Saturday, 28 August 2021 12:59

የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ስለ ኢትዮጵያ ምን አሉ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    “የውጭ ጣልቃ ገብነት ችግሩን ያባብሰዋል

              የተባበሩት  መንግሥታት  ድርጅት  የፀጥታው  ምክር  ቤት  በሰሜን  ኢትዮጵያ  የተከሰተውን  ግጭት  በተመለከተ  ሐሙስ ነሐሴ  20 ቀን 2013  ዓ.ም ውይይት አድርጓል።
ምክር ቤቱ የትግራይ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለበርካታ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ በዝግና በይፋ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። የአሁኑ ስብሰባም በከፊል ክፍት የነበረ ሲሆን ከመጀመሪያው ዙር ውይይት በኋላ ውይይቱ በዝግ ተደርጓል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ቀውስ አስተያየት ሰጥተዋል። ማን ምን አለ?
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ከትግራይ ተነስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ቆሞ፣ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር መምጣት አለባቸው ሲሉ ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።
ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ በተደጋጋሚ የጠየቁት ዋና ጸሐፊው፤ በትላንቱ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤም ይህንኑ አቋም አንጸባርቀዋል።
“ሁሉም ወገን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁሞ ወደ ድርድር መምጣት አለበት። ስለ ኢትዮጵያ ሲሉ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ ማድረግ አለባቸው። ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል። የውጭ ኃይሎችም ከአገሪቱ መውጣት አለባቸው” ብለዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊትም ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ የጠየቁት ጉቴሬዝ፤ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደተነጋገሩና ራሱን የትግራይ ክልል ሕጋዊ አስተዳዳሪ እያለ የሚጠራው አካል የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ደብዳቤ እንደላኩላቸው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከአፍሪካ ሕብረትና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ድጋፍ እንደሚሰጥ ጨምረው ገልጸዋል።
“ወታደራዊ ግጭት መፍትሔ እንደማያመጣ ሁሉም ወገኖች መገንዘብ አለባቸው” ሲሉም ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሸን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር በመጣመር እያካሄደ ያለው ምርመራ እየተጠናቀቀ እንደሆነ ጉቴሬዝ ጠቁመዋል።
ጉቴሬዝ ያነሷቸው ሦስት ቁልፍ ነጥቦች ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ተኩስ እንዲያቆሙ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ መንገድ አመቻችተው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች መልሰው እንዲከፈቱና በኢትዮጵያ የሚመራ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር ነው።
“የኢትዮጵያ አንድነትና የቀጠናው ሰላም አደጋ ውስጥ ወድቀዋል” ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከመስፋፋቱ ባሻገር ሌሎች ቀጠናዊ ኃይሎች እንደገቡበትም አክለዋል።
“ነገሮችን የሚያቀጣጥል ትርክትና ብሔርን ተመርኩዞ ሰዎችን ኢላማ ማድረግ ተባብሷል። ሴቶችና ሕፃናትም ወሲባዊ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። ይህን እጅግ በጣም አወግዛለሁ” ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ከሰብአዊ ቀውሱ ባሻገር የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እየተሽመደመደ መምጣቱንም ተናግረዋል። የአገሪቱ እዳ እየጨመረ፣ ብድር የማግኘት እድል እየቀነሰ፣ የዋጋ ንረት እየተባባሰ፣ መሠረታዊ ምግብ አቅርበት እያለቀ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁም ህወሓት እንዲቀበል ጫና መረደግ አለበት” ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮ በገንቢ መንገድ ብቻ አገሪቱን ማገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል።
“የእኛ ግብ ሰላም ነው። ህወሓት ግን በሰላምና በኢትዮጵያ መካከል ቆሟል። ህወሓት ተጎጂ ሳይሆን አጥቂ ነው” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲወርድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህወሓት ላይ ጫና እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ሰብአዊ እርዳታ በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ያለውን ፍተሻ ለመቀነስና ፍተሻውን በዘመናዊ መሣሪያ ለማድረግ ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሰብአዊ በረራ እንደተፈቀደም አክለዋል።
