Print this page
Sunday, 22 August 2021 13:11

ሴፊኒ፡- ፍፁም አይፈፀምም

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

 …ይኼ ታሪክ፣ አንዱ ሞቶ ሌላኛው ደግሞ ወደ ፅርሃ አርያም የሚያርግበት አይደለም፡፡ የልብ መስቀያ ሽቦ መሸጥ ትርፉ ኪሳራ መሆኑን ለማሳየት ታቅዶ የተፃፈ ነውና!
       
           “የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ” የሚል ሀገር በቀል ብሂል አለ፡፡ ብሂሉ የሚገልፀው ከአህያ ይልቅ የሰው ልጅን ነው፡፡ በተለይ ሴፊኒን፡፡
ትክክለኛ ስሙ ሰይፉ ነበር፡፡ ከደህና ቤተሰብ የተወለደ የከተማ ልጅ በመሆኑ፣ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት እየተማረ፣ በደንብ ነብስ ለይቶ ከማወቁ አስቀድሞ ስሙ ወደ ሴፊኒ በክፍል ጓደኞቹ ተለውጦ ተጣበቀበት፡፡
ሴፊኒ፣ ተፈፀመ ወይም አለቀ ማለት ነው፡፡ ለምን ስሙ እንደወጣለት እና በማን ወደኋላ ተመልሰን የክፍል ጓደኞቹንና መምህሮቹን፣ አበል ከፍለን ሰብስበን ብንጠይቃቸው የምናገኘው አጥጋቢ መልስ አይኖርም፡፡ ሁሉም ግን ስለ ስም አወጣጡ ከራሳቸው አንፃር መነሻ ነው ብለው የሚያምኑት፣ የሚመስላቸው ነገር አለ፡፡ ሁሉም በአንድ ላይ የሚስማሙበት ትዝታ የላቸውም። በፈረንሳይ ቋንቋና ባህል ስር ተምረው በማለፋቸው ከአበሻ ትህትና እና ስነምግባር በመጠኑ እንዲጎድሉ አድርጓቸዋል፡፡
…ስሙ የወጣበት ምክኒያት ላይ አይስማሙም ብቻ ሳይሆን፣ የአንዱ ትዝታ የሌላኛው የቅይምታ መንስኤው ነው፡፡ የመሃል ጣታቸውን እየቀሰሩ ነው የተሳሳተውን ሰው የሚኮንኑት፡፡ ግን አንባጓሮ አይፈጥሩም፡፡
ሴፊኒ ተብሎ በተሰየመበት የጨቅላ እድሜው ዘመን፣ ምንም አይነት ነገር ገና ያውቅ እንዳልነበረ፣ የዋህ ልጅ እንደነበር፣ የስሙ ባለቤት እጅ መትቶ ይምላል፡፡ “አለቀ” የሚል ስም ሲወጣለት፣ ገድሉ የማያልቅ ሰው እንደሚሆን ተተንብዮ እንዳልሆነ፣ እኔ በእዛ ዘመን ባላውቀው እንኳን እመሰክርለታለሁ።
ሴፊኒ ማነው? ከተባለ “የተዋጣለት የአህያ አለሌ” ነው የሚለው ነጥብ ላይ ግን በቅርበት የሚያውቀውም ሆነ በሩቅ ገድሉን የሰሙለት ሁሉ ይስማማሉ፡፡ በአህይነቱ ረገድ፣ ሀገራዊ አባባሏም የምትመጥነው አይነቱ አህያ ነው፡፡ የተወለደው ከሀብታም ቤተሰብ፣ የተማረው በጣም ሀብታም የሆኑት ተመርጠው ከሚማሩበት ትምህርት ቤት፤ ያውም በፈረንሳይኛ ቋንቋ፡፡ ግን ልጁ የሚገኘው መሰሎቹ እንዲውሉ በታቀደላቸው አይነት ስፍራ አይደለም፡፡ በዚህ ምክኒያት ነው አህያ መሆኑ ላይ እሱ ራሱም የሚስማማው። አህይነቱ፣ በተለይ፣ በሴት ምርጫው ላይ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ተራ ሴቶች ይወዳል። የጭቃ ረጋጭ፣ የሽንኩርት ሻጭ ልጆች፡፡
ጭንቅላቱ ከሌላው ተማሪ የተለየ አይደለም፡፡ በቅርፅም ሆነ በይዘት፡፡ አህያ ከመሆኑ በስተቀር ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ተማሪዎች በመደዳ ተደርድረው ውሃ ቀኑን ሙሉ በሚያጥበው የትምህርት ቤት  ገንዳ ላይ ሽንታቸውን ሲሸኑ፣ የሴፊኒ ሽንት ብቻ ከሁሉም ተለይቶ፣ በገንዳው የጠጠር ሞዛይክ ላይ ሲፈርጥ በሚፈጥረው ድምፅ ተለይቶ ይጎላ ነበር፡፡ ትርጉሙ በዛ እድሜ እያሉ አብረውት የሚማሩት አይገባቸውም፡፡ የሽንት መወፈርም ሆነ የሽንት ማፍሰሻ መርዘም፣ ምን የተለየ ሚስጥር እንዳለው ፈፅሞ አያውቁም ነበር፡፡
