Saturday, 28 August 2021 14:27

ስብሐትኢዝም ምንድን ነዉ?

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(9 votes)

  ስብሐትኢዝም የደራሲዉ ተከታዮች ነን የሚሉ ቡድኖች በአኗኗራቸዉ ያንፀባርቁት የነበረ የደራሲዉን አኗኗር እንደወረደ በመቅዳት ሲተገበር የነበረ አሉታዊ የኑሮ ዘዬ ነበር፡፡ በወቅቱ የደራሲዉ ግብረ መልስ ዝምታ ብቻ የነበረ ቢሆንም ንቅናቄዉ ደራሲዉን የሚገልፅ አልነበረም፡፡
– ደራሲ እና ሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ
ስብሐት ገብረእግዚአብሔር አብዛኛዉን የሕይወት ዘመኑን ማኅበራዊ የወል የግብረ ገብ እሴቶችን ቸል ብሎ ለሥጋዊ የተድላ ኑሮ ቅድሚያ ሰጥቶ የኖረ ሰዉ በመሆኑ ኤስቴቲክ (aesthetic life) ለተሰኘዉ ለሶረን ኪርክጋርድ የኤግዚስቴንሻል ፍልስፍና አስተምህሮ ዐቢይ ምሳሌ ሆኖ የሚቀርብ ደራሲ ነዉ፡፡
– ረዳት ፕ/ር በለጠ ሞላ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
ስብሐትኢዝም በዘነበ ወላ የተጻፈዉን “ማስታወሻ” የተሰኘ ግለታሪኩን ለህትመት መብቃት ተከትሎ በሁለት ጎራ የተከፈሉ ተከታዮቹ የመሠረቱት ንቅናቄ ነዉ። አንደኛዉ ንቅናቄ ይበልጥ የስብሐትን የአኗኗር ዘዬ እንደወረደ መቅዳት ላይ ያመዘነ ንቅናቄ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ንቅናቄ በተቃራኒዉ የደራሲዉን የሕይወት አስተምህሮና ፍልስፍና በማራመድ የሚገለፅ ንቅናቄ ነበር፡፡
– ደራሲ ዮሐንስ ኃብተማርያም
አንጋፋዉ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በሕይወት በነበረበት ዘመን (አፍላ ወጣት ሳለሁ) የደራሲዉን የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች በሚያደንቁ ወጣት ወዳጆቹ እንደተመሠረተ የሚነገር “ስብሐትኢዝም” የተሰኘ ንቅናቄ አንደነበር በስፋት ሲወራ እሰማ ነበር፡፡ ይህን አጭር መጣጥፍ እንድጽፍ ዐቢይ ሰበብ የሆኑኝም፣ ከአስር ዓመት በላይ ዉስጤ ሲመላለሱ የቆዩ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡” እነዚህ ጥያቄዎች፣ ስብሐትኢዝም ምንድን ነዉ? ንቅናቄዉስ እንደ ንቅናቄ በግልፅ የተደነገጉ አስተምህሮዎች (precisely formulated ideology) አሉት? ንቅናቄዉ በግልፅ የተደነገጉ አስተምህሮዎች ካሉትስ እነዚህ መሠረታዊ አስተምህሮዎች ምንድን ናቸዉ? ደራሲዉስ ንቅናቄዉ መኖሩን ያዉቅ ነበር? ደራሲዉ የንቅናቄዉን መኖር ያዉቅ ከነበር በግልፅ ለንቅናቄዉ የሰጠዉ እዉቅናስ ነበር? ንቅናቄዉስ ዘመናችን ድረስ በህልዉና ዘልቋል? የሚሉ ናቸዉ፡፡     
አንጋፋዉን ደረሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን በቅርብ የሚያዉቁት ደራሲያን እንደነገሩኝ፣ “ስብሐትኢዝም” የተሰኘዉ ንቅናቄ በገሀድ የተቋቋመ ንቅናቄ ነበር፡፡ ይህ ንቅናቄ ነፃ የሐሳብ ዉይይት (dialogue) ባሕል እንዲዳብርና ጠንካራ የኪነ-ጥበብ ሂስ እንዲኖር በሚል በጎ እሳቤ በስብሐት አጋፋሪነት ተመሥርቶ የነበረዉን ምሁራዊ ክበብ (intellectual circle) ተከትሎ እንደተመሠረተ፣ በወቅቱ የደራሲዉ የቅርብ ወዳጅ የነበሩ ደራሲያንና የሥነ-ጽሑፍ ምሁራንን በአካል ቃለ-መጠይቅ አድርጌ አረጋግጫለሁ፡፡
