Saturday, 28 August 2021 12:42

“በምስራቅ ወለጋ፡ የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ሊጠናከር ይገባል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮምያ ክልል፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ነሃሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም.  በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ፣ ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የ”ኦነግ ሸኔ” ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸው በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገለጸ።   በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎች ሰዎች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።
በዚህም የተነሳ ሌላው የወረዳው ነዋሪዎች፣ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውንና በቀጣይ ቀናት ከነዋሪዎች የተውጣጡ ሰዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የአጸፋ ጥቃት በማድረሳቸው 60 ሰዎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎችም ወደ አማራ ክልልና ወደ ኪራሙ ከተማ መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ተረድቷል።
በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ወደ አከባቢው በመመለሳቸው ጊዳ ኪራሙ ወረዳ የተረጋጋ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዱ ቢሆንም በጊዳ ኪራሙና በሌሎች አጎራባች ወረዳዎች አሁንም ድረስ የፀጥታ ስጋት አለ።
ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ክትትሉን የሚቀጥል ሲሆን፣ የአካባቢው ፀጥታ የደረሰበት አስጊ ደረጃ ወደ አጎራባች አካባቢዎች እንዳይዛመትና የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያደርስ አስቸኳይ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በቀዳሚነት የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲቀናጁና የአካባቢውን ነዋሪዎች ደኅንነት እንዲያረጋግጡ ፤ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለጥቃቱ መፈፀም ክፍተት የፈጠረውን የፀጥታ ሀይሎች ከአካባቢው መውጣት ምክንያትን እንዲያጣሩ በአጽንዖት ጥሪ አቅርበው፣ “በተለይም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ስምሪትና እንቅስቃሴን በተመለከተ አሰራር ተገቢው ምርመራ ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል። አሁንም ለታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ወደነበረበት ለመመለስና የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠርና የፀጥታ ኃይል በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ እና በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላትን የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የፌዴራልና የክልሉ ኃላፊዎች በቅንጅት እንዲሰሩ ያሳስባል።


Read 696 times