ሴፊኒ ምንም አይነት የማፈር ተፈጥሮ ከመነሻው ስላልፈጠረበት እንጂ፣ ከሌሎቹ መለየቱ ብቻ ሊያሸማቅቀው በተገባ ነበር። ተደብቆ መሽናት ነበረበት፡፡ በእድሜ እኩያ ከሆኑ ልጃገረዶች መሃል ቀድማ ጡት ያበቀለችዋ፣ ያበቀለችውን ለመደበቅ ከመሸማቀቅዋ ብዛት ትከሻዋ ሊጎብጥ እንደሚችለው ማለት ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ከሌላው በምንም ረገድ መለየት የሚያኮራ ነገር የለውም፡፡ ኩራቱ ቀስ እያለ የሚመጣ ነው፡፡ የተለየው ነገር አስፈላጊነት ሲታወቅ ቀስ ብሎ የሚመጣ ነው፡፡ ትንሽ በእድሜ ከፍ ካሉ በኋላ፣ ማነፃፀር ሲጀምሩ ይስቁበት ጀመር፡፡ ሳቃቸው የማንኳሰስ ሳይሆን፣ እንዲያውም ወደ ማድነቅ ያደላ ነበር፡፡ የሆነ የመታደል ንጥረ ነገር እንዳለው በግርድፉ ገብቷቸዋል፡፡ ወዲያው እንደገባቸው መቅናት ጀመሩ፡፡ ከእሱ ጎን ቆሞ የሚሸና እየጠፋ መጣ፡፡
እዛ ሊሴ ተማሪ ሳሉ ሁለት ጫፍ የቆሙ የከፍታ እና የዝቅታ ማነፃፀሪያዎች ነበሩ። ከፍታው ሴፊኒ ላይ ያርፋል፡፡ ዝቅታው ቁጢላ የተባለው ልጅ ነው፡፡ የእጅ ትንጧን ጣት የምታክለውን መፀዳጃውን ከሰባተኛ ክፍል በኋላ ሰው ባለበት ለሽንት ተጠቅሞባት አያውቅም፡፡ ነፍስ ሳያውቅ በፊት ግን ትርጉሙ ስለማይገባው የትም ይመዛት ነበር፡፡ የሚመዘዝ ነገር ባይኖራትም። ነፍስ እንዲያውቁ በተፈጥሮ እና በእድሜ ተቀስቅሰው ሲነቁ፣ ባለ ትንሹ የትንሽነት ስሜት ይረብሸው ጀመር። የትንሹን አካሉን ጉድለት ለማካካስ በጭንቅላቱ መበርታት እንደነበረበት በደመነፍስ ሳያውቅ አልቀረም። ተሰጥኦው ከወደ ጭንቅላቱ ነበር፡፡ የወጣለት “ቀለም” ሆነ፡፡ ቀንም ማታም የሚያጠና፣ የተዋጣለት ቀለም ተማሪ ሆነ፡፡
ሴፊኒ ትምህርት ገብቶት አያውቅም። ወደ አዋቂነት እድሜ ግን፣ ያወቀም ያላወቀም፣ መግባቱ ዞሮ ዞሮ አይቀርም፡፡  ሴፊኒ ማወቅ ሲጀምር ማንም ሳያስረዳው የገባው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ስራ እንዳለበት ነው፡፡ የሚሰራው ስራ በተፈጥሮ ከተሰጠው የመስሪያ መሳሪያ ብቃት ጋር ይያያዛል። ማንም በተሰጠው ነገር አማካኝነት ነው ለተግባር ዝግጁ የሚሆነው፡፡
ጭንቅላት ያላቸው የጭንቅላት ስራ ለመስራት ባለው አማራጭ ካደጉ በኋላ እንደተሰማሩት፣ ሰይፉ ደግሞ የተሰጠውን የሚያወጣበትን ዝንባሌ አዳበረ፡፡ ሴቶችን በሁሉም ጊዜ እና ሁኔታ ውስጥ ማደን። የተሰጠው አቅም ከአፍ ጋር የተያያዘ ስላልሆነ በአፉ አብዝቶ አይጠቀምም። የተሰጣቸው አቅም በምላሳቸው ጡንቻ ላይ የተቋቋሙት ለማንኛውም ተግባር ግባቸውን የሚያመቻቹት በቅቤ ምላሳቸው አንጥረው ነው፤ ወይንም አነጣጥረው፡፡ ሴፊኒ እንደ አህያ ከባዱን ሸክም ለመሸከም እንደተፈጠረ ያወቀው አመድ ላይ በደንብ ተንደባሎ ነው፡፡ ይሄኔ ነው አህይነቱን የተቀበለው፡፡ ያወጡለትን ስም የዋጠው። ስለራሱ ካወቀ በኋላ ያወቀውን ለአለም አስተዋወቀ፡፡ አልጋ ሳይሆን አመድ ነው፣ የአህያ ተፈጥሮ የሚወደው፡፡ የሴፊኒ ውድቀትም በዚህ ሀገራዊ ተረት እና ምሳሌ ውስጥ በደንብ ይጠቃለላል፡፡
አንድ ብሎ ተግባሩን ከጀመረበት እለት አንስቶ፣ አንድም የእሱን አስተዳደግ እና ማህበራዊ አመሰራረት የምትተካከል እኩያው ከሆነች ሴት ጋር በአልጋ ላይ ወድቆ አያውቅም፡፡ ከጀመረበት እለት አንስቶ ገድሉን አጠናቆ “እሩጫዬን ጨርሻለሁኝ” እስካለበት ቅፅበት፣በአመድ ላይ ሲንከባለል የሚገኘው ከአመዳሞቹ ጋር ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ገና ሳይወጣ ነበር የመጀመሪያውን ምናባዊ ግንኙነት ከትምህርት ቤቱ የፅዳት ሰራተኛ ጋር የጀመረው፡፡ የከንፈር ፍቅር ነበር፡፡ በከንፈር ተጀምሮ፣ ከንፈር በከንፈር ላይ በሚሰራው ገድል የተቋጨ ተሞክሮ ነበር፡፡
