Sunday, 22 August 2021 13:07

የሠዓሊው የሕይወት ፈለግ በዳሰሳ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(0 votes)

 መነሻ
የአንዳንድ ሰዎች ታሪክ እንደ ትኩስ ወለላ ማር ለልብ ይጣፍጣል።  አጥንትን ያነቃቃል። ረቂቁን የሕይወታቸውን ፈለግ ብንከተለው የእውነት፣ የእውቀት ጸዳላችን ይበልጥ ይበራል። “እግረ-ነፍሳቸው” ከአጽናፍ የራቀ  ነው። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሰዎች አገር በታሪኳ፣ በፍልስፍናዋ፣ በጥበቧ፣ ሌጣ ሆና እንዳትቀር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል ለማለት ያስደፍራል። በአገራችን ለሠዓሊያን እምብዛም ክብር አይሰጣቸውም፤ ዘመን ተጭኗቸው ዝም ብለው ኖረው፣ ዝም ብለው ወደ ዘላለማዊ ዕረፍታቸው ይንደረደራሉ፡፡ ዝምታን መስማት የማን ፋንታ ይሆን? አላውቅም!
ሰሞኑን አንድ የሕይወት ታሪክ አነበብኩ። ታሪኩ የሠዓሊ ዘሪሁን የትምጌታ ነው። የተጻፈው በእሰየ ገብረ መድኅን ሲሆን መጽሐፉ በሁለት መቶ ሰማኒያ አራት ገጾች የተቀነበበና በአራት ክፍሎች የተከፋፋለ ነው። የሽፋን ምስሉ ለሠዓሊ የሕይወት ታሪክ የሚሆን ነው። አልፎ አልፎ ከተደጋገሙት ቃላት በስተቀር ጥንቅቅ ያለ አርትዖት እንደተደረገበት ግልጽ ነው። “የመጨረሻው ቅዱስ ሰውም ስድነት አያጣውም!” እንዲል አዳም ረታ፣ ጸሐፊው ሁለቱንም ዘሪሁንን አሳይተውናል። [ተነጫናጩን እንዲሁም እንስፍስፉን] ሠዓሊው በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተባሉ ናቸው። እንደ ሠዓሊና እንደ ተራማጅ ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። ታሪካቸው ተሰንዶ በዚህ መልክ በማንበቤ እድለኝነት ተሰምቶኛል።
ውልደት፣ ማንነትና ልጅነት
ሠዓሊው ዘሪሁን፣ ከአባቱ የትምጌታ በለጠና ከእናቱ ወይዘሮ የኔነሽ መኮንን፣ ሐምሌ 21 ቀን 1932 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ውስጥ ወደዚህች ምድር ተቀላቀለ፡፡ “በልጅነቱ አባቱ ከደብረ ጽጌ እያመላለሱት አዲስ አበባ አባ ኮራን ሰፈር መኖር የጀመሩትን እናቱንና አዲስ አበባ የተወለዱትን ወንድሞቹን ይጠይቅ ነበር። በዚህ ጊዜ የተፈጠረው ኹኔታ ይመስላል፣ ዉሎ አድሮ የዘሪሁን የማንነት ጥያቄ ፍልሚያ ቅርጽ እንዲይዝ የረዳው (ዘኒ ከማሁ) “ዘሪሁን ሠዓሊ ለመኾንና ሠዓሊ ለመባል ይናፍቅ ነበረ" (ገጽ 37) አስራሁለተኛ ክፍልን ሲጨርስ አጎቱ ሥዕል ትምህርት ቤት ወስዶ አስገባው። “በወቅቱ አራት ኪሎ መደበኛ የሥነ-ሥዕል ትምህርት በቀሰሙ ሠዓሊያን የደመቀች ነበረች” (ዘኒ ከማሁ) ይህ ሁኔታ ዘሪሁንን ይበልጥ ሥዕልን እንዲገፋበት አደረገው፤ ሥዕልና ዘሪሁን ነፍስና ሥጋ ሆኑ፡፡
