Print this page
Sunday, 22 August 2021 12:14

‹የያ ትውልድ› መርገምት

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

  (የአንዲት ገጽ ሙሾ ለመከነው ትውልድ)
                                 
            ሰሞኑን ደርሶ በል በል የሚለኝ ደመነፍሴ አንደርድሮኝ፣ የአስማማው ኃይሉን ‹ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሺንግተን ዲሲ› የተሰኙ ሁለት ቅጽ መጻሕፍት ለሦስተኛ ጊዜ እያነበብኩ ነበር፡፡ ሦስተኛ ዙር ንባቤ ልክ የመጀመሪያ የሆነ ያኽል አቅሌን እስክስት ድረስ መቆዘምን አሸከሞኝ ሰነበተ፡፡ ስለ ብዙ ነገሮች አውጠነጠንኩ፡፡ ከሁሉ በላይ አዕምሮዬን የተቆጣጠረው ግን ተሸንፎ በየፈተታው የሸሸው የዚያ ትውልድ አኳኋን ነበር፡፡ ያ ትውልድ መከረኛም፣ ጉደኛም፣ ጀብደኛም እኮ ነው፡፡  
አያ ሻረው በዚሁ መጽሐፉ ቅጽ አንድ ገጽ 62 ላይ፣ አንድ ለየት ያለ የዚያን ስደተኛ ትውልድ ሕይወት አሳጥሮ የሚገልጽ ታሪክ ይተርክልናል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ ታማኝ ውሻ የነበረው አልቃድር የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ኑሮ አልሰምርለት ሲል የመከራ ጎጆውን ዘግቶ ላይመለስ ተሰደደ፡፡ ውሻው ለሳምንታት በቤቱ በር ላይ ኩርምት ብሎ ጌታውን ሲጠብቅ ከሰነበተ በኋላ በተኛበት ሞቶ ተገኘ፡፡ ምናልባት እኮ የመንደሩ ሰው የሚሰጠውን ምግብ ሁሉ ለጌታው ያለውን ታማኝነት ለማሳየት ሲል፣ እስከ ሞት ችላ ብሎም ይሆናል፡፡ ሌላኛው ይሄንኑ የአልቃድርን ውሻ መጨረሻ የተመለከተና ሕይወት የከፋችበት የመንደሩ ነዋሪ፣ ይህችን አንጀት የምታላውስ ቅኔ እያንጎራጎረ ተሰደደ።
‹‹እሄዳለሁ እንጂ እሄዳለሁ የትም
እንደ አልቃድር ውሻስ ስጠብቅ አልሞትም››  
ለእኔ ስደተኛው ያ ትውልድ፣ የአልቃድርን ውሻ መሆንን እንደሸሸው፣ የዚያች መንደር ነዋሪ ነበር፡፡ ከኤርትራ ተራሮች እስከ አሲምባ፣ ጸለምትና በለሳ የተፋፋመው የሜዳ ትግል፣ ቀስ በቀስ ተዳከመ፡፡ የከተማ የትግል መረቡ በመጣጠሱም የተቀናጀ አመራር የሚሰጠው አካል ጠፋ። መላኩ ተገኝ በቅርቡ፤ ‹ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም› በተሰኘ የዚያን ትውልድ ዝንቅ ገድል የሚያወሳ መጽሐፋቸው፤ የኢሕአሰን ትግል ለማስቀጠል የተደረገው ሙከራ ምን ያህል የተወታተበ እንደነበር በጥቂቱ ዘግበውታል፡፡ በሌላኛውም ፈርጅ፣ በየፊናው የተፋፋመው ትግል ‹በፊሽካ› ተበትኖ፣ ወደ ስደት የተተኮረው ወዲያው ነው፡፡ ሁሉም ነገር ያበቃው በድንገት ይመስላል፡፡ ለአያ ሻረውና መሰል የዚያ ትውልድ አባላት፣ አሲምባ ከፍራንክፈርትና ለንደን ይልቅ፣ ለቸንከር ተክለሐይማይኖት ይቀርባል፡፡ የተገኙት ግን የጥያራ ሰረገላ እየጋለቡ ኒውዮርክ ሆነ፡፡ ምናልባት ከዚያ የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም ይሆናል፡፡
