Saturday, 28 August 2021 14:25

የሆዴን እሳት እኔው ራሴ ካላጠፋሁት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    ...እስከ መቼ? እላለሁ።  "እስከ መቼ እንደዚህ የተደጋገመ ጣዕም አልባ ኑሮ እኖራለሁ፤ እንኖራለን?  ሰዎች ይወለዳሉ፤ ሰዎች ይወልዳሉ፤ ሰዎች በምቾትና በአግባብ የማያሳድጉትን ልጅ ይወልዳሉ፤ ሰዎች ይበደላሉ፤ ሰዎች ይበድላሉ፣ ጥፋተኞች የወንጀላቸውን ዋጋ አያገኙም። እንዴት ነው ነገሩ? ይሄን ሁላ እየታገስን የምንኖረው እስከ መቼ ነው?’ የሚሉ ጥያቄዎችን አደብ የሚያስገዛልኝ የልማዴን አንድ ስኒ ቡና ስጠጣበት ነው። ከዚህ ሁሉ ነገር ጋር ‹ኦኬይ› ሲያስኮነኝ የዚህን ዕጽ አታላይነት አትኩሬ አሰላስላለሁ። ሆኖም በሚቀጥለው ቀንም እሱው ነው በስመአቤ። ከልጅነት እስከ እውቀት ስንት አዳዲስ ነገሮች ሞክሬ ስተው እስከዛሬ ድረስ ‹ፍሰስ በገላዬ› እያልሁት ከኔ ጋር የቀረ ይሄ ባለ ካፌይን አጅሬ ነው።
“ፍጥረት ተሰቃየ፤ ፍርድ ተጓደለ፣ እናት ልጆቿን የምታበላቸው አጥታ አለቀሰች፤ እህት ቤተሰቧን ለመርዳት አረብ ሀገር ሄዳ ተደፈረች፤ እና ምን ይጠበስ አንቺ ፈጥረሻቸዋል? የሚያምኑት አምላክ ምን ይሠራል? አርፈሽ ኑሮሽን ኑሪ፤ ቢሆንልሽ በተሰማራሽበት የሥራ መስክ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ ከልብሽ ሥሪ” እያለ መቀመጫዬን እየኮረኮረ፣ የሚያነቃቃኝ ይሄ ጉዳ ጉድ ነው። እሺ ብዬው በጧት ተነስቼ ሥራዬ ላይ ተደፍቼ ውዬ ብገባም፣ ለሊቱን የማሰላስለው ግን መፍታት ስለማልችለው በየትኛውም ዓለም ስላሉ ፍጡራን ሁሉ ችግር ነው። እንዲህ የሚያደርገኝ ደሞ ስለ ሁሉ ነፍሳት የመቆርቅር ዓላማ ሳይሆን ‹እኔ ብሆንስ› የሚለው ሀሳብ አንገፍጋፊነት ነው።
ቡናዬን ከጠጣሁ በኋላ ሳቅ ሳቅ እያለኝ፣ ዳማሴን እያሽከረከርኩ እጓዛለሁ። ዝናቡ ጥሎ በቅቶት አየር ላይ ያለው ወደ ላይ ለመውጣት ወይ ወደ መሬት ለመውረድ ያልወሰነ የሚመስል ብናኝ የውሃ ቤተሰብ ነው። ወደ መሬት ይወርዳል ቀስ እያለ። ዳር ላይ የቆሙ ከባድ መኪናዎች ካልሆኑ ብዙ ተሽከርካሪ አስፓሉቱ ላይ ሲንቀሳቀስ አለማየቴ በጧት መነሳቴን አስታወሰኝ። የአስፓልቱ ጽዳት መንፈሴን ጥርት ያደረገልኝ ይመስለኛል። ወይም ቡናው ይሆናል እንጃ ብቻ። ቀዝቃዛ አየር ፊቴን እየዳበሰኝ ዐይኔን ጥቁር አስፓልት ላይ ተክዬ እየነዳሁ የማስበው የተገነፈለ በቆሎና ትኩስ የበቆሎና የደንጎሎ ንፍሮ ነው። እነዚህን ሁለቱን እያሰብኩ ምራቄ አፌ ላይ፣ በምላሴ መቅመሻዎች አዳምጣለሁ። አንድ የልጄ ተውኔት እኩያ የሚሆን ልጅ ባጃጅ እያሽከረከረ ቀደመኝና ከፊቴ ዚግዛግ እያደረገ ማሽከርከር ጀመረ። ጉሮሮዬን አንቆ አላስተነፍስ የሚል እልህ ሰፈረብኝ። አፍንጫውን በሽቶ ጠርሙስ ልሰብርለት አስቤ መኪናዬን ዳር አስይዤ አቁሜ ልወርድ ስል ፍጥነት ጨምሮ ይርቀኛል። መኪናዬን ቀስቅሼ መንገድ ስጀምር ዝግ ብሎ ይጠብቀኝና እንደ መጀመሪያው ፊት ፊቴ፣ እንደ ልጄ እንደ ተውኒዬ ውሻ፣ ባጃጁን ሱት ሱት እያደረገ ይሄዳል።
***
የዚህ ያልተቆነጠጠ ቀንበጥ ድርጊት በሕይወቴ ዳር፣ መሃል፣ ዙሪያና ጫፍ ያለፉትን ወንዶች ሁሉ ተራ በተራ እያመጣ ዐይነ ልቦናዬ ፊት አመላለሰብኝ። አባቴ ከቤት ውጪ በሥነ ምግባሩ የተመሰገነ፣ በሥራውም የሚጨበጨብለት ነበር። ልጆቹን ይወደን ነበር። በእንክብካቤው ችግርን ሳናውቅ ነው ያደግነው ልጆቹ። ከነዚሁ ሁሉ በልጦ በአዕምሮዬ ስለእሱ ደምቆ የተጻፈው ግን እናቴን በቀበቶ የሚገርፋት ነው።  ቀጣዩ ወንድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ እወድሻለሁ ይል የነበረ ሰውነቱን ያደለበ ወጣት ነው። እንዲህ ያለ ቀልድ አይመቸኝም አልኩት። አንድ ቀን ከትምህርት ስንለቀቅ በር ላይ ጠብቆ ፈሱን እጁ ላይ ፈስቶ፣ አፍና አፍንጫዬን በዚያ እጁ አፍኖ ያዘኝ። የምሞት መስሎኝ ነበር በሰዓቱ። የተውኔትን አባት እስክተዋወቅ ድረስ ወንዶች ሁሉ "ግማታሞች" ይመስሉኝ ነበር።
ቲያትር ይወድ ነበር። ልጃችንን ተውኔት ብሎ ስም ያወጣላት እሱ ነው። ፍቅር መስጠትም ይችል ነበር። መሥራትስ ቢሆን። ብቻ የበላይ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል ሁልጊዜ። የጀብዱ ፊልሞች እያየ ይመጣና አለቃ ነኝ ይላል። በሕይወቴ አለቃ ሲሆኑብኝ አልወድም። ያላወቅሁትን ሲያስረዱኝ እንጂ ሲጮሁብኝ አልወድም። ላጠፋሁት ሲመክሩኝ እንጂ ሲቆጡኝ አይስማማኝም። እጁን ሰንዝሮ ደብድቦኝ አያውቅም። ያም ሆኖ ለኔ በቂ አልሆነም። በአካልም ሆነ በመንፈስ መለካካት የሌለበት ሕይወት ካልሆነ አሻፈረኝ አልኩ። አንዴ ወጣ አንዴ ወረድ ማለት ‹ኖርማል› ነው አልኩት። ያንን አምኖ መቀበል አልሆነለትም። እያለቀስኩለት ተለያየን።  ከምሳሳላት ከልጄ ከተውኔት ጋር እንደ ሩቅ ዘመድ የተራራቅሁት በወንድ ነው። ከወንዶች ጋር ሳያት፤ ወንዶቹን። ድርጊቴ ሲደጋገም የሆነ ቀን ክፉኛ ተጣላችኝ። የምትወደው ልጅ በኔ ጸባይ ተማርሮ እንደተጣላት ምናምን ለፈለፈች። ምን አስቤ እንደነበር አላውቅም። አሁን አሁን ስናስበው በዚያ ሁኔታዬ ጭራሽ ያለወንድ ላኖራት እችል እንደነበረ እያሰብን እንስቃለን። በዚያ ትቷት የሄደ ፍቅረኛ ሰበብ ተሸካክረን ብዙ ከረምን። ከሌላ ወንድ ጋር ሳያት መላ ሰውነቴን ቢያሳክከኝም፣ የበለጠ እንዳትጠላኝ ብዬ መቆጣቴን ተውኩ። በነጭናጫነቴ ተማርራብኝ አባቷ ጋር ጥላኝ ባለመሄዷ ተመስገን እያልኩ አርፌ እታዘብ ጀመርኩ፤ ኑሮዋን።