ሕይወት እንደ መምህር
ተጽዕኖ ስንል መነቃቃት የፈጠረበትን ለማለት ነው። ተጽዕኖና ሥነ-ጥበብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ፍጹም እከሌን መምሰል ለጥበብ ሰው ውርደት ነው። ግን በተጽዕኖ ውስጥ የራስን ቀለም ማሳየት ጀብድ ነው (ለእኔ)፡፡ የዓለም ታላላቅ የጥበብ ሰዎች ተጽዕኖ ያሳደሩባቸው ሰዎች አሉ፤ ለምሳሌ የሊባኖሱ ባለቅኔና ሠዓሊ ጅብራን ካሊል ጅብራን፣ የብሃኢ እምነት መስራቹ አብዱል በሃ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ይናገራል። ጅብራን ካሊል ጅብራን እንዲህ ሲል ስለ አብዱል በሃ ተናግሮ ነበር፡- “እሱ ታላቅ ነው! በነፍሱ ውስጥ ጥልቅ ዓለም አለ!” የራስን ነፍስ ሲያነቡ የሌላውንም ማንበብ ነው። ተጽዕኖ ማለት ስለዛች ነፍስ መሳሳት ያችን ነፍስ በራስ ቀለም ማስቀጠል፣ ዘላለማዊ እንድትሆን መሰንደቅ ነው።  የጅማው ባለቅኔ ከዲር ሰተቴም ስለ አያሙሌ እንዲህ ይላል፡- “ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያሙሌ) አንድ ሰው ነው። ልበ-ስስ ልበ-ብርሃን ባለ ቅኔ፣ የተገፋ ልባም ገጣሚ ወዳጄ ወሎየው፣ የካህሊል መንገድ ልክፍተኛ!......” ይህ ነው! አንደኛው ባለቅኔ አንደኛውን ያነቃው ነበር ወይም በነፍስ ይቀናኑ ነበር (እንደ እርሱ ብሆን)፤ ተጽዕኖ ማለት ይህ አይደል?
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጥበብን ለጥበበኛ የሚል መርህ ዓለም ተከትላለች፤ ይህ መሆኑ ሥነ-ጥበብ ወደ አዲስ ዐውድ ፊቷን እንድታዞር አድርጓታል፤ ወደ ድህረ - ዘመናዊነት (Postmodernism) ከዚህ በፊት ሥነ ጥበብን ለአንዳች ማህበረሰባዊ ፋይዳ እናውል፥ የሚል መርህ ነበር፤ ድህረ ዘመናዊነት ግን ጥበብ ራሷን እንድትችልና የፈጣሪዋን ነጻነት እንድታከብር የሚደግፍ ነው። ይህንን ይከተሉ የነበሩት ደግሞ በሥነ-ሥዕል ፒካሶና  ቫንጎ ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ ሠዓሊ እስክንድር ቦጎስያን (የዘሪሁን የቅርብ ወዳጅ) “እስካሁን ከፒካሶ ጋር እየታገልኩ ነው” ይላል። (“ሰው” ኃይለ ጊዮርጊስ ማሞ፤ ገጽ 432) እንዲህ ነው። ትስስሩ እስክንድር ላይ ፒካሶ ተጽዕኖ አሳደረበት፤ እስክንድር ዘሪሁን ላይ (ሠዓሊ መርዕድ ወርቁ ቅጽል ስሙ ፒካሶ ነበር፤ ድሬድዋ ካፈራቻቸው