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የአሜሪካው ተወካይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስተጓጎል ከተቹ በኋላ ነው።
እንደ መብራትና ስልክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን መተመለከተ “አገልግሎቱ የሚጀመረው ሰላምና ሕግ ሲሲፍን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስና ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ለመስጠት ቢሆንም፤ ህወሓት ጦርነቱን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች አስፋፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ህወሓት የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ቡድኑ በአገሪቱ አለመረጋጋት እንደፈጠረና መንግሥትም ሰላም ለማስፈን ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ አስረድተዋል።
ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን ክስ በተመለከተ “ብሔርን መሠረት ያደረገ አድልዎ የለም። መርህ አለን። ለዓመታት ማኅበረሰባዊ መስተጋብራችን የቀጠለው ልዩነትን መሠረት አድርጎ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱን ውይይት አስመልክተውም “ጉዳዩን ማግነን እና ፖለቲካዊ ቅርጽ መስጠት የኢትዮጵያን መንግሥት ውሳኔ እንደማይለውጥ” አስታውቀዋል።
አሜሪካ
ለተኩስ አቁምና ለብሔራዊ ውይይት ጥሪ ቢደረግም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት እያንቀሳቀሰ መሆኑንና ህወሓትም ጥቃቱን ወደ አፋርና አማራ ክልል በማስፋት በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህም በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁት የአሜሪካው ተወካይ ናቸው።
የኤርትራ ኃይሎች ወደ ትግራይ ተመልሰው ገብተዋል በማለት በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ወታደራዊ ትብብር ሰፊ ጦርነትን የመቀስቀስ ስጋት ይፈጥራል ብለዋል።
አሜሪካ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና የሚፈጸሙ ጥቃቶች በእጅጉ እንዳሳሰባት ያመለከቱት ተወካዩ፤ ሁሉም ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ፤ መንግሥትና ህወሓት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲፈቅዱ፣ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም እንዲደረግና የኤርትራ ኃይሎች ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሚሊዮኖች እርዳታ በሚፈልጉበትና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሆን ብለው የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ እንዳይገባ አደንቅፈዋል ሲሉ የአሜሪካው ተወካይ የከሰሱ ሲሆን ይህም በአስቸኳይ ተስተካክሎ እርዳታ እንዲቀርብ መደረግ አለበት ብለዋል።
የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተም በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ሪፖርቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አማራ ክልል ውስጥ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ በህወሓት ኃይሎች መገደሉን እንዲሁም የእርዳታ መጋዘን በህወሓት መዘረፉን ገልጸዋል።
ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በማባባስ በኩል ያላትን ሚና አሜሪካንን በእጅጉ እንደሚያሳስባት የተናገሩት ተወካዩ፤ ይህም ተኩስ አቁም ለማድረግና በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
የኤርትራ ሠራዊትን በሰብአዊ መብቶች ጥሰት የከሰሱት ተወካዩ በቅርቡ የጦሩ ኤታማዦር ሹም ላይ አሜሪካ የጣለችውን ዕቀባ በማስታወስ ተጨማሪ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የኤርትራ ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ እንደማያመጣ ተቀብለው፤ ተኩስ አቁም ለማድረግና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ በአስቸኳይ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ጠይቀዋል።
ሕንድ
ጦርነቱ በህወሓት አማካይነት ወደ አማራና አፋር ክሎች እንደተዛመተና ይህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንዲሁም ልጆችን በተዋጊነት የማሰማራት ከባድ ችግር ማስከተሉን የሕንዱ ተወካይ ገልጸዋል።
በሰኔ ወር የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለማሻሻል ወሳኝ እርምጃ እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን በሌላኛው ወገን የተኩስ አቁሙ ተቀባይነት ሳያገኝ ጦርነቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋቱ የሚደርሰው ጉዳት መጨመሩን ጠቅሰዋል።
