Print this page
Saturday, 14 August 2021 00:00

"እንዴት ነው የሚተኛው?"

Written by  መሳይ ደጉአለም
Rate this item
(3 votes)

 አልተኛም...
ከምወደው እንቅልፌ ከተኳረፍኩ ሰነባብቻለሁ...
በርግጥ "ከምወደው እንቅልፌ.." የሚለው ማሽቋለጥ፣ እንቅልፋም መሆኔን የሚመሰክር አይነት በፍፁም አይደለም።
ቀድሞም "ሰው ከሙሉ ቀኑ ከስድስት የሚዘለውን ሰዐት ጨፍኖ ማሳለፍ የለበትም... ኪሳራ ነው!" ብዬ ወገቤን ይዤ የምከራከር አይነት ነኝ።
ቢሆንም ቢሆንም... ሩብ ቀኔን በሰላም የምተኛው ቆንጆ እንቅልፍ ነበረኝ።
እና ሰሞኑን የተነጠቅኩት... ይሄንን አጣብቤ የማጣጥመውን የሰላም እንቅልፌን ነው።
ወዳጆቼ... "የሀገሪቱ መፃዒ ተስፋ እያስጨነቀህ ነው የሚሆን..." እያሉ ከጋዜጣ በቃረሙት አማርኛ ይደመድማሉ።
እሷ... "ግዴለም... ወደኸኝ ነው... ፍቅር ሲጀምር እንዲህ ነው የሚያደርግ!" እያለች ትመፃደቃለች።
ከትላንት በስቲያ ያየሁት ዶክተር... "ጨጓራህን አሞህ ነው! አንገትህን ቀና አድርገህ ተኛ! ይኼንንም ክኒና ከመብላትህ ግማሽ ሰዐት እየቀደምክ ዋጥ!" ብሎ ያስፈራራኛል...
ስለ ክኒኗ ሳስብ እናቴ ነች ትዝ የምትለኝ...
ዶክተሩ የቸከቸከበትን ወረቀት ይዤ ወደ መድሀኒት መደብሩ ስሄድ፣ ልደውልላት እየተወሰወስኩ ነው የደረስኩት...
እናቴ ኪኒን የሚባል ነገር አብዝታ ነው እምትጠየፍ...
የት እንደሰማችው እንጃ... የሁልጊዜ ምክንያቷ ደግሞ "ጨጓራህን ይነካሀል!" ነው።
እንደውም ልጅ እያለሁ ኪኒናው በውሀ ተወራርዶ ከጉሮሮ ዝቅ ሲል ቅርፅ ቀይሮ ጨጓራ መንኪያ እጅ የሚያበቅል ሁላ ይመስለኝ ነበር...
ክረምት ሲገባ እረክሶ እንዳይበላሽ በገፍ የሚሸጥ ቃርያ በደቃቁ ከተከተፈ ሽንኩርት ጋር ጠብሳ ስታበላ ያሳደገቺኝ ሴትዮ "...ጨጓራህን" የሚል ስጋት ማንሳቷ በራሱ ያስቃል...
ለነገሩ አሁን "ሽንኩርትና ቃርያ የድህነት ነበር" ብል ማን ያምናል?
ብቻ ዶክተሬን ሰምቼ መድሀኒቴን ልሸምት እያዘገምኩ አስቤ ብቻዬን የሳቅኹበት ሙግቷ እሱው ነው...
ደውዬ "ኦሜፕራዞል የሚባል የጨጓራ መድሀኒት ታዞልኝ እየገዛሁ ነው።" ብላት...
አቋርጣኝ "ውይ እሙሹ ይቅርብህ... ጨጓራህን ይነካሀል!" ብላ መቆጣቷ አይቀርም...
እኔ ግን እላለሁ... "እንቅልፌን ያጣሁ አንድም በራሴ ነው... አንድም በሁሉም ነው!"
ወይ ሰው... ወይ እኔ... እየገባኝ አይደለም ነገር!
በቀደም አሁን "ሰዎችን በቁምነገር መውሰድ ከባድ ነው!" ብያት አንድ ወዳጄ ሙሉ ለሊት ወረደችብኝ።
"ግዴለም... ስንቱ ሲወረድለት እኔ የተወረደብኝ ቢገ'ባኝ ነው..." ብዬ ዝም ብዬ ሰማኋት።