እንቁ ሠዓሊያን አንዱ ነው። መርዕድ የድህረ ዘመናዊ ሠዓሊያን ተጽዕኖው ቀላል አልነበረም) “ዘሪሁን ከሚያደንቃቸው መምህራን ብዙ ነገር ቀስሟል። ከሐንሰን ሙያን ማክበርን፣ ታታሪነትን፣ ጠንካራ ሰራተኝነትን፤ ከገብረ ክርስቶስ ጠቅላላ የፈጠራ ነጻነትንና ድፍረትን ፣ በቀለም ሃይል ምስልን አሸበራርቆ መፍጠርን  የተማረ ሲሆን ከእስክንድር ደግሞ ለልማዳዊ ኪነ-ጥበባትና ለጃዝ ሙዚቃ ፍቅር ማዳበርንና ሥዕል ማለምን ተምሯል።”(ዘኒ ከማሁ)
ኢትዮጵያዊነት
ምንም እንኳ የድህረ ዘመናዊነት ተጽዕኖ ሥዕሎቹ ላይ ቢታዩም፣ በወቅቱ የነበረው የሥነ-አሳሳል ሥነ-ዘዴ ከድህረ ዘመናዊነት ቀርቦ የራቀ ነው።  ስለዚህ ሠዓሊው ዘሪሁን አገራዊ ለዛውን አለቀቀም፤ እንደውም ሥዕሎቹ ሰምና ወርቅ ያላቸው፣ ወደ ጥንቱ የኢትዮጵያ አሳሳል የሚጠጉ ግና የዘመኑ ናቸው። ሠዓሊው ለአገሩ ልዩ ፍቅር አለው፤ ወደ ውጪ አገር የመሄድ እድል ያለው ቢሆንም፣ እንደውም “ኢትዮጵያ ሕዝቧ ሳይሆን መሬቷም ይፈልገኛል”(ገጽ-52) በማለት ተናግሯል። “ራሱን ኢትዮጵያዊም አፍሪካዊም አድርጎ ይቆጥራል። የኢትዮጵያውያንና አፍሪካን ጥበብ ፣ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ አደረጋቸው።” (ዘኒ ከማሁ) በሥዕሎቹ ኢትዮጽያዊና አፍሪቃዊ መንፈስ ሆኖ ቢታይበትም፣ አለማቀፋዊ ፍልስፍናዎችና ርዕዮቶች ይቀነቀኑ ነበር።
የማይነቀነቀውን ዘገር መነቅነቅ...
ያ ትውልድ የሚታገለውን አልተረዳም እንጂ ታጋይ ነበር፤ የአገር ነጻ መውጣት የሕዝብ አርነት በእጅጉ ያሳስበው ነበር፤ ለሕዝብ ነጻነት አንገታቸውን ለስለት አሳልፈው ይሰጡ ነበር፤ በድርሰት (እነ አቤ ጉበኛ፣  በዓሉ ግርማ) በግጥም (እነ ዮሐንስ አድማሱ) ተጠቃሽ ናቸው። ሥነ - ሥዕል ለተሳለበት  ዘመን ጥበባዊ አንደበት ነው። በገሃድም ይገለጥ፣ በረቀቀ መንገድ ይቅረብ የዘመኑን መንፈስ የመቅረጽ ሚና አለው። የሠዓሊውን ፖለቲካዊ አቋም እናይበታለን፤ ርዕዮተ ዓለማዊ ድምጹን እናደምጥበታለን። አንዳንዴም፣ በተለይ ከታላላቅ ተመስጦና አንጽሮት የሚወለዱ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ትንቢታዊነት (Prophetic voice) አይታጣባቸውም (ድምዳሜው የኅያሲ ቴዎድሮስ ገብሬ ነው። እኔ ሥነ-ሥዕል ብለውም እርሱ ሥነ-ጽሑፍ ይለዋል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለሥነ-ሥዕልም ተስማሚ አንጽሮት ነው፤ ብሎ ያምናል።) ሠዓሊ ዘሪሁን ፖለቲካዊ አቋሙ ባይታወቅም፣ ሥነ ጥበብ በሰጠችው ነጻነት፣ ለሕዝብ ነጻነት ይታገል ነበር። “ከ1960ዎቹ ጀምረው በውጪ አገርና