Friday, 27 August 2021 00:00

በእውነታ ላይ የተመሰረተ ወግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ትዝ ይላችኋል፤ በዚያን ሰሞን እንኳን ዶከተር ዐቢይ በቴሌቪዥን ቀርቦ “የሕዳሴው ግድብ ፍፁም ሆኖ መጠናቀቅ አለበት” እያለ በቴሌቪዥን ሲያወራ። ካልረሳችሁት እሱን ተከትለው ሌሎችም ኢትዮጵያውያን፣ “ግድቡ የእኔ ነው፤ ግድቡ የእኛ ነው” እያሉ በቴሌቪዥን ቀርበው ሀሳባቸውን ሲያንፀባርቁ  ነበር። አሁን ትዝ አላችሁ?!
ታዲያ በዚያን ጊዜ አንዲት እንጨት ተጠግርራ የተሸከመችና ከእንጨቱ ብዛት የተነሳ ከወገቧ በላይ ያጋደለች የምትመስል ሴት አላያችሁም? ያችን ሴት እያሳየ በሚመስል ሁኔታ ዶ/ር ዐቢይ ታዲያ “አባይ የሚገነባው የእነዚህን የእንጨት ተሸካሚዎች ድካም ለመቅረፍ ነው” በሚል መልክ እጁን እንጨት ወደ ተሸከመችው ጎባጣ ሴት እየጠቆመ፣ ደጋግሞ ያችን ሴት ለህዝብ ያሳያት ነበር። እናም ያቺ ሴት ታዲያ፣ የእናቴ ጓደኛ ነች። አጓንዴ ትባላለች።
ታዲያ እናቴና አጓንዴ አንጨት ለመልቀም እንጦጦ ሲወጡ አይለያዩም። አጓንዴ ከሽሮ ሜዳ ዶርዜ ሰፈር ትነሳለች። እናቴ ደግሞ ከቀጨኔ ወጣ፣ ከጨፌ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው  ከጉራጌው  አርጋው ቤት አካባቢ ትነሳና፣ ከባዱን የእንጦጦን ዳገት መውጣት ከመጀመራቸው በፊት ቁስቋም  ማርያም ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገናኛሉ። ከዚያም የቁስቋሟ ማርያም እንድታበረታቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ሰው እየሰማቸው በጋራ ሆነው ይፀልያሉ። ከዚያም የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤትን አልፈው፣ ሽቅብ የእንጦጦን ዳገት ይያያዙታል።
ዳገቱን ሲወጡ ከላያቸው ላይ ለጠፍ የሚያደርጓት ትንሽ ብጫቂና እድፋም ነጠላ ለብሰው፣ ወገባቸውን እንደዚሁ በረጅም አዳፋ ነጠላ ጠምጥመውና በብብታቸው አካባቢ እንጨት የሚያስሩበትን ገመድና እንጨት ለመተፍተፍ የምትረዳ አነስተኛ መጥረቢያ ሸጎጥ አድርገው ነው።
