጋሎ መጠጣት ከመረሳሳት ጋር ምን አገናኘው? እግዜር ይወቅ
አስቴር ጋር ያለው የግጥም ፋላሲ የትም የለም። የአስቴር አድናቂ ነኝ። ዝም ብላ የኔ ቢጫ ወባ የሚል ዘፈን ሁሉ ብትሰራ ደጋግሜ የምሰማው ይመስለኛል። ከአስቱካ ዘፈኖች ለኔ አንደኛ «ሱፉን ግጥም አርጎ ተከርክሞ ፀጉሩን
መላክ መስሎ ታየኝ አይ ያለው ማማሩ» የሚለው ነው።
አባዬ፤ ወንድ ልጅ ከሆንክ ተፍ ተፍ ብለህ ወጥረህ ሰርተህ፣ ተባልተህ፣ ተባጥሰህ ራስህን ለውጥ! ፀዳ በል። ፀጉር ካለህ ፀጉርህን ተከርከም። ከሌለህ መቼስ ማል ጎደኒ ፂምህን ተንከባከብ። ፂም ከሌለህ ....... አቦ ተፋታኝ የራስህ ጉዳይ ነው! ... ብቻ ዘንጥ! ልብስህንም ኑሮህንም ቀይር፤ በፈጣሪ ነው የምትልህ አስቴር። «አይ ያለው ማማሩ» እኮ አለችህ። ወንድ ከሆንክ አይኔ አፍንጫዬ ሲክስ ፓኬ ገለመሌ አትበል። እሱን እሱን ለቺቺኒያና ለታይላንድ ቺኮች ተውላቸው። “ውበትህ የላይፍ ስታንዳርድህ ነው” እያለችህ ነውኮ አስቱካ። አይ ያለው ማማሩ ስትልህኮ “ከሌለህ ብታምርም አታምርም” ማለቷ ነውኮ። ማይ ብራዘር፤ መልክህን አሳምረህ ስትንቀዋለል ውለህ እንደ ምስጥ አፈር ውስጥ ለማደር ከገባህ በቃ አንተ ... አልተማርክም! ዝም ብለህ የማህበሩ ተላላኪ ነህ ማለት ነው እያለችህ ነውኮ አስቱካ ነፍሴ። ያንተ አይነቱን ወንድ የወሎ ገጣሚዎች እንዲህ ይሉታል፡-
«መልኩን አሳምሮ እንደወሎ ፈረስ
ሶስተኛ ክፍል ነው እስከዛሬ ድረስ»
አስቱካ አንዳንዴ ታዲያ ግጥሞቿ ግራም ቀኝም ያጋቡኛል። ለምሳሌ የሆነ ዘፈኗ ላይ «ቁጭ በል ከሶፋው ሂድ ይመሽብሃል» ትላለች አረ ሴቶች ግራ አታጋቡን በናታችሁ። ወይ ሸኙን ወይ አስቀምጡን
እሺ ሰርግ ላይ ያሉ ግጥሞችስ፣ እኔን ብቻ ነው ግራ የሚያጋቡኝ። ለምሳሌ በሁሉም ሰርግ ላይ የሚዘፈነው «አባው ጃልዬ» ምንድነው? ሐገር ነው? ወንዝ ነው? ሰው ነው? (ሰው ከሆነ እኔ ሰርግ ላይ ምናባቱ ይሰራል?)
ስለ ሰርግ ዘፈን ስናነሳ ነፍሱን ይማረውና ታደሠ አለሙን ሳናነሳ አንቀርም። ታዴ ድምፀ መረዋ ነው። ብዙ ጣፋጭ የሰርግ ዘፈኖች ሰርቷል። ብዙዎችን ቆሞ ድሯል። አንድ የሰርግ ዘፈኑ ግን እስከዛሬም ደጋግሜ ስሰማው ግራ ያጋባኛል። የሰርግ ዘፈን መሀል ምን ሲደረግ እንዲህ አይነት ግጥም እንዳስገባ ወደፊት ስሄድ እጠይቀዋለሁ። መፅሀፍ ቅዱስ ዘፋኝ መንግስተ ሰማይ አይገባም ካለ በኋላ በቅንፍ (ከኢትዮጵያ ዘፋኝ ውጪ) ቢል ጥሩ ነበር። እነ the weekend እኮ ኦልረዲ መንግስተ ሰማይ ናቸው የኛ ዘፋኞች በየመድረኩ ሲደርቁ ከርመው በመዋጮ ታክመው ነው የሚሞቱት። በምድርም በሰማይም ሲኦል አይነፋማ!
ለማንኛውም ታዴ የሰርግ ዘፈኑ ውስጥ እንዲህ አይነት ግራ አጋቢ ግጥም አስገብቷል...
“አረ አበባ አበባ
አረ አበባ አበባ
አበባው አብቦ ማሩም ሞላልሽ
ከንግዲህ ያገር ልጅ ማር ትበያለሽ” ካለ በኋላ መልሶ ደሞ እንዲህ ይላል--
“እንኳን ማር ልበላ አላየሁም ሰፈፍ
እንዲሁ ኖራለሁ በህልሜ ስንሳፈፍ” ብሎ ግራ ያጋባናል። ታዴ ዘፈኑን የአንድ ማር ነጋዴ ሙሽራ x wife ስፖንሰር አድርጋው የሰራው ነው የሚመስለኝ
ታዴ ይሄን የሰርግ ግጥም ታዲያ «ና ገዳይ ያገር ልጅ ፣ ና ገዳይ ያገር ልጅ» እያለ ነው የሚዘጋው ለጦርነት ብሎ ያዘጋጀውን ግጥም አቀናባሪው በስህተት የሰርግ ዘፈን ውስጥ ሳይጨምርበት አልቀረም
ለነገሩ ገዳይ እንወዳለን።
«ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል
ገዳይ ገዳይ ያልሽው ወንድምሽ አይገድል
አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል» ብለን ገበሬነትን አኮስሰን፣ ነፍሰ ገዳይን የምናሞግስ ህዝቦች እኮ ነን። ቅልጥ ያለ የፍቅር ዘፈን ውስጥ ሳይቀር ጦርና ምንሽር ካልገባ መች ደስ ይለናል? ፍቅርና ግድያን አስታርቀን የምንኖር ተአምረኛ ህዝቦች። ምሳሌያችን ሁሉ ከመገዳደል አያልፍምኮ። “ቆንጆ ነው” ለማለት ራሱ “ገዳይ ነው” እንላለንኮ አስቡት ነጮች ጋ ሄዳችሁ ይሄ ሰው ቆንጆ ነው ለማለት This guy is a killer ብትሏቸው ወዲያው ነው 911 ደውለው የሚያሳስሩት
በጣም አሳቅከኝ ለማለት ራሱኮ “በሳቅ ገደልከኝ” ነው የምንለው። ገደልከኝ ገደልኩህ ካላላችሁ አታውሩ ያለን አለንዴ? “ገዳይ ገዳይ” ስንል አድገን ይሆን እንዴ መገዳደል እንዲህ የቀለለብን? የኔ ፍቅር ጂጂዬ ራሱ የሆነ ግዜ አንድ ፀዴ ልጅ አይታ እንዲህ አለች
«አይኑ ገዳይ
ጥርሱ ገዳይ
ስንቴ ልሙት በሱ ጉዳይ»
አረ ከመገዳደል እንውጣ ሚመናን


Read 1509 times