በውስጥ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሠዓሊያን ከታጋዮች ጎን መቆማቸው አልቀረም። እነዚያ ህልቆ መሳፍንት የሌላቸው ችግሮችና የችግራቸው መልክ፣ በመልክዓ ምድር፣ በከተማና በፈራረሱ መንደሮች፣ ብጥስጣሽ በለበሱ ገጸ-ባህሪያት ይንጸባረቁ ነበር። የችግሮች ስቃይና መከራ፣ የጎበጠው ጀርባቸው፣ ቀጫጭን አጥንታቸው፣ የታጠፈው አንጀታቸው፣ የደከሙና የጠነዙ፣ ያረጁና ያፈጁ አዛውንቶች ሳይቀሩ ይቀርቡ ነበር።” (ገጽ 118) “የዘሪሁን ትውልድ ሠዓሊያን ከሞላ ጎደል በኅብረተሰብ ጉዳይ ላይ ያተኮሩና ከዚያው የፈለቁ በመሆናቸው፣ እንደ ሌላው የአገሪቱ ታጋይ ምሁር ሁሉ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ይከተሉ እንደ ነበር እያደር ብዙ መረጃዎች ተገኝተዋል።” (ዘኒ ከማሁ)
አሌክስ አብርሃም "ዶክተር አሸብር እና ሌሎችም" በሚለው አጫጭር ልቦለዶቹ ላይ ያሬድ በተሰኘ ገጸ ባህሪ፣ የሥነ ሥዕልን ፋይዳ እንዲህ ይተነትናል፡- “የሥዕልም ይሁን የሌላ ኪነ-ጥበባዊ ፈጠራ አላማው ሰዎችን በሰሩት መንገድ ላይ ሲረግጡ እንዲኖሩ ጫማ ማቀበል አይደለም፤ አዳዲስ ጫካዎችን መንጥሮ አዲስ መንገድ መፍጠር ነው። ነገሮችን ከተለየ አቅጣጫ ማሳየት ነው። አዲስ የሕይወት ቅመም፣ አዲስ ጠብ የሚል ፋይዳ ያለው ሕይወት..”
የሥዕሉ ሰምና ወርቅ
ድህረ-ዘመናዊ ሠዓሊያን ነባሩን የሥነ አሳሳል ፍልስፍና ወደ ጎን ትተው ረቂቅ ጉዳዮችን መግለጥ ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል። ድህረ ዘመናዊያን፤ ነገሮችን እንዳለ ገልብጦ መሳል ያረጀና ያፈጀ ዘዴ ነው፤ ይላሉ። ፒካሶ የራሱ የሆነ የሥነ-አሳሳል ዘዴ ከጓደኛው ጋራ በመሆን ፈጥሯል። ኩቢዝም  ይባላል። ኩቢዝም (cubism) በውስጡ ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም መጠነኛ Abstract (ሥውር አስተኔ) ጥበብ የሚንጸባረቅበት የሥነ-ሥዕል መንገድ ነው። በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ሥነ-ሥዕሎች ለአንዳንዶች ያጥወለውላቸዋል። አንዳንዶች ውበት ነው፤ ይላሉ፡፡ ሌሊሳ ግርማ (ደራሲና አሰላሳይ) እንዲህ ይላል፡- "የቫንጐን starry night በሁለት ጽንፍ የሚረዱ ሃሳባዊያን አሉ፡፡ አንዳንዶች አስተማማኝነት የሌለው፣ እንደ አዙሪት እይታን የሚያጥወለውል እይታ ነው ይላሉ:: ሌሎች ደግሞ በጨለማ የተዜመ፣ ልብን የሚያሳዝን ግን መንፈስን የሚያክም ውበት ነው ይላሉ፡፡ አሉም አላሉም ነጥቡ ወዲህ ነው፡፡ ውበት ያከራክር ይሆናል