እንዲህም  ሆኖ ወደ እንጦጦ ሲወጡ፣ ዝናብም  ሆነ ፀሐይ፣ ብርድም ኖረ ነፋስ፣ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ዳገቱን የሚወጡት እየሳቁ፣ እየዘፈኑ፣ ማርያምን እያመሰገኑ፣ ለማንም በሚገርም ሁኔታ የደስተኝነት ስሜት ተላብሰው ነው። በተጨማሪም በመንገድ ሲሔዱ ያዩትን ሰው ሁሉ ሰላም ሳይሉ አያልፉም። ለነገሩ በመንገድ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰላም ማለት ለአጓንዴ ጭምር ያስተማረቻት እናቴ ነች።
አንድ ቀን እናቴን፤ “ያገኘሽውን በሙሉ የፍቅር እስከ መቃብሩን በዛብህን ይመስል ሰላም ማለት አይሰለችሽም እንዴ? “ብዬ ጠየቅኳት። “በዛብህ ደግሞ ማን ነው? እኔ የማውቀው ሠላምተኛ  የእናቴ  (ያያትህ) ጎረቤት የሆኑትን አቶ አርጋው ጨንገሬን ብቻ ነው “አለች። ቀጠለችናም፤ “ስለ አቶ አርጋው ሰላምተኝነት ብትሰማ ምን ልትል ነው፣ እኔን በዚች የሰናፍጭ ቅንጣት በምታክል ሰላምታ ሰጭነቴ የምታደንቀኝ!” አለችኝ።
 እናቴ ስትነግረኝ፤ “(ጎረቤቷ አቶ አርጋው) ድሮ ታክሲ እንዳሁኑ ባልበዛበት ጊዜ ጧት ተነስተው በእግራቸው መርካቶ እስኪደርሱ ድረስ፣ ባርኔጣቸውን አንስተው ያገኙትን ሁሉ (ትግሬ ሆነ አማራ፣ ጉራጌ ሆነ ኦሮሞ፣ ነጭ ሆነ ጥቁር፣ ቀጭን ሆነ ወፍራም፣ ደርግ ሆነ መኢሶን) ምንም ሳይመርጡ ሰላምታ ሲሰጡ ይቆዩና፣ ባርኔጣቸውን መልሰው በራሳቸው ላይ የሚያጠልቁት እግቢያቸው ሲደርሱ ነው” አለችኝ።
 እናም  እናቴ እየተደነቀች በምትነግረኝ በአቶ አርጋው አስደናቂ ምግባር ተመስጬ፣ እስከ አሁን ድረስ ያገኘሁትን ሁሉ ሰላም ማለት ያስደስተኛል፣ደግሞም ሰላምታ መስጠትን እመቤቴ ማርያምም ትወደዋለች” አለችኝ።
ታዲያ የእነዚህን እንጨት ለቃሚ እናቶች ውጪያዊ ጉስቁልና አይቶ፣ በአንጻሩ እየሳቁና ተደስተው፣ ላዩት ሁሉ ሰላምታ እየሰጡ፣ በምስጋናና በተስፋ ሲኖሩ የተመለከታቸው ሁሉ ግራ ይጋባል። እኔም እንደ ውጪው ሰው፣ የእናቴ ሁኔታ ድንገት በአዕምሮዬ ውስጥ ሲታወሰኝ በእጅጉ ግራ እጋባለሁ።
ድሃ ሆነው፣ እንጨት ለቅሞ ለመሸከም ቀን በቀን ተራራ እየወጡና እየወረዱ፣ እንዴት ሁሉ ነገር እንደተሟላለት ሀብታም ሲፍለቀለቁ ይውላሉ” እላለሁ።
እንደገና ደግሞ ምን አለ፣ በዚህ ትዕግስታቸው፣ በዚህ ሰላምታ አሰጣጣቸው፣ በዚህ ማመስገን አወዳደዳቸው፣ ከዚህ የእንጨት ሸክም ስራ አንስቶ እኔ ያለሁበት መስሪያ ቤት፣ የሽያጭ ክፍል ሠራተኛ የሆኑትን እነ አልማዝ በለጠን ወዲያ አሽቀንጥሮ በእነሱ ምትክ የሽያጭ ሠራተኛ ቢያደርጋቸው እላለሁ።
