Sunday, 22 August 2021 13:16

ፊት የሌለው ዐይን

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(2 votes)

 “ልብና  መንፈስህ  አውርተዋል?” አካል ሲጠየቅ “አልነበርኩም  አለ!”
(1)ትምክ...(2)ትምክ...(3)ትምክ....(4)ትምክ
(5)ትምክ...(6)ትምክ...(7)ትምክ....(8)ትምክ
እግዜር ሕመሜ አያመውም (እውነት)፤ ቁስሌ አይጠዘጥዘውም (ይህም)፤ ሰቆቃዬ አያሰቃየውም (እንዴት)፤ ዳንቴል ገላዬ በድንጋጤ ተተርትሮ ውሉ ሲጠፋ ልቤ በቅስሜ ላይ ሲቅ-ለጠ-ለጥ አጥንቴ ሲሰነጠር የት ነበር? ሕመም አያመውም ምክንያቱም እንደ እኔ እናት “እናት” አልሆነም (ሕመም፣ ቁስል፣ ሰቆቃ በእናቴ ሠማይ ላይ በነጫጭ ወልጋዳ ደመኖች የተጻፉ በአጥንቷ የተሸጎጡ ቃላት ናቸው። በእነርሷ አንጀት ካለ በእኔም አንጀት አለ፤ እነርሷ እኔ ናት! እኔ እነርሷ ነኝ!) እናቴ ቢቸግራት ወጥ ተበደረች፤ ሌማታችን ራቁቱን ከቀረ ሳምንት ሆኖታል እኮ። “ቢቸግር ወጥ ብድር!” የእናቴን አኗኗር (ረቂቁን) ከመረዳት በቅጽበት የገነትንና የገሃነምን ሚስጥር መረዳት ከእፉዬ ገላ ሳይቀል አይቀርም። እናቴ አርባ ሽንሽን ለብሳ በጭስ ተጨናብሳ ስትታይ በምዕራብ ያለች የዛለች ፀሐይ ትመስላለች (ይህ ምስል ሕልማዊ ጥላውን ፊቷ ላይ ጥሎት ማዲያት ሆኖ ተገልጧል። አይገርምም? አውሎ ንፋስ እራሱ ሥዕሉን አይበተንም ከዘላለም ይጸናል። ድምጹ ጭውውውውውው ያለ ከጽንፍ ትንሽ የራቀ ነው።) እኔ በእርሷ መልክ ብሆን ውስጣዊ (ማለዳዊ) ገጼ ሲቃ ሆኖ በጀንበር ገላ ላይ ቀዝቅዞ ይንቆረቆር ነበር፤ ክብ መስታወት በጭቃ የተመረገ ቤታችን ግድግዳ ላይ የተስፋ ሚስማር ገምጦ ያብረቀርቃል። ማለዳ ማለዳ መልኬን ለማየት ስጠጋ የእናቴን ሕልምና ቅዠት በፊቴ ጥላ ዐየዋለሁ (አንድ ቀን ጎረቤታችን ጡሩነሽ አረፉ፤ ጡሩንባ ነፊው ዘለቀ ለማኝ ሳይነሳ ሲለፍፍ እናቴ ሠማች፤ ኩርትምትም ብላ ተፊቴ ተስለችብኝ ምነው ምን ሆንሽ? እማ አልኳት፤ እኔ እያለሁ እኔ ብሞት ይሻላል ብላ ጣቶቿን ጨብጣ የተረቷን ከበሮ ደለቀችው፤ ይሄ ውስጤን ፈልቅጦ የገባ ምሬት ነበር) ከሠማይ ማህደር  አፈትልካ ከወጣች ፀሐይ የበር ንቃቃት ይሰነጥቃታል። ሞት-ዐልቦ የብርሃኗን ጠበሏን በትንሿ በቤታችን ትረጫለች (አንዳንዴ)፤ ጡኒ እና ስሚኒ ከየት እንደሚመጡ ባላውቅም የሞቀሞቀውን በር ይቆረቁሩና ይሮጣሉ፤ ወቅቱ ክረምት ነው። ፀሐይ ብኩን ንዳዷን ከጨረር ከፈለቀቀች ቆይታለች አልፎ አልፎ ብቅ ትላለች:-
የጎማ = ውንበር
ያልበሰለ=ጎበን
ያለቀሰ= ሻማ
የተበታተነ=መጽሐፍ
የሸክላ = ጀበና
የከሰለ = ከሰል ደርዝ ሳይዙ ተዘበራርቀዋል። ተነሳስቼ ብርቅርቅ መስታወቷን ገርምሜያት ብቅ አልኩ:-
“ስሙኒ...? ስሙኒ...?
ና! ናማ እስቲ እካ ዳቦ ግዛልኝ?”
“ኧረ ላሽ! አይታይሽም እንዴ ጀለሴ ግድብ እየሰራን እኮ ነው።”
“ለምን?”
“በኋላ ልናፈርሰው!”
