Sunday, 29 August 2021 00:00

የልጆቻችን በራስ የመተማመን ምስጢር

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ (birhanubasefa@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

    “ለልጆች የምንሰጠው ትልቁ ስጦታ ጊዜ ነው”
                                 
            በቤተሰብ አማካሪዎች ዘንድ አንድ የተለመደ አባባል አለ፡፡ “ልጅ ፊት ያለን ድንጋይ አታንሳ፤ ድንጋይ እንዳለ ንገረው" ይላሉ፡፡ የቤተሰብ ድርሻ ልጁን በመረጃ ማስታጠቅ ነው፡፡
ልጆቻችንን የምናስታጥቅበት ፣ በራስ የመተማመን አቅማቸውን የምናጎለብትበት አንዱ መንገድ ደግሞ ከእነርሱ ጋር በምናሳልፈው ጊዜ ይወሰናል፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ ዓላማ በወላጅ (በአሳዳጊ) እና በልጅ መካከል በጋራ የሚያሳልፉት ጥቂት ደቂቃዎች ተአምራዊ ለውጦች ሊያመጣ እንደሚችል ማሳየት ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት የጊዜ ብዛት (Quantity time) ሳይሆን ጥራት ያለው ጊዜ (Quality time) በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ ተአምራዊ በጎ ተፅኖ ያሳድራል። ለዚህ ፅሁፍ (Quality time) የሚለውን ፍሬያማ ጊዜ ብዬ መግለፅን መርጫለሁ፡፡
እንደ ጥናቶቹ ከሆነ፣ ፍሬያማ ጊዜ (Quality time) የሚባለው ከልጆች ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ከጊዜ እርዝመት  ይልቅ ተከታታይነት ያለው በየእለቱ የሚከናወን ጣፋጭ  የጋራ ጊዜ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው፡፡  በልጅና በወላጅ  መካከል ያለው ፍሬያማ ጊዜ በየእለቱ ለደቂቃዎች የሚቆይ አጭር ጊዜ ነው፡፡
አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ አሜሪካዊያን ወላጆች  ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ቀን ውስጥ ለ37 ደቂቃዎች  ፍሬያማ የአብሮነት ጊዜን ያሳልፋሉ፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው በየእለቱ የሚፈልጉት ይህ ትንሽ ደቂቃ በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ በርካታ አዎንታዊ አበርክቶ አለው፡፡
ወላጅ (አሳዳጊ) ኑሮን ለማሸነፍ በተለያዩ የእለትተእለት እንቅስቃሴ ሊጠመድ ይችላል፡፡ በዚህ የህይወት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገባው ሰርቶ ልጁን ለማሳደግ መሆኑ እሙን ቢሆንም ከልጅ ጋር ፍሬያማ ጊዜ የማሳለፍ ዋጋን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ምናልባትም “ሁሌ አብረን አንድ ቤት አይደለም እንዴ የምናሳልፈው” ብለን ቀለል ልናደርገው እንችላለን፡፡ ነገር ግን የወላጅና የልጅ ፍሬያማ ጊዜ የሚባለው፣ ወላጅ ከማንኛውም ስራ ራሱን አግልሎ ከኤሌክትሮኒክስ መገልገያ በመራቅ በሙሉ ሃይሉና በሙሉ ስሜት ትኩረት በመስጠት ከልጅ ጋር ማሳለፍ ሲቻል ነው፡፡
ይህ ጊዜ በአጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ታስቦበት ከልጄ ጋር ማሳለፍ እፈልጋለሁ ተብሎ የታቀደበት ሊሆን ይገባል፡፡ ለልጆች የምንሰጠው ትልቁ ስጦታ ጊዜን ነው፡፡ “ከልጅ ጋር አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት  ” አመለካከትን መስበር ይጠበቅብናል፡፡