“አይመቹኝም” ይላል፤ የእሱ አይነት መሰረት ላይ የበቀሉ ሴቶች ለመቅረብ እንደማይሞክር ጓደኞቹ የተጨነቁለት መስለው ሲወተውቱት፡፡
“ሁሌ ከማድ ቤት ሰራተኛ፣ ከሴት ደንብ አስከባሪ ወይንም ሴት ፌደራል ፖሊስ… ወይንም ደግሞ የምትሰራበት መስሪያ ቤት ካለች ጠራጊ… ቤትህን ስታስገነባ በነበርክበት ጊዜ ደግሞ አርኪቴክቷን ትተህ… ድንጋይ በባሬላ ስትሸከም ከነበረችዋ የቤት ሰራተኛ ጋር በፍቅር ስትወድቅ ነበር። መብትህ ሊሆን ይችላል፡፡ የመረጥከውን ማፍቀር አትችልም አይደለም እያልንህ ያለነው፡፡ አትችልም ሳይሆን… መቻልማ ሁላችንንም በሚያሸማቅቅ አኳሁዋን ችለህ አሳይተኸናል፡፡ አትችልም ሳይሆን… አይዘልቅም ማለታችን ነው” ይሉታል። አብሮ አደጎቹ ስለሆኑ እና ስለሚቀርቡት እንጂ በሰው ህይወት እና የቀሚስ ምርጫ መግባት ነውር መሆኑን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡
“ለምን አይቻልም?” ይላቸዋል፡፡ ተገፍትሮ የሚወጣ እና ወዲያው ትልቅ የሚሆን ሳቅ አለው፡፡ በሌላ ሰው ላይ ግን ስቆ አየሁት የሚል ማንም የለም፡፡ በራሱ ላይ ለመሳቅ ግን ሁሌም ዝግጁ ነው። በማስመሰል ፍሪኩዌንሲው ያልተገደበ ሳቅ። በራሱ ሲስቅ፣ ወቃሹ ተጨማሪ ትችት እንዲሰነዝር የልብ ልብ ይሰጠዋል፡፡ በሳቁ ተደፋፍረው ጓደኞቹ የበለጠ ጫን ብለው ጠየቁት፡፡
“ለምን አይቻልም ትለናለህ ደግሞ? … ለምን እንደማይቻል ህግ ደንግገን የከለከልንህ አስመሰልከው፡፡ … የማህበረሰብ ደንብን እኛ አይደለንም የፈጠርነውኮ! ሁሉም ከመሰሉ ጋር የሚውለው እኮ ወዶ ሳይሆን ግዴታ አስገድዶት ነው፡፡ አንተ አውቀህ አልሸነፍም ባይ ለመባል ነው ይሄንን ክርክር የምትገጥመን፡፡ የገበሬ ልጅ ወይንም ባሁኑ ዘመን ደግሞ ራሷ ገበሬ ከሆነች ሴት ጋር ትዳር ለመሆኑ ለመመስረት ትችላለህ?... እንደው እስቲ በናትህ ለክርክር ልዕልና ሲባል በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ሃሳብህን አካፍለን፡፡ አጭር መልስ ሳይሆን እስቲ የሚሰማህን ልብህን ከፍተህ አወያየን”  አብሮ አደግ ጓደኞቹ ብዙ ሆነው ሃሳባቸው ግን አንዳይነት ስለሆነ፣ በአንድ ሰው አንደበት የተናገሩት ያስመስልባቸዋል፡፡ ግን በተናጠል ተወልደው በተለያየ ሰፈር ያደጉ ናቸው፡፡
ሴፊኒ ማብራራት ቢፈልግም፣ ንግግሩን ከአጭር ምላሽ ለማሳለፍ ሲፈልግ ይጨንቀዋል፡፡ እግሩን ደራርቦ በተቀመጠበት ይቁነጠነጣል፡፡ ፀጉሩን በእጁ ያካል፡፡ እና ከጉሮሮው እየተንከባለለ በሚወጣ ጅረት መሳይ ድምፅ ይስቃል፡፡ ለምን እንደሆነው ሆኖ ራሱን እንዳገኘው፣ ከማንም የበለጠ የሚገርመው እሱኑ ራሱን መሆኑን በሚያመለክት አኩዋኋን ነው ደግሞ የሚጨነቀው፡፡ በተፈጥሮው የንግግር ሳይሆን የተግባር ሰው ነው፡፡ አደርጋለሁ ብሎ ሲዝት ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ካደረገው በኋላ፣ ወሬው በሌሎች አፍ ላይ ፋፍቶ ተመልሶ ወደሱ ጆሮ ይመለሳል፡፡
