Sunday, 22 August 2021 13:04

ጥበብና የጠየመች ሐዘን

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

  …በመጨረሻ የጥበባት ሁሉ ቅመም ሐዘን ነች ወደሚል መደምደሚያ ለመድረስ ተቃርቤያለሁ፡፡ በእርግጥስ በሰው ልጆች የጥበብ መዓድ ላይ ለሺህና ለመቶ ዓመታት የሚሰለጥኑት ዕፁብ ድንቅ ጥበባት የሚቀሰሙት ከመቃብር አፋፍ፣ ከብቸኝነት ገደል ጫፍ፣ ከወናነት ክቡድ ጥላ ማጥ፣ ከውድቀት አዘቅት ዘብጥ ሳይሆን ይቀራል? ከሆሜር ድንቅ ስራ ‹‹የትሮይ ጦርነት›› እስከ ዊሊያም ሼክስፒር ግሩም ተውኔቶች እና የራምብራንት አስደማሚ የራስ ምስሎች (self portraits) እንዲሁም የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን እና ደበበ ሰይፉ ነፍስን የሚነዝሩ ምትሀተኛ ግጥሞች ድረስ ጥበብ የምትቀነቀነው የጠየመ ሐዘንን እንደ ምህዋር በመጠቀም ይመስላል፡፡ Neil Straussept የተሰኘ አሜሪካዊ ፀሐፊ ከመስከረም አስራ አንዱ የኒውዮርክ አደጋ ሁለት ቀናት በኋላ በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ በፃፋት መጣጥፉ ‹‹nothing provokes artistic sensibility like grief.›› ብሏል፡፡
ራምብራንት እጅግ የተደነቀ ሆላንዳዊ ሰዓሊ ነው፡፡ ገና ከለጋነት እድሜው ጀምሮ የተሰጠውን መክሊት በመጠቀም የራሱን ምስሎች (self portraits) በብሩሹ እየከተበ ማስቀመጥ ጀመረ፡፡ በእያንዳንዱ የሕይወት ዘመኑ በግንባሩ ላይ የምትታየውን ጥቂት የሽብሽባት ለውጥ በነፍሱ ጥልቅ ስርቻ ከሚካሄደው የማያባራ ፍልሚያ ጋር እያናበበና በሐዘን እያጠየመ ሳለ፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ይህንን ሂደት ከቀጠለበት በኋላ የራሱን ምስሎች ስብጥር እስከተሸከሙት ጠጣር የሕይወት አስተውሎት ለእይታ አበቃቸው፡፡ ይህንን ከተመለከተ በኋላ ይመስላል ዓለም በሙሉ ያደነቀው እስፓኛዊው የቅብ ሰው ፓብሎ ፒካሶ፣  እሱም በራሱ መንገድ ‹‹ሁላችንም [ሰዓሊያን] መሆን የምንፈልገው ልክ እንደ ራምብራንት ነው›› ብሎ ያጀገነው። የራሱም የፒካሶ ‹‹Guernica›› የተሰኘው ሐዘን የተሸከመ የስዕል ስራው የተጠነሰሰው በእስፓኝ አሰቃቂ የእርስበእርስ ጦርነት ጊዜያት ነበር፡፡ እንግሊዛዊው የተውኔት ሰው ዊሊያም ሼክስፒርም ቢሆን የተወደዱለትን የመድረክ ስራዎች የጻፈው የልጁ ሞት ከፈጠረበት ጥልቅ ሐዘን በኋላ እንደሆነ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡
