Saturday, 14 August 2021 00:00

የዕምነት ጉዳዮችን በአካዳሚያዊ የትምህርት ስርዓት አላዝቦ በመተርጎምና በመፈተሽ ለማቅረብ የቻለ መፅሐፍ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የመፅሐፉ ርዕስ:- ”ነገረ ድርሰትና የዓለማተ አማንያን ተረኮች"
                                   የገፅ ብዛት:- 253
                                   ፀሐፊው:- ዶ/ር በጎሰው የሽዋስ
                                   የመጽሐፍ ዳሰሳዊ ገምጋሚ:- አለልኝ አሥቻለ (ዶ/ር)


                የመፅሐፉ ርዕስ:- ”ነገረ ድርሰትና የዓለማተ አማንያን ተረኮች"
የገፅ ብዛት:- 253
ፀሐፊው:-  ዶ/ር በጎሰው የሽዋስ
የመጽሐፍ ዳሰሳዊ ገምጋሚ:- አለልኝ አሥቻለ (ዶ/ር)
መግቢያ
መፅሐፉ በሁለት ክፍሎች የቀረበ ሲሆን  በእየአንዳንዱ ክፍል አስር እና አስራ አንድ በጥቅሉ ሃያ አንድ ንዑስ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ ደራሲው የመረጣቸው ሁለት ቁልፍ ይዘቶችን በያዙ ክፍሎች አማካኝነት ለተደራሲያን በግልጽ ለማቅረብ መርጧል::
በመጀመሪያው ክፍል፣ የድርሰትን ምንነትና የተለያዩ የድርሰት ዓይነቶችን በማብራራትና በምሳሌ በማስደገፍ ስላስቀመጠልን፣ እከሌ እንዳለው እከሌ እንዳለው ብቻ በማለት የአንድ ወይም የሁለት ደራሲያን መብቶችን ቁጥር ከፍ አድርጎ፣ ሀሳብ በተለያዩ ምሁራንና ከተለያዩ ምንጮች ፈልቀው በቀጣይ የደራሲያንና ተመራማሪዎች ስራዎች ውስጥ እንዲንፎለፎሉ አድርጎልናል (He has properly maintained discourses of evidentiality and sincerity)፡፡
ደራሲው ስራውን ሲያቀርብ በተለይ በመጀመሪያ የመጽሐፉ ክፍል ከዚህ ቀደም ቀርበው ከነበሩት የምሁራን ስራዎች ውስጥ ያልተካተቱትን በማካተት የበሰለ የአካዳሚክ እውቀት ምንጭ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ በትክክለኛና አማራጭ ምሳሌዎች በማስደገፍና በመተርጎም፣ በሰው ልጆች የጥናትና ምርምር እንዲሁም የተመስጦ ደረጃ ያልተመለሱ ጉዳዮችን በማንሳት ለመመለስ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የዕምነት ጉዳዮችን በአካዳሚያው የትምህርት ስርዓት አላዝቦ በመተርጎም፣ በማወዳደር፣አተያይ በመቀየር፣ ምሳሌ በማቅረብና ምናባዊ ምስል በመቅረጽ ለማቅረብ የተጠቀመውም የአፃፃፍ ዘዴም አዲስ የጽሑፍ ሞዴል ነው። ይህ አቀራረብ የተመሳሳይ ጽሑፎችን መነሻ ትርጉም ለማያውቁ ወይም ጀማሪ ለሆኑ ስራቸውን ያቀለለና ለተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ተመራማሪዎች ቀዳሚ ዋቢ ስራ የሆነ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የቀደመ ንባብና ዕዉቀት ላላቸው ሁሉ አማራጭ እይታ የፈጠረና መርጠው የሚያነቡት ክፍል ያለው የፈጠራ የአቀራረብ / የአፃፃፍ ስልት ይዞ ቀርቧል፡፡
