Friday, 27 August 2021 00:00

ቱርክ፤ ኢትዮጵያና ሱዳንን ለማሸማገል ትፈልጋለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶኻን በድንበር ይገባኛል ውዝግብ የከፋ መቃቃር ውስጥ የገቡትን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለማሸማገል ሐሳብ አቀረቡ። ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን ለትግራይ ውጊያ በለዘብተኛ አካሄድ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኤርዶኻን ኢትዮጵያ እና ሱዳንን የማሸማገል ሐሳብ ያቀረቡት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 12 ቀን 2013 በአንካራ በሰጡት መግለጫ ነው።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ ተነስተዋል። “ኢትዮጵያ በስሱ ሒደት ውስጥ እያለፈች ነው” ያሉት ኤርዶኻን፤ በአፍሪካ አላት ያሉትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና ጠቀሜታ ጠቅሰው ለሀገሪቱ ሰላም፣ ጸጥታ እና አንድነት ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
“የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት ከመጠበቅ አኳያ ለወቅታዊው ችግር በለዘብተኛ አካሄድ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን” ያሉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት፤ ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረው ውጊያ ከተባባሰ ዳፋው በአካባቢው አገራት ሊዳረስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።  
ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚወዛገቡበትን የአል-ፋሽጋ አካባቢ ጉዳይን በጋዜጣዊ መግለጫው ያነሱት ኤርዶኻን፤ ሀገራቸው ሁለቱን ጎረቤታሞች ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት ጠቆም አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ “ውዝግቡ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ውይይት በመልካም ጉርብትና ላይ በመመስረት እንዲፈታ የልብ ፍላጎቴ መሆኑን ገልጪያለሁ። ቱርክ ጉዳዩ በሰላም እልባት እንዲያገኝ ሽምግልናን ጨምሮ ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ናት” ብለዋል።
ኤርዶኻን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ከመገናኘታቸው አንድ ሳምንት ገደማ በፊት፤ ወደ አንካራ ከተጓዙት የሱዳኑ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር። ከሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ ኤርዶኻን በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ “በጋራ ውይይት እና መግባባት” ሊፈታ ይገባል ብለው ነበር። ሀገራቸው በመጪዎቹ ጊዜያት ከካርቱም ጎን እንደምትቆም ማስታወቃቸውም ይታወሳል።
በጉብኝቱ፤ ቱርክ እና ኢትዮጵያ በውሃ ዘርፍ፣ በገንዘብ ዕገዛ እና ወታደራዊ የገንዘብ ትብብርን የተመለከቱ አራት ስምምነቶች መፈራረማቸው ተገልጿል። ኢትዮጵያ እና ቱርክ 125 አመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። በረጂብ ጣይብ ኤርዶኻን መንግስት ላይ ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ሽብርተኛ ብላ ከፈረጀችው የሃይማኖት መምህሩ ፌቱላህ ጉለን በምታደርገው ውጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ በኢትዮጵያ ተከፍተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ለቱርኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን መተላለፋቸውንም ፕሬዝዳንት ኤርዶኻን አረጋግጠዋል።
በአወዛጋቢው የፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ አማካኝነት በአዲስ አበባ ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አራት ትምህርት ቤቶች በቱርክ መንግስት ስር ላለው ማሪፍ ፋውንዴሽን ተላልፈው የተሰጡት ሰሞኑን። በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ህብረት፣ ሳር ቤት፣ ፈረንሳይ እና ሲ ኤም ሲ አካባቢዎች የሚገኙት አራቱ ትምህርት ቤቶች ለማሪፍ ፋውንዴሽን የተላለፉት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው።
 (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Read 1247 times