“እና?”
“እናማ አወላከፍከኝ!”
“አልገዛም ነው የምትለኝ?”
“እሺ በቃ”
ተነጫነጨ፡፡ ካፍንጫው የሚንፈላሰሰውን ንፍጡን በትንሽ እጁ እየጠረገ፤ በትናንሽ እግሮቹ የመሬቱን ጥርስ እየረገጠ አንድ እጁን እያወዛወዘ፣ በሶምሶማ ወደ ሱቁ አቅጣጫ ተሰወረ፤ ትንሽ ትንሽ ብርሃን ሠማይ ይጨምቃል። ከነ ትርፌ ከነ አሰለፍ ቤት የሚመጣው ጭስ፤ እንደ ጥቁር ሐውልት ወደ ላይ ይጨልማል። አሃ! ትላንት ለማሰብ ያወላወልኩት  የእግሬን ነፍስ፣ ያነቃነቅሁት ያ-ያ-ያ ያ-መንገድ ረቂቅ ነው። ረቂቅ ጠመዝማዛ ቀጥ ያላለ ወልጋዳ፣ የእኔን የውስጥ ጩኸት የሰማ ማንም አልነበረም፤ እናቴ ራሱ አልሰማችም፤ እኔ ለእናቴ አዝኜ ሕይወቴን ባጠፋ ለእግዜር መራራ ወይን ይሆንበታል፡፡ ለእናቴ ደግሞ ሃሞቷ ምርር ይላታል እንጂ ልቤ ልቤን ያውቃል፤ አንድ ቀን መኖር መኖር ሆኖልኝ አያውቅም! የሕይወት ዐይን ላይ እፍ እፍ ያልተባለ ጉድፍ ገብቷል።
(ሕብረ-ዝማሬ ለውስጥ)
“ኧረ ተይ ዝንጀሮ ልቤን ቆረጥሽው
ለፍቼ ለፍቼ ሰብሌን ጨረሽው”
“ማን ቆረጠው?”
“ሕይወት”
“ማናት?”
“የምንኖራት እንጂ ዝንጆሮ አይደለችም”
“ገደል ገብቼ ልወጣ ስል
ጅቡ መጣብኝ ከቂጤ ስር”
“ከዛስ?”
“አልወርድ”
“እሺ?”
“አልወጣ ገደል”
“ከዛስ?”
አልገባ ፍርፋሪ ሸለቆ! አፈርኩ ሰውነቴን ላብ አነቀው እግዜር ሳቀ አሉ፤ እግሬ የመሬት ጠረን እንደራቀው አላውቅም፤ እስታሁን አንድ ሙዚየም “የተሳቀቀች ነብስ” ተብሎ ተሰቅሎ ይሆናል፤ ሰው ሲያየው ምጽ! እያለ ከንፈሩን ይመጣል ግን ያስቃል፤ የሚያስቀው ያስለቅሳል። የሚያስለቅሰው ያስቀናል። ነፍስ ሲያለቅስ ዕንባ ይደርቃል፤ ስሙኒ ያንጯልቃል:-
“ስሙኒ ና ግባ? አፍረህ ነው?”
“አይ ሰው ቤት እንዳትገባ ተብያለሁ”
“ዝብርቅርቅ”
“እኔ ዝብርቅርቅ?”
“ሁሉም”
“እኛ ሰፈር ዳቦ የለም ሩቅ ሰፈር ሄጄ ገዛሁ!
“ጎበዝ!”
“እማማ የሉም?”
“አዎ ለቅሶ ሄዳለች!”
“ብትገባ ይሻልሃል፤ ተቀመጥ ሻይ ጠጥተህ ትሄዳለህ”
“አይ እነ ጺጺሮ ግድቡን ያፈርሱታል ልሂድ”
“እሺ ሂድ”
(የተስፋ-መዝሙር)
የድምጽ መዝገብ ሸሸኝ፤ የአንድ ቅርንጫፍ ወመከራ የድብርት ቅጠሉች ቤት ፈሰው ቅርንጫፉ ሲያብብ ቅጠሉ ሲያብብ ነጸብራቁ ገላዬ ላይ ሲቁነጠነጥ ይታያል። ታመመች ጊዜ አታውቅም፤ ልቧ ታጥፏል በአጥንቷ ውስጥ የእንጉርጉሮ ግጥም ገብቷል። ቀጥ ያለለ ጉጥ ጎኗ ተጎጥጉጧል። ትድናለህ የመዳን ጠበሌ በአንተ ቤት ይፈሳል። በገላህ ላይ ይንቆረቆራል ትድናለህ ተብያለሁ? በሥውር በግልጥ አንድ ዓላማ አለ፤ፈጣሪ ያውቃል።
(ክረምት አግቢዎች)
ክረምት አግቢዎች ልባቸው አልተረጋጋም፤ ቅርንቡስ ሸሻቸው መሰል። በቃብር አቅፈቃው ብጭቅጫቂ ጎህ ለብሰው ከመላዕክትን ክንፍ ተውሰው ለሕጻናት የማይሰማ የመንግሰተ ሰማይን መዝሙር ይዘምራሉ:-
ዓለም = በሌላ ዓለም
ጨለማ ምድር = በብርሃን እንዲጥለቀለቅ
ሙት = ሕይወት
ምድር = ዘላለማዊ እስትንፋስ ሲሉ አየዃቸው፤ እግሬን ኮረኮሩት፤ ሕጻናት በቅጠል ሲያባርሯቸው እያየሁ-በቀስታ ከመኃላቸው ገባሁ:-
“ባንመጣ ክረምት ይገባ ይሆን?”