ሆኖም አያ ሻረው፣ እንደ ሺህ ዘመናት የራቁ፣ ሰላሳ ዓመታት እስቲፈራረቁ፣ ወደ ቸንከር ተክለሐይማኖት አልተመለሰም፡፡
‹‹የቤታችንን አቅጣጫ አልሳትኩትም። ደመነፍሴ እየመራ ወስዶኛልና፡፡ ሠላሳ ዓመታት በሕይወቴ ላይ ያስከተሉትን ለውጦች አጉልቶ ያሳየኝን ያህል ትልቁን መረጃ ግን አላካተተልኝም፡፡ በቸንከር ተክለሐይማኖት መንደር መሀል ቆሜ ቸንከርን እየተመለከትኩ ቸንከሬ መሆን አቃተኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሬ በሕሊና ታቅፌው ስዞር የከረምኩት የአስተዳደጌ ትዝታ ከእውነታው ጋር አልተዛመደም። ቤታችንን ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ባይወስድብኝም የቆየኝ ስዕል ግን ከሠላሳ ዓመት በኋላ እንደተመለሰ ሳይሆን፣ ከኖህ ዘመን የውኃ ጥፋት  በኋላ የተረፈ ሕይወት ለመፈተሽ የመጣሁ ታዛቢ አስመሰለኝ፡፡›› (ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሺንግተን ዲሲ፤ ቁጥር 2፤ ገጽ 174)
የሌላውም የአብዛኛው ስደተኛ ትውልድ እውነት ከዚህ የተለየ አይመስለኝም። ያ ትውልድ፤ ለትግል አጋሮቹ የገባውን ቃልኪዳን ጠብቆ፣ እንደ አልቃድር ውሻ መሆን አልተቻለውም፡፡ እናም ርዕዩን፣ ጓዶቹን፣ ሀገሩን፣ ማንነቱን ተዘርፎ እርቃኑን ተበተነ፡፡ በዓለም ላይ ያልገባበት የለም፡፡ እነሆ በዚያ ትውልድ ሰበብ፣ ስደት ከረሀብ እኩል፣ የኢትዮጵያችን አንገት መድፊያ ከሆነ ይሄው ድፍን ሀምሳ ዓመት ሊሞላው ምን ቀረው?
እኔ ግን ዘወትር የአያ ሻረውን የመሳሰሉ፣ የምር ከተኖረ ሕይወት የተጨለፉ መጻሕፍት ሳነብ፣ የአንድ ደቂቃ ስልጣን በኖረኝ ይሉት የጅል ምኞት እመኛለሁ፡፡ የአንድ ደቂቃ ስልጣን ባገኝ ተጣድፌ ሁሉም ሰው ለህሊናው ታምኖ፣ ግለ ታሪኩን ይጽፍ ዘንድ አዝዝ ነበራ! እመኑኝ፤ግለ ታሪኮችን ማንበብ ሌላ ማንኛውንም ነገር ከማንበብ በላይ የሚያስጎመጅ፣ የሆነ የሚፋጅ ሕያው ትንፋሽ ነገር አለው፡፡
ዘወትር የሚሆነው እንዲያ ነው፡፡ የምር ከተኖረ የህይወት ምንጭ የሚቀዱ መጻሕፍት ነፍሴን ለሳምንታት የማስቆዘም ኃይላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እኔ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (አንዳፍታ ላውጋችሁ)፤ ‹ግለ ታሪክን መጻፍ የእወቁኝ ቅስቀሳ ነው› አልልም፡፡ እንዲያውም በሌላ ዘመን፣ በሌላ ቦታ፣ በሌላ ሰው ምናብ፣ በሌላ ሰው የነፍስ መሻት ውስጥ የመመላለስ የቅንጦት ግብዣ እንጂ…
ራልፍ ኤመርሰን በ1841 እ.ኤ.አ በጻፈው history በተሰኘ አስደናቂ መጣጥፉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹There was neither history nor fiction- ONLY biography. If the whole of history is one man, it is all to be explained from individual experience.››
