Saturday, 28 August 2021 12:54

የኑሮ ውድነቱ - ማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

  ባለፉት 4 ዓመታት የሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ትልቁ ፈተና በሆነበት ኢትዮጵያ ከዕለት ተለት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመጣው የሸቀጦች ዋጋ ንረት ሳቢያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ፣ አገሪቷን ለከፋ ማህበራዊ ቀውስና ለውስብስብ ችግሮች ሊዳርጋት  እንደሚችል ተገለፀ።
መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እየወሰደ ያለው እርምጃ ለችግሩ ተገቢውን መፍትሄ  እንደማያመጣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዓመት ዓመት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ሳቢያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት፣ ዜጎችን ብርቱ ለሆነ ችግርና ፈተና እየዳረጋቸው መሆኑን የሚናገሩት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶ/ር ፋሲል ተስፋዬ፤ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊፈልግና ዜጎች ለከፍተኛ ማህበራዊ ቀውሶች እንዳይዳረጉ ሊከላከል ይገባል ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱ የኢትዮጵያውያንን ደጃፍ ማንኳኳት ከጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን በአገሪቱ ታይቶ በማታወቅ ሁኔታ ከግብርና ምርቶች ጀምሮ በኢንዱስትሪ ተመርተው እስከሚወጡ ዕቃዎቻቸው ድረስ ሁሉም በከፍተኛ መጠን ጭማሪ አሳይተዋል።
ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በዚህ ዓመት በሸቀጦች ዋጋ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ እስከ ዛሬ ድረስ በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ነው።
የዋጋ ግሽበት መጠኑ በ18.6 በመቶና በ22.9 በመቶ መካከል ሲዋዥቅ መቆየቱን ያመለከተው የኤጀንሲው መረጃ፤ የምግብ ዋጋ ግሽበቱ ደግሞ ከ20 በመቶ ሳይወርድ መቆየቱን ይጠቁማል። ባለፈው ዓመት ዝቅተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በጥር ወር 2012 ሲሆን መጠኑም 20 በመቶ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
በዛው ዓመት መጋቢት ወር የዋጋ ግሽበቱ ወደ26.7 በመቶ በማደግ በዓመቱ የምግብ ዋጋ ግሽበት ጣራ የነካበት ወር ሆኖ አልፏል። በያዝነው ዓመት መገባደጃ ላይ ይኸው የምግብ ዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ በላይ ደርሷል።
ከ2009 እስከ 2013 ኣ.ም ድረስ ባሉት ጊዜት የብር የመግዛት አቅም በ54 በመቶ የወረደ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታትም የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ በመቶ እጅ መውደቁን ባለሙያው ይገልፃሉ።
ባለፉት 4 ዓመታት በአገሪቱ በተከሰቱት ጦርነት አለመረጋጋት፣ የኮረና ወረርሽኝና መሰል ክስተቶች በአገሪቱ ምጣኔ ሀብትና በህዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከባድ ጫና ማሳደራቸውን የሚገልፁት ዶ/ር ፋሲል፤ ከዕለት ዕለት እየጨመረ የሚገኘው የሸቀጦች ዋጋ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን አክለዋል።
የዋጋ ጭማሪው በተለይም አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ሸማች በሆነባቸው የከተሞች አካባቢ የዜጎችን ዕለታዊ ኑሮ የከፋ አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል።
ለዋጋ ግሽበቱ መጨመርና ለኑሮ ውድነቱ መናር የምርት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የስራ አጥ ዜጎች መበራከት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመርና የማምረቻ ግብዓቶች ዋጋ  ማሻቀብ  ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
“አቅርቦት ሲቀንስ ዋጋ ይጨምራል፤ በተፈጠረው የአቅርቦት እጥረት ሳቢያ- ገበያ ውስጥ ያለውን ጥቂት አቅርቦት መቀራመት በሚፈልጉትና ንረቱን በማባባስ የግል ጥቅማቸውን ለማካበት በቆሙ አንዳንድ ነጋዴዎች ምክንያትም የዋጋ ንረቱ በከፍተኛ መጠን ሊጨምር ይችላል” ብለዋል።
አሁን በአገራችን ውስጥ እየታየ ላለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መነሻ ምክንያ የነዳጅ ዋጋና የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪው እንደሆነ የሚናገሩ ወኖች እንዳሉ የጠቆሙት የኢኮኖሚ ባለሙያው ይህ ግን ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለውና አሳማኝ  ያልሆነ ጉዳይ ነው።
“ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ የሚታዩትን የዋጋ ጭማሪዎች ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪውና ከታሪፍ ማስተካከያው ጋር ስናነፃጽረው ፈፅሞ የማይገናኝና የብዙ እጥፍ ልዩነት የሚታይባቸው ግልፅ ብዝበዛ የሚስተዋልባቸው የተጋነኑ ጭማሪዎች ናቸው። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ምክንያት በማድረግ በህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ይህንን አይን ያወጣ ዝርፊያ ግን ሃይ የሚል የሚከለልና ስርዓት የሚያስይዝ አካል ባለመኖሩ፣ የዋጋ ንረቱ ህዝቡን ለከፍተኛ ምሬት ዳርጎታል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ አገሪቷን ለተወሳሰቡ ችግሮች ይዳርጋታል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እያረጋጉ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።
ከነዚህ ጥረቶች መካከልም የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ወገኖች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰድ፣ እንደ ስኳርና ዘይት ያሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን በተለያዩ  መንገዶች ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ ማድረግ ጥቂቶቹ ናቸው።
ባሳለፍነው ሳምንትም 53.9 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ህብረተሰቡ ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
ይህ የከተማው አስተዳደርና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ ወቅታዊ እርምጃ የዋጋ ንረቱንና ኑሮ ውድነቱን በማሻሻሉ ረገድ እምብዛምጠቀሜታ ያለው ጉዳይ አለመሆኑን ደግሞ የህግ ባለሙያው አቶ ዮናስ ዘውዱ ይናገራሉ። እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ ማህበረሰቡ በገበያ ውስጥ እንደ ልቡ ማግኘት በማይችላቸው ሸቀጦች ላይ ከነጋዴው ጋር ዋጋ ተደራድሮና ከዚህ በላይ ልትሸጥ አትችልም ብሎ ሞግቶ መግዛትና ጥቅሙን ማስጠበቅ የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ እየታወቀ የንግዱን ማህበረሰብ ያለማሰሪያ ገመድ፣ በስመ ነጻ ገበያ መልቀቅና ሸማቹን አደጋ ላይ መጣል አሳዛኝ ጉዳይ ነው። “በ2006 ዓ.ም የወጣው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ፣ ለሸማቹ ማህበረሰብ ጤናማ የሆነ የግብይት  ስርዓት መዘርጋትና ከአወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ ዕቃ ወይንም አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል አለበት ይላል። ይህ ግን አንድም ጊዜ  ሲደረግና ሲፈጸም ነጋዴው ያለምንም ምክንያት በየጊዜው የሚያደርገውን የዋጋ ጭማሪ በመቆጣጠር ሸማቹ ለከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ ዕቃ ወይንም አገልግሎት እንዲገኝ ሲደረግ አይታይም” ብለዋል ባለሙያው በማብራሪያቸው።
ህብረተሰቡ በተለያየ ወቅት ቅርፅና ምክንያቸውን እየለዋወጡ በየሚከሰቱ የኑሮ ውድነት ሰቆቃዎች ገፈት  ቀማሽ ለመሆን ተገድዷል  የሚሉት አቶ ዮናስ፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ተከትሎ ዕለታዊ ገቢው አብሮ እየተቀየረ የማይመጣ በርካታ የማህበረሰብ ክፍል በሚኖርበት አገር ውስጥ የሸማቹን መብትና የገበያውን ስርዓት የሚቆጣጠረው አካል ከፍተኛ ስራ ይጠበቅበታል ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱን ጨምሮ ለሌሎች በርካታ የአገሪቱ ችግሮች መነሻ የሆነው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊፈጠር ይገባል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ፋሲል፤ የአገሪቱ ሰላም የሚረጋገጥበት መንገድ አፋጣኝ ዕውን መሆን ያለበት ጉዳይ ነው ባይ ናቸው። ከቀን ወደቀን እየቀነሰ የመጣው የብር የመግዛት አቅም በአስቸኳይ መቆምና በውጭ ምንዛሬ ላይ ማስተካከያ በማድረግ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ማድረግ መሰረታዊ መፍትሄ ነው የሚሉት ባለሙያው ለኑሮ ውድነቱ መሻሻል ጊዜያዊ መፍትሄው በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ያለአግባብ  የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን የሚቆጣጠረው አካል በትኩረት መከታተልና ህገ-ወጥነትን መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።



Read 12093 times