በሁለተኛው ክፍል ደግሞ የሐይማኖት ተረኮችን በአዲስ የአቀራረብ ዘዴ ይዞ ቀርቧል:: ይህ መጽሐፍ ዓለም በዕምነትና ኃይማኖት ጉዳይ ከማህበራዊ ሚዲያ እስከ ቴሌቪዥን ድረስ ድምጹን ከፍ አድርጎ በሚንጫጫበት በዚህ ወቅት መታተሙ ደግሞ የብዙ ጥንቁቅ አንባቢያንና ሰባኪያንን አይን ይገልጣል፤ የዕይታ አድማስንም ያሰፋል፡፡ በተለይ በዚህ በሁለተኛው ክፍል የተካተቱት ኃይማኖታዊ ጉዳዮች በዳዊት፣ ጀማልና መገርሳ ተብለው በተሰየሙና የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ሊወክሉ በሚችሉ ተዋንያን መካከል በተደረገ ገለፃዊ ውይይት (Inclusive participation through objective symbolization and descriptive dialogue) መልክ ስለቀረቡ ሳቢ ከመሆናቸውም በላይ የእይታን አድማስ በማስተካከልና ንጽጽራዊ አረዳድን በማሳደግ የንባብ ጉሮሮን በሰፊው ይከፍታሉ፡፡
 
የመፅሐፉ ይዘትና ትንታኔ
“ነገረ ድርሰትና የዓለማተ አማንያን ተረኮች መጽሐፍ” ስለ ድርሰት ምንነትና የተለያዩ የድርሰት ዓይነቶች በግልጽ በማስረዳት ለተማሪዎች፣ ለመምህራን፣ ለተመራማሪዎችና የእምነት አባቶች/ ሰባክያነ ቃል በስፋት እንዲያግዝ አድርጎ የራሱን አሻራ ከማስቀመጡም በላይ በጉዳዮቹ ላይ ያለውን ለየት ያለ ያረዳድ መጠንና ጥልቀት አስፍሯል፡፡ በመሆኑም ይህ መጽሐፍ ማንበብ ለሚችሉትም ይሁን በዕውቀትና በክህሎት አንቱታን ላተረፉ ሁሉ ጠቀሜታው የትየሌለ ነው፡፡ በርግጥም በመጽሐፉ ውስጥ (በተለይም በክፍል ሁለት) ለቀረቡት የተለያዩ ተረኮች የግል ትንታኔ (Analysis)፣ ትርጓሜ (Interpretation) እና ድምዳሜ (Summary/Conclusion) ስላልቀረበ ግላዊ ፍረጃን ያስቀረ መሆኑ ለግል መተርጉማን ሰፊና ነፃ ቦታ ያተረፈ ነው። ይህም የበሳል ደራሲያን ባህሪ በመሆኑ የጽሁፉን ተዓማኒነት ጨምሮታል፡፡
በይዘት ደረጃ ደራሲው በመፅሐፉ ውስጥ ያካተታቸውን ቁልፍ ነገሮች በዲስኩራዊ ትንታኔ (Discourse Analysis) በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡
ሀ) ይዘት
የመጽሐፉ ይዘት መረጣና ስደራን ስንመለከት በመጀመሪያው ክፍል ላይ የተካተተውና ስለ ነገረ-ድርሰት የሚያትተው ክፍል በቀደምት ደራሲያን (ጸሐፊያን) እና መምህራን በተደጋጋሚ የቀረበ ስለሆነ ገና ከጅምሩ የግልብጥብጦሽን (Copy and Paste) አባዜ የተጠናወተው ማስመሰሉ አልቀረም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በአግባቡ ያልተካተቱና ያፃፃፍ ስልታቸው ያልተዳሰሱ እንደ ዜና መዋዕል፣ መልክአ መልክእ፣ ገድል፣ ድርሳንና ስንክሳር መካተታቸውና በምሳሌ በመቅረብ መገለፃቸው (መተንተናቸው) ይህን ስራ ልዩና ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
በሁለተኛው ክፍል ግን ደራሲው ልዩ ሆኖ የቀረበበትና የተረክ እይታዎችን በአስደማሚ አቀራረብ ያስነበበበት ክፍል ነው፡፡ ይህም የክርስትና፣ የእስልምናና የዋቄፋና የእምነት አይነቶች ስለ ነፍስ አወጣጥና ጉዞ፣ ስለ ዓለማተ ምድር መገኛ፣ ስለ ዓለመ ዋቄፋና፣ ስለ ገነት/ጀነት ምንነትና መገኛ፣ ስለ ሲኦል መገኛና ምንነት፣ ስለ ዕለተ ምጽዓትና ዓለማተ ሰማያት፣ እንዲሁም ስለ ነገረ ሰይጣን/ሸይጣንና መልክአ ሳጥናኤል እንዴት እንደሚረዱት በግሩም ሁኔታ የቀረበበት ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የይዘት ምጣኔን ስንመለከት በዳዊት የቀረበውና የክርስትና ሀይማኖትን ጉዳይ በማንሳት የተተነተነው የተረክ ክፍል እጅግ ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ማለት ደራሲው ስለዚህ ይዘት ጠለቅ ያለ እውቀት፣ መረጃና ማስረጃ እንዳለው ያመላክታል፤ አልያም ጉዳዩ ደራሲውን እጅግ በተለየ መልኩ አሳስቦታል ወይም እንዲታወቅለት ፈልጓል ማለት ነው የሚል መነሻዊ ምልከታዬን አስቀምጣለሁ፡፡ በተጨማሪም በጀማልና በመገርሳ የቀረቡ ገለፃዊ ምልልሶች፣ ስለ ነገረ ሰይጣንና ስለ መልክአ ሳጥናኤል የቀረቡት ይዘቶች ጸሐፊውን በልዩ ሁኔታ አካታችና ደፋር በማለት እንድገልጸው አስገድዶኛል። በእርግጥ በጀማልና በመገርሳ የቀረበው ተረካዊ ምልልስ አቀማመጥና የጥልቀት ደረጃ እንደ ቫን ሊዊን (1996፤ 2008) የዲስኩር ትዕምርታዊ አመዳደብ መሰረት ኋሌ-ዳራዊ (backgrounding) የበዛበት ነው፡፡  
ለ) ዲስኩራዊ ይዘቶች
1ኛ) የጊዜና ቦታ ምጠና
በጊዜ ምጠና መሰረት ይህ ስራና ይዘቱ ህያው ነው፡፡ የሰው ልጅ መወለድ፣ ማደግና መሞት የቀን ከቀን ዕውነታ አድርጎ ተገንዝቦ እየኖረበት ስለሆነ ከሞት በኋላ ስለሚሆኑ ነገሮች በብዛት አጥብቆ ይጨነቃል፡፡ ይህን ጭንቀቱን የሚገላግለው ዓለማቀፋዊ ጥናትና ምርምር ስላላገኘ ሁሌም በተረክና መሰል ስራዎች ራሱን ለማሳመን (ለማጽናናት) ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቆይቷል፣ አሁንም እያደረገ ይገኛል፣ ወደፊትም ያደርጋል። በቃ ይህ የማይቋረጥ ተግባር ስለሆነ ይህ ድርሰትም ጊዜውን የተገነዘበ ታላቅ ስራ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ መሞት በስነ-ሥርዓት መቀበርን ወይም ከንቱ መጣልን፣ በእሳት መቃጠልን፣ በውኃ መወሰድና መበስበስን ወይም በአራዊትና አዕዋፋት መበላትን ያስከትላል፡፡ ብዙ ሰዎች “ከሞትኩ በኋላስ ለስጋዬ ምንም አልጨነቅም” በማለት ደንታቢስ መሆናቸውን ቢገልጡም፣ “አሟሟቴን አሳምረው” እያሉ የሚጸልዩ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንደሆኑ እንገነዘባለን፡፡ ይህ የዕምነት ተረኮች ስደራ፣ ገለጣና ትንተና ስራ በመሆኑ በሞት ጊዜ ስጋ እንደለበሱ ከፈጣሪ ጋር መነጋገርን እንዲሁም ወደተለያዩ ብሔራት መወሰድን፡- ለምሳሌ ወደ ብሔረ ብጹዓን (ዞሲማስ ባህታዊ የጎበኛት ዓለመ ምድር ናት) እና ወደ ብሔረ-ሕያዋን (ሔኖክና ነብዩ ኤልያስ የሚኖሩባት ዓለመ ምድር ናት) የሁሉም ነገር ታላቅ ምድራዊ ክስተት አድርጎ ይጠቅሳል። አለማተ ገነትና ገሀነም፣ ጀነትና ጀሀነም እንዲሁም ምድር (ለምሳሌ እንደ ዋቄፋታ አመለካከት) እንደ እምነቱ ተከታዮች የተለያየ ቅርጽ፣ መልክ፣ ክብርና የአኗኗር ሁኔታ በግልጽ ስለሚያስረዳ አንባቢያን የራሳቸውን የመንፈስ እጣ ፋንታ እንዲወስኑ እንዲረዳ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ አለማተ ሰማያት የሚባሉትን ጽርሐ አርያም፣ መንበረ ምንግሥት፣ ሰማይ ውዱድ፣ መንግሥተ ሰማይ፣ ኢዮር፣ ራማና ኤረር ደግሞ ልዩ ቦታ ሆነው የተቀመጡ ቦታዎች መሆናቸውን ድርሰቱ በግልጽ አመላክቷል፡፡  
ደራሲው በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል የተለያዩ መልካምነት (ልዩ የደስታና የፌሽታ ማሳለፊያ) ቦታዎችና የጊዜ ቆይታ ምሰላዎችን (use of positive diatopic–diachronic syntagmatic settings) መጠቀሙ የሰዎች ባህሪያት፣ አስተሳሰብና ድርጊቶቻቸው  ወደ መልካምነት፣ ታዛዥነት፣ እውነት፣ አመስጋኝነት፣ እና በጎነት እንዲያጋድል መፈለጉን መረዳት ይቻላል፡፡ ስሙስ በጎሰው የሽዋስ አይደል!