እውነትስ በእያንዳንዱ ግለሰብ እርቃን የነፍስ ጥጋት ተጠልለን ካላደመጥነው፣ ታሪክ ራሱ ምንድን ነው? በየትኛምው ሀገር ስለ ማንኛውም ዓይነት ሰው ይጻፍ፣ ግለ ታሪክ ዘወትር ለንባብ የሚያስጎመጅ ምርጫ ነው፡፡ በተማሪነት ዘመኔ የመጨረሻ ዓመታት (ከሚሊኒየሙ ማግስት) የአያ ሻረውን ‹ታሪካዊ ልብወለድ› የሚል ማደናገሪያ የተሸከመውን ይሄንኑ ቅጽ አንድ መጽሐፍ መንገዶች ላይ ባየሁት ጊዜ ሁሉ ፈገግ ያሰኘኝ ነበር፡፡ ርዕሱ አለቅጥ በመርዘሙ ይዘቱም የሆነ በተሀ ነገር መሆን አለበት የሚል የተሳሳተ ቅድመ ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን ላይ ሳስበው አያ ሻረው ልክ ነበር፡፡ ይሄን ለመሰለ ቅጥ አምባር የሌለው የዘመን ስሪትና ሕይወት፣ ፌዝ የመሰለ ርዕስ ብቻ ነው የሚመጥነው፡፡     
ያ ትውልድ ግን እውነትም ግራ ነገር ነበር… ሕይወት፣ ቀያይ መጽሐፍ እየገለጠ ሀገር ለምትቀድምበት ጓዳዊ ሕልም ተንጠራውዞ፣ ወፍ ዘራሽ ትልም እንዲያጠምድ ስትፈርድበት፣ በእልህ ባወገዛቸው ኢምፔሪያሊስቶች መንደር፣ ሰብሳቢ እንደሌላቸው ጫጩቶች፣ ለግርድና በተነችው፡፡ ግርድና እና ባርነቱ ከትውልዱ አልፎ፣ ለልጅ ልጅ ልጁ ሁሉ የሚተላለፍ ፈውስ የለሽ ደዌ የመሆኑ ነገር፣ ለአያ ሻረው፣ በመጀመሪያዋ የአሜሪካን ሀገር አዳሩ ፍንትው ብሎለታል፡፡
‹‹በዚህች የመጀመሪያ እንቅልፍ የለሽ ሌሊት፣ ከክላሽን እስከ ልዩ ልዩ ከባድ መሳሪያዎች ታጥቀን ድባቅ ልንመታው ክፉኛ የዛትንበት ኢምፔሪያሊዝም፣ አንድም ጥይት ሳያጮህ እያባበለ፣ በሰፊው ሆዱ ውስጥ ካስገባን በኋላ፣ ድራሻችንን የጨው ዘር ማድረግ እንደሚችልም ተሰማኝ፡፡›› (ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሺንግተን ዲሲ፤ ቅጽ አንድ፤ ገጽ 11)
ያ ትውልድ፣ የተሳከረ ሕልሙ ሲፈርድበት፣ ከሜዳ ቀሰስተኛ ሕይወት በአንድ ጊዜ ወደ ኒውዮርክና ፍራንክፈርት ጥድፊያ አንደረደረው፡፡ እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋው ‹ሰርቦላ› ሆነ፡፡ ለዓላማ ሲባል ዓይኑን አጉረጥርጦ ለሞት ይጣደፍ የነበረው ትንታግ መንጋ፣ በአንዳች ምች ተጠናግሮ፣ ለፍቅር ባይተዋርነትን ተከናነበ፡፡ ከታንክ ጋር የተናነቀው ጓድህ፣ ለሴት ግልምጫ ተልፈስፍሶ፣ በበር ቁጡ ጥፊ በርገጎ አየነው። ብቸኛ መጽናኛው፣ በውስኪ አርጩሜ የሚደነብር የስካር ፈረስን እየጋለቡ፣ ትዝታን ማባበል ሆነ… ይኸው ካላመንከኝ አንብበው። ሆኖም አያ ሻረው፣ ከሌላው የትግል ጓዱ በተለየ ግልጽና ደፋር ሆኖ ከትግል መልስ የገጠመውን ፈተናና ገመና ገላልጦ፣ ሕይወቱን ለውይይት ክፍት በማድረጉ ልናወድሰው ይገባል እኮ…
አንተ ለመፋቅ ካልታከተህ ያት ትውልድ፣ ዘወትር ሌላ ገጽ አለው ጓዴ፡፡ ዘወትር ያልደረስክበት፣ያላወቅኸው፣ ያልዳሰስከው ሌላ ጉደኛ ታሪክ አለው፡፡ በባዶ ሜዳ በየቁጥቋጦው ስር ያቃተተው ምኞቱ፣ እንደ መጸው ደመና የተራቆተ ነው፡፡ እውነትም ‹ማማ በሰማይ› ዓይነት… ዛሬ በሰራው እንዳይኩራራ እንኳን የድል ዜማው አዝማቹ ተዛብቷል፡፡ የሽንፈት እንጉርጉሮውም እንደቆረፈደ ልቅሶ፣ የሚያባባ ቃናው መቅን ያንሰዋል፡፡ ዘፈኑም ሙሾውም ቀስ በቀስ ሰሚውን ሰልችቶታል፡፡
ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉቬራ  
ብሎ ፉከራ አሁን ላይ ሲያስቡት የነበረ እንኳን አይመስልም አይደል? አዎ በውጥን የቀረው ሕልሙ፣ በጅምር የተረሳው ምኞቱ፣ ለዘለዓለም አስታዋሽ ያለውም አይመስልም። የሚኩራራበት ገድሉ አይደለም፤ ለእኔ እና አንተ እንዲሁም ለነጭ አሳዳሪዎቹ፣ ለወለዳቸው ልጆቹ እንኳን የሚዋጥ አልሆነም፡፡ ይህንን አጋጣሚ የሚነግረን አያ ሻረው፣ ከላይ በጠቀስኩልህ መጽሐፉ ቅጽ ሁለት ላይ ነው፡፡ ልጆች በዕድሜ ከፍ ከፍ ማለት እንደጀመሩ፣ ወላጆች አንድ ቀን ቁጭ አድርገው፣ ለሀገር ሲባል ጠብመንጃ አንግበው የሚታገሉ፣ ትንታግ የሜዳ ሰዎች እንደነበሩ በኩራት መናገር ጀመሩ፡፡ ወዲያው ልጆች በድንጋጤ በርግገው፤ ‹‹Oh God ! you killed people ?›› (አምላኬ ሆይ! ሰው ገድላችኋል ማለት ነው?) ብለዋቸው ቁጭ። እናስ ልጅ የማይዘምረው የእናትና የአባት ገድል ምን ዓይነት ገድል ነው?
ስደተኛው ያ ትውልድ፣ የሚጋልብበት ኢምፔሪያሊስታዊ ቅኝት፣ የባህል መጠናገር ቀንበርን አሸክሞ ረብ ለሌለው የግዞት ሕይወት፣ ሌሊት ተቀን ሲያጣድፈው አየነው። ትናንት ላንቺ ነው እያለ እየተመጻደቀ የገደለባትና ሊሞት የቆረጠላትን ሀገር ክዶ፣ ‹ለግሪን ካርድ›ና ‹ለፉድ ስታምፕ› (food stamp) የሚኮለኮል ምንዱብ ወጣው፡፡
በእርግጥ ያ ትውልድ እነ አፈወርቂን፣ እነ ዜናዊን፣ እነ ስምዖንን፣ እነ ጉዲናን፤ የገደለውን፣ የሞተውን፣ የኮበለለውን፣ የጠቀለለውን፣ ሪቮውን፣ ሳቦተሩንም ሁሉንም ያካትታል፡፡ ያ ትውልድ ሲያድር፣ አሰላለፉ የየካቲት ስደተኛም ይሁን የግንቦት አብዮተኛ፣ ከወቀሳ አያመልጥም። ዛሬም በውጭም በውስጥም ተሰግስጎ፣ የዚህችን ድሃ ሀገር ጉሮሮ የሚያደማው እሱ ነዋ። ዛሬስ በየጎሬው መሽጎ መንጋ ሊያዘምት፣ ጭብጥ የለሽ ጠማማ የታሪክ ትርክት ሊጎትት የሚማስነው ማን ሆነና ነው? እሱ እኮ ነው፡፡ አየህ ዛሬም ከትናንት ያደረ የአብዮተኝነት እልህ ይተናነቀዋል። ጸጸት? ኸረ ምን በወጣው! ሲያልፍም አይነካው። ዛሬም ከአርባ ዘመናት በኋላ፣ በደም ባቀለመው ፍኖቱ፣ ገድሎም ሆነ ሞቶ የበቃው አይመስልም፡፡
በእውን ኢትዮጵያ "የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት" የሆነችው በእነ ዋለልኝ መኮንን የልደት አዳራሽ ድንፋታ ዘመን ወይስ ዛሬ? እንደ አቦማ ምትኩ ዓይነት፣ የእነ አብዲሳ አጋ መሰል ብሔራዊ ስሜት የተሸከሙ ትንታጎችን፣ በአንድ አዳር ወደ ጠባብ ብሔርተኝነት ያንደረደረው ምን ሆኖ? ለመሆኑ ያ ትውልድ፣ ከራሱ አልፎ ለዚህች ብዙ ፍላጎቶችን የተሸከመች መከረኛ ሀገር የሚበቃ ውስጠ ዴሞክራሲያዊነት ነበረው? ነበረውን? ኢትዮጵያዊነት ዛሬ እንዲህ እጅ እግር የሌለው ማጥ ውስጥ የገባው በዚያ ትውልድ ከእነ ጭራሹ ብስለት የሌላቸው መራዎጦች አይደለምን? እናት ሀገር እንዳትድን ሆና የታመመችው በማን ሆኖ?
