Thursday, 26 August 2021 00:00

የአፍጋኒስታን ነገር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በስተመጨረሻም፤ “ተማሪዎቹ” ከ20 አመታት በኋላ በድል ዝማሬ ታጅበው ወደ ቀደመ ርስታቸው፣ ወደ ተነቀሉባት መናገሻቸው ወደ ካቡል ተመለሱ። በአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታንና ኢራን በብዛት ከሚነገረው ፓሽቶ የተሰኘ ቋንቋ የወሰዱትንና “ተማሪዎቹ” የሚል ትርጉም ያለውን “ታሊባን” የተሰኘ ቃል መጠሪያቸው ያደረጉት ታጣቂዎች፤ ከሁለት አስርት አመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ዳግም በአፍጋኒስታን ምድር ከፍ ብለው ታዩ፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 ወርሃ መስከረም መጀመሪያ በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት ለፈጸመው የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ከለላ ሰጥቷል በሚል በጥቅምት ወር ላይ በአሜሪካ መራሹ ጦር ክፉኛ መደብደብ የጀመረውና በሁለተኛ ወሩ ፍርስርሱ ወጥቶ ወደ ተራራ የሸሸው የአፍጋኒስታኑ የታሊባን አስተዳደር፤ ለሁለት አስርት አመታት በየተራራው ስር አድፍጦ በተወንጫፊ መሳሪያዎች ሲያደባያት ወደነበረችው ካቡል ሰተት ብሎ ገባ፡፡
ከሳምንታት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ጦራቸው በአፍጋኒስታን የነበረውን የ20 አመታት ቆይታ አጠናቅቆ እንደሚወጣ በይፋ ሲያስታውቁ፣ አለም በመገረምም በመደነቅም ነበር የሰማቻቸው። ባይደን በተናገሩት መሰረት የአሜሪካ ጦርና የሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል አገራት ጦር አፍጋኒስታንን መልቀቅ በጀመሩበት ቅጽበት ነበር፣ የታሊባን ወታደሮች የአፍጋኒስታንን ቁልፍ ከተሞች መቆጣጠርና ወደፊት መግፋት የጀመሩት፡፡
አሜሪካ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ አድርጋ ያቋቋመችው የአፍጋኒስታን መንግስት ጦር፣ የታሊባንን ጥቃት መቆጣጠር የሚችልበት አቅም አላገኘም፡፡
ባለፈው ዕሁድ ማለዳ…
ታሊባን በድል እየገሰገሰ መዲናዋን ካቡል ተቆጣጠረ፤ ፕሬዚዳንት አሽረፍ ጋኒ፣ ቤተ መንግሥታቸውን ለታሊባን ታጣቂዎች ትተው፣ ወደ ጎረቤት አገር ታጃኪስታን  ጥለው ተሰደዱ፡፡
ታሊባን እሁድ ዕለት ካቡልን መቆጣጠሩን ተከትሎ፣ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ያሳሰባቸውና የታሊባን ቀጣይ እርምጃ ለነፍሳቸው ያሰጋቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታውያን፣አገር ጥለው ለመሰደድ፣ ወደ አውሮፕላን ማረፊያዎች መጉረፍ ያዙ፡፡
ታሊባን ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ የበቀል እርምጃዎችን ይወስዳል፤ የአክራሪነት አመለካከት የሚያንጸባርቁ ፈታኝ ህጎችን በመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል የሚለው ስጋት፣ ብዙዎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንዳነሳሳቸው ነው የሚነገረው፡፡  
ከታሊባን መስራቾች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ሙላህ ባራዳርን ጨምሮ ለአመታት በኳታር በስደት የኖሩ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አፍጋኒስታን መመለስ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አካታች እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲል ከአውሮፓውያን መንግስታት ጋር ይሰሩ ነበር ያላቸውን ጨምሮ ለሁሉም የቀድሞ መንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ባለስልጣናት ሙሉ ምህረትና ይቅርታ ማድረጉን በይፋ ያስታወቀው ታሊባን፤ በማንም ላይ የበቀል እርምጃ እንደማይወስድ በመግለጽ፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሴቶች በሸሪአ ህግ መሰረት መብታቸው ተከብሮላቸው እንደሚኖሩ ቃል የገባው ታሊባን፤ መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲሰሩ እንደሚፈቅድም ተናግሯል፡፡ ታሊባን በአፋጣኝ ህጋዊ መንግስት ለመመስረት ከቀድሞው የአፍጋኒስታን መንግስት አመራሮችና ፖለቲከኞች ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ቢያስታውቅም፣ በአብዛኛው ዜጋ ልብ ውስጥ ግን መጪው ጊዜ የጭቆና እና የእርስ በእርስ ብጥብጥ ይሆናል የሚል ስጋት መፈጠሩን ዘገባዎች ያትታሉ፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ ቀጣዩ ሁኔታ ያሰጋቸው ከ60 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውንና የኤምባሲ ሰራተኞቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት ርብርብ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ አሜሪካ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ 3 ሺህ 200 ያህል ዜጎቿን ለማውጣት መቻሏን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ አፍጋኒስታውያን ስደተኞችን ለመቀበል በራቸውን ክፍት እንደሚያደርጉ የሚያስታውቁ አገራትም እየተበራከቱ ሲሆን፣ እንግሊዝ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ለመቀበል ማቀዷን አስታውቃለች፡፡ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ከአሜሪካ በቀረበላት ጥያቄ መሰረት 2 ሺህ ያህል አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ለመቀበል መስማማቷን ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ ማስታወቃቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ለመሰደድ የተዘጋጁ አፍጋኒስታናውያን ቁጥር በእጅጉ በተበራከተበትና እነ ጀርመንን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን በጦር አውሮፕላኖች ጭምር ለማስወጣት ርብርብ በማደረግ ላይ በሚገኙበት በዚህ አደገኛ ወቅት፣ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች በአገሪቱ አየር ክልል የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸው ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው እየተነገረ ነው፡፡
የአፍጋኒስታን የአየር ክልል ላለመጠቀም የበረራ አቅጣጫቸውን እየቀየሩ በፓኪስታንና ኢራን የአየር ክልሎች በረራ ማድረግ ከጀመሩ አየር መንገዶች መካከል ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ብርቲሽ ኤርላይንስ እና ቨርጂን አትላንቲክ እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ታሊባን አገሪቱን ተቆጣጥሮ መንግስት ለመመስረት ደፋ ቀና እያለ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት ለቡድኑ ፈጥነው እውቅና መስጠት እንደማይፈልጉ በይፋ እያስታወቁ ነው፡፡
አሜሪካ ከ20 አመታት በፊት ታሊባንን ከስልጣን ለማውረድ ወደ አፍጋኒስታን ጦሯን ካዘመተችበት ጥቅምት ወር 2001 አንስቶ በነበሩት 20 ያህል አመታት፣ ከ3 ሺህ 500 በላይ የጥምር ጦር ወታደሮች በጦርነቱ መሞታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። ከእነዚህ ወታደሮች መካከል 2 ሺህ 300 ያህሉ የአሜሪካ ወታደሮች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከ20 ሺህ 660 በላይ የሚሆኑ አሜሪካውያን ወታደሮች ደግሞ ቁስለኛ መሆናቸውን ያብራራል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከአፍጋኒስታን ብሄራዊ ጦርና የፖሊስ ሃይል ከ69 ሺህ በላይ ወታደሮች እንዲሁም ከ47 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች በጦርነቱ ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ታሊባንን ጨምሮ ከአማጽያን ቡድኖች ደግሞ 84 ሺህ ያህል ታጣቂዎች መገደላቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
አሜሪካ አፍጋኒስታንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ ከጦርነት ጋር በቀጥታ በተያያዙ የተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 241 ሺህ እንደሚደርስ ብራውን ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ባወጣው የጥናት ውጤት ማመልከቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ባለፉት 20 ያህል አመታት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ጦርነቱን በመሸሽ አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ፓኪስታን መሰደዳቸውን የዘገበው አልጀዚራ በበኩሉ፤ በአፍጋኒስታን በዚህ አመት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 18.4 ሚሊዮን መድረሱንም አስነብቧል፡፡
አሜሪካ ባለፉት 20 ያህል አመታት በአፍጋኒስታን በየዕለቱ 300 ሚሊዮን ዶላር ያህል ለጦርነት ወጪ ታደርግ እንደነበር ያስታወሰው ፎርብስ መጽሄት፣ በጦርነቱ ያወጣችው ወጪ በድምሩ ከ2.26 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚደርስም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ ከዚህ ወጪ መካከልም 85 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ያፈሰሰችው በሳምንታት ውስጥ ብትንትኑ ለወጣው የአፍጋኒስታን ጦር ስልጠና መሆኑንም ዘገባው ያስረዳል፡፡


Read 5035 times