የፍሬያማ ጊዜ ዋነኛ ማዕከል ልጆች ናቸው፡፡ በልጆች ምርጫና ፍላጎት የሚከናወን የጋራ ጨወታ ወሳኝ ነው፡፡ ለአብነትም፡- ድብብቆሽ፣ ጌም፣ መፅሐፍ ማንበብ፣ እንቆቅልሽ፣ ተረት ተረት፣ የልጅ እድሜን ያገናዘበ የቤት ውስጥ የጋራ ስራ ማከናወን፣ አየር ለመቀበል  ወደ ውጭ በጋራ መውጣት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡
ለመሆኑ ከልጅ ጋር ጊዜን ማሳለፍ ለምን ያስፈልጋል? ጥናቶች እንዳረጋገጡት፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ፍሬያማ ጊዜን የሚያሳልፉ ልጆች ከሌሎች ልጆች በተሻለ በራስ የመተማመን አቅም አላቸው ፡፡ ወላጅ ፍቅሩን በቃላት “እወድሃለሁ/ሻለሁ” ሊል ይችላል፡፡
ለልጆች ፍሬያማ ጊዜ ለየት ያለ ትርጉም አለው፡፡ ተፈላጊነታቸውን፣ በወላጆች ዘንድ ያላቸውን ዋጋና፣ መወደዳቸውን ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ሌላው ጥናቶች ያረጋገጡት በፍሬያማ ጊዜ  ተጠቃሚዎች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡ ወላጆች ውጥረት ከተሞላበት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ወጥተው በግንኙነቱ መንፈሳቸው ይታደሳል።
ከዚህም በተጨማሪ  የስሜት ትስስራቸው ይጠናከራል፡፡ በወላጅና በልጅ መካከል ያለው መተሳሰብ ይጎለብታል፡፡ የልጆች የስሜት ብስለት ክህሎትም እንዲዳብር ይረዳል ፡፡
በዚህ ወቅት ታዲያ አንዳንዴ በጫወታ መካከል ይህ/ች ልጅ ቀበጠ/ች እንላለን። ይሁን እና ልጆች በህይወታቸው የሚፈልጉትንና የሚያረካቸውን የፍቅር ከባቢ ሲያገኙ ስሜታቸውን የሚገልፁበት መንገድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቅብጠት ሳይሆን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እያጣጣሙ ነው፡፡ እኛ ቅብጠት የምንለው ልጆች ስሜታቸውን  የገለፁበት መንገድን ነው፡፡
ፍሬያማ ጊዜ ከልጆች ጋር ማሳለፍ የልጆችን የአእምሮ ጤናም ያበለፅጋል።  የድባቴ፣ የጭንቀት ስሜትን በመግፈፍ መንፈሰ ጠንካራ ስብእና ያጎናፅፋቸዋል። በተለይም የወላጅና የልጅ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታ ደግሞ የልጆችን የመሰማት እድል ያሰፋል፡፡ ልጆች ሃሳባቸው፣ ድርጊታቸው ተቀባይነት እንዳለው እንዲረዱ ያደርጋቸዋል፡፡ “ዋጋ አለኝ”፣ “ተፈላጊ ልጅ ነኝ”፣ “የሚሰማኝ አካል አለ” የሚለውን ትልቁን ጥያቄያቸውን ይፈታላቸዋል ፡፡
በአሪዞና ዩኒቨርስቲ በተደረገ አንድ ጥናት መሰረት፣ ከቤተሰብ ጋር የጋራ ጊዜ የሌላቸው ልጆች ለአልኮልና ለሱስ የመጋለጣቸው እድል እጥፍ ነው፡፡
ፍሬያማ ጊዜ ደስተኛ ቤተሰብን ይፈጥራል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ጊዜያቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያሳልፉ ልጆች ለጭንቀትና ለብቸኝነት የመጋለጥ  እድላቸው  ጠባብ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ እነዚህ ልጆች ችግር እንኳን ቢገጥማቸው ከቤተሰባቸው ጋር በገነቡት መልካም ግንኙነት ችግሩን ተቋቁመው የመውጣት (Resilience) አቅም አላቸው፡፡
በመሆኑም ወላጆች (አሳዳጊዎች) ከልጆቻቸው ጋር ፍሬያማ ጊዜን  የማዳበር ልምዳቸውን እንዲያበረታቱ ይመከራል፡፡ ሰላማችሁ ይብዛ!


Read 3461 times