Saturday, 04 September 2021 17:14

የምርቃናዎች ወግ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

በጫት ሳቢያ ከሥራ ተባርሬያለሁ፡ የምቅመው ለማንበብ ነው፡፡ ሰሞኑን የሊዮ ቶልስቶይን War and Peace በቶልስቶይ አይነት ተመስጦ እያነበብኩ ነው፡፡
የመቃሚያ ብር የለኝም፡፡ እንዳልኩት የምቅመው ለማንበብ ነው፡፡ መቃሚያ ብር ስላልነበረኝ ግን War and Peace ን ሸጬ ወደ ጫት ቤት ሄድኩኝ፡፡
እንግዲህ ጫት እዚህ ድረስ ነው፡፡ ለማንበብ ብሎ የሚቅም ሠውን መጽሐፍ አስሽጦ ያስቅማል። አብዛኛው ጊዜ ቃሚዎች ጫትን እንደ ግብአት ተጠቅመው ምርቃና ላይ ለመድረስ ለመነቃቃት ወይም ለመዝናናት እንደሚቅሙ ያስባሉ፡፡ (ይህን ሲያስቡ ወይም ሲሰሙ ምርቃናዎች ሁሉ ይስቃሉ)
በነገራችን ላይ ምርቃናዎች ቃሚዎችን እንደ አሻንጉሊት ነው የሚያዩዋቸው።
ነገርየው የተገላቢጦሽ ነው፤ እስከዛሬ ስናስብ እንደኖርነው አይደለም፡፡ ግብአቱ ሠው፤ መዳረሻው ደግሞ “ምርቃና” ነው፡፡
ምርቃናዎች ወዳሰኛቸው መንገድ፤ በተመቻቸው ሁኔታ ነው ቃሚውን የሚጋልቡት፡፡ ይህ መገለጥ የተከሠተበትን አጋጣሚ ልንገራችሁ፡፡ በአንድ ወቅት እንደተለመደው ጫት ቤት ጎራ ብዬ የተለመደውን አዝዤ ጥጌን ይዤ ተቀምጫለሁ። ጫት ቤት ደርሰው ወይም ቅመው የማያውቁ ሠዎች ቢሠሙት የሚገርማቸው ቃሚዎች ደግሞ ሁሌ የማያስተውሉት አንድ ነገር አለ። ጫት ከታዘዘ በኋላ የመጀመሪያውን ጉንጭ ለመጉረስ ያለው ማመንታት እና ውዝግብ ይገርማል፡፡ ቃሚዎች በዚህ ሁኔታ ባሉበት ሰዓት ካለሁበት ገዢ ቦታ ሆኜ ቃኘሁ። የሁሉም ፊት ይገርማል፡፡ ያሳዝናል፡፡
ሁለት ጓደኛሞች ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ገንዘብ አጋጭተው እንኳ ለአንድ ሰው ፍጆታ ብቻ የሚሆነውን ለሁለት ለመቃም እየተጉ ቢሆንም አሁንም ፍራንክ ያጥራቸዋል፡፡ ከፊቴ የተቀመጠው ሰውዬ አለቃው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው ከትላንት በስቲያ መርቅኖ ነግሮኛል። ከሱ በስተግራ በኩል የተቀመጠው ጫት ዱቤ ተከልክሏል፡፡ ለማልቀስ አምስት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከሱ አጠገብ ያለው ደግሞ በር በሩን ይመለከታል። ከሚያውቃቸዉ ሠዎች አንዱ በተአምር ብቅ እንዲል ይጠብቃል። ለሌላ አይደለም፤ አንድ ሁለት እንጨት የሚረብሠው እግዜር እንዲልክለት ነው፡፡