“ስብሐትኢዝም” ደራሲዉ በሕይወት ሳለ በወጣት የሥነ-ጽሑፍ አድናቂዎቹና ወዳጆቹ  (በወቅቱ አብዛኛዎቹ የደራሲዉ ወዳጆች የኪነ-ጥበብ ዝንባሌ የነበራቸዉ ወጣቶች እንደነበሩ ይነገራል) ተመሥርቶ በስፋት ይቀነቀን የነበረና በግልፅ የተደነገገ (በጽሑፍ የተቀመጠ) ቋሚ አስተምህሮ ያልነበረዉ ንቅናቄ ነዉ፡፡
“ስብሐትኢዝም” በሚል ስያሜ ከተመሠረቱት ሁለት ንቅናቄዎች አንዱና ብዙ ተከታዮችን አፍርቶ የነበረዉ ንቅናቄ፣ የደራሲዉን ግላዊ ዓለማዊ የእለት ተእለት አኗኗር በመኮረጅ ብቻ ይገለፅ የነበረ ንቅናቄ ነው፡፡ የሥነ-ጽሑፍ ምሁሯ ዶ/ር ፀደይ ወንድሙና ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ እንደገለፁት፣ የዚህ ንቅናቄ ዐቢይ አቀንቃኝ ነን የሚሉ ወጣቶች የደራሲዉን የመጠጥና ሐሺሽ አዘዉታሪነት፣ ያልታረመ የቋንቋ አጠቃቀሙን፣ ለቁሳዊ ጥሪት ግድየለሽ መሆኑን … ወዘተ ብቻ ኮርጀዉ የሚተገብሩ ነበሩ፡፡
“ስብሐትኢዝም” በሚል ስያሜ የተመሠረተዉን ሁለተኛዉን ንቅናቄ አስመልክቶ ልብወለድ ጸሐፊዉና ገጣሚዉ ዮሐንስ ኃብተማሪያም እንዳወጋኝ፣ የዚህ ንቅናቄ ዐቢይ አቀንቃኝ የነበሩ ቡድኖች የደራሲዉን የንባብ ባሕል፣ የሥራ ትጋት፣ የሙያ ልህቀት … ወዘተ በመቅሰም ታላቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጉ የነበሩ ናቸዉ፡፡ አብዛኛዎቹም ኋላ ላይ ስኬታማ ጸሐፍትና ሠዓሊያን ለመሆን በቅተዋል፡፡
ደራሲ ስብሐት ከላይ የጠቀስኳቸዉን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ንቅናቄዎች መኖር በግልፅ ያዉቅ ነበር፡፡ ስብሐት ግን ንቅናቄዉን ከመንቀፍም ሆነ ከመደገፍ በመቆጠብ በዝምታ  መመልከትን የመረጠ ገለልተኛ ሰዉ ነበር፡፡ ንቅናቄዉ የደራሲዉን ህልፈት ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ከስሟል። እስካሁንም፣ የዚህ ንቅናቄ አቀንቃኝ ነን የሚሉ ቡድኖች ስለመኖራቸዉም በቂ ማስረጃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡
ደራሲ ዮሐንስን ጨምሮ አንዳንድ የሥነ-ጽሑፍ ሐያሲያን፣ ስብሐት በገሀድ ሲከተለዉ የነበረዉን የአኗኗር መንገድ ዋቢ በማድረግ፣ ደራሲዉን የሚገልፁት ኒሂሊስት አድርገዉ ነዉ፡፡ በግሌ፣ የስብሐት አኗኗር፣ የኒቼ እና የሳርተር የኤግዚስቴንሻል ፍልስፍና ቀጥተኛ ተፅእኖ ያደረበት አኗኗር ነበር ባይ ነኝ፡፡ በመሆኑም፣ ከግላዊ አኗኗሩና ከሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቹ በመነሳት ስብሐት ደንበኛ ኤግዚስቴንሻሊስት ጸሐፊ ነዉ የሚል አቋም አለኝ፡፡ ስብሐት በአደባባይ ያንፀባርቀዉ የነበረዉ የአኗኗር መንገድ፣ ደራሲዉ በግልፅ የጋርዮሽ እሴት ተቀናቃኝ (ethical antagonist) መሆኑን በግልፅ ይመሰክራልና፡፡ ቸር ሰንብቱ!
ከአዘጋጁ፡ ከላይ የተንጻባረቀው ሃሳብ የጸሃፊው ብቻ መሆኑን እየገለጽን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ Telegram:@MekonnenDefro77 ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 386 times