Saturday, 04 September 2021 17:39

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!
                            ጌታቸው ሽፈራው


             አሸባሪው ትህነግ ያኔ ድሮ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ሲመጣ በአደባባይ የታገለ ሰው ነው። የአዲስ አበባ ወጣት ብሶቱን የሚተነፍስለት ሲያጣ ጮህ ብሎ የተናገረለት ታማኝ ነበር። ፖለቲከኛ አልነበረም፣ አርቲስት ለመንግስት በሚያለቀልቅበት ሀገር አርቲስቱ ታማኝ ነው ድምፅ የሆነው፣ ተስፋ የሰጠው። የትህነግ አመራሮችም ባሉበት ሳይቀር ሳይፈራ የሚናገረው ታማኝ በየነ ነበር።
ለዛም ሲባል ወጣቱ “ግባ በለው! ታማኝን ግባ በለው” እያለ ጮኾለታል። ስሜቱን፣ ብሶቱን በደንብ ስለሚገልፅለት ነበር። እውነታውን ስለሚናገርለት ነበር። ታማኝን በገዳዩ በመለስ ለቅሶ ላይ ጥልመት ለብሶ ሲነፋረቅ አላገኘኸውም። ታማኝ ለሕዝብ የተገኘው መለስ ዜናዊ ገና በአፍላው በሙሉ አቅሙ ንፁሃንን ሲገድል ነው።
ታማኝ ለገዳይ አልቃሽ ሆኖ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ድምፅ ሆኖ ነው ያገኘነው። የረባ ሰው ባልነበረበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ተስፋ ባጣችበት ወቅት!
ያ ክፉ ትህነግ ሰሞኑን ታማኝ ሲያጋልጠው ስለኖረ፣ በታማኝ በየነ ቤተሰቦች ላይ ያደረገውን ሰምተናል። ታማኝ ያኔ በወጣትነት እድሜው ትህነግን የተቃወመው ቤተሰቤ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ አይደለም። ሀገሬ ላይ ችግር ያደርሳል ብሎ ነው። ለረዥም ዘመን የተቃወመው፣ ብቻውን በሚባል ሁኔታ ገመናውን ያጋለጠው ለሀገሩ እንጅ ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም። በሁለተኛው ወረራም፣ በዚህ ወቅት በፈፀመው ወረራም ታማኝ አሸባሪውን ትህነግ ያወገዘው ለቤተሰቡ ብሎ አይደለም።
ትህነግ ገና ወረራ ሲፈፅም ታማኝ በየነ ተረባርበን ወረራውን መቀልበስ እንዳለብን አስረድቶናል። የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ነግሮናል። በእርግጥ ታማኝ በአሸባሪው ትህነግ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌላው ጉዳይም ከሀገሩ ጉዳይ ተነጥሎ አያውቅም።
ያም ሆኖ ግን እሱ አሸባሪውን ትህነግ ሲቃወም ፖለቲካ የሚባል የማያውቅ፣ አንዳንዱ በሕይወትም ያልነበረ ሳይቀር ሲተቸው አያለሁ። የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ፣ ትህነግ ብዙዎቹን ያኮላሸበትን የሽብር አዋጅ ያስፀደቀው ኤርሚያስ ለገሰ እንኳን ታማኝ ሳያውቅ የወጣን አንድ ባነር አንጠልጥሎ ሲተቸው አይቻለሁ። አለማፈሩ!
አንዳንዶቹ “አማራ አማራ” ካላለ ብለን እንተቸዋለን። የእኛ ሰው የትም ሆኖ እንዲጠቅም እንኳን እድል አንሰጥም። የእኔን ቅላፄ አንተም ድገመው እንላለን። ደብረፅዮን ወይንም ጃል ማሮ “ኢትዮጵያ” ቢል ፕሮፋይል ለማድረግ የምንዘጋጅ ሰዎች፣ ታማኝ ከድሮም የጮኸላትን ሀገር ስም እንዳያነሳ ከፈለግን ችግሩ ከራሳችን ነው። ፌስቡክና ዩቱዩብ ላይ ፖለቲካ የጀመረው ሁሉ ያለ አግባብ ይወቅሰዋል። ታማኝ ግን አሁንም አለ።
ከአቋሙ ሳይዋዥቅ አለ። በእርግጥ አንዳንዴ የሚደርሱ ትችቶች ካለው ተቀባይነት አንፃርና፣ ያደርገዋል ተብሎ ከሚታመነው አንፃር ሊሆን ይችላል። “ይህን ቢልልኝ” ከሚል ነው። ራሳችን ማድረግ ያቃተንን እሱ እንዲያደርግ ከመፈለግ ነው።
ታማኝ በለግላጋ እድሜው ጀምሮ አሁንም ሽበት በሽበት ሆኖ እንቅጭ እንቅጩን እንዲናገርልን እንፈልጋለን። የሳምንት አጀንዳ አስመርሮት ፌስቡኩን ሰግቶ የሚወጣ ትውልድ ታማኝን እድሜ ልክህን ተናገርልኝ ይለዋል። ታማኝ እየተናገረ ነው፣ ወገኑን እያገዘ ነው። ሁሉን እንዲያደርግ፣ ችግር ባለበት ሁሉ እንዲደርስ አትጠብቅ። አንተም የራስህን አድርግ!
ታማኝ ሰው ነው። እድሜውን ሙሉ የታገለ። ከምን መጣ የማይባል አሸን ልፍለፋም ሊያሰላቸው የሚችል ሰው ነው። ያም ሆኖ አሁንም አለ። ከእነ አቋሙ። እኛ የረባ ያልጮህነው “ጩህልን” ስላልነው ሳይሆን ለህሊናው ብሎ ይጮሃል፣ ይረዳል፣ ይታገላል። ያኔ ያወገዘውን ትህነግ፣ ሲያጋልጠው የኖረውን ትህነግ አሁንም እንታገለዋለን እያለ ነው። ይህን የመሰለ ሰው አሁንም “ታማኝን ግባ በለው!” ብለህ የምትጮህለት እንጅ፣ የምትጮህበት አይደለም!



Read 1550 times