በር ላይ የተቀመጠው ወጣት ልጅ ነው። አስር ሲደመር ሁለት ይማራል፡፡ ቤተሰቦቹ ኮሌጅ ገብቶ የአዋቂዎች አዋቂ እንዲሆን፣ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቃ አጥብቀው ይፈልጋሉ። ጫት መቃም መጀመሩን ሲሰሙ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ደነገጡ፡፡ መጀመሪያ መከሩት። ከዚያ በጓደኛ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በሰፈር ሽማግሌዎች አስመከሩ፡፡
በየተራ ለሁሉም ታቦቶች ተሳሉ። አንዳቸውም ተሳስተው አልሠሙም፡፡ ፀበሎች ባሉበት ይዘውት ዞሩ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ ሳይካትሪስቶች ሁሉ በሠዓት እየተከፈላቸው አዋሩት፡፡ (ይህ ሁሉ
የምርቃናዎች ወግ ሲሆን ልጁ ይበሳጫል። ምርቃና ደግሞ የበለጠ ትበሳጫለች፡፡)
ያው በመጨረሻ እቤት ውስጥ ያለውን እቃ ሸጦ ሳይጨርስ ብለው ለመቃሚያ በቂ በጀት በጀቱለት። ይኸው ከትምህርት ቀርቶ እየቃመ ነው፡፡
ልክ ከዚህ ወጣት ፊት ለፊት ፀጉራቸው ጥጥ የመሠለ ሽማግሌ እየቃሙ ነው፡፡ ጡረታ በ55 አመታቸው ከወጡ በኋላ ነው መቃም የጀመሩት፡፡ አሁን 65 አመታቸው ነው፡፡ በአስር አመታት ውስጥ ግን አንድ ሠው በእድሜ ዘመኑ የሚቅመውን ያህል ቅመዋል፡፡ ወጣት እና ትጉህ እያሉ፣ በጉብዝናቸው ወራት ምንም ሱስ አልነበራቸውም፡፡ (…,ሽማግሌው ሚስት አላገቡም። ልጅ የላቸውም፡፡) ጥሩ ጥሪት ቋጥረዋል። ቋጥረው ነበር፡፡ በአስር አመት ውስጥ አወደሙት። አብራቸው የኖረችውን ማርቼዲስ መኪና በቅርቡ ነው የሸጡት፡፡ ብቻቸውን ይኖሩበት የነበረው እና በደህና ጊዜ የሠሩትን ቪላ አከራይተው እራሳቸው አንዷ ሠርቪስ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እየቃሙ ነው፡፡
እዚህ ቤት ደንበኛ የሆኑ እና እዚህ የተዋወቁ ሶስት ሴት ቃሚዎች አንድ ላይ ተቀምጠዋል። አንዷ የህግ ምሩቅ ናት፡፡ ኮሌጅ ለጥናት ብላ የጀመረችው ጫት ሡስ ሆኖ ቀረ፡፡ አንደኛዋ ሴተኛ-አዳሪ ናት፡፡ ለምን እንደምትቅም ስትጠየቅ “ለራስ ነዋ” ትላለች፡፡ “መጠጡን እንዴት ሳልቅም እችለዋለሁ?!” ትላለች፡፡ ስትቅም ግን ብዙ፤ በጣም ብዙ እንደምትጠጣ ማወቅ አትፈልግም፡፡
“በዚያ ላይ የዚያን ሁሉ ሠው ፀባይ እንዴት ያለ ምርቃና እችለዋለሁ?!” ብላ ትጠይቃለች። “ባልቅም ይኼኔ አሳብደውኝ ነበር” ትላለች እየሳቀች፤ ሳቋ የሰማይን ጣራ አልፎ እየተሰማ። “መርቅኜ ግን ስንቱን አሳብጄዋለሁ መሰላችሁ?!” ቁጥሩን የምታውቀው እሷው ናት፡፡ የምታውቀው አትመስልም እንጂ፡፡
ሶስተኛዋ ከተማው ውስጥ በደንብ የሚታወቅ ሚሊየነር ልጅ ናት፡፡ ገና አስራ ሰባት አመቷ ነው፡፡ ፍቅር ያስጀመራት የሷው ቢጤ የቱጃር ልጅ ነው፡፡ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ጫትም አብሮ ነው ያስጀመራት፡፡