“እኔ ትዳር መመስረት ስለማልፈልግ ነው እንጂ… ለምን እናንተ አሁን ከዘረዘራችኋቸው አይነት ሰዎች ጋር እንደማልገናኝ እኔም አይገባኝም፡፡ ስለዚህ መከራከሪያ ማቅረብ አልችልም፡፡ እንድንወራረድ ከሆነ የፈለጋችሁት እሱም ላይ ጥሩ አይደለሁኝም። ቁማር አልወድም…።” የደከመው ይመስል በረጅሙ ይተነፍሳል። እንደዚህ አይነት ረጅም አረፍተ ነገር ተናግሮ ከዚህ ቀደም የማያውቅ ይመስላል። ጓደኞቹ ተማክረው፣ ድንገት በዛ ቀን፣ ፀሐይ መጥለቂያ ላይ ያዘመቱበትን ክርክር ለመመለስ ባለመፈለጉ ድርቅናው ውስጥ የሸፈተ መስሏቸው እንዳያዝኑ… አቅጣጫ ማስለወጫ ሃሳብ ያመጣል፡፡ ሃሳቡን ገና ከማመንጨቱ ወደ ተግባር ለመለወጥ ተስፈንጥሮ በመነሳት ይቁነጠነጣል፡፡
የመኪናውን ቁልፍ አሹሎ፣ አንዲከተሉት በእጁ እየጋበዘ ፡-
“ለምን ሄደን ቀዝቃዛ ቢራ እየጠጣን… ፀሐይዋ ወደ ማይቀረው ጎሬዋ ገብታ ስትደበቅ አንመለከታትም?” ከዛ “ቅኔ ነው የተናገርኩት አይደለም?” ብሎ ከትከት ብሎ ይስቃል፡፡
አልተደሰቱበትም፡፡ በቀላሉ ሊተዉት ግን አልፈለጉም፡፡ “አይ ዛሬ መልስ ሳትሰጠን በቀላሉ አንላቀቅም …ድንጋይ ተሸካሚዋን ፍቅረኛህን አግብተህ ወደ ሚስት መቀየር እችላለሁ የምትል ከሆነ አድርገህ አሳየን… የማይሆን ከሆነ ደግሞ የማይሆን አቋም ላለመሸነፍ ስትል ይዘህ በግድ አትድረቅ”
“ልክ ናችሁ ደረቅ ነኝ…ለዚህ ነው እኮ እንደናንተ ሚስቶች ቆነጃጅት ሴቶች የማይቀርቡኝ”  እንዲከተሉት እየጋበዛቸው ነው ይሄንን የሚላቸው፡፡ እነሱ ግን እንዳይወጣ በሩን አንቀው ይነዘንዙታል፡፡
“በመኪና እየሄድን መቀጠል እንችላለን ጨዋታችንን”
“አይ ይሄ ማጭበርበሪያህ እንኳን ተነቅቷል… በዛ ላይ ሁላችንም በየራሳችን መኪና ስለሆነ የምንከተልህ በመሃል የጀመርነው ጨዋታ ይረሳሳል፡፡ እዚሁ ውይይታችንን እንጨርስ፤ ካልሆነ ይህ የያዝከው ባህል ይሁን ሱስህ ትክክል አለመሆኑን ተቀብለህ እኛ የለገስንህን ምክር ተቀበል”
“እሺ ምከሩኝ፡፡ ግን ምክሩ ግዴታ እዚሁ መሆን የለበትም ነው ያልኳችሁ… ምክር ያለ ማለስለሻ የመካሪውንም ልብ ይፍቃል አይመስላችሁም?” ብሎ ትልቁን ሳቅ ያፈነዳዋል፡፡ ሳቁ ሲተልቅ ልክ እንደሚያስመልስ ሰው ከወገቡ ጎንበስ ብሎ… በሁለት እጆቹ የጉልበቶቹን መታጠፊያ ለመደገፍ ይገደዳል፡፡
***
ምክሩ ቢራ በሚጠጡበትም ቦታ ቀጠለ። ሴፊኒ በመሃል ከመሳቅ እና ጭንቅላቱን ከመነቅነቅ በስተቀር ምክሩን ለመቀበል አንዳችም የማቅማማት ምልክት አላሳየም። ይሄ ጠባዩ በዛ እለት ድንገት የተጀመረ ሳይሆን አብሮት ያደገ እና የጎለመሰ ነው። እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ መቀበል የማይፈልጉት እነሱ እንጂ ሰይፉ አይደለም፡፡
ረጅሙ የምክር ሰንሰለት በአንዱ ጓደኛው ላይ ጀምሮ ተጎንጉኖ እና ተገምዶ ሳያልቅ ሌላኛው ደግሞ ይቀጥልበታል፡፡ ምክር ደግሞ በባህሪው ዝግ ባለ አንደበት የሚካሄድ እና በቀላሉ ተጀምሮ የማያልቅ ረጅም ነገር ነው፡፡ መካሪው በከፍታ ቦታ ላይ ይቆምና… ምክር ተቀባዩን ደግሞ ከተራራው በታች ኮሰስ ብሎ እንዲውል ያደርገዋል፡፡ ተመካሪው በመመከር ሂደቱ ላይ እንዳለ… አንገቱን ሰበር… ትከሻውን ወደ መሃል ደረቱ ጠውለግ አድርጎ እንዲቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡
ምናልባት ሴፊኒ ላይ ያባከኑት የምክር ውለታ በድንጋይ ላይ የፈሰሰ ውሃ መሆኑን እርግጠኛ የሆኑት… ይሄንን የአካል ምክር መቀበያ ቅርፅ በሰይፉ ላይ ተንፀባርቀው ስላላስተዋሉዋቸው ብቻ አልነበረም። የቢራ ጠርሙሶቹ፣ ሁለት የድግግሞሽ ሳይክላቸውን እንኳን በቅጡ ሳያጠናቅቁ… መካሪዎቹ በአብሮ አደግ ጓደኛቸው መበሳጨት ጀመሩ፡፡ ምክር ወደ ቁጣ ሲለወጥ፣ አንደበት የቃላት አወጣጥ ፍጥነቱን ይጨምራል፡፡ እንደ አለንጋ “ሾጥ” እያሉ ብልጭታ ለመፍጠር የሚዳዳቸው ቃላት ይፈተለካሉ፡፡ ቁጣው በለበጣ በተሸራመሙ ከናፍሮች መሃል እየሾለኩ ነው የአድማጫቸውን ቀልብ ለመግዛት የሚጥሩት፡፡ አድማጫቸው ሴፊኒ ነው፡፡ አብሮ አደግ ጓደኛቸው፡፡