አንድ ዕለት ሶፋ ላይ ጋደም ብዬ ቴሌቪዢን እመለከታለሁ። ልጄ እያለቀሰች መጥታ በር ላይ ቆመች። ድምጽ አታወጣም፤ በአፍንጫዋ አየር ስትስብ ያወጣችው የሚነፋነፍ ድምጽ ነው፤ እያለቀሰች መሆኗን ያስታወቀኝ። ቀና አልኩና ፊቷን አትኩሬ ማየት እንደጀመርኩ፣ ያልጠራሁት እንባ ከዐይኔ ክንብል አለብኝ። ምክንያቱን እንኳን አልነገረችኝም፤ ገና እየተያየን እናለቅሳለን። “ማሚ ቺት አረገብኝ እኮ” አለችኝ፤ ከቆመችበት ሳትነቃነቅ። ልትጠጋኝ ፈልጋ በመሃላችን የከረመው መገራመም እንደተገዳደራት ገመትኩና እጄን ዘረጋሁላት ‹ነይ› እንደማለት። በመሃላችን ያለው ሦስት የትልቅ ሰው እርምጃ ቢሆን ነው። ከውጪ በር እንደምትመጣ ነገር እየሮጠች መጥታ አንገቴ ሥር ገባች። አለቀሰች፤ በመከፋት። አለቀስሁ እኔም። ለሁለት ነገር፥ አንድም ልጄን ስላስለቀሰብኝ፣ አንድም ልጄን ማቀፍ ስለቻልኩ ተደስቼ። በአንድ ነገር  እየተከፋሁ ተደሰትኩ።  ልጄ ከፍቷት መጥታ ለማልቀሻ የኔን አንገት መምረጧ አዲስ እንደወለድኋት ያህል አንሰፈሰፈኝ። ደስታዬ ግን “ብየሽ ነበር ድሮም” የሚለው ሳይሆን ወንድ ልጅ ከሚባል ነገር እጆች ውስጥ ልጄ በመውጣቷ ቢሆንም ይሄን በሚያህል ጥላቻዬ ራሴን እየታዘብኩ ነበር። መብቴን አላስነካም በሚል ሰበብ ልጄን ከመብቷ እየከለከልኩ ልኖር እንደነበር ሳስብ፣ የልጄን እንቢ ባይነት አደነቅሁ፤ ምንም እንኳን መጨረሻ ላይ እኔ ያልኩት ቢሆንም።
ስሜት መንበልበል ሲደክመኝ ተረጋግቼ ማዘን ጀመርኩ። ልጆቻችን ወንድነታቸውን የሚያሳዩበትን መንገድ አለማወቃቸው ሆዴን አስጨነቀው። የኔን መኪና የያዘው ወንድ ቢሆን ኖሮ ልጁ እንደዚህ እንደማያደርግ አውቃለሁ። ልረግመው አስባለሁ፤ አንዱ ባለተሳቢ መኪና በሆነ ጎደሎ ቀን ከነባጃጁ ጨፍልቆት ሲሄድ ቁልጭ ብሎ እየታየኝ። ሲመስለኝ ብዙ መልስ ያጣንላቸው ክስተቶች የሚፈጠሩት በእርግማን ምክንያት ነው። አሁን ይሄ ልጅ ባደገበት ሰፈር የተመረቀ፤ እናትና አባቱን ያስመሰገነ ይሆናል።  