Print this page
Sunday, 22 August 2021 13:12

ቀስቶ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

(የአጭር አጭር ልብወለድ)
                 

          ቀስቶ በስካር ካልናወዘ፣ እርቃኑን የሆነ ይመስለዋል፡፡ በተለይ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ከብርሌ ጋር ተኳርፎ ብልጧን መጨበጥ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ፤ አዲስ ዓመል አውጥቷል፡፡ ጥቂት ከውሃው ከወሳሰደ፣ ምላሱ እንደ ቀትር እባብ ነው፤ የሚንቀለቀለው፡፡ ስካሩ፣ ትላንቱን እንደ መስታወት ወለል አድርጎ ያሳያዋል። ቆብ የደፋበት የጥናት መስክ፣ አውላላ ላይ እንደጣለው የሚታወቀው፤ ናላው ሲዞር ነው፡፡ ለጊዜው ለጎተራው ፈጥኖ ደራሽ የሆነለት፤ የሸክም ሥራ ብቻ መሆኑ ሲገባው፤ለራሱ ይደንቀዋል፡፡ “ጫንቃዬ ለዘለለም ይኑር!” ሰርክ ከቀስቶ አንደበት የምትስፈነጠር መፈክር ነች፡፡
ዞሮ መግቢያ ጎጆው፣ በተአምር የቆመች አስማት ናት፡፡ በወፍራም ንጥሻ፣ የምትፈርስ ትመስላለች፡፡ ከእርሷም ብሶ፤ ወር በመጣ ቁጥር፣ ኪራይዋን ለመክፍል፤ የማይቧጥጠው ዳገት አይኖርም፡፡ የቤቱ ቀጭን ጌታ፣ ባሻ ኪራይ ከመድረሱ ሁለት ቀናት ቀደም ብለው፣ በአካባቢው መለስ ቀለስ በማለት፤ የማሳቀቅ ሥራን በመሥራት ነው፤ የሚታወቁት፡፡ ቀስቶ፣ ባሻን ለሚቀበላቸው መሬት ሁሌም እንዳዘነ ነው፡፡  
በተበሳሳው ሰንበሌጥ ግድግዳ፣ የገባው የብርሃን ጨረር፤ ከፊቱ ላይ ብትን አለበት። የካቲካላው አንጎበር አለቀቀውም፡፡ ባለ በሌለ ኃይሉ አፋሻከ፡፡ የወደቀበት ፍራሽ፣ ወደ ምንጣፍነት ተቀይሯል፡፡ ደግነቱ፣ የመኝታው ቁርቋሬን የሚሰማበትም፣ አቅል ኖሮት አያውቅም ፡፡ በስካር የደነዘዘ በድኑን ይጥላል፤ ሲነጋ ለዕለት ጉርሱ ይሮጣል፡፡
የዕድር ጥሩንባ ለፋፊ የሆኑት ጎረቤቱ፣ የሚወቅጡት ቡና አናቱ ላይ የሚወቀር መሰለው፡፡
“እመት አዛሉ ዱላው አልበዛም?” አለ በተግሳጽ ድምጸት፡፡
“በገዛ ሙቀጫዬ….” ግርምት አዘል አጸፋቸውን ለመስጠት አልዘገዩም፡፡
“ጡሩንባ የሰማው መሰለኝ ልበል?”
“የሰፈሩ አድባር ተቸነፉ”
“ምነው መቸነፋቸው ደነቀዎት? እርስዎም ምንጣፍ ጎታች ነበሩ እንዴ?” ቀስቶ እመት አዛሉ ላይ ካራ ወረወረ፡፡
“ከተናግሮ አናጋሪ ሰውረኝ ጌታዬ፣ ለነገሩ ጥሩንባ አልተለፈፈልህም እንጂ፤ የሙታን ምድብተኛ ከሆንክ ሰንብተሃል፤ማዘን ለአንተ ነው!”
እመተ አዛሉ፣ የጠዋት ቀለቡን አፉ ላይ አደረጉለት፡፡ በንዝንዙ መዝለቅ አልፈለገም። ቀስቶ፣ ባዶ ቀፈቱን በጥፍሩ ሞረድ ሞረድ አደረገና  ለሽቀላ ሥራው፣ እግሩ ወደ መራው አቅጣጫ አመራ፡፡