በቁጣ ማሳመን መጨቆን ስለመሆኑ ለጊዜውም ቢሆን ተዘንግቷቸዋል፡፡ ሴፊኒ፣ ለሚሰነዘርበት ቁጣ ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት የማይመለስ ሰው ቢሆን ኖሮ… የተወለደው የክርክር፣ ምክር፣ ለበጣ፣ ቁጣ… ዝግመተ ለውጥ መጀመሪያውኑ ተወልዶ አይድህም ነበር፡፡ የልብ ልብ የሚሰጥ አይነት ሰው በመሆኑ ነው፣ የልብ ልብ የተሰማቸው ሁሉ ከራሳቸው ጭላት እና አመድ ውስጥ እየተነሱ እሱን የበታች አድርጎ እንደ ልባቸው ለመናገር የማያፍሩት፡፡
ጭቃ ረጋጯን እና አይነ ስውር ሎተሪ ሻጯን ወደ አልጋ ጨዋታ በቀላሉ የሳባቸው በዚህ ጠባዩ ምክኒያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ትከሻው ሁሉንም በቀላሉ ለማፈናጠጥ ቀላል መወጣጫ ስላለው… ማንም እንጣጥ ብሎ ይፈናጠጥበታል፡፡ ጓደኞቹ በዚህ ባህሪውም ጭምር ነው የሚበሳጩት፡፡
የሴፊኒ ጓደኞች፣ ብዙ ዋጋ የከፈሉባቸው ሚስቶች አሏቸው፡፡ እንደ አንጡራ ሀብት የሚቆጥሯቸው፡፡ በብዙ መሃላ፣ በመንግስት ተወካይ እና በቄስ ፊት ቆመው ቃል የገቡላቸው፡፡ ከባድ ካራት ወርቅ፣ አንዳንዶቹም አልማዝ አሰርተው ያጠለቁላቸው ሚስቶች ባለቤቶች ናቸው። ለእኒህ ሚስቶቻቸው የሚመጥን ኑሮ እና መኖሪያ ቤትም ቀልሰውላቸዋል፡፡ ግን ደስተኛ አይመስሉም፡፡
ሽንጣቸውን ገትረው በዛ ምሽት ሲከራከሩ ላያቸው፣ ከደስተኝነታቸው ጋር ያቆራረጣቸው ሴፊኒ ይመስላል፡፡ “ደስተኝነታችንን መልሰህ ስጠን” እያሉ የሚወተውቱት ይመስላሉ፡፡ ምሽቶቻቸው ምሽቱ ገፋ እያለ ሲሄድ ይደውሉላቸዋል ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፡፡ ሴፊኒ እንደዛ ብለው ከሚያስቡ የዋሆች አንዱ ነው፡፡ ምክር እና ቁጣቸውን በታላቅ ይቅርታ መሃል በሃል ላይ እያቋረጠ “አይመሽባችሁም?” እያለ ይጠይቃቸዋል። ሚስቶቻቸው የባሎቻቸው ማምሸትን ከእሱ ጋር አያይዘው እንዳይወቅሱት ፈርቶ አይደለም፡፡ እሱ ገና ግድ እንዲሰጠው ሆኖ ገዝፎ አልታየውም፡፡ ሁል ጊዜ ግዱ አጠገቡ ስላለው ሰው ነው፡፡ ቅርቡ ለሚያገኛቸው ማንኛይቱም አይነት ሴት ግድ መስጠቱ… በቀላሉ ወደ ፍቅር ግንኙነት ተለውጦበት ያገኘዋል፤ እንጂ ሌሎቹ እንደሚያስቡት ተራ አህያ አይደለም፡፡ ማንኛውም አይነት አመድ ላይ ካገኛት ሴት ጋር ከመንደባለል ራሱን መቆጣጠር የማይችል ሆኖ አይደለም፡፡
“ስለኛ ተውና ስለ ራስህ አስብ… አካሄድህ ጥሩ አልመሰለንም፡፡ አስበንልህ ነው፡፡ በሽታ ላይ ትወድቅብናለህ፡፡ መገኘት በሌለብህ ቦታ ከማትመጥንህ አይነት ሴት ጋር ስትሆን … በስተ መጨረሻ የጉዳቱ ሰለባ ዞሮ ዞሮ አንተው ራስህ ነህ እያልንህ ነው፡፡ አሁን አሳሳቢው ጉዳይ የእኛ ሳይሆን የአንተ ነው…።” እያሉ ይመልሱለታል፡፡ እሱ የሚያስበው ግን የእውነት ስለነሱ ነው፡፡ መሆኑን ደግሞ እንደ ውለታ ቆጥሮ አያከማችም፡፡ “እንዲህ አድርጌልህ” ለማለት አቅደው የእርዳታ እጅ ከሚዘረጉት መሃል አይደለም፡፡ እንዳይደለ ራሱም ያወቀ አይመስልም፡፡ እነሱ ግን ያውቃሉ፤ ይበሳጩበታል፡፡
