Print this page
Saturday, 28 August 2021 13:21

‘ታላቅ ቅናሾች’... ‘ፕራንካችሁን’ ተዉንማ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ ደስ የምትል  የታላቅ ቅናሽ ነገር አለች... “እውነተኛ ታላቅ ቅናሽ!” የምትል። የምር ግን... አለ አይደል....ለእነኚህ ሊጨበጨብ ይገባል፡፡ አሀ...ሲያምኑስ! “ታላቅ ቅናሽ ስንላችሁ የነበረው ፌክ ነው፤ የአሁኑ ግን እውነተኛው ነው፣” ወይም በዘመኑ ቋንቋ “ፕራንክ ስናደርጋችሁ ነበር!” ብለው ራሳቸው ሲያምኑስ! እናማ...በቦተሊካውም፣ በምኑም በምናምኑም “እስካዛሬ ፕራንክ ስናደርጋችሁ ነው የከረምነው!” የሚሉ ጠፍተው ነው እኮ ነገሩ ሁሉ ካብ ለካብ መተያየት አይነት የሆንብን።
“በቀደም በቴሌቪዥን ላይ በነበረው ውይይት የደርጅታችን ዋነኛ ዓላማ ህብረተሰቡን ከዘርፈ ብዙ ችግሩ ለማውጣት ነው!” ብዬ የነበረው ፕራንክ ሳደርጋችሁ ነበር፡፡ እውነተኛው ዓላማችን ቪዛ በቀላሉ እያገኘን አውሮፓና አሜሪካ ለመንሸራሸር ነው፣” የሚል ‘ጉደኛ’ ቦተሊከኛ ከእለታት አንድ ቀን ይመጣ ይሆናል!
እናላችሁ.... ገና ከአሁኑ በየሱቁ የሚሰቀለው አልበቃ ብሎ ስንት ዜናና ሀተታ እያነፈነፍን ባለበት ሰዓት ፌስቡክ በ“ታላቅ ቅናሽ” ማስታወቂያዎች እየተጨናነቀብን ነው፡፡ (ስሙኛማ... የትኞቹ ‘መደበኛ’ ታላቀ ቅናሽ፣ የትኞቹ ‘እውነተኛ’ ታላቅ ቅናሽ መሆናቸውን መርምረው የሚነግሩን ‘ኢንቬስቲጌቲቭ’ ጋዜጠኞች የት ናቸውሳ!)
እንዲሁ ያልጠረጠረ ተመነጠረ የሚል ተረት ሰላለን ሳይሆን ዙሪያችንን ከምናየው፣ ከምንሰማው….“ታላቅ ቅናሽ” የሚሉት ነገር እንጠራጠራለን፡፡ ራሳቸው መደበኛ ብለው በወሰኑት ዋጋ እንኩዋን እንዳይሸጡልን አጋጣሚ እየጠበቁ ምርት ደብቀው ዋጋ የሚቆልሉብን፣ እንዴት ብለው ነው መደበኛ ከሚሉት ዋጋ? ወይ የመላእክት ክንፎች ተቀጥለውላቸው ከሆነም ያሳዩን፡፡ አለበለዛ ወደ ‘ፋክት ቼክ’ መደወላችን ነው!
እኔ የምለው... አንድ ጫማ “ኪስን በማይጎዳ ዋጋ… ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ብቻ!” የሚባለው ነገር... በቃ ለሰዉ ሞራል ማሰብ እንኳን ቀረ! ኸረ እባካችሁ ጡር የሚባል ነገር የምታውቁ ከሆነ ጡር ይሆንብናል በሉ! ወይም እኛ እንበልላችሁ… “ተዉ ጡር ይሆንባችኋል!” ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር! እ! እስቲ ድገሙልንማ...ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ነው ኪስ የማይጎዳው! ቆይማ ጥያቄ አለንማ… መለኪያችሁ፣ ወይም ውሀ ልካችሁ የእነማን ኪስ ነው!  እናማ…ስንት ብር ሲሆን ነው ኪስ የሚጎዳው!?
ቆየኝማ፣ እኔ የምለው…በፈለጋችሁ ጊዜ አስገድዳችሁ ያለችንን ቤሳ ቤስቲኒ ሳይቀር ካስተፋችሁን፣ በዓልን አስታኮ እኛን በ‘ፌክ’ ታላቅ ቅናሽ ‘ፕራንክ’ እያደረጋችሁ...(ይቺ ቃል ልትለምድብኝ ነው አንዴ!) አለ አይደል...“አያ በሬ ሆይ፣ አያ በሬ ሆይ፣ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ፤” የሚለውን እንድንተርትባችሁ አታሰገድዱንማ! በልባችሁ... “እነኚህ ሰዎች እንዴት ነው የጠገቡት! ምን እንዳያመጡ ነው!” ልትሉ እንደምትችሉ ቀልባችን ይነግረናል፡፡ (’ቀልብ’ በገንዘብ የሚሸመት ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ አልቆልን ነበር! ቂ...ቂ...ቂ...)
