Saturday, 28 August 2021 12:53

ወደ ትግራይ ሊወሰድ የተከማቸ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ሊመረመር ነው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

    ከበላይነህ ክንዴ አዲሱ የዘይት ማረቻ ፋብሪካ የተገዛና በጉና ንግድ ድርጅት መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ላለመበላሸቱ የማረጋገጫ ፍተሸ እንዲደረግለት ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ።
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምግብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ከትናት በስቲያ በዋለው ችሎት እንደገለጸው፤ በጉና ንግድ ድርጅት መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘው 1.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት እንደሚበላሽና እንደማይበላሽ  በኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒት ባለስልጣን በኩል ምርመራ እንዲደረግበት አዟል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ ከበላይነህ ክንዴ የዘይት ፋብሪካ ተገዝቶ ወደ ትግራይ ሊላክ የነበረ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በጉና ንግድ ድርጅት መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱን ጠቅሶ፤ መጋዘኑን እንዳሸገው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። “ዘይቱ በቆይታ ብዛት እንዳይበላሽ በሸማቾች በኩል እንዲሸጥና ገንዘቡ በዝግ ሂሳብ እንዲቀመጥ” ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል ፖሊስ፡፡
የጉና ንግድ ስራዎች ጠበቃ በበኩላቸው፤ በመጋዘኑ ውስጥ ተከማችቶ የተገኘው ዘይት ህጋዊ መሆኑንና በንግድ ሚኒስቱር ቁጥጥርና የዋጋ ተመን ወጥቶለት ከበላይነህ ክንዴ ዘይት ፋብሪካ በህጋዊ መንገድ የተገዛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጉና የንድ ድርጅት በኩል በትግራይ ክልል እንዲከፋፍል ፍቃድ የተሰጠው ነው ብለዋል።
የትግራይ ክልል መንገድ በመዘጋቱና ጊዜያዊ አስተዳደሩም ቦታውን በመልቀቁ ምክንያት ዘይቱ በመጋዘኑ ውስጥ ሊቆይ መቻሉንም አስረድተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፤ የጉና ንግድ ድርጅት ተወካይ በተገኙበት መጋዘኑ እንዲከፈትና ዘይቱ መበላሸት አለመበላሸቱ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባስልጣን በኩል እንዲጣራ ውሳኔ አሳልፎ ጉዳዩን ለነሐሴ 25 ቀን 2013 ቀን ቀጥሮታል።



Read 12580 times