“ደማቅ ጮራ ይከናነባት ነበር?”
“ጭጋጉን ማን ይግፈፈው?” አሉ
የቢራቢሮዎች የናፍቆት ሕብረ ዝማሬ:-
የፀሐይን የመራቅ ገላ ድቅድቅ ክረምት አዝሎ ከጭጋግ ጓዳ ጥጋጥግ ከሚመላለሱ፣ ከሚርመሰመሱ ካለፍናቸው የዝንጋኤ ፍዳ ማምለጥ ቢያቅተን ከሳቅሽ ፍል-ቅል-ቅታ እንደሚፈልቅ ሃዘን ሐሳብ እየቀዳን እየበረርን - እየበረበርን፣ ምጽአትሽን፤ እንጠብቃለን ተፈጥሮ እስቲስቅ እግዜአር በዐዕዋፍ ድምፅ ከበሮ እስኪደልቅ፤ ማለዳ-ሳይጸዳዳ ወደ ደጅ አፍ ወጣ የአምላክ ሳቅም ቆመ፤ ድቅድቁ ገነነ ዓይንሽን ሳያየው ማሸለብ ሆነ መች አዘነ፤ እናቴን አይደለ? እናቴን አይደለ? ክንፋችን መርገፉ ምን ቢሆን እውን መድረስ ባንችል ከግብ-ንጋት ጥዝዝዝዝዝዝዝዝዝ! ጥዝዝዝዝዝዝ:-
(የእናቶች ሕብረ ዝማሬ)
“ኧረ አምሳለ?
ኧረ አምሳለ?
ኧረ ወይ!
ኧረ ወይ!
ኧረ እንዴትነሽ?
ኧረ እንዴት ነሽ?
አለሁ በመከራ፣
ዕንባዬን ሳዘራ፤
ለምን ታዘሪያለሽ?
አገዳ እየበላሽ፣
አገዳም የለኝ፤
ምስኪን ድሃ ነኝ!
ምስኪን ድሃ ሆነሽ፣
ምን በልተሽ ታድሪያለሽ?
ባገኝ በልቼ
ባጣም ተደፍቼ!
ይድፋኝ ይደፋፋኝ
ጦም ማደርሽ ከፋኝ”
እነ ስሙኒ ያፈረሱት ግድብ ድምጽ አወጣ ረበሸኝ፤ የክረምት አግቢዎቹ ክንፋቸው ተነቃቅሎ መሬት ላይ ይንፏቀቃሉ፣ ብልቃጥ=ቅጠል= ሕጻናት ከበውኛል፤ ዐይን እንጂ ፊት የሌላት እናቴን ከሩቅ አየዃት:-
እኔ     እናቴ    
ድንቡሽብሽ   ከሲታ
ረጂም    የጎበጠች
መልከ-መልካም   መልከ-ቀዝቃዛ
ደመ-ሞቃት      ደም-ፍላታም
ለፍላፊ   ዝምተኛ
ሩቅ አሳቢ   ቅርብ አዳሪ
የተንጠለጠለ አገጭ  ቁልቁል የወደቀ
ያልጎደለ አንጀት    ጢል ያለ
መዳፈ ለስላሳ     መዳፏ-ሸካራ
በነጭ ነተከበበ ብሌን  የቀላ ጥቁር ነጥብ
ትንሽ አሳዘነችኝ ዐይኗን አስለቅሳው ይሆን? ፊቷን ጠርጋው ይሆን? = ቦዘብኝ መሰል ዐይኔ ተንቀጠቀጠ፣ ጠፍቶብኝ ነው? ተዛሞብኝ ነው? ወይስ ስለራቀች ይሆን? የቅዠት ምናቤ አስነከሰኝ እያነከልኩ ፊቴን አዙሬ ወደ ቤቴ ገባሁ:-
“ልብና መንፈስህ አውርተዋል?” አካል ሲጠየቅ
“አልነበርኩም አለ!”
እንትና እኮ ሞተች ምነው እሷ ከምትሞት እኔ አፈር በጋጥኩ ትለኝ ይሆን? የ ሰ-ቀ-ቀ-ን ጽምጽ ጆሮዬ ላይ ያንሾካሹካል።
ዝም
ዝም
ዝም

Read 440 times