Print this page
Saturday, 28 August 2021 12:48

በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከጥር 2013 ወዲህ ባለው የ6 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በጦርነት እና በግጭት ምክንያት አንድ ሚሊዮን ሶስት ሺህ ያህል ዜጎች  ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አመለክቷል፡፡
በትግራይ ያለው ጦርነት ጨምሮ በአማራ፣አፋር ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች በእርስ በእርስ ጎሳ ተኮር ግጭቶች እና በታጣቂ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች የተነሳ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከመፈናቀላቸው ባለፈ ግጭቶች ባለመቆማቸው ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ አውቆ ድጋፍ በማድረግም አዳጋች መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በኦሮሚያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው “    ሸኔ” እና የመንግስት ሃይሎች መካከል ባለው ግጭት እንዲሁም የታጠቁ ሃይሎች በሚፈፀሙት ዘር የለየ ጥቃት በቦረና እና  ጉጂ ዞን ብቻ ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው መረጃ እንደሚገኝ ሪፖርቱ በተጠናከረባቸው አራቱም የወለጋ ዞኖች ማለትም ቄለም ወለጋ፣ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋና ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች በመቀጠላቸውና ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ግድያዎች እና መፈናቀሎች በመኖራቸው የተጣራ መረጃ ማቅረብ እንደተቸገሩ ተቋሙ አመልክቷል፡፡
በእነዚህ ግጭቱ በቀጠለባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው ያሉበትን ሁኔታ ማወቅም ሆነ እርዳታ ማቅረብ አለመቻሉን በማመልከትም ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስታወውቀዋል፡፡
ከፍተኛ ግጭትና መፈናቀል  ካስተናገዱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ማንነትን መሰረት ባደረገው ጥቃት 5 መቶ ሺህ ያህል ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል፡፡
በግንቦት 2013 በተከሰተው የሰሜን ሸዋ እና በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ግጭትም 2 መቶ ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውንና አሁንም እርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኞች በተፈጠረው ግጭት ደግሞ በአፋር በኩል 39 ሺህ፣በሶማሌ ክልል በኩል 67 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በአማራ ክልለ በቅማንት ወረዳ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት 17 ሺህ ሰዎች ሲፈናቀሉ በደቡብ ክልለ 70 ሺህ ያህል በኮንሶ 50 ሺህ ያህል በቤንች ሸኮ አካባቢ ተፈናቅለዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡
በትግራይ ክልል ቀደም ሲል 60 ሺህ ያህል ሰዎች ሀገራቸውን ጥለው ወደ ሱዳን መሰደዳቸው የተገለፀ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ መመለሳቸው ተመልክተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ይሄን ሪፖርት ሲያወጣ በቅርቡ በአፋርና በአማራ ክልል በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወኃት የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች አለማካተቱ ተመልክቷል፡፡
መንግስት በበኩሉ በሁለቱ ክልሎች ላይ በተፈፀመው ጥቃት በአጠቃላይ ከ7 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ስለ መፈናቀላቸው ይፋ  አድርጓል፡፡



Read 11049 times