Saturday, 11 September 2021 00:00

ራሷ ከትፋው ታነቀች፣ ራሷ ጠጥታው ትን አላት፣ ራሷ ሰቅላው ራቀ፣ ራሷ ነክታው ወደቀ!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 በአሜሪካኖች ዘንድ የሚነገር አንድ ቀልድ መሳይ ተረት እንዲህ ይላል:-
ከዕለታት በአንደኛው አዲስ ዓመት ዕለት አምላክ ሶስት ታዋቂ ሰዎችን ጠራ 1ኛ/ ቢል ጌትስን 2ኛ/ ቦሪስ ዬልሲንን 3ኛ/ ቢል ክሊንተንን
 ከዚያም “የጠራኋችሁ አንድ አስቸኳይ መልዕክት ስላለኝ ነው” አለ፡፡
ሁሉም በችኮላና በጉጉት “ምንድን ነው?” “ምንድን ነው?” “ፈጥነህ ንገረን” አሉት። አምላክም፤ “ይሄንን መልዕክት እንደ አዲስ ዓመት መልዕክት ቁጠሩት፡፡ ምክንያቱም በመልዕክቱ በመጠቀም ብዙ ህዝብ ታድኑበታላችሁ” አለና፤ “በመጀመሪያ፤ ዬልሲንን፤ ‘ጠጋ በል ዬልሲን፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ዓለም ትጠፋለች፡፡ ስለዚህ ወደ ሩሲያ ህዝብ ሄደህ ይህንኑ አሳውቅ” አለው፡፡ ዬልሲን ወደ አገሩ በረረ፡፡
ቀጥሎ ክሊንተንን “ጠጋ በል፡፡ ለአሜሪካን ህዝብ መንገር ያለብህ መልዕክት አለ። በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ ዓለም ልትጠፋ ነውና የአሜሪካ ህዝብ እንዲዘጋጅና እንዲጠብቅ ንገር!” አለው፡፡ ክሊንተንም አፍታም ሳይቆይ ወደ አገሩ በረረ፡፡
በመጨረሻም አምላክ ቢል ጌትስን “ና ወደ እኔ፡፡ እንደ ሌሎቹ ሰዎች ለአንተም መልዕክት አለኝ፡፡ በቴክኖሎጂው ማህበረሰብ ውስጥ እጅግ ታዋቂ እንደመሆንህ ለኮምፒዩተር ሠሪውና ተገልጋዩ ህዝብ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ዓለም እንደምትጠፋ ደጋግመህ አሳውቅ” አለው፡፡ ቢል ጌትስም፤ “አሁኑኑ ባለኝ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘዴ በፍጥነት እገልፃለሁ” ብሎ ፈጥኖ ሄደ፡፡ ሦስቱም መልዕክቱን ያስተላለፉት እንደሚከተለው ነበር፡፡
ዬልሲን ለሩሲያ ህዝብ እንዲህ አለ:- “አንድ መጥፎ ዜናና አንድ አስደንጋጭ ዜና ልነግራችሁ ነውና አዳምጡ:- መጥፎው ዜና - በዕውነት አምላክ መኖሩ መረጋገጡ ነው። አስደንጋጩ ዜና - ከእንግዲህ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ አናመርትም፡፡ የአገሮችን ዕዳም ምረናቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዓለም በሚቀጥለው ሣምንት ትጠፋለች” አለ፡፡
ክሊንተን ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጥ ስብሰባ ጠራ፡፡ ከዚያም፤ “አንድ ጥሩ ዜናና አንድ መጥፎ ዜና ስላለኝ የአሜሪካን ህዝብ ስማ፡፡ ጥሩው ዜና - አምላክ በዕውነት መኖሩ መረጋገጡ ነው፡፡ In God we Trust (በአንድ አምላክ እናምናለን) ብለን ዶላራችን ላይ መፃፋችን አኩርቶናል፡፡ መጥፎው ዜና - በሚቀጥለው ዓመት ከማንኛውም አገር ጋር ተኩስ አቁም ስምምነት እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም ዓለም በሚቀጥለው ሣምንት ትጠፋለች” አለ፡፡
ቢል ጌትስ በበኩሉ ወደ ሬድሞንድ ሄደ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሚሰጥ በጣም ሰፊ ስብሰባ እንዲጠራ አዘዘ፡፡ ከዚያም፤ “አንድ ጥሩ ዜናና አንድ አስደናቂ ዜና አለኝ፡፡ የመጀመሪያው - አምላክ እኔ ምን ዓይነት አስፈላጊና ትልቅ ሰው መሆኔን ማወቁ ነው! ሁለተኛውና አስደናቂው ዜና - በሚቀጥለው ዓመት የኮምፒዩተር ጥገና ሥራ የለብንም” አለ፡፡
መጪውን ጊዜ ሁሉም እንደየቁቡ፤ ሁሉም እንደየፍጥርጥሩ ነው የሚተረጉመው፡፡ ሁሉም እንደየኪሱ ነው የሚመነዝረው፡፡ አዲሱ ዓመት ከብዙ ችግሮች ይሠውረን ዘንድ እንመኝ፡፡ ልባችንንም ይከፍትልን ዘንድ ተስፋ እናድርግ፡፡ ከገባንበት አስከፊ ጦርነት የምንገላገልበት ዘመን ያድርግልን፡፡ አዲሱ ዓመት ዜጎች በማንነታቸው የማይገደሉበትና የማይፈናቀሉበት ያድርግልን፡፡ የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅና የይቅር ባይነት ዘመን እንዲሆንልን አጥብቀን እንመኝ፡፡  ሀቀኛ ፖለቲካዊ ውይይት፣ የእርስ በርስም፤ ከራስ ውጪም ተቻችሎ የመነጋገር ዘመን ያድርግልን፡፡ ያነሰ ምሬት፣ የበዛ አዝመራ፣ ከቂም በቀል የፀዳ ዓመት ያድርግልን!!