እንጂ መካድ አይቻልም፡፡" ይህ የድህረ ዘመናዊያን ሠዓሊያን አመለካከት በኢትዮጵያ ዘመናይ ሠዓሊዎች ምን ያህል ጥላውን እንዳጠላ ተመልክተናል። ሠዓሊው ዘሪሁን ግን እንዲህ ይላል፡- "ማንኛውም ሰው የሥዕሎቼን ልዩ ቀለምና አቀባብ ተመልክቶ ፍጹም ኢትዮጵያዊነታቸውን ይገነዘባል።" (አዲስ ልሳን ጥር 25፣ 1987) ሆኖም ሠዓሊው እጅግ ዘመናይም እንደሆነ ይናገራል። “ዘመናዊን የሥነ ጥበብ ውጤት ለማድነቅም ኾነ ላለማድነቅ ምንም እንኳን የጥበብ ሰው መኾን ባይሻም ከዘመናዊ ሕይወት ጋር መተዋወቅና መላመድ ይጠይቃል” (አስኳል፣ ግንቦት 28፣ 1993) ሆኖም እኛ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር ለመቀበልና ስውር አስተኔ የሆኑ ነገሮችን ለመረዳት እንደሚያዳግተን፣ ራሱ ሠዓሊው “የኛ ሰው ጥርስና ዐይን ብሎም ጆሮ ካላየ ሥዕል ያየ አይመስለውም።" (ኔሽን፣ ግንቦት 27 1997) ሲል ተናግሯል፡፡ "ሆኖም ሠዓሊው ዘሪሁን ግን በፈጠራ ምናቡና በሕልሙ እየተመራ በፈጠራ ቅኝት ጊዜ የሚከሰቱትን ከጥንት ኪነ ጥበባት፣ ከመንፈሳዊና ልማዳዊው አሰራር ጋር በማዋሐድ ከፍተኛ የፈጠራ ፍትወቱን፣ አርያሙን ለማግኘት የተለየ ተሠጥኦ ሲኖረው፣ ለኪነ ጥበቡ የመጨረሻ እስትንፋስ ለመስጠት ይህ ነው የማይባል ጊዜና ሃይል ያጠፋል” ሲሉ  ጸሐፊው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ሠዓሊው በሚስላቸው ሥዕሎች እጅጉን ረቂቅ፣ ለውበት የቀረቡ፣ ከተፈጥሮ የተቋረቡ፣ ሠምና ወርቅ ያላቸው ዘመን የማይክዳቸው እውነትና ዕንባ እንዳዘሉ እሙን ነው። ስለዚህ የአሳሳል ሥነ ዘዴውን ሳናደንቅ ማለፍ ንፉጉነት ይሆናል።
የትዳር ሕይወት (እንደ ማጠቃለያ)
ሠዓሊው በጥበብ ዘርፍ ብቻም ሳይሆን በትዳሩም ደስተኛ ነበር፡፡ ከትዳር አጋሩ ከእታገኘሁ ወልዴ በሁለት ፊደላት የሚጠሩትን ልጆቹን አፍርቷል (ኢት፣ ጮራ፣ ጸጋ፣ ጤና)፡፡ ሚስታቸውም ለሥነ ሥዕል ያላት ፍቅርና ለሠዓሊው ያላት ክብርና ድጋፍ (ሞዴል እስከ መሆን) እጅጉን ያስደንቃል። የህይወት ታሪክ ጸሐፊውም ህያው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፡- “እታገኝ የዘሪሁን ባለቤት ብቻ ሳትሆን ያዘቦት ቀን የቅርብ አማካሪው ናት” (ገጽ-129) ይላሉ።
በፈጠራ፣ በትጋት፣ በውጣ ውረድ፣ በርምደት የተሞላውን የሠዓሊውን የህይወት ታሪክ ማንበብ በህይወታችን ላይ አዲስ እውቀት፣ ግንዛቤና ተመክሮ ስለሚጨምርልን  ልናነበው ይገባል።
መልካም ሳምንት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 250 times