ስብሰባውን የመሩት የሕንድ ተወካይ ጨምረውም መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና ከሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን በመግለጽ፣ ባደረገው ጥረትም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑ በመረጃ መደገፉን ጠቅሰዋል። ይህም የእርዳታ አቅርቦት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላት እንደሚገባና በተለይ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት ችግሩን ለመፍታት ድጋፍ ማድርግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማምጣት በኢትዮጵያ በእራሷ የሚመራና በሕገ መንግሥቷ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን እንዳለበት በመግለጽ፤ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መተማመን፣ እርቅና ውይይት መኖር እንዳለበት አመልክተዋል።
በማጠቃለያቸውም አገራቸው ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛቷ መከበር ህንድ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ኬንያና ሌሎች
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሐሳብ ያቀረቡት የኬንያው ተወካይ ከእራሳቸው አገር በተጨማሪ የኒጀር፣ የሴንት ቪንሰንትና ግሪናዲስን እንዲሁም የቱኒዚያን ጭምር መሆኑን አመልክተው፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።
ተወካዩ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎች በተለይ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጉዳትን እንዲያስቆሙ፣ እርዳታ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲደርስ እንዲፈቅዱ፣ ተኩስ እንዲቆም፣ ለድርድር መንገድ ለመክፈት የአገሪቱ ምክር ቤት ህወሓትን ሽብርተኛ ያለበትን ውሳኔ እንዲያነሳና ሁሉም ወገኖች ለድርድር ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
ጨምረውም፤ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ፣ ሀብታም አገራት ለሰብአዊ እርዳታ በቂ ገንዘብ እንዲያቀርቡ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ፣ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ድቀትን ሊያስከትል ከሚችል ማንኛውንም የተናጠል ማዕቀብ ከመጣል እንዲቆጠቡ እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ሰላም በማምጣት በኩል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ቻይና
የቻይናው ተወካይ በኢትዮጵያ መረጋጋት ማስፈንና የተለያዩ ብሔር ተወላጆች በሰላም እንዲኖሩ ማስቻል ከአገሪቱ ባለፈ ለቀጠናውም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
“ሁሉም ወገኖች ችግሩን በፖለቲካዊ ውይይት ይፈቱታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ ቻይና ትደግፋለች” ብለዋል።
ሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰ እንደመጣና በአማራና በአፋር ክልሎች እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ተናግረው፤ ሁሉም አካሎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በትግራይና በሌሎችም ቦታዎች ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩና የተባበሩት መንግሥታት መርህን እንዲከተሉም የቻይናው ተወካይ ጠይቀዋል።
ቻይና እያደረገች እንዳለችው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ ለዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ እርቅ እንዲቆም ጠይቀዋል።
“በሰብአዊ እርዳታ ስም የውጪ ጣልቃ ገብነት መኖር የለበትም። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ይፈታ” ሲሉም ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረሩና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሱ እንደሆኑ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ሩሲያ
የሩስያዋ ተወካይ በበኩላቸው፤ ወደ ትግራይ እርዳታ ለመላክ በሰመራ የተቋቋመው መተላለፊያ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
አይይዘውም፤ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብአዊ ሁኔታ ከፖለቲካ ጉዳይ መነጠል ያስፈልጋል። በትግራይ በሚደረገው ሰብአዊ እርዳታ መድልዎ መኖርም የለበትም። አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ለምክር ቤቱ የሩሲያን አቋም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚያስፈልግና ይህም በኢትዮጵያውያን መሪነት መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል።
“የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የፖለቲካ ነጻነት በጠበቀ መልኩ ነው መሰጠት ያለበት” ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አገሪቱን በአንድነት ወደ ሰላም የመውሰድ አቅም እንዳለው አክለዋል።
እንደ ቻይናው ተወካይ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን አውግዘው፤ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ምክረ ሐሳብ መካተት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
(ቢቢሲ አማርኛው)


Read 4708 times