እኔ የምለው…… ወይም “ማስታወቂያው እናንተን አይመለከትም፡፡ ታርጌት ኦዲየንሳችን እናንተ አይደላችሁም፣” በሉንና ቁርጣችንን እንወቅ! እንደዛ ከሆነ…የሰፊው ህዝብ ንብረት ከሆነው ከፌስ ቡክ ዘወር በሉልና! ቂ…ቂ….ቂ… (እኔ የምለው… እነ ዙከርበርግ ደግሞ ምን እንሁን ነው የሚሉት! እንቅቡም ሰፌዱም በነገር አየጎሸመን ተቸገርን እኮ! የምር... የሚገርም እኮ ነው! ስለ እኛ ስንትና ስንት ጉድ በሚጻፍበት፣ ቅልጥ ያሉ ስድቦች፣ ዘለፋዎች፣ ፉከራዎችና ከዛም የባሱ ነገሮች በሚለጠፉበት፣ ስንትና ስንት ‘ጉድ’ በሚወጣበት፣ ስለ ሀገራችን የሚጻፉና አልፈው የማንንም መብት የማይነኩ በጎና አዎንታዊ ነገሮች ሲለጠፉ ተሽቀዳድመው አካውንቶቹን በሰረገላ ቁልፋቸው የሚከረችሙት ምን እንሁን ነው ነገሩ!  የሚገርም እኮ ነው! እኔ የምለው የፌስቡክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውስጥ ‘ስማቸው የማይገለጽ’ አባላት አሉ እንዴ!…  
(እኔ የማለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንዳንድ  ነገር ላይ ፈረንጅ አፍ ጣል ማድረግ ከ‘ባ’ የቀለለ ለሆነው ነገርዬ ክብደት ለመስጠት መሞከር ያስመስልብን ይሆን እንዴ! አሁን “አት ሊስት...” ገባች፣ ቀረች ምን ሊመጣ፣ ምን ሊቀር ነው! ቂ…ቂ…ቂ….)
ደግሞላችሁ... አንዳንድ ቤቶች አሉ…አለ አይደል… ከድፍን ዓመቱ አስራ አንድ ወር “ታላቅ ቅናሽ” የሚባል ነገር የማይነሳባቸው።
“ይሄ ሙሉ ልብስ ስንት ነው?”
“ለአንተ ነው?”
ምን አይነት ጥያቄ ነው!...
“አዎ፣ ለእኔ ነው፡፡”
"ለአንተ ከሆነ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አደርግልሀለሁ፡፡" ዙሪያችሁን አየት ታደርጋላችሁ፡፡ የሌሎች ሰዎች ንግግር እየሰማችሁ ነው ወይስ ባለቡቲኩ ነው ያቺን ቁጥር የጠራው! በዛ ሰዓት አጠገባችሁ ደገፍ ልትሉት የምትችሉት ወንበር መኖሩን አየት ማድረጉ አይከፋም፡፡ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፡፡ 
ኪሳችሁ “ምን ላድርግ የእንትን ሰፈር ሰው ብሆንም በቦሌዎቹ ዋጋ ልግዛ እንጂ!” ብላችሁ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ነው የያዛችሁት! “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ” የምትለውን ግጥም በደንብ ትሞከሯታላችሁ፡፡ በአፉ ሙሉ ሦሰት ሺህ አምስት መቶ! ልብሱን እኮ ጠርዝ፣ ጠርዙን ገልበጥ አድርጋችሁ አይታችሁ በሆዳችሁ… “ዩሬካ! ሳላቫጅ!” ብላችኋል፡፡ መለየት ያቃታችሁ ከአሌፖ ይምጣ ከባግዳድ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
ምን ይደረግ…. "ታላቅ ቅናሽ" የኮፒራይት ጥያቄ አይነሳበት ነገር! አንድ ጊዜ የሆነ ሱቅ ነገር ላይ… “የደንበኞቻችንን ጥያቄ በመቀበል ታላቅ ቅናሽ አድርገናል” የሚል ጽሁፍ  ነበር፡፡ ነገርየዋ ትንሽዬ  የፈጠራ ሙከራ ትመስላለች፡፡ ልክ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን ላይ “በህዝብ ጥያቄ የተደገመ” እንደሚባለው አይነት፡፡ “ስንተዋወቅ አንተናነቅ የምትለዋን ተረት ለመጀመሪያ ጊዜ ያላት ሰው ካለፈ ሀምሳም ዓመት ይሁነው፣ መቶም ዓመት ይሁነው የኮፒራይት መብቱ ይጠበቅለት፡፡ አሀ...ለዘመናችንም የምታገለግልና ገና ብዙ ዘመን ‘ይዞታዋን ሳትለቅ’ የምትዘልቅ አሪፍ አባባል ነቻ!
