Saturday, 28 August 2021 14:45

የግመሉ ወግ (የአፍጋኒስታን ስነ-ቃል)

Written by  ዶ/ር ኤልያስ ገብሩ
Rate this item
(0 votes)

  ከኢድሪስ ሻህ
ዛሬ ደግሞ ወደ አፍጋኒስታን ተረትና ስነ-ቃል ልውሰዳችሁና አንድ ውብ ወግ ላውጋችሁ። ይህንን ወግ በልጅነቴ የማውቀው ቢሆንም፣ አሁን በማወጋችሁ ቅርጽ ተጽፎ ያነበብኩት ከኢድሪስ ሻህ ድርሰቶች ጋር ከተዋወቅኩ በኋላ ነው። ኢድሪስ ሻህ በአባቱ አፍጋናዊ፣ በእናቱ ደግሞ ስኮትላንዳዊ ሲሆን በአፍጋኒስታንና በመካከለኛው እስያ የሚነገሩትን ጥዑም የሆኑ የሱፊ ወጎችንና ህዝባዊ ስነ-ቃሎችን በተለያዩ መጻሕፍት አሰባስቦ ለዓለም ህዝብ በማስነበቡ ይታወሳል። ከኢድሪስ ሻህ ድርሰቶች መካከል ዝነኛ ለመሆን የበቁት በሙላህ ነስሩዲን ላይ በተከታታይ የጻፋቸው መጻሕፍት ናቸው።
ስለ ኢድሪስ ሻህ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ለጊዜው ይበቃል። አሁን ወደ ተረቱ ልውሰዳችሁ።
ሶስት ባልንጀራሞች ወደ ሩቅ ሀገር ጉዞ ጀመሩ፡፡ የመንገዱን አጋማሽ ከሄዱ በኋላ የግመል ፋንዲያ ታያቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “ይህንን ፋንዲያ የጣለው ግመል ጅራተ-ቆራጣ ነው” አለ፡፡ ሰዎቹ እንደገና ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂት ከተጓዙ በኋላም ምሳ መብላት አሰኛቸውና ከአንድ ዛፍ ጥላ ስር አረፉ፡፡ እዚያ ሳሉም የቡድኑ ሁለተኛ ሰው ወደ ላይ አንጋጦ እያየ “ከዚህ ዛፍ የበላው ግመል አንድ-ዐይና ነው” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ምሳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንደገና መጓዛቸውን ቀጠሉ፡፡ በመንገዳቸው ላይም ግመል የሄደበትን ፋና አዩ፡፡ በዚህን ጊዜም የቡድኑ ሶስተኛ ሰው “ይህንን ዳራ (ፋና) በአሸዋው ላይ ያሳረፈው ግመል ከባድ እቃ ተጭኖበታል” በማለት ተናገረ፡፡
ሰዎቹ ጥቂት ከተጓዙ በኋላ “አንድ ግመል ጠፍቶብኛል፣ በዚህ መንገድ ስትመጡ አይታችሁታል?” ከሚል ሰው ጋር ተገጣጠሙ፡፡
አንደኛው ሰውዬ: “ግመልህ ጅራተ-ቆራጣ ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “ግመልህ አንድ ዐይና ነው?”
ባለ ግመል፡ “አዎን! ትክክል ነህ”
ሶስተኛው ሰው፡ “ግመልህ ከባድ እቃ ተጭኖበታል?”
ባለ ግመል፡ “በትክክል!”
ሶስቱም በአንድነት፡ “ግመልህን አላየነውም፣ ሂድና ፈልገው ወንድም”
ባለ ግመል፡ “እንዴ ምልክቱን አንድ በአንድ እየነገራችሁኝ ሂድና ፈልገው ስትሉኝ አታፍሩም? ግመሌን ስርቃችሁታልና ቶሎ መልሱልኝ፡፡ አለበለዚያ ከዳኛ ላይ ከስሼ አስቀፈድዳችኋለሁ”
ሶስቱ ሰዎች፡ “በእውነት እኛ አላየነውም”
ባለግመሉ በሶስቱ መንገደኞች አባባል ተናድዶ ከዳኛ ላይ ከሰሳቸው፡፡ ሶስቱ ሰዎች ከተከሰሱበት ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ ዳኛውም “እናንተ ግመሉን ለምን ሰረቃችሁት?” አላቸው::
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ አልሰረቅነውም። ጭራሽ ግመሉን አላየነውም”
ዳኛው፡ “ታዲያ ሰውየው ግመሌን አይተውታል ነው የሚለው?”
ሶስቱ ሰዎች፡ “እኛ ስለግመሉ የተናገርነው በመንገድ ላይ ካየናቸው ምልክቶች ተነስተን ነው” ዳኛው፤ “እስቲ ያያችኋቸውን ምልክቶች ንገሩን”
አንደኛው ሰውየ፡ “እኔ ግመሉ ጅራተ ቆራጣ ነው ያልኩት በመንገድ ላይ ካየሁት የግመሉ ፋንዲያ ተነስቼ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያየሁት ፋንዲያ በአንድ ቦታ ተከምሯል። ግመሉ ጅራት ቢኖረው ኖሮ በጅራቱ እየመታው ስለሚበታትነው በአንድ ቦታ አይከመርም ነበር፡፡ ስለዚህ ፋንዲያው በአንድ ቦታ የተከመረው ጅራት ስሌለው መሆን አለበት”
ሁለተኛው ሰውዬ፡ “እኔ “ግመሉ አንድ ዐይና ነው” ያልኩበት ምክንያት በግመሉ የተበላውን ዛፍ አይቼ ነው፡፡ ያየሁት ዛፍ በአንድ ጎኑ ብቻ ተበልቷል፡፡ የዛፉ ሌላኛው ክፍል ግን ምንም አልተነካም፡፡ ግመሉ በሁለቱም ዐይኖቹ የሚያይ ቢሆን ኖሮ ዛፉን በሁለቱም በኩል ይበላው ነበር፡፡ አንድ ዐይና በመሆኑ ግን የዛፉን ሌላኛውን ክፍል ሳይነካው ሄዷል”
ሶስተኛው ሰውዬ፡ “እኔም ግመሉ ከባድ እቃ ተጭኖበታል ያልኩት የግመሉን ፋና አይቼ ነው፡፡ የግመሉ ፋና ወደ አሸዋው ውስጥ ሰርጉዶ ገብቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግመሉ ከባድ እቃ የተጫነበት በመሆኑ ነው፡፡ ግመሉ ቀላል እቃ የተሸከመ ቢሆን ኖሮ የእግሩ ፋና ከአሸዋው ውስጥ ጠለቅ ብሎ አይገባም ነበር”
ዳኛው በሰዎቹ ብልህነትና አስተዋይነት ተገረመ፡፡ ከዚያም “በጣም አስገራሚ ሰዎች ናችሁ፡፡ እጅግ በጣም አስገራሚ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፡፡ የማስተዋል ችሎታችሁ ያስደምማል፡፡ እናንተ ከግመሉ ስርቆት ነጻ ናችሁ” በማለት አሰናበታቸው።


Read 707 times