2ኛ) የአማንያን መረጣ
የተመረጡት አማንያን የሚወክሉት የክርስትናን፣ እስልምናን እንዲሁም ዋቄፋናን እምነት ነው፡፡ ሦስቱ ዕምነቶች ደግሞ በኢትዮጵያ ረዘም ያለ ታሪክና መስተጋብር ስላላቸው የስራውን ሀገራዊ ጠቀሜታ ያጎላዋል፡፡ በእርግጥ የሦስቱን ዕምነቶች ተረክ ከሌሎች እምነቶች፡- ለምሳሌ ከአይሁድ፣ ከሂንዱ ከቡድኻ፣ ከሽንቱ፣ ወዘተ ተረኮች ጋር ተሰናስሎ የመቅረብ እድል ቢኖር ኖሮ፣ ያለንን ከሌለን ጋር በማመሳከር የዕይታ መነጽራችንን እንድናስተካክል እድል ይፈጥርልን ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንድ ሀይማኖት ውስጥ ያሉ ልዩነቶች፡- ለምሳሌ በአንድ የክርስትና ኃይማኖት ውስጥ በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክና በፕሮቲስታንት (በጴንጤ) ኃይማኖቶች መካከል የማያለያዩ ልዩነት ካሉ ይህን በሚያንጸባርቅ መልኩ ቢቀርብ የበለጠ አትራፊ ልንሆን እንችላለን ብዬ እገምታለሁ፡፡
3ኛ) የአፃፃፍ ስልት ቅኝት
 በክፍል አንድ
ዶ/ር በጎሰው ጽሑፉን አጠር ባለች ምስጋናና ሰፋ ባለ መቅድም ጀምሮ ነገረ ድርሰትን ስለ ድርሰት ምንነት ዓይነቶች በተለመደው አፃፃፍ አስረድቶን ሲያበቃ፣ ወደ አዲስና የደራሲውን ስራ ለየት አድርጎ ወደሚያሳየው ስራ ያስገባናል፡፡ ይኸውም የደራሲው ስራ ስለ ዜና መዋዕል፣ መልክአ መልክእ፣ ገድል፣ ድርሳንና ስንክሳር ለየት ባለ መልኩ በማቅረቡ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ጽሑፎችን ስም፣ ይዘትና የአፃፃፍ ስልት የማወቅ ዕድል ላልገጠማቸው አንባብያን ከፍተኛ አበርክቶ ነው፡፡
የአፃፃፍ ስልቱም የእያንዳንዱን ድርሰት ዓይነት ትርጓሜ (Definition) በማስቀደም መፃፍ የተጀመረበትን ዘመንና የእድገት ደርጃውን (History)፣ ጸሐፊዎች እነማን እንደነበሩ፣ ስማቸውስ ምን ይባል እንደነበር በማስከተል ስለ ተመሳሳይ ስራዎች አፃፃፍና ዋና ዋና ስልቶች እንዲሁም ዋና ዋና ይዘቶች / ክፍሎች በምሳሌ በማብራራት (Content identification and exemplification) ያቀረበ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ዜና መዋዕል
- “ዜና” ዜነወ ነገረ፣ አበሰረ፣ አስረዳ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን “ዜና መዋዕል” ደግሞ የቀድሞ ነገሥታት የጦርነት፣ የፍርድ ችሎት እና የዕለት ውሏቸው ተመዝግቦ የሚገኝበት ጽሑፍ ነው፡፡ (ገጽ 22)
- በኢትዮጵያ ዜና መዋዕል መፃፍ የተጀመረው … (ገጽ 22)
- የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ (ገጽ 26)
- የዜና መዋዕል አፃፃፍ …. (ገጽ 28)
- የዜና መዋዕል መክፈቻና መዝጊያ …. (ገጽ 30)
- የዜና መዋዕል ዋና ዋና የአፃፃፍ ስልቶች .… (ከገጽ 31 - 36) እያለ በማቅረብና በምሳሌ በማስረዳት ያስነብባል።
በክፍል ሁለት