x   x   x
በሰጎን ቅልጥሙ፣ ከሲታዋን ጎዳና ቀነሰና፣ ከጭርንቁሷ ካቲካላ ቤት ተሞጀረ፡፡ የሳቅና ጨዋታ ወደብ የሆነችው፤ ጭርንቁሷ ቤት፣ መጠጊዬ ብለው  በታደሙ መሸተኞች ጭንቅ ጥበብ ብላለች፡፡ ቀስቶ፣ በብልጧ ጉሮሮውን ለማርጠብ ተጣድፏል፡፡ ጥግ ፈልጎ ተወሸቀ፡፡ በዐይኑ፣ የሰርክ ታዳሚ መሸተኞችን መመዝገብ ያዘ፡፡ አንዲት ቀትረ ቀላል ሴት ጎድላለች፡፡ በቀሪ መዝግቦ፣ ከራሱ ጋር  መነጋገሩን ለጠቀ፡፡
ኳ....... ኳ “ድገሚኝ ባክሽ” የኮሶ መድኃኒት የጠጠ ያህል ፊቱን ኩምትር አደረገ፡፡
የመጀመሪያዋን ካቲካላ፣ እንዴት እንደጨለጣት አልታወቀም፡፡ “ሁለተኛውን ካቲካላ፣ መጀመሪያ የጠጣኸው ካቲካላ ነው፣ የሚያዘው፤" የሚለው የመሸተኞች ቀልድ፣ ትዝ አለውና ፈገግ አለ፡፡
የሚንተፋተፈው ቴፕ፣ ዘፍን የሚመስል ጭል ጭል የሚል ድምጽ ያሰማል፡፡ ቁብ የሰጠው የለም፡፡ መሸተኛው በራሱ ታንኳ እየተንሳፈፈ ነው፡፡
መቃብር ቆፋሪው ነውጤ፣ ባርኔጣውን ከፍ አድርጎ ጭርንቁሷን ቤት ተወዳጀ። ቀስቶ፣ ይኽን ሰው ደርሶ ኮከቡ አይወደውም። የሰፈሩ ቁጥር አንድ፣ ምንጣፋ ጎታች ነው፡፡ እንደ ምንጣፍ ጎታችነቱ ግን፤ አልቀናውም። ያው እንደ ቀስቶ፣ ኑሮው ከመሬት ከፋ አላለም፡፡ ቀስቶ ቢያንስ፣ ኅሊናውን ሳይበድል ከድህነት ጋር ተከባብሮ ይኖራል፡፡
“ዛሬ አፈርን በአፈር አይደለም የመለስኩት፡፡ ትልቅ ሰው ነው፤ ያጣናው። የሰፈሩን ቀጭን ጌታ፤  የተቀበለቻቸው መሬት፣ መቼም ዕድለኛ ናት፡፡” አለ መቃብር ቆፋሪው፣ በነገር የጨቀየ ዐይኑን እያጉረጠረጠ፤
“ደግሞ፤ ለበድንም ደረጃ ማውጣት ጀመርክ ?” ቀስቶ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ አቃተው፡፡
“እንዴታ! ከቀብርም ቀብርም አለው እንጂ፤ የእንተ ቢጤን ለመቅበር፣ ጀማው አያስፈልግም፤ በጥድፊያ ማለባበስ ነው፡፡”
“አሳማን ሊፒስትክ ብትቀባው፣ አሳማነቱን አይቀይርም፤ በድንም የጌታ በለው፣ የሎሌ፤ ያው ነው፡፡ እስትንፋሱን ተነጥቋል፡፡”   
“ቀስቶ፣ ጭንቅላትሽን ማሰራት ጀመርሽ  ማለት ነው? ግን ጭንቅላትሽን ሞት ላይ ባታባክኚው ግሩም ነበር፡፡”
ከዚህ በላይ መመላለሱ፣ ጉንጭ ማልፋት እንደሆነ ተሰማውና ሥካሩን ለማጣጣም፤ አንደበቱን ለጉሞ በወስጡ ያጉተመትም ያዘ፡፡ የወሰደው ካቲኪላ፣ ቀስ በቀስ ምላሱን እንደ ካራ ሲስለው ይሰማዋል፡፡ መቃብር ቆፋሪው የወረወረው የነገር ፍላጻ፣ ከስካሩ ጋር ውስጡን ዘልቆ አመመው፡፡ የመልስ ምት፣ ማስወንጨፍ እንዳለበት ወሰነ፡፡ ዘግይቶ መሸተኛውን ለተቀላቀለው አዝማሪ፣ እንዲህ የሚል ሽሙጥ አዘል ስንኝ አቀበለ፡፡
ተቀበል
ኩርማን ለማትሞላው፣
ለዚች አጭር እድሜ ፣
ምንጣፍ አልጎትትም፣
እኖራለሁ በአቅሜ፡፡


Read 1909 times