አንድ ገጣሚ፤ “ነብሩን እየጋለበ፣ ሰውዬው እጫካ ገባ ኋላ ቆይቶ ቆይቶ፣ ነብሩ መጣ ብቻውን ላዩ የነበረው ሰውዬም፣ ሆዱ ውስጥ ነው አሁን፤ ሰው ማለት ይህ ነው በቃ ከላይ ሲጋልብ ቆይቶ፣ ሆድ ውስጥ ነው ’ሚያበቃ!” ይላል፡፡
በዚህ ዓመት ከዚህም ይሠውረን፡፡ በዚህ ዓመት፤ ከጠባብ የዘረኝነት አስተሳሰብ ተላቅቀን ለህይወት ዋጋ የምንሰጥበት ይሆን ዘንድ እንጸልይ! የነፃ የሀሳብ ገበያ እንደ ልብ የሚኖርባትና መብት የማይገደብባት ኢትዮጵያን ለማኖር ከባድ ርብርብ እንደሚጠበቅ አውቀን እንትጋ፡፡ በዚህ ዓመት ውዳሴና ሙገሣን እንደምንቀበል ሁሉ ትችትንና ነቀፋንም ለመቀበል ልብና ልቦና ይስጠን፡፡ የህትመት ውጤቶች የህዝብ ዐይንና ጆሮ ይሆኑ ዘንድ፣ የጠባቂነት ሚናቸውንም በወጉ ይጫወቱ ዘንድ፤ ነፃነታቸው መጠበቅም፣ መከበርም ይገባዋል፡፡ ለእነሱም የዕውነትን፣ የመረጃን ትክክለኛነትና የሚዛናዊነትን ሥነምግባር የሚጐናፀፉበት ዓመት ያድርግላቸው፡፡ በዚህ ዓመት ቢያንስ ዐይን ካወጣ ሙስና ይሰውረን፡፡ ወጣቱ አገሩን ከልቡ ይወድ ዘንድ፣ ምንም ዓይነት ካፒታሊስታዊ ማማለያ እንዳይበግረው ከልብ እንመኝ!! አስማተኛ ካልሆነ በቀር አገርን ብቻውን የሚገነባ ማንም አይኖርም፡፡ አንዱ የሌላውን አቅም ይፈልጋል፡፡ ከሌላ ጋር ካልመከሩ፣ ከሌላ ጋር ካልተረዳዱና ሁሉን ብቻዬን ልወጣ ካሉ አንድ ልሙጥ አገር ናት የምትኖረን። የተለያየ ቀለሟ ይጠፋል፡፡ ልዩነት ከሌለ ዕድገት ይጠፋል፡፡ VIVE La difference - ልዩነት ለዘላለም ይኑር ማለት አለብን፡፡ እየተራረሙ መሄድ እንጂ እየኮረኮሙ መሄድ የትም አያደርሰን፡፡ አንዱ ኮርኳሚ ብዙሃኑ ተኮርኳሚ ከሆነ እጅም ይዝላል፡፡ ራሳችን ባወጣነው ህግ ራሳችን አጥፊ ሆነን ከተገኘን፣ ለጥቂቶች ብቻ የሚሠራ ደንብ አውጥተን ብዙሃኑን የምንበድል ከሆነ፣ ራሳችን ሠርተን እራሳችን የምናፈርስ ከሆነ፣ ራሳችን አሳዳጅ ራሳችን ተሳዳጅ ከሆንን፣ ከዓመት ዓመት “የዕውነት ዳኛ ከወዴት አለ?” የምንባባል ከሆነ፤ ምን ዓይነት ለውጥ፣ ምን ዓይነት ዕድገት እየጠበቅን ነው? “ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ” ነውና በርካቶችን የሚያሳትፍ ሥርዓት ይበረክታል ብለን የምናስብበት ዘመን ይሁንልን፡፡ አለበለዚያ፤ “ራሷ ከትፋው ታነቀች፤ ራሷ ጠጥታው ትን አላት፡፡ ራሷ ሰቅላው ራቀ፡፡ ራሷ ነክታው ወደቀ” የሚል ህዝብ ብቻ ነው የሚኖረን፡፡ ያለ ህዝብ የት ይደረሳል? አዲሱን ዘመን አሳታፊ ያድርግልን!!
 መልካም አዲስ ዓመት!!

Read 11124 times