Saturday, 28 August 2021 13:17

ከፍርስራሽ ውስጥ ህንፃ እናቁም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ መሰንቆውን ይዞ ያንጎራጉራል። ለአንድ ባለፀጋ ሰው ነው የሚገጥመው።
“የኔማ ጌትዬ  ዘረ መኳንንት
ስጋ አልበላም አለ ትከሻው ከብዶት…”
ጌትዬውም፤
“ይበል ይበል…
ንሳ አንተ አሽከር፣አንድ ብርሌ ስጠው…” አሉ።
አዝማሪው ብርሌውን ተቀበለ።  ጎርጎጭ፣ ጎርጎጭ አደረገና፤ እንደገና አቀነቀነ፡-
“አንተ ሰው ጥርስህን አኑረው በዋንጫ የሷው ይበቃል ለእህል ማላመጫ…” አለና ገጠመ።
“ይበል ይበል…
ንሳ አንድ ብርሌ ጨምርለት” አሉ ጌትዬው።
አዝማሪው ተቀበለና ግጥም አድርጎ ጠጣና፣ ማሲንቆውን በዕጣን አዋዛ። ከዚያም ቀጠለና፤
“አንተ ሰው ጥርስህን፣ አንቆርቁረው በቅል፤
እንዘራዋለን ምናልባት ቢበቅል” አለ ሞቅ አድርጎ።
ጌትዬውም በድምፁ ማማርና በዜማው አወራርድ እጅግ አድርገው ተደሰቱና፤
“ንሣ አንተ አሽከር አንድ እጀ-ጠባብ አምጣና ስጥልኝ…” አሉና ከጠጁ እሳቸውም ደጋገሙ።
እዝማሪው ፊቱን ወደ እመቤትዬው አዙሮ፤
“እሜቴ ጥሩወርቅ ውጪ ተከስሻል
እንዲህ ያለ መኳንንት ማን ውደጅ ብሎሻል”
*   *   *
“ጫማውን አውልቆ በእግሩ አይመጣም ወይ
አንቺ ልከሽበት ሊቀር ነበር ወይ?!”
ቀጥሎ
ወደ ጌትዬው ዞረና፡-
የአገር ሁሉ አዋይ
እሜቴ ሲጠሩ ዝም ይላሉ ወይ?
መውዜርዎ ሳያንስ
ጎራዴዎ ሳያንስ
ሽጉጥዎ ሳያንስ
ሻቦላዎ ሳያንስ
ምነው መርጠው ዋሉ፣ የዝምታ ድግስ?” አላቸው። ይሄኔ ጌትዬው እልህም የንሸጣ ስሜትም ተሰማቸውና፤
“ከንግግር በፊት የአርምሞ ዝምታ
ከጦርነት በፊት የዝግጅት ፋታ
ዛሬም የልባም ልጅ ያንድ አፍታ ፀጥታ።
ነገ ግን ይዋጋል መፋለሙ አይቀርም
ታሎ ያሸንፋል ጥርጥር የለኝም” ብለው አዝማሪውን ረቱት ይባላል።
ከልቡና አንቅቶ ቅፅበታዊ ምላሽ ለመስጠት መቻል ታላቅ ተሰጥኦ ነው። ይህን ዓይነቱ ክህሎት ከባድና የረዥም ጊዜ የአዕምሮ ዝግጁነት ይጠይቃል። ይህ ማለት ግን ለሁሉም በጥድፊያ ምላሽ ካልሰጠሁ ብሎ መሯሯጥ አይደለም። “የእነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰምበሌጥ” የሚል ድንቅ ተረትና ምሳሌ አለመዘንጋት ነው! ብዙዎች ሁሉን በፍጥነት እንሰራለን ብለው፣ “ሲሮጡ የታጠቁት፣ ሲሮጡ ሲፈታባቸው” ተስተውለዋል።”
“Rome was not built a day “ የሚለውን አባባ በጥልቀት ማጤን ነው። “ሮሜም በአንድ ቀን አልተገነባችም” እንደ ማለት ነው። የሮማ አወዳደቅን ላወቀ የተባለ ጭንቅላት ያለው ሰው ከፍርስራሽም ውስጥ ቢሆን ህንፃ ሊያም እንደሚችል ያያል። ይህ ለሀገራችን ቁልፍና አመርቂ ልህቅና የሚያበረክት ዕውቀት ነውና የሁላችንን ማህበረ-ሱታፌ (Social Participation) የሚፈልግ ነውና ልብ ሊባል ይገባዋል።


Read 12768 times