ግርም የሚል እኮ ነው.... “ጾም ሊገባ ነው፣” ብለው ዘይት የሚደብቁ ጉዶች ያሉባት ሀገር! በተዘዋዋሪ... አለ አይደል... “ለእኛ ሲሉ ከፈለጉ ለምን በውሀ እያራሱ አይበሉም የማለት አይነት ነው፡፡ ተዉ! ተዉ! ተዉ! እብሪትና “ምን እንዳያመጡ ነው!” አይነት መታበይ መጨረሻ ላይ የሚያመጣውን ነገር ከምታዩት በላይ ምን ሊመጣ ነው! ተዉ! ተዉ! ተዉ!
መንገድ ሊዘጋ ነው ምናምን ብሎ ጨውን ከአስራ አራትና አስራ አምስት ብር እስከ ሀያ ምናምንና ሲብስም እስከ አርባ ብር ማድረስ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው!! ተዉ! ተዉ! ተዉ! ስግብግብነት ልክ አጣ!
"እመኛለሁ ዘወትር በየዕለቱ
ላሳካ ኑሮን ከብላቱ"
ተብሎ የለ፡፡ ምኑን አሳካነው! ቀበሌ ሉካንዳ እንኳን ሁለት መቶ ምናምን ብር ሲሸጥልን የከረመውን “ምንም አይልም” የሚባለውን  ሥጋ ሦስት መቶ ሲገባ ምኑን ተሳካልን... ተሰካብን እንጂ! (ግዴላችሁም ግጥም ቢጤ ብሞከር ባያጨበጭቡልኝም ላያጨበጭቡብኝ ይችላሉ! አሀ... ሞባይላቸው ላይ አፍጥጠው ሱፐርማን ምናምን ጌም እየተጫወቱ ትዝ አልላቸውማ!)
ሀሳብ አለን... ሀገር አቀፍ የዱቤ ፖለሲ ይውጣልን! አሀ…መከራችንን መብላት አለብን እንዴ! ለጎመንም ሆነ ለጎድን ብድር መጠየቅና ማግኘት ልዩ ጥቅም ሳይሆን ሰብአዊ መብት ነው፡፡ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም አካል የሥራ ፈቃዱ ተነጥቆ ሀላፊዎቹ ለህዝብም፣ ለሀገርም የሚጠቅሙ ስለማይሆኑ ደንበር ድረስ ተሸኝተው፣ ከዛም በኋላ የራሳቸው ጉዳይ!” የሚለው አንቀጽ መግቢያውም፣ ማጠቃለያውም ላይ ይካተትልን፡፡ ደግሞም... “ብድሩ እስከ አምስት ወር ድረስ ካልተከፈለ አንዳልተሰጠ ይቆጠራል፣” ቢባል ስር ነቀል ፖሊሲ ይላችኋል የዚህ አይነቱን ነው፡፡
እናማ...‘ታላቅ ቅናሾች’ ፕራንካችሁን ተዉንማ!
ስሙኝማ... ይህ ሁሉ ተብሎ ግን ዘንድሮ ስለ በዓል ስናወራ ዋነኛው አጀንዳችን መሆን ያለበት እኛ በሰላም ወጥተን እንድንገባ፣ ሀገር ሉአላዊነቷ ተጠብቆ እንድትቀጥል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የህይወት መስዋአትነት ለመክፈል የተሰለፉትንና እየተፋለሙ ያሉትን የሀገር መከላሳች፣ የፈዴራልና የአካባቢ ፖሊስ ሀይሎች፣ የክልል ልዩ ሀይሎች፣ ሚሊሽያዎች፣ አርሶ አደሮችና ከመላዋ ሀገሪቱ ተውጣጥተው የዘመቱ ወጣቶችን በማሰብና በምንችለው ሁሉ በመደገፍ መሆን ይኖርበታል... ሁሉም በሀገር ነውና፡፡
አባት የሞተ እንደሁ በሀገር ይለቀሳል፣
እናት የሞተች አንደሁ በሀገር ይለቀሳል
ሀገርስ ከሞተች ወዴት ይደረሳል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 666 times