አሁን አብረው አይደሉም፡፡ አሁን የሱ አይደለችም፡፡ አሁን የማንም አይደለችም፡፡
አሁን የሁሉም ናት፡፡ አሁን የጫት ሆናለች። (የሌሎቹን ቃሚዎች ጉድና ገመና በኋላ ምርቃናዎች ይነግሩአችኋል) እየቃምኩ ነው ይህን ሁሉ የምከታተለው፡፡ ሁሉም ቃሚዎች ጫታቸውን ማላመጡን ተያይዘውታል። በደንብ መርቅነው አፋቸው ከመለጎሙ በፊት ተራ እየተሻሙ ሁሉም ይንጫጫሉ። ጨዋታው ደራ፡፡ ሠዓቱ በሄደ መጠን እንደሚጠበቀው እና እንደተለመደው ቀስ እያለ የጨዋታው ድምጽ እየከሠመ መጣ። ሁሉም ቃሚ እንደ ቀንድ-አውጣ እየራሱ ቀፎ ውስጥ ገባ፡፡ ፀጥታ ሠፈነ፡፡ እና፣ እና፣ እና …
በዚህ መሀል ልክ አርኬሜዴስ የተባለው ጥንታዊ ሳይንቲስት የግኝቱን ቅፅበታዊ መገለጥን የገለፀበት  ሁኔታ በኔም ደረሠ፡፡ “Eureka!” አልኩ፡፡ “Eureka! ድምፅ አገኘሁ፡፡” (ይህ ግኝት አርኪሜዴስ እና ግሪኮች እንደሚኮሩበት ግኝት እኔና ኢትዮጵያዊያንም በመጪዎቹ ግዜያቶች እንኮራበታለን ብዬ አስባለሁ)
ድምጽ ሠማሁ፡፡
ሁሉም ፀጥ ብሏል ብያችኋለሁ፡፡ ታዲያ የምን ድምፅ ሠማህ? አትሉም? የምርቃና፡፡
የምርቃናዎች ድምፅ ሠማሁ፡፡
ብታምኑትም፣ ባታምኑትም ምርቃናዎች እርስ በርስ ሲያወሩ ሠማሁ፡፡
ምርቃና አንድ፡-
ለወትሮው ለወሬ ቀዳሚ የነበረችው ምርቃና እንደ ቃሚዋ ጨምታለች፡፡ “ያንቺ ሠውዬ ዛሬም እንደተለጎመ ነው አይደል?” አላት አንድ ቀዥቃዣ ምርቃና፡፡
“እስከ ዛሬ የደበቅኋችሁን አንድ ነገር ልንገራችሁ ወይም አልንገራችሁ ወይስ ምን? እያልኩ እያሰብኩ ነበር”
“ንገሪን”
“አትንገሪን”
“እንደፈለግሽ”
“እነግራችኋለሁ”
“እንደፈለግሽ ተብለሻል”
“እስከዛሬ በምርቃና አለም ተከስቶ የማያውቅ ነገር ስለሆነ ነው እስከ አሁንም ዝም ያልኳችሁ። አታምኑኝም ብዬ፡፡ አላስቻለኝም ዛሬ፡፡ የኔ ሰውዬ መርቅኖ አያውቅም”
“ምን?!”
“ምርቃና ሆዬ መርቅነሻል መሰል!”
“እንዴት ነው በየቀኑ ሁለት ሙሉ በለጬ እየቃመ የማይመረቅነው?!” ተንጫጩ ምርቃናዎቹ
“ከፈለጋችሁ እሱ የሚቅመው ምርቃናውን ለመስበር ነው”
“ያንተ ያለህ! ጉድ ሳይሰማ ምርቃና አይሰበርም አሉ” አለ አንዱ ምርቃና፡፡
“አያችሁ ታሪኩ ትንሽ ሳይወሳሰብባችሁ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ቶሎ ያልገባችሁ” አለች የጭምቱ ምርቃና ሚስጢራዊ በሆነ ድምፅ፡፡
“አቦ እንዳልመረቀነ ነገር፣ ነገር አታንዛዢ፡፡ ንገሪና፡፡ ምንድነው ቅሞ ሳይመረቅኑ ምርቃና በጫት መስበር ማለት?”
“አብሽር እንግራችኋለሁ፡፡ ሠውየው የተወለደው መርቅኖ ነው እና የግድ እንደ ሌሎች ሰዎች ለመሆን መቃም አለበት፡፡ የሚቅመው ምርቃናውን ለማጥፋት ነው፡፡ የተፈጥሮ-ምርቅን ነው ባጭሩ፡፡ ገቢቶ?!