ግን ሴፊኒ የእነሱን ሚስቶች ሲያማግጥ አግኝተውት አያውቁም፡፡ ሚስቶቻቸውን እንደ እናቱ ነው የሚያከብራቸው፡፡ እናቶቹ ናቸው፡፡ እናት፣ ማህፀን እንጂ ወሲብን የሚያሳስብ ማንነት የላትም፡፡ ሲፊኒ ፈፅሞ እንደሚወራበት አህያ ብቻ አይደለም፡፡ እንደዛ ተደርጎ እንዲሳል ከቀደመ እድሜ ጀምሮ.ከእሱ እኩል ጎርምሶ ያደገ ትርክት ሲሰራበት ኖሯል፡፡ ስራው የአንድ ባለቤት አሻራ ብቻ ደግሞ ያለው አይደለም፡፡ ሁሉም አስተዋፅኦ አድርገውበታል፡፡ ሁሉም፣ አሁን በዙሪያው፣ በዛ ምሽት እንደከበቡት ጓደኞቹ… በተናጠል ብዙ ቢሆኑም… አንድ የተጠቀለለ አመለካከት አሰባስበው የሚያራምዱ ናቸው፡፡ ሴፊኒ ከሚያራምዱት ጋር መራመድ ነው ያቃተው፡፡ እሱ የእነሱን ሚስቶች አይፈልግም፡፡ ሚስቶቹም ቢሆኑ፣ ባሎቻቸው የሚግሯቸውን አዘውትረው ስለሚሰሙ፣ ሴፊኒ የያዘውን ህይወት አምርረው ይነቅፋሉ፡፡ አዲስ ያከናወነውን ገድል ግን ከባሎቻቸው ሳይሰሙ ውለው ማደር አይችሉም፡፡ ሳይነግሯቸው ከቀሩ ይቀየማሉ፡፡ ባሎቻቸውም፣ የራሳቸውን የህይወት ከፍታ የሚለኩት ትቢያ ወርዶ ዘውትር ሲርመጠመጥ ከሚገኘው የትምህርት ቤት አብሮ አደጋቸው ጋር በማነፃፀር ብቻ ስለሆነ… የሰይፉን የህይወት ገድል ይከታተላሉ፡፡
“ደግሞ ከአማኑኤል ሆስፒታል አገግማ ከወጣች እብድ ጋር ግንኙነት ጀምሯል አሉ…” ይላሉ፣ የሚስቶቻቸውን የወሬ ጉጉት እንደ ክራር ሲቃኙ፡፡  “ደህና ነገር እኮ አይታየውም… ደህና የሆኑ ነገሮችም ፈፅሞ ወደ እሱ አያዩም… መረገም አይደለም እንዴ ይሄ ታዲያ? የጎዳና ተዳዳሪም ሞክሯል፡፡ … ለማኝ ወይንም የስጋ ደዌ በሽተኛ የሆነች ኮረዳ ብቻ ትቀረዋለች ብዬ ልከራከር ነበር… ግን የስጋ ደዌ በሽታ በከተማ ስለጠፋ አስይዤ ለመከራከር አይመችም…”
***
ሴፊኒ የተግባር ሰው ነው፡፡ ተግባሩ ግን የሚጀምረው ከየት ነው? ከእውነተኛ ማንነቱ ወይንስ በሚቀኑበት ቆርጦ ቀጥል ጓደኞቹ ከተወራበት? ከአህይነቱ ወይንስ ከአማልክትነቱ? ይሄንን የጥያቁ አቅጣጫ ማንም ማንሳት የፈለገ አልነበረም፡፡
ሲወዳቸው ያዝንላቸዋል፡፡ ዚያዝንላቸው ቀርቦ ያናግራቸዋል፡፡ ካናገራቸው በኋላ ይረዳቸዋል፡፡ ሲረዳቸው ያቅፉታል ወይንም ያቅፋቸዋል፡፡ ወደ አልጋ እንደ ጎተታቸው የሚወራበት ከዛ በኋላ ነው፡፡ እሱም ባይጎትታቸው በራሳቸው ፍላጎት እሱን መጎተታቸው አይቀርም፡፡
አብዝቶ መናገር አይችልም፡፡ ወይንስ የሚያውቀው ተግባራዊ ንግግር ልብስ ባልተዳበለው ገላ በአግድም ተንጋሎ የሚከናወን ብቻ ነው? ወይንስ እንደ ማግኔት ነው ቲዎሪው የሚሰራው? በስጋ እና በስጋ መሃል ያለው የተፈጥሮ ስበት? ሲቀርባቸው ይጣበቁበታል፡፡
ጓደኞቹ ስላላሰቡት፣ ወይንም በዛ አቅጣጫ የማሰብ አቅም ስላላደረጁ እንጂ… አንገታቸውን አዙረው መጠየቅ ቢችሉ … ለምን እነዛ ሁሉ ሴቶች በሴፊኒ የተግባር ተሞክሮ ስር ያለፉ… የዝቅተኛ የመደብ ክፍል የሆኑ ሴቶች… የእሱ ስም ሲነሳ አንድም ክፉ ቃል ስለተነሳው ስም መናገር ያቅታቸዋል?
ግን እነዛ አብሮ አደግ ጓደኞቹ ይህንን ጥያቄ ጠይቀው ወደ ትክክለኛ መልስ ሊደርሱ ይችላሉ? አይችሉም፡፡ እነሱ የሚሰሙት ወሬ ከአንድ ጎን ምዘና የሚመነጨውን አሉባልታ እና ፍረጃ ብቻ ነው፡፡
እነዛ… ጭቃ ረጋጭ፣ ብሎኬት አምራች፣ የቤት ሰራተኛ፣ የፓርኪንግ ቲኬት ቆራጭ፣ ባህላዊ ንቅሳታም፣ ያልተማሩ፣ እንግሊዘኛ የማይገባቸው፣ መፅሐፍ የማንበቢያ ጊዜ የሌላቸው፣ እዕዮተ አለማዊ እይታቸው የማይታወቅ ወይንም የሌላቸው፣ እውቀታቸው በሚሰሙት የሬዲዮ ጣቢያ እና በስልካቸው ላይ ጭነው ደጋግመው በሚሰሙት ሙዚቃ የተወሰነ፣ ከድህነት ንፍቀ ክበብ ባሻገር ምንም ማንነት የሌላቸው…
እነዚህ ሴቶች ስለ ሴፌኒ የሚሰጡት ምስክርነት አብሮ አደግ  ጓደኞቹ ከሚሰጡት ጋር በምንም በኩል ሊገጥም … ዝንተ ዓለም አይችልም፡፡ የሊሴ ገብረማሪያሞቹ በየት በኩል ያድምጡት?
እንደ አህያ ስጋ አልጋውን ትቶ አመድ ላይ የተንከባለለው ሰውዬ፣ በአመዳሞቹ ግዛት ደግሞ ሌላ ትርጓሜ እንዳለው ማን በነገራቸው፡፡
ለምሳሌ፣ እማዋይሽ የምትባል፣  ጠንካራ ጠረኗ ዘወትር ከአጠገቧ የማይጠፋ፣ ደምደሳም ኮረዳ፡- “ጋሽ ሰይፉ እኮ ልቤ ዝም ባለ ሰዐት ብቻ የማስታውሰው የእንጉርጉሮ መዝሙሬ ነው፡፡ … ሰው አይደለም ፈፅሞ ሰው አይደለም እሱ፡፡ እሱን ብቻ አየሁኝ። የሰው ፍጡሮች ላይ ፈፅሜ ተስፋ ቆርጬ ጨካኝ እንዳልሆን እንደ ማታረቂያ ያስቀመጠልኝ ስጋ ለባሽ ምልክት ነው” ትላለች፡፡ በቅርቡ ቡና አፍልታ መሸጥ የጀመረች፣ ከዛ ቀደም ሲል ከሴተኛ አዳሪ እስከ ቤት ሰራተኛ ያልሆነችው የሌላት ሴት ናት፡፡
የሰይፉ ፍቅር በጭኖቿ መሃል ብቻ እናዳልገባ ጆሮ ሰጥቶ የሰማት ይጠረጥራል። ወሲብ ብቻ አይመስልም መንፈሳዊም ጎን አለው፡፡ ምን እንዳደረጋቸው ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ሰይፉ ራሱ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ተግባር ብቻ ነው፡፡ ከድሮውንም ጀምሮ ተግባር ብቻ ነው። ተግባሩ ደግሞ ወደ ሰዎች ነበር፡፡ ነበር ምን ያደርጋል፡፡ ከሰዎች መሃል የእይታ መደባቸውን ከፍለው፣ ራሳቸውን የተለዩ አድርገው የቆጠሩ የሰይፉን ተግባር የአህያ አደረጉት፡፡ ከአህያም በአንድ የአካል ክፍሉ ላይ ተመስርተው፣ ያንን የአካል ክፍሉን  አልፎ አልፎ፣ ወቅት ጠብቆ በሚገለገልበት አኩዋሁዋን ላይ ተመርኩዘው፡፡  መሰረታዊውን የእንስሳውን ተልዕኮ ጥለው  እነሱ የሚፈልጉትን ብቻ ደግሞ በምትኩ አንጠልጥለው፡፡
በመሰረቱ አህያ… እነሱ ከልጅነት ተመግበው ያደጉትን እህል ከወፍጮ ቤት እስከ እናታቸው ጓዳ ሲያመላልስ የኖረ ነው። ግን ይሄንን ውለታውን ልብ አልሉትም። አባታቸው ይነዳ በነበረው መኪና እና ሌላ ቅራቅንቦ ላይ ነበር ትኩረታቸው። አህያው ተሸክሞ ያመጣውን ጤፍ ማን ዘርቶ እንዳበቀለው ፈፅሞ የማሰብ አቅም የላቸውም፡፡ አህው የተሸከመውን እህል ሰራተኛ እንጀራ አድርጋ ስትጋግርላቸው እና ሲመገቡ እንደነበርም ትዝ አይላቸውም። እክኒያቱም ያ ለእነሱ ተራ ነገር ነው፡፡ በስጦታ ወረቀት ተጠቅልሎ ስላልመጣ፣ ዱቄቱንም ሆነ እንጀራውን ወይንም ከወፍጮ ቤት ተሸክሞ ያመጣውን እንስሳ አያስታውሱትም፡፡
ዋናዎቹን ነገሮች እንደ ድጋፍ ሰጪ አድርገው መቁጠራቸው ነው ዋና ስህተታቸው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ፣ ተራውን ነገር እንደ አልፋ እና ኦሜጋ ለጥጠው እንደ ምድር እና ሰማ መቁጠራቸው፡፡ ሰይፉ ይህንን ስህተት አልሰራም፡፡
***
ሰይፉ የያዘው አካሄድ ስላልጣማቸው ሊሆን ይችላል “ተፈፀመ” የሚል ቅፅል ስም ያወጡለት፡፡ ቅፅል ስም እንደ መደበኛው፣ ወላጎች ለሚወዱት ልጃቸው እንደሚያወጡት ስም የመልካም ተስፋ እና የምኞት መግለጫ አይደለም፡፡ ከፍርሃት አቅጣጫ ወይንም ከጥላቻ አዝማሚያ የሚነሳ ነው፡፡ እንደ አስካሪ መጠጥ የሚጠነሰስ ነው፡፡  አንዳች ባህሪ ወይንም ተሞክሮ በተሰያሚው ላይ ሲስተዋል ሰያሚው ስም ለማውጣት ይመጣል፡፡ የወጣውን ብዙሃኑ ካፀደቀው ይጣበቀወበታል፤ እድሜ ልኩንም ሊያላቅቀው አይችልም፡፡
ቅፅል ስም የመደብ ባህሪን ገላጭ ነው። “በዚህ አካሄድህ ከቀጠልክ ያቅልሃል” ብለው የፈሩ ናቸው ቅፅ ስሚን የጠነሰሱት። ያለቀላቸው ግን ስም አውጪዎቹ ነበሩ። አተረጓጎሙ በሌላ ጎን ጎልቶ ቢወጣም፣ በመደብ ጭቆና ቋንቋ ተብራርቶ ከታየ ሰይፉ አብዮተኛ ነው፡፡ “ተፈፀመ” ሳይሆን ይሄኔ የስሙ ትርጉም “ፍፁም” ይሆናል፡፡
