Print this page
Saturday, 04 September 2021 13:53

“…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ከት/ቤት ተመልሶ ወደ ቤቱ ይመጣል። እቤትም ሆኖ ክፉኛ ያለቅሳል።
አባት ከደጅ ሲመጡ ልጁ ሲያለቅስ ያዩትና፤
“ና አንተ አሽከር፣ ልጄ ምን ሆኖ ነው የሚያለቅሰው? እስቲ ሂድና ጠይቀኸው ና?” ይሉታል።
አሽከር እጅ ነስቶ የታዘዘውን ሊፈጽም ይሄዳል።
ልጁ ዘንድ ሄዶም፣
“ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?”
ልጁም፤
“ምንም አልሆንኩም” ይላል።
አሽከር፣
“እንዲሁማ አታለቅስም፤ ዕውነቱን ተናገር” ይለዋል።
ልጅ፣
“የኔታ መትተውኝ ነው”
አሽከርም ወደ አባትዬው ተመልሶ ሲመጣ፣ አባትዬው፡-
    “እህስ ጠየከው?”
አሽከር- “አዎን ጌታዬ”
አባት- “ምን አለ?”
አሽከር- “የኔታ መትተውኝ ነው”አለ።
አባት “ለምን መቱት?”
አሽከር- “እሱን አልነገረኝም”
አባትዬው ተነስቶ ወደ ልጁ ሄደና “ልጄ ለምን ታለቅሳለህ?”
ልጅ- “የኔታ መትተውኝ ነው!” አለ።
አባት- “ለምን መቱህ?”
ልጅ-  “”ሀ” በል ቢሉኝ እምቢ ብዬ ነው”
አባት - “የሞትክ! ሰነፍ! “ሀ” ማለት አቅደህ ትገረፋለህ!”
ልጅ- “አይ አባዬ፣ የየኔታ  ጉዳቸው መች ያልቃል- “ሀ” ስል “ሁ” በል ዠይሉኛል፡፤ “ሁ” ስል “ሂ” በል ይሉኛል። “ሂ” ስል “ሃ” በል ይሉኛል። እንዲህ እያሉ እስከ “ፐ” ድረስ ሊያስለፉኝ እኮ ነው።” አላቸው ይገባል።
*   *   *
ወጣቶች እውቀትን ከሚሸሹበት ዘመን ይሰውረን። አንድ ያገራችን ገጣሚ እንዳለው፤
“… ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ!”
ወጣቶች ለመማር ዝግጁነታቸውን እንዲያጠናክሩ
ሀ. ወላጆች
ለ. መምህራን
ሐ. ራሳቸውና ባልንጀሮቻቸው
ሊያበረታቷቸው ይገባል። አዲሱ አሮጌውን መውረሱ ከአበው ጊዜ ጀምሮ የሚነገር ሀቅ ነው። በፈረንጅኛው THE NEW IS  INVINCIBLE ይባላል። “አዲሱ አሸናፊ ነው” እንደማለት ነው። አንድ ስርዓት ተለዋዋጭ ትውልዶችን ያስተናግድ ዘንድ ግድ  ነው። አንጋፋው ለጎልማሳው፣ ጎልማሳው ለወጣቱ ማውረስ አለበት፡፡ ማውረስ ስንልም ጤናማና ያደገ ውርስ ማለታችን ነው! በትምህርት፣ በጤና፣ በመወያየት ባህል የጠነከረ ማህበረሰብ መገንባት ማለታችን ነው። ይህ ማህበረሰብ ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች ላይ የሚሰራና በትኩረት ነጋ-ጠባ የሚተጋ ኃይልን  የሚፈጥር መሆን አለበት። በዚህ ረገድ የመንግስት ሚና የማይናቅ ነው። መንግስት ቢሮክራሲ የፀዳ መሆንና የተቋማት መጠናከር ልዩ ትኩረትን ይጠይቃል። ዛሬም ከገጣሚ ገሞራው ጋር፣
    “… ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
         ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…”
እንላለን። ሁሉም ጥብቅ ህብረተሰቡን የሚገነባ ነውና  ከተተገበረ ዋና ነገር ነው። ለዚሁም ብርታቱንና ጥናቱን ይስጠን!


Read 14930 times
Administrator

Latest from Administrator