ሁሉም ምርቃናዎች አጉረመረሙ፡፡ በሰው ልጆች ላይ በተለይ በቃሚዎች ላይ (በቃሚዎች በኩል በሌሎች ላይ) በሚያሳድሩት ተፅእኖ ሁሌም እንደኮሩ ነበር፡፡ ለካ እንዲህ አይነትም ሠርጎ ገብ አለና! ላለመመርቀን መቃምም አለ ለካ!
 ወይ ጉድ! ይኼን ሌሎች እንዳይሰሙ ብቻ፡፡)
“ይህቺን ‘ምርቃና’ በሌላ የምርቃናዎች ስብስብ እናወራታለን፡፡ እኔ ይህ ቃሚ በጣም ገርሞኛል፡፡ ‘የባሰ አለና አወዳይን አትልቀቅ’ ያለው ማነው?!” አለ የአወዳይ ምርቃና፡፡
ምርቃና ሁለት፡-
“የኔ ሠውዬ” አለች አንዷ ጠይም ምርቃና፣ ምርቃና አንድ የፈጠረችውን አግራሞት ለማሸነፍ እየጣረች። “የኔ ሠውዬ ጫት መቃም ደብሮታል፡፡ በመከራ ነው የሚቅመው። አሁኑኑ ጉንጩ ውስጥ ያለውን ተፍቶ ተነስቶ ሁለተኛ ባይመለስበት ደስ ይለዋል”
“ለምን ይቅማል ታዲያ?” የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡
“ለሚስቱ ብሎ”
“ኡውውድ” በአንድ ላይ፡፡
ይኼኔ አንድ ሽማግሌ ምርቃና አግራሞቱን ገለፀ፡- “ዛሬ ምንድነው የምሰማው አንዱ ላለመመርቀን ይቅማል፡፡ አንደኛው ደግም ጫት ለጉድ ቀፎታል ግን ለሚስቱ ብሎ ይቅማል፡፡
ምንድነው ነገሩ? እስከዛሬ ስንት ሚስቶች ናቸው ስንት ባታሊዮን ሽማግሌ አሰልፈው ውድ መርቃኞቻችንን ከኛ የለያዩት? ስንቶቹስ ናቸው ‘ከጫት እና ከኔ ምረጥ’ ብለው ምራጭ የሆኑት?! ይህ እኛ ምርጥ ተመራጭ ለመሆናችን በቂ ምስክር ነው፤ ጉራ አይሁንብኝና፡፡
እና ዘንድሮ ምን አይነት ባልና ሚስት መጡ ልትሉኝ ነው? ‘እባክህ ቃምልኝ’ የምትል ሚስት ወይስ ‘ላንቺ ስል የማልሆነው የለም፤ መመርቀን ጭምር’ የሚል ባል መጣ?! ጉድ እኮ ነው፡፡ ምርቃና ሁለት ምርቃና አንድ የተናገረችውን ቃል በቃል ኮርጃ እንዲህም አለች፡- “አያችሁ ታሪኩ ትንሽ ሳይወሳሰብባችሁ ምርቃና ከገፅ 17 የዞረ
አይቀርም፤ ለዚህ ነው ቶሎ ያልገባችሁ”
“የምርቃና ዋነኛውና ትልቁ ቁም ነገር፣ ነገር ማወሳሰብ ሳይሆን ማቅለል ነው፡፡ We are here to make things simple. Not complex. Not at all’ ይል ነበረ አንድ መርቃኝ መሀንዲስ።” አለ አንድ ብልህ ምርቃና፡፡ “ይኸውላችሁ ነብሶቼ እንዲህ ነው፡፡
የኔ መርቃኝ ምርቃናዎች ብቻ ሳይሆን ሴቶችም የሚሳሱለት ነው፡፡ ቆንጆ ነው፡፡ አሪፍ ስራ አለው፡፡ ታማኝ ነው፡፡ ምርጥ brain አለው፡፡ ሁሌም ትሁት ሁሌም ፍቅር ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ he is a man of all season.” “አቦ አሳጥሪው!”