***
ማንም ባለበት የሚቀጥል የለም፡፡ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ እነዛ ጭቃ ረጋጭ እና ሰው እንዳያያቸው “ጓዳ ተደበቂ” የሚባሉ ልጃገረዶች፣ ቀስ በቀስ በመለወጥ ላይ ናቸው፡፡ ሰይፉም ምንም አልሆነም፡፡ የሰይፉ አብሮ አደጎች ብስጭት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
ቀስ በቀስ ጓዳ እንጀራ ትጋግር የነበረችዋ ልጅ… ትምህርቷን ጨርሳ ስራ ትይዛለች። ራሷን የማስተዳደሪያ አቅም ታገኛለች። እዚህ ላይ ሁለት መስቀለኛ ማቋረጫ አለ፡፡ አንደኛው የመጣችበትን መንገድ የምታስታውስበት እና በዛ የመለወጥ ጎዳና ላይ ያሉት ሁሉ አመድ እና ትቢያ አለመሆናቸውን የምታስተምርበት አማራጭ ነው፡፡ ሌላኛው ግን፣ የመጣችበትን ጠልታ፣ ስሟን ከማንነቷ ጋር ክዳ… የሊሴ እና የናዝሬት እስኩል ተማሪዎች የሚሆኑትን እየተከታተለች በማጥናት እነሱን ለመሆን መጋጋጥ እና መጣር ነው፡፡ ሙከራው ግን መቋጫ የለውም፡፡ “ሆኜ ጨረስኩ” ሲባል ሊሆን ይችላል ስቃዩ በአዲስ መልክ የሚያገረሸው፡፡ …የሰይፉ የትምህርት ቤት አብሮ አደጎች እና ሚስቶቻቸው የገቡበት አይነት እርካታ የሌለው ስቃይ ጭንቀት እና የማስመሰል ህይወት፡፡
***
የሰይፉ ፍፃሜ ጓደኞቹ እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ እንደ አማልዕክት ሆኖ ቀጠለ። በእሱ እጅ ወይንም በእሱ አልጋ ላይ የተጋደሙ ሴቶች አመዳቸውን እያራገፉ ተስፋ ወዳለው ህይወት ማደግ ቀጠሉ። ተስፋ አገኙ፡፡ ወደፊት ህይወታቸውን የሚለውጡበት ነጥብ ላይ ሲደርሱ መስቀለኛው አማራጭ ይደቀንባቸዋል። ሰይፉ ያላቸው ይሄኔ ትዝ ይላቸዋል፡፡ ያኔ መምረጥ ያለባቸው “ድሮ የነበሩትን ወደፊትም ሳይረሱ አንዲቀጥሉ ብቻ” መሆኑን ደጋግሞ ነግሮአቸዋል፡፡ በነብሳቸው ላይ ንቅሳት ሆኖ ሳይደበዝ አብሮአቸው እንዲከርም በማድረጊያው የሴፌኒ የተሰጥኦ መንገድ፡፡ በፍቅር መንገድ፡፡ ተምኔታዊውን የህልም ፍቅር ሳይሆን ተጨባጩን ፍቅር፡፡
***
“እንደ እሱ አመድ ላይ እድሜ ልኩን ተንደባላችሁ ምንም የአዕምሮ ቀውስ ሳይደርስባችሁ ለመቆየት ዝቅተኛ ንቃተ ህሊና እና እሱን የሚስተካከል የኒያንደርታል የአካል ክፍል ያስፈልጋችኋል” ብሎ ባለፈው አንዱ የጥንት ጓደኛው ሲናገር ነበር፡፡
ሁሉም ደስተኛ አይደሉም፡፡ ለምን እንዳልሆኑ መመርመር ሞኝነት ይመስላቸዋል፡፡ “አህያ ሞኝ ነው” ብለው ያምናሉ፡፡ አህያን መሆን አይፈልጉም፡፡ ሁሉም የመጀመሪያ ሚስታቸውን በሁለተኛ ለውጠዋል፡፡ አሁንም ሲያመሹ፣ ለምን አዲሷ ሚስታቸው ስልክ እንደማትደውልላቸው ሴፊኒ አብሮአቸው ካለ ይጠይቃቸዋል፡፡ አሁንም ቀጥተኛ መልስ አይሰጡትም፡፡
“ሲጀመር… ሚስት አግብቶ ከማያውቅ ሰው ምክር አንቀበልም… ኖሮ የማያውቅ ሰው የኑሮ ዘዴ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሊያስተምር ይችልም” ይሉታል፤ በጉራማይሌ የፈረንሳይኛ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ድብልቅ፡፡
“እስቲ ዛሬ ለለውጥ አይታችሁ የማታውቁት አለም ወስጄ ሌላውን የህይወት ገፅታ ላስጎብኛችሁ” ይላቸዋል፡፡
“ወይ ጠላ ቤት አልያም አረቄ ቤት ነው ያንተ ግብዣ… ከዛ አያልፍም” ብለው በብሽቀታቸው ይቀጥላሉ፡፡


Read 1021 times