እዚህ ደሞ እኔ ጋር መጥቶ እንዲህ ያለ ያልተገባ ነገር አደረገ። ‘ረገምሁት እንበል። ባለተሳቢ መኪና ይወጣበታል። [‘ርግማንሽ እንደሚደርስ በምን አወቅሽ የሚል አይጠፋም፡ አጭርና ግልጹ መልስ “ስለተበደልኩ” የሚል ነው። በአካላዊ የመልስ ምት ወይም በሰዎች ፍርድ ልቀጣው ወይም ላስቀጣው ስላልቻልኩ በልቤ   እፈርድበታለሁ። ይህም ይፈጸማል። ሞኚት ያሉኝ እንደሆነ፣ የራስዎት ጉዳይ]  ታዲያ የሰፈሩ ሰዎች “ውይ ምን አገኘው? ምን መዐት መጣበት?” ይባባላሉ። መዐቱን ራሱ ላይ እንዳመጣ ግን ማንም አያውቅም። በዚህች ቀላል በመሰለች ትዕቢቱ፣ እናት አባቱን ሀዘን ላይ ይጥላል፤ የሰፈሩን ሰዎች ከመረጃ ውጪ ያስኬዳል፤ የባለተሳቢውን መኪና ሾፌርና  የሚያስተዳድረውን ቤተሰብ የእንጀራ ገመድ ይበጥሳል።
እንዲህ ዐይነት ጉዳይ ታዲያ እስከ ሀገር ድረስ ሊሰፋ ይችላል። መጠርጠር ነውኮ። መንስኤና ውጤቱ ርቱዕነት እጅጉን የጎደለው መሆኑ እንዳለ ሆኖ  ይሄን ጉዳይ [የእርግማኑን ተፈጻሚነት] ማን እንደሚያስፈጽም ብትጠይቁኝ አላውቅም። ግን ያዘነች ልብ በጽኑ የሻተችው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምላት ከሰው ሰምቼ ሳይሆን በሕይወቴ ያየሁት ነው። በእድሜዬ ከዚህም በላይ ንቅዘቶችን የተመለከትኩ ነኝና እናትም ስለሆንኩ የልጅን ነገር ስለማውቀው፤ ወዲህም እነዚህን ወንድ ልጆች ከድርጊታቸው ለማቀብ ያደረግሁት አንድ እንኳን የሚጠቀስ እኔቅስቃሴ ስለሌለኝ፤ ይኸም ከኃላፊነት እንደመጉደል ተሰምቶኝ ‹እንግዲህ ይሄ ልጅ እናቱ እድሜ የጠገቡ ደሃ ይሆናሉ፤ ይቺን ባጃጅ የገዙለት ቦታቸውን ሸጠው ይሆናል› ምናምን ምናምን በሚሉ ማስተባበያዎች ራሴን አግባብቼ ሳልረግመው ቀረሁ። እድሜ እንዲህ እንዲህ ያሉትን ብስለቶች እየደረበብኝ ሲሄድ እመለከታለሁ በየጊዜው። ይሄንን እያሰብኩ ፈገግ አልኩ።
ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንደዚያ እያደረገ ካሽከረከረ በኋላ ሰለቸው መሰለኝ፤ ወይም ረሳው... በሥርዓት ማሽከርከር ጀመረ። በቀስታ ተከታተልኩትና ከሚያቆምበት ራቅ አድርጌ መኪናዬን አቆምኩ።  ከመኪናው ወርጄ በግሬ ሄድኩና በኋላው በኩል አልፌ ዞሬ ከፊቱ ቆምኩ። “የኔ ልጅ አንዴ ላናግርህ?” አልኩት። እኔ መሆኔን ሲያይ ደንገጥ አለ። ፈገግ አልኩለት አደጋ እንደማይመጣበት እንዲያውቅ ብዬ።
“ቅድም ያደረግኸው ትክክል ነው?” አልኩት
“ይቅርታ” አለኝ። አንገቱን ደፋ።
“የጠየቅሁህ ግን ይቅርታ እንድትለኝ አይደለም”
“ትክክል አይደለም”
“ታዲያ ለምን አደረ’ከው?”
አቀርቅሮ ዝም አለ። ምክንያቱን ልቤ ይነግረኛል።  ምክንያቱ ጓደኞቹ ያደረጉትን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት ነው፤ ምክንያቱ ተሞላቅቀው ያደጉ የሀብታም ልጆች ያደረጉትን ድርጊት ሁሉ አራዳነት አድርጎ መውሰድ ነው።


Read 2113 times