ደግሞም ቀጠል አደርግና፣ አሁን እነ አልማዝ እንግሊዝኛ ከመናገር ውጪ ሌላ ምግባር የሌላቸው ሽያጭ ሠራተኛ ይባላሉ! አንድ ደንበኛ እንኳን በቅንነት ሲያናግሩ ተሰምተው የማያውቁ ወስላቶች! ፀረ ሙስና ከዚህ በለቃቀማቸው!” እላለሁ።
ይህንን ብሶት ሳሰማ የሚሰማኝ ያ የቢሮ ጎደኛዬ (ደርጋጎ)፤  ወደ ጆሮዬ ጠጋ ይልና “ፀረ ሙስና ምን ጥፍር አለው፣ጥፍሩ እኮ ለስላሳ ነው” ይለኛል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ እናቴና አጓንዴ ፣እንጦጦ እንጨት ያለበት ደን ውስጥ የሚገቡት በቀጨኔ በኩል አድርገው፣ ጥድ የሚባለውን ተራራማ ስፍራ አቋርጠው ነው። እናቴ እኔን የወለደችው ፣አጓንዴም ታምሬን የወለደችው በጥድ ብቻቸውን ሲጓዙ በወንዶች ተደፍረው ነው። ሁለቱም ባንድ ቀን ተደፈሩ፤ በተመሳሳይ ቀን ማርገዛቸውን አሳውቀው ወንድሞቻቸው ጋር በመኖር ከንጨት ለቀማ ቀሩ፤ በተመሳሳይ ቀን ልጆች ወለዱ፤ ልዩነቱ እናቴ እኔን (ወንድ) ወለደች። አጓንዴ ደግሞ ታምሬን (ሴት) ወለደች።
ታዲያ ሁለቱም እንጨት ቆራጭ የሆኑት የእናቴና የአጓንዴ ወንድሞች በጧት ተነስተው፣ የእንጨት መቁረጫ ስል መጥረቢያቸውን ይይዙና፣ "በድጋሚ እንዳትደፈሩ ሸኝተናችሁ፣ ጥድን አሳልፈናችሁ እንመለስ" ሲሏቸው የሚሰጡት መልስ የሚገርም ነው።
"እንኳን ተደፈርን ምን ሆንን?  ልጆች አገኘን፣ በእጃችን ፍቅርና ተስፋ ገባ” ይላሉ።
ምን አይነት አገላለጽ ነው!? እኔማ ይህ አነጋገራቸው ስጋት ያሳድርብኛል። እንዲህ ሲሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ወይም አምነስቲ የተባለው ድርጅት ሰራተኞች ይሰሟቸውና፣ በደፋሪው ምትክ እነሱን እስር ቤት እንዳያስገቧቸው እላለሁ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ከባድ እንጨት ተሸክመው፣ ከእንጨቱ ክብደት የተነሳ አጎንብሰው፣ በሁለቱም እጆቻቸው ዱላ ተመርኩዘው፣ እንደ አህያ በአራት እግር በሚመስል ሁኔታ ሲጓዙ፣ ሰው አይቶ “አሁንስ አህያ መሰላችሁ”  ይላቸዋል። ታዲያ ለዚህ አባባል እነሱ ግድም አይሰጣቸው። "ኤዲያ! እንምሰላ! በማን እድላችን! አህያ እኮ ጠንካራ ነች፤ እንደዚሁም የእግዚአብሔር ፍጥረት ነች፤ እንዳህያ ጠንካራ ብንሆንማ ለልጆቻችን እንደ ሐብታም ልጆች ሚሪንዳ እየሰጠን፣ ሁለት ሁለት ፓስቲና ሳንቡሳ ገዝተን እያበላን እናሞላቅቃቸው ነበር” ሲሉ የሰሟቸው ሰዎች ነግረውኛል። በእነሱ ቤት ሚሪንዳ ፓስቲና ሳንቡሳ ትልቅ መጠጥና መብል መሆኑ ነው።