በክፍል ሁለት ላይ የዓለማተ አማንያን ተረኮችን የልብ ጓደኛሞች የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመምረጥ (የሁላችንንም የልብ ጓደኝነትና ተማሪነትን ለማመስጠር ይመስላል) በገላጭ ውይይት፣ በተግባቦታዊ ጭውውት (Descriptive dialogue in consensus) መልክ መቅረቡ ኃላፊነት ያለበት የገላጭ - አድማጭ - ተደማማጭ - ስምምነት ንግግራዊ ሒደትንና ጥምር ተግባቦትን ለመፍጠር የተደረገው ጥረትና የተኬደበት ርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
 በክፍል ሁለት ላይ ደራሲው ማካተት የሚገባውን ይዘት ሲወስን፣ በነፍስ አወጣጥና ጉዞ (መንገድ) ይጀምርና በመልክአ ሳጥናኤል ማጠናቀቁ ግርምትን ፈጥሮብኛል፤ በግሌ ደስም አላለኝም (ሳሳቅቅቅ) “አጨራረሴን አሳምርልኝ” አይደል የሚባለው ፤ መዝጊያዬንሰ በመልክአ ሳጥናኤል አታድርግብኝ፡፡ እናም ደራሲው ሰው ከሞተ በኋላ ያሉት የተጋረዱ የምድርና የሰማይ ዓለማት እጅግ እንዳሳሰበውና ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ መጠናት እንዳለበት (ይህም ከተቻለ ነው) ለማሳሰብ የፈለገ ይመስላል፤ ይህንን መጽሐፍ በማቅረቡም የበኩሉን አስዋጽኦ አድርጓል፡፡ ቁልፍ ይዘቱ የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ ነፍሱ እንዴት እንደምትወጣ፣ የወጣችዋ ነፍስ ወደ የትና ከማን ጋር እንደምትሄድ፣ ምንና እነማን እንደሚያገኟት እንዲሁም በሄደችበት ቦታ ምን ሊገጥማት እንደሚችል ይገልፃል፡፡
ደራሲው ከፈጣሪ በታች በመላእክትና በሰይጣናት፣ በቅዱሳንና በርኩሳን፣ በበጎና በክፉ (በመጥፎ) ነገር እንዲሁም በገነት (መንግሥተ ሰማይ) እና በሲኦል (በገሀነም) መካከል ያሉ ልዩ ሁኔታዎችን፣ ምስሎችንና ባህሪያትን በልዩ ሁኔታ መርጦና አመጣጥኖ ማካተት የፈለገው ምዕናባዊና ድምበር ተሻጋሪ የአውድ፣ የምስል፣ የባህሪና ድርጊት ግንኙነቶችን (Integrating metatextuality and hypertextuality systems of thought and actions) አሰናስሎ ለማስረዳት ያደረገው ብርቱ ጥረት ይመስላል፡፡ በዚህ ጥረት ደግሞ ሰዎች፡-
1ኛ) የእውቀት ምህዋር / ፈርጅ (Axis of knowledge) ውስጥ እየተሽከርከሩ የደረሱበትን ደረጃ እንዲያመላክታቸው ተደርጓል፡፡
2ኛ) በየትኛው የስነ-ምግባር/ግብረ ገብነት ፈርጅ (Axis of ethics) እንደሚገኙና መገኘት እንደሚገባቸው ይጠቁማል፡፡
3ኛ) የትኛው የክፋት፣ የተንኮል፣ የእርኩስ መንፈስ ወይም ሀጢአት ፈርጅ (Axis of evil) ውስጥ እንደሚገኙና ወደፊት ከማን ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉ ያመላክታል፡:
4ኛ) የምድርና የሰማይ ህይወት የተመዛዛኝነት (ሚዛናዊነት) ወይም የተመጣጣኝነት ፈርጅና ተዛምዶ (Axis of symmetry) በቅድስና፣ ንጽህና፣ ደግነት፣ ታዛዥነት ፈርጅ (Axis of saint ship, purity, kindness and obedience) እና በእርኩሰት/ሀጢአት ፈርጅ (Axis of evil) ልኬታ ላይ የተቀመጠ ስለሆነ የእያንዳንዳችንን የህይወት መስመርና የጥራት ደረጃ እንድንፈትሽ አበክሮ ያመላክታል፡፡