“አቦ ተረጋጋ፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ እየመጣሁ ነው። ሚስቱ ትወደዋለች፡፡ ወይ መውደድ! በቀን አርባ ስምንት ሰዓት ስለሱ ነው የምታስበው፡፡ ፍፅምናው ያስፈራታል። አንድ ድክመት እንዲኖረው ትፈልጋለች። አስተውላችሁ ካያችሁ ጥንካሬ ብቻ ሣይሆን ድክመትም ፍቅርን የሚያደረጅበት ሁኔታ አለ”
“አቦ አትፈላሰፊ”
“እፈላሰፋለሁ”
“እሺ ታሪኩን ንገሪን”
“Okay”
“እንግሊዝኛ አታብዢ ደሞ”
“Okay”
“እባክሽን ንገሪን፣ ለምንድነው ለሚስቱ ብሎ የሚቅመው?”
“ፍቅራቸውን ለማደርጀት፡፡ ጓደኞቼ፣እሱ ጫት መቃም ያቆመ ለታ ስለምን ያወራል? ስለምንም። እሱ ስለምንም አያወራም ድሮም። እሱ የሚቅም ከሆነ ግን እሷ ቢያንስ ‘ፍቅርዬ ይኼን ነገር ለምን አትተውም? አይጎዳህም?’ ብላ ወሬ መጀመሪያ ታገኛለች። ፍቅሯንም፣ ለሱ ሃሳቢነቷንም መግለጫ ይሆናታል፡፡ እንጂ ሁልጊዜ ከመሬት ተነስቶ ‘እኔ እወድሃለሁ’ ሲባል አይኖር ነገር። ምክንያት ያስፈልጋል ፍቅርንም ለመግለፅ፡፡”
ምርቃና ሶስት፡- “የእነሱ እንኳን ደስ ይላል፡፡ አለላችሁ እንጂ ይኼ”
“የቱ?”
“ይሄ ወዲያ ማዶ ጥግ ላይ የተቀመጠው ቀፋፊ ነዋ! ይኼ ትልቅ ጭንቅላቱ በምን ሀሳብ እንደተሞላ ታውቃላችሁ?”
“በብር”
“አይደለም”
“በተንኮል?”
“አይደለም አቦ”
“በዕውቀት?”
“እንዲያም አድርጎ የለምi”
“በፍርሃት?”
“ሌላ”
“በስልጣን ምኞት?”
“አሁንም ሌላ”
“እና ታዲያ በምን?”
“በሴቶች”
“እና ታዲያ ይኼ ምኑ ይገርማል?” “አሁን እራሱ እዚህ ተቀምጦ ምን እያደረገ እንዳለ ብታውቁ ‘ታዲያ ይሄ ምኑ ይገርማል?’ አትሉም ነበር፡፡”
“ምን እያደረገ ነው በአላህ?”
“እየባለገ በሃሳቡ፡፡ ይህቺ ቃሚዎችን ከምታስተናግደው ልጅ ጋር በሀሳቡ እየባለገ ነው። ማታ አብሯት ነው ያደረው የሚገርማችሁ”
“ምን አይነቱ ባለጌ ነው?”
አለች አንዷ ጨዋ ምርቃና፡፡
“የክፍለ ዘመኑ ባለጌ!” አለች ሌላዋ፡፡
እስካሁን ዝም ብላ የነበረች ምርቃና፡- “እናንተ?!” አለች በቀስታ፡፡
“እህስ?!”
“እኔ ፈርቻለሁ!”
“ምንድነው ያስፈራሽ?”
“የኔው መርቃኝ በቅርቡ ሊያብድ ይችላል፡፡”
ሁሉም ምርቃናዎች ዞረው የተፈራለትን ሠውዬ አዩት፡፡ ቀይ፣ ረዥም፣ ቀጭን ሠው ነው። ፊት ለፊቱ ያለው ግድግዳ ላይ አፍጥጧል፡፡ “እውነቴን ነው በቅርቡ ሳያብድ አይቀርም። ውጪ አያስታውቅበትም እንጂ ውስጡ ተመሳቅሏል፡፡”
ልክ ይኼን እንዳለች ሶስት በስድስት የሆነችው ጫት ቤት በጩኸት ተሞላች፡፡ ሠውዬው ነው የጮኸው፡፡ ሁሉም ምርቃናዎች ደንግጠው ወደ መርቃኞቹ ተመለሱ፡፡
ከአዘጋጁ፡- (የልብወለዱን አዝናኝነትና አስተማሪነት በማየት በድጋሚ ለህትመት ያበቃነው መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፤ ከአዲስ አድማስ ድረገጽ፣ ጃንዋሪ 19፣ 2013)



Read 2088 times