ደግሞም ሰው አህያ ሲባል “አንተ ነህ አህያ ብሎ” ለፀብ ይጋበዛል እንጂ እንዴት በማን እድላችን ብሎ፣ ባህያ ጥንካሬ ተመስጦ፣ ‘እንኳን ‘ብሎ መልስ ይሰጣል። አይ እናቴ! አይ አጓንዴ! የሚገርሙ ናቸው።
እንጨት ለቅመው ከእንጦጦ ሲመለሱ አንዱ ከፊት ሌላው ከኋላ ሆነው፣ ፊትና ኋላ መሆንን እየተለዋወጡ፣ አንዱ ሌላውን እየመራ፣ ማርያም ወንዝ እሸቴ አስፋው ጠጅ ቤት በታች፣ እንጨት የሚሸጡበት ቦታ ድረስ ይጓዛሉ።
አብዛኛውን ጊዜ የሚሸከሙት እንጨት ወደ ጎን ሲታይ፣ ረጅም ስፍራ ስለሚይዝ ባስፋልት ላይ ሲሔዱ የመኪና መንገዱን አብዛኛውን ስፍራ ይሸፍኑታል። ከዚህ የተነሳ እነሱ ባሉበት አካባቢ ከታች በኩል ሆነ ከላይ በኩል የሚያልፍ እግረኛ፣ ባለ አህያም ሆነ ባለ መኪና እንደ ልቡ መንቀሳቀስ ይቸገራል።
አንዳንድ ጊዜማ እነሱ በስፋት ሲሔዱ መንገድ ይዘጋጋና፣ በመንገዱ ላይ ትልቅ የመኪና አደጋ እንዳጋጠመ አይነት መንገዱ ጭንቅንቅ ብሎ ክላክስ በክላክስ ይሆናል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ የገበያ ቀን በሚባሉ ቀኖች፣ ባህያ ዕቃ ተሸክመው ወደ ከተማ የሚሔዱ አህዮች ስለሚበዙ የእናቴና የአጓንዴ እንጨት አስፋልቱን ይይዘውና፣ አህዮቹ መተላለፊያ ያጣሉ፡፡ ይህን ጊዜ ታዲያ “ጎዲን ጎዱን “የሚለው የአህያ ባለቤቶች ማስጠንቀቅያ ይበረክታል።
አንድ ቀን ከላይ ከሱልልታ የሚመጡ ባለ አህዮች እንደተለመደው፣ “ጎዲን ጎዲን” በማለቴ እናቴንና አጓንዴን በጣም ግራ አጋቧቸው፤ “ምን ጎዲን ጎዲን ትላላችሁ፤ አታዩም እንዴ? እኛም እኮ አህዮች ነን፣ ባለ አህያ ሆናችሁ፣ ለአህዮች አታስቡም እንዴ?; አለቻቸው እናቴ።
አጓንዴ ደግሞ በተራዋ “እኛም እኮ እንቸኩላለን፣ ማርያም ወንዝ እኮ ቡና ሱሳቸውን ለማስታገስ፣ ቆሎ ቆልተው የልጆቻቸውን ርሐብ ለማስታገስ፣ እንጎቻ አንጉተው ለሚወዱት ባላቸው ለማብላት፣ በማርያም ወንዝ እንጨት ገበያ ተሰብስበው የሚጠብቁን ብዙ ደንበኞች አሉን። እነዚህ ደንበኞች እኮ እንደ ሌሎች ሰዎች የኮረንቲ ምጣድና ምድጃ የላቸውም” ስትል ንዴቷን ገለፀች።
ይህን ጊዜ “ጎዲን ጎዲን” የሚሉት ባለአህዮች፣ የእናቴንና የጓደኛዋን ሁኔታ የተመለከቱት ሁለት ኦሮሞ ሴቶች በጣም ስላዘኑ፣ ያህዮቻቸውን ጭነት አሸጋሽገው እናቴና አጓንዴ የተሸከሙትን ባህዮቻቸው ጭነው፣ እንጨት የሚሸጡበት ማርያም ወንዝ ድረስ አድርሰውላቸዋል። ሌላ ጊዜም ተመሳሳይ የመንገድ መጨናነቅ ተፈጥሮ፣ የተፈጠረውን የትራፊክ ችግር ለመፍታት አንድ የሚኒ ባስ ሹፌር ጭነታቸውን በታክሲው ጭኖ እዚያው መሸጪያ ቦታቸው ድረስ አድርሷቸዋል።