5ኛ) እውነት ከሆነ ሁሉም የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ መልካም ቦታ መግባትና ማረፍ (ጽድቅ ማግኘት) - ገነት/ ጀነት/ መንግሥተ ሰማይ መግባት ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ሰው ስህተት ተብለው የተቀመጡትን ቢሰራ ወይም ሕግ ቢተላለፍ ይቅርታ እንዲደረግለት፣ በፈጣሪው እንዳይረሳ - ፈጣሪው በምህረቱ እንዲያስበውና ይቅር ብሎ ወደ መልካም ቦታ እንዲያስገባው መማጸን፣ ንስሀ መግባት፣ መስገድ፣ መጸለይ፣ መልካም መስራት፣ ወዘተ እንዳለበት (Axis of appeal and excuse) ድርሰቱ ደጋግሞ ያሳስባል፡፡
“ነገረ ድርሰትና የዓለማተ አማንያን ተረኮች” ጽሑፍ በተለይ ዜና መዋዕል፣ መልክአ መልክእ፣ ገድል እንዲሁም ድርሳን በልዩ ሁኔታ መርጦና በአቀማመጥ ሰድሮ (maintaining discourses of content and relevance) እንዴት እንደሚፃፉ አመላክቷል፡፡ የደራሲው ትኩረትም ከላይ የተዘረዘሩት ነገረ ድርሰቶች ሲፃፉ እንዴት ራስን (የራስን) በልዩ ሁኔታ ከፍ አድርጎ ማንቆለጳጰስና ተዓምር ማሰራት (infinite self-glorification and miracle performances)፣ በልዩ ሁኔታ መቀደስና ማወደስ (unique personalization and acknowledgement)፣ ለንዋያተ ቅድሳት፣ ለጸሎት መጻሕፍት እና ለረቂቅ ሀሳቦችም የተደረሱ መልክኣት እንዳሉና ልዩ ዋጋ እንዳላቸው ማስረዳት (ገጽ 42) (personification, spiritual symbolization and functionalization)፣ ወዘተ እንደሆነ በምሳሌና በሚገባን ቋንቋ ለማስረዳትና ለማሳየት ነው፡፡
በመጨረሻም
ደራሲው ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ የተነሳሳው (እኔ በተረዳሁበት ልክ ማለት ነው) ስለድርሰት ምንነት ለማስረዳት፣ ስለተለያዩ የድርሰት አይነቶች ገለፃ ለማድረግና በተለይም ከእምነት ጋር የተቆራኙ የድርሰት አይነቶችንና የአፃፃፍ መልካቸውንና ስንክሳራቸውን በግልጽ ለተለያዩ አንባቢያን በምሳሌ አስደግፎና 87 የሚሆኑ በተለያዩ ዋቢ መጽሐፍት ምንጭ አጣቅሶ ለማሳወቅ ነው፡፡ በመሆኑም የሀሳብ ዝናፌ የማይታይበት፣ የመረጃ ድርቀት የሌለበት (87 ዋቢ መጽሐፍትን በአግባቡ በመጠቀሙ)፣ ተዓማኒነቱ ከፍ ያለና በግልጽ የሰፈሩ ሀሳቦችን ያካተተ ወርቅ ስራ ነው። በመሆኑም ይህ መጽሐፍ የተለያዩ አካዳሚያዊ፣ ማህበራዊና መንፈሳዊ እውቀት እንድናገኝበት ተደርጎ በጥንቃቄ ተሰናስሎ የተጻፈ ስለሆነ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ አለውና የትምህርትና ምርምር ተቋማትና ማዕከላት፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች፣  የህዝብ ቤተ-መጽሐፍትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መስጫ ማዕከላት፣ እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማትና ቤተ-ዕምነቶች መጽሐፉ ለብዙኃን ተደራሽ ቢሆን ዋጋው የላቀ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ  መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ሰላም!!!



Read 949 times