የግጥምና የቅላፄ ውህድ የሆነው ሙዚቃ ይሉት የጥበብ ምትሃት ግን የሆነ የተለየ አቅም አለው፡፡ ሆኖም በእኔ ሙዚቃን የማጣጣም አቅም ሙዚቃ ምታዊ ስልቷ (Rhythm) እጅግ እየፈጠነ የድምፁም ከፍታ እያደገ ሲሄድ ለዛዋ በዛው መጠን ሲኮሰምን አያለሁ፡፡ ሙዚቃ እንደ መደባበስ፣ በስሱ እንደ መሳም፣ የሚፋጅ ትንሽ አንገት ስር እንደ መተንፈስ ቅመራዋ ሁሉ ለልከኝነት (perfection) በተጠጋ ምጣኔ ሲሆን ታስደንቀኛለች።
የትኛውም የጥበብ ስራ ምርጥ ይሆን ዘንድ ካስፈለገ በውስጡ የግድ የጠየመ ሐዘንን መሸከም ይኖርበታል፡፡ የጠየመች ሐዘን የጥበባት ሁሉ ቅመም እንደሆነች አትስቱትም መቼስ… የምትወዷቸውን ሙዚቃዎች ስትሰሙ ከመንጋው ጋር ሆናችሁ እንኳን ብቻችሁን የሆናችሁ ያህል ብይተውርና እንዲሰማችሁ ያደርጓችኋል፡፡ ሙዚቃ ልሳኗ ብዙ ነው፡፡ የልጃገረዷ መልስ ያላገኘ ናፍቆት፣ የጉብሉ ድብቅ ፍቅር፣ ባሏ የሞተባት ሴት እህህታ… የእናት እና ልጅ መፈላለግ… ወዘተ ወዘተ ሁሉ ይሰበክበታል።
ሙዚቃ ወደ ሰዎች ጥልቅ የነፍስ ስርቻ ገብታ ንዝረትን በመፍጠር የሚስተካከላት የለም፡፡ ይህን ግዙፍ አቅም ያዳበረችው ከጠየመ ሐዘን ጋር ባላት ጥብቅ ትስስር ይሆን? ሊሆን ይችላል፡፡ ኦስካር ዋይልድ እንዲህ ይላል፡- ‹‹one thing is dead in each of us. That dead thing is hope.›› እውነት ነው፡፡ ሆኖም እኔ ይህን የጽልመት መጋረጃ ሰብሬ ስለ ዓለም ጥቂት ፈገግ እንድል የምታደርገኝ ሙዚቃ ብቻ ነች፡፡
ሙዚቃ… ጥልቅ የነፍስ እርግብግቢት፣ የትንፋሽ ውልብታ፣ ሙዚቃ… ድቅል የስሜት ውል፣ የቃልና የፊደል ሽልምልም ፈትል፣ ሹክሹክታ፣ ውልብታ… ሙዚቃ… ስሜትና ብስለት ባለበት ሁሉ የትም የምትገኝ እንቁ፣ የሁሉም ጌጥ፣ የሁሉም ፈርጥ፣ የሁሉም ልሳን፣ የሁሉም ቋንቋ… ሙዚቃ…     
 በሰው ልጆች የጥበብ ገበታ ላይ ዘመናትን የሚሻገሩት የጥበብ ስራዎች የሚፈሉት ከሚያባብለውና በሳቅ የተሸፈነው የሕይወት ውጫዊ ወለል በታች በሐዘን ጥላ ስር ይመስላል፡፡ ብዙ ሰው ሀዘንና ደስታ ሁለት የተለያየ ጣዕም ያላቸው  የሕይወት መንታ ገጾች እንደሆኑ አድርጎ ያስባል፡፡ ይሄንን ሚሊዮን ምንትስ ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ ሆኖም ራሱን ችሎ ለብቻ የሚቆም ልሙጥ ሐዘንም ሆነ ደስታ የለም፡፡ ከደስታ ይልቅ ሀዘን በልባችን ላይ ዕድሜዋ ረጅም ነው፡፡
ግን ግን ደስታ ይሉት ስምየለሽ ቅኔ ከጥላነት ያለፈ ሕልውና እንደሌለው እንዴት ላስረዳችሁ ይቻለኛል? ለምሳሌ ከመስተዋት ፊት ለፊት እርቃናችሁን ቆማችኋል እንበል፡፡ በመስታወቱ ውስጥ የሆነ ሞጋጋ የራሳችሁ ምስል አጎንቁሎ ይታያችኋል፡፡ እናም የወረሳችሁትን እናንተነት ረስታችሁ በመስታወት ውስጥ ለምትመለከቱት ምስል ትማረካላችሁ፡፡ ሆኖም ልትጨብጡትም ሆነ ልትዳስሱት የማይቻል እንዲሁ አጥበርባሪ ምስል ይሆንባችኋል፡፡