ከዚህ የተነሳ እናቴም ሆነች አጓንዴ እነዚህን ሁለት ኦሮሞ ሴቶችና ባለሚኒባሱን ጨምሮ፣ የቁስቋም ማርያም ማህበር ሲደግሱ ሳይጠሯቸው ቀርተው አያውቁም። ባለአህዮቹም ሆነ ባለሚኒባሱ እቤታቸው ድግስ ካለ፣ በተመሳሳይ፣ እናቴና አጓንዴን ጠርተው ይጋብዟቸዋል።
በዚህ የተነሳ እናቴ ልትድረኝ የምትፈልገው፣ ሱሉልታ ድግስ ተጠርታ ሔዳ ያየቻትን፣ ከእነዚያ ቅንና ደግ ከሆኑ ኦሮሞዎች ውስጥ ያንዱ ልጅ የሆነችውን በቀሉን ነው። አይገምም! እንግዲህ እነዚህ ባንድ ቀን ተደፍረው ባንድ ቀን ያረገዙ፣ በተመሳሳይ ቀን የወለዱ፣ ተደፍረው ልጅ መውለዳቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚመለከቱ፣ እንጦጦ ሲወጡ ተለያይተው የማያውቁ፣ ከእንጦጦ እንጨት ተሸክመው ሲመለሱም ፊትና ኋላ ሆነው ዳገቱን ከመውረድ ውጪ ተራርቀው የማያውቁ ጓደኛሞች፤ ሰሞኑን ግን አጓንዴ ከእነ ጥግርር እንጨቷ፣ በቴሌቪዥን ከዶ/ር ዐቢይ ኋላ ሆና ብቻዋን ታየች።
ለነገሩ "ብቻዬን ሆኜ ፍቶግራፍ አታንሱኝ፣ ጓደኛዬን እምሬን ጠብቋት፣ ከኋላዬ እየመጣች ነው፣" አያለች ነው አሉ፣ ፎቶግራፍ አንሺዎቹ ቸኩለው፣ አጓንዴን ለብቻዋ አንስተው በቴሌቪዥን እንድትታይ ያደረጓት። በዚህ የተነሳ አጓንዴ ብዙ ጊዜ ትፀፀታለች፤ “እንዴት ተለያይተን የማናውቀውን ሰዎች፣ ካንቺ ከጓደኛዬ ለይተው፣ ከዶ/ር ዐቢይ ፊት ለፊት እንድታይ ያደርጉኛል፤ የኦሮሞ ባለ አህያ ሴቶችና ባለሚኒባሶች ይህንን ጉድ በቴሌቪዥን ሲያዩ ምን ይላሉ!?” ትላለች።
አሁንማ እንኳን ለአባይ ግድብ፣ እንኳን ለእንጦጦና ሸገር ፓርክ፣ እንኳን ለደን ልማት ፕሮግራም ---ወዘተ አጓንዴና እናቴ ስራ አግኝተዋል። የሸገር ፓርክ ሠራተኛ ሆነዋል። ከደን ነቀላ ወደ ደን ተከላ ስራ ተዛውረዋል። ቢሆንም ግን እነዛ የእነሱን ጉልበት ጠብቀው
የእለት እንጎቻቸውን አንጉተው የሚበሉ፣ የዕለት ቡናቸውን አፍልተው ፉት የሚሉ የእንጨት ደንበኞቻቸው ጉዳይ አሳስቧቸው ነበር። ሰሞኑን ደግሞ የህዳሴው ግድብ ድምፁ ሳይሰማ ሞልቶ ተገኘ ተባለ። እናም "እኛ ከእንጨት ሸክም እንደወጣን ሁሉ፣ ደንበኞቻችንም ከጭስ አፈና ሊወጡ ነው" እያሉ ነው። እንዳፋቸው ያድርግላቸው፡፡Read 3311 times