Saturday, 28 August 2021 12:35

የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች በአፋርና አማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ጎብኙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች በአፋርና አማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችና አካባቢዎች ጎብኙ፡፡
 በአፋር ክልል በኩል ጉብኝት ያደረጉት አመራሮች ሰመራ ከተማ በመገኘት ከክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ወደ ጭፍራ በማምራት ሕወሃት በፈፀመው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የሚገኙበትን ሁለት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን ጎብኝተው፣ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጭፍራ ከሚገኙ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
 በጭፍራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በጭፍራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች የክልሉ አደጋ ዝግጁነትና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራምና የቀይ መስቀል ማኅበር በኩል እገዛ እያገኙ ቢሆንም ተጨማሪ የምግብና የሕክምና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ተችሏል።
በደሴ በኩል የተጓዙት አመራሮች ሕወሃት ጥቃት ከፈፀመባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ በሚገኙ አምስት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የጎበኙ ሲሆን በግዳጅ ላይ እያሉ አደጋ ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አግኝተው አበረታተዋል።
 ሕወሃት ባደረሰው ጥቃት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች  ድጋፍ እያገኙ የሚገኙ ሲሆን የከተማው ነዋሪ በራሱ ተነሳሽነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም እንዲሆን ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በቦታው የተገኙት አመራሮች ተረድተዋል። መንግሥትና ግብረሰናይ ድርጅቶችም በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን እገዛ ለማድረስ በበለጠ ፍጥነት መሥራት እንደሚገባቸው ታዝበዋል።
በጎንደር በኩል የተጓዙት አመራሮች በደብረ ታቦር፣ ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች በመገኘት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችንና በግዳጅ ላይ እያሉ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ወገኖችን የጎበኙ ሲሆን እነዚህን ወገኖች ለማገዝ የሚሠራው ሥራ የተቀላጠፈና የተቀናጀ መሆን እንደሚገባው ታዝበዋል። አመራሮቹ በየአካባቢው ያሉ የኢዜማ አባላት በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ሕዝብን ለማንቃት፣ አካባቢው ተደራጅቶ እንዲጠብቅ እንዲሁም የደጀንነት ሥራዎችን ከመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመሆን እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ አበረታተዋል።  
ኢዜማ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሆን ብር 250 ሺ ብር  በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል ለመስጠት ቃል መግባቱ ይታወሳል።

Read 846 times