ደስታ ለእኔ እንዲያ ነው፡፡ ልክ እንደ ዲምላይት የሚብለጨለጭ ሆኖም የማይዘገን የማይጨበጥ… አዕምሮአችሁን በሚገባ ካሰለጠናችሁትና ካበቃችሁት ሳቅ ከስቃይ ምርቅዝ ቁስል በጭካኔ የሚገሸለጥ ገላ እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ የእኛ ሳቅ (ደስታ) ውልደቷ ዞሮ ዞሮ በሌሎች ሰዎች ሐፍረት፣ ውርደት፣ እጦት መሆኑ ነጋሪ አያሻውም። በአንደኛው ውርደት ሌላኛው ሳቅ የሚሸምትበት የሕይወት ቅዝምዝም ቅኔ ግን አይገርምም? ጊዜው ሆኖ ሌሎችም ከእናንተ ስቃይ፣ ሐፍረትና ውርደት ርካሽ የሳቅ ትርፍ የሚያጋብሱበት ቀን ይመጣል፡፡ እንዲያው በሌጣው እናውራ ከተባለ ደስተኛ የመሆን መንጠራወዝ ከሚያንዘፈዝፍ ረሀብ በኋላ ፈንዲሻ በልቶ ለመጥገብ እንደ መሞከር አድካሚ ይሆንብኛል፡፡
ሰው የመሆን መውተርተር ራሱ ሰው በመሆን የተጣለብንን ስቃይ የመቀነስ አታካች ጉዞ አይደለምን? አስቀድሞውኑ እንድትታገላት እንጂ እንዳታሸንፋት ሆና በተሰራች ዓለም በብዙ ታግለህ በመጨረሻ በእጅህ ምንም የለም፡፡ ግን ይሄ የምነግርህ ሀቲት የሚገለጠው ከየትኛውም ሕይወትን መመልከቻ የዋህ መነፅር (perspective) ነፃ ሆኖ ሕይወትን በሌጣው ለሚመለክት ሰው ነው፡፡
ሐዘን ግን ቅመም ነች፡፡ ጥበብን ወደ ዘላለማዊ ማንነት የማሸጋገሪያ ቅመም…ወዳችሁ የምትሰሟቸውን ዘፈኖች አጢኑ። አብዛኞቹ የጠየመ ሐዘን ያጠላባቸው ሆነው ታገኟቸዋላችሁ፡፡ እመኑኝ የትኛውም ሰው ንጉሥ ወይም ቱጃር፣ ወይም ውበቷ የዓለምን ስቃይ  ሁሉ ልታባብል የምትጥር ልዕልት ሁሉም በየዕለቱ በራቸውን ዘግተው ለብቻቸው የሚያለቅሱበት አብይ ጉዳይ አላቸው፡፡ ጥበብ ይህን ክቡድ የብቻነት ዓለም እንደ ጌጥ ጥለት እየፈተለች ትዋብበታለች፡፡
የሰማይና የምድሩ የሚታየው የማይታየው፣ የሚዳሰሰው የማይጨበጠው ሁሉ ጌታ እንደሆነ የምናምንበት ኢየሱስ ራሱ በምድር ላይ በተመላለሰባቸው ጊዜያት ሙሉ ሀዘንተኛ ነበረ፡፡ ነገርየው ከሀብት፣ ከዝና፣ ከውበት፣ ከጌትነትም ይሻገራል፡፡ ይጠልቃል፡፡ ይረቃል፡፡ በሰው ልጆች የኪነጥበባት አድማሳት ላይ ከፍ ብለው የታዩ አስደናቂ ከያንያን እንዲሁ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በሕይወት የሀዘን ባህር ውስጥ ተዘፍቀው አረፋ የሚደፍቁ ነበሩ፡፡ ሚካኤል አንጀሎ፣ ቪትሆቨን፣ ፍራንዛ ካፍካ፣ ቪንሰንት ቫን ጎ፣ አርተር ኬስለር፣ ፍሬድሪክ ኒቼ… ሌሎች ሺዎችን መጥራት ይችላል፡፡  
ማወቅ የሚባል የለም፡፡ ያለው መንቃት ብቻ ነው፡፡ እናም በሕይወት ምህዋር ላይ በንቃት ስትመላለስ ይህን የሲሲፐስ ጥብቅ ቀንበር የመሸከም ግዴታ አለብህ፡፡

Read 908 times