ሲደክማት ጠብቄ "ይኸውልሽ እንደሱ ያልኩትኮ ቅድም አንድ ወዳጄ... 'ለምን መኪና ትከራያለህ? መኪና ብትገዛ እኮ 'ሀሴት' ይሆንሀል...' ብሎ መክሮኝ ነው።" አልኳት በትህትና።
እርግጥ ነው 'asset' ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ይገባኛል... ግን ደግሞ እንዴት አባቴ አድርጌ በቁምነገር ልውሰደው?...
ሀሳቤ ገብቷት ያንን ልቤን የሚኮረኩረውን ሳቋን ሳቀችልኝ።
ግን ደግሞ መልሳ ኮስተር ብላ "እውነቱን ነው!" እያለች ተቆጣችኝ...
ቆይ እንዴት ነው እማልወዛገብ?
ልክ መሆኔ ልክ የማይሆን?
እና "እንቅልፌ ጥሎኝ የበረረው እንዲህ-እንዲህ እየተወዛገበ ነው!" ባይ ነኝ።
አንድም በኔ... አንድም በሁሉ...
ለነገሩ እናቴ ናት "ሰይፈ" ብላ ጉድ የሰራችኝ። ስቆላመጥ እንኳ "ሰይፍ" ነው የምሆን። ሰዎች ስሜን ሲጠሩ subconsciously "ጅማትና አጥንትን የሚሰነጥቅ"... "በሁለት በኩል የተሳለ"... ምናምን የሚሉ አሰቃቂ ጥቅሶች እየታወሳቸው ነው።
ሰው በሀኪም ቀጠሮ... አልያም ቤተሰቦቹ በበረዳቸው ቀን አጋጣሚ... ሐምሌ ፲፱ በመወለዱ ብቻ እንዲህ ያለ የሚያስገፋ ዕድል አይገባውም ባይ ነኝ!
የመጣጣም ችግር እንዳለብኝ ለመጀመርያ ጊዜ የተረዳሁት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው።
በብዙ እድልና ትኩረት መፅሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምረኝ የተመደበልኝ መምህር፣ ድንገት አንድ ቅዳሜ ከመሬት ተነስቶ፣ "ትላንት ራዕይ አየሁ..." አለኝ እየፈነደቀ።
አፌን ከፍቼ ተዐምር ለመስማት ተዘጋጀሁ...
ሰውዬው ከነመነቃቃቱ ቀጠለ...
በራዕይ አንዲት የብርሀን ጣት ከግድግዳው ላይ በወርቅ የፃፈችውን የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ነገረኝ።
ያው የብርሀን ጣቱን መረዳት እምብዛም አልቸገረኝም...
እድሜ ለእናቴ ኪኒን ጣት ሲያወጣ እየሳልኩ ነው ያደግሁ...
ትንሽ ጣቴን አገጬ ላይ ደግፌ "እንዴ... እንዴ...?" ያስባለኝ ሰባኪዬ፣ አነበብኩት ብሎ የነገረኝ ዐረፍተ ነገር ከባድ የgrammar ስህተት ያለበት መሆኑ ነው።
"መቼስ አንድዬ በኔ የሰባተኛ ክፍል እንግሊዝኛ አይመዘንም..." ብዬ እንዳልተወው ዐረፍተ ነገሩን አስተካክሎ ፅፎለትም ቢሆን፣ ሰውዬው ከገባው የተለየ ነገር አይገባውም ነበር...
ስቃይ እኮ ነው...
ሰው እንዴት ያነበበውም... የተረዳውም ከራሱ ይሆናል?
እናም ደግሜ እላለሁ... እንቅልፌን የወሰደው ይኼ ነው!
ወይ እኔ... ወይ ሁሉ...
ብቻ አንዳችን ሀርድ ውስጥ ነው ያለነው!
እንዴት ነው የሚተኛው?

Read 1893 times