ሻራኒያ ሀሪዳስ የተሰኘች አሜሪካ ውስጥ የምትኖር ወጣት ህንዳዊት እንዲህ ትላለች፡- ‹‹A generation is not defined by the option it has but by the choice it makes.›› እናም እባክህ ዘመኑ ዓለም በሁለት ጎራ የተከፈለችበት፣ ቅኝ ግዛት… ዓይነት የሰለቸ ለቅሶህን ተወኝ፡፡ ለሁለት ጎራውም ቢሆን ሶሻሊዝም የአንድ ወቅት ፋሽን ሆኖ ኢትዮጵያን ባጥለቀለቀበት ሰሞን፣ የግራው ዓለም ቁንጮ ማሳያዎች፣ ሶቤት ህብረቶች እንኳን መሻገር አቅቷቸው የቁልቁለት ጉዞውን እየጀመሩት እንደነበር ንባባችን ይነግረናል፡፡
ያም ሆኖ ‹ያ ትውልድ› ሊደነቅ የሚገባው መልካም ገጽ አልነበረውም የምል ጭፍን አይደለሁም፡፡ ሆኖም ይህን ሀምሳ ዓመት ሙሉ የተዘፈነለት ጀብድ፣ ደግሜ በመዘብዘብ የተሰጠችኝን ኩርማን ገጽ የማባክን ጅልም አድርገህ አታስበኝ። ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ መላኩ ተገኝ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው፤ ‹ከሰንጋተራ እስከ አምስተርዳም› ማጠቃለያ ላይ፤ ‹‹ያ ትውልድ በ‹ቸ› እና በ‹ሸ› በባዕድ ርዕዮተ ዓለም የሰከረ ‹‹ከይሲ ትውልድ› ነበር፤ ለሚሉን ይህን የዳዲሞስን ባለ ሁለት ስንኝ ግጥም እጋብዛለሁ፡፡
‹‹ምን ይል ይሆን ዛሬ በትናንት ቢቃኘው
አንበሳ ተከሶ ዝንጀሮ ቢዳኘው፡፡›› ይሉናል፡፡
አንበስነቱን ውሰዱት፤ አንከለክላችሁም። ነገር ግን ያ ትውልድ፣ አጥፍቶ ጠፊ ወይም የእሳት ራት ካስመሰለው ክልፍልፍ ድፍረቱ ውጭ፣ ለዚህች ሀገር መድህን የሚሆን ምን የረባ ነገር ነበረው? አቶ መላኩ የራሳቸውን መጽሐፍ መልሰው ቢያነቡት እንኳን ያ ትውልድ፣ በውኃ ቀጠነ እሳት የሚወራወር ትውልድ እንደነበረ መታዘብ አይከብዳቸውም፡፡ አይግለበለብም እንጂ ይሄስ ትውልድ መመለስ ላይችሉ ነገር፣ የዚያ ትውልድ ጀብደኞች ከየአቅጣጫው በፉጨት የጠሩትን ጋኔል (የዘር ውርዴ)፣ ለመገላገል የሀሳብ ትግል እያደረገ እንደሆነ አያለሁ፡፡
የቀድሞው የደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ (ዳግላስ ጴጥሮስ) በረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዕትም፣ ‹‹ዘመነ ትውልዶች ‹ያትውልድ› ‹ይሄ ትውልድ››› በተሰኘ መጣጥፋቸው፤ ‹‹‹ያ ትውልድ› እያለ ለራሱ ስም የሚሰጠውን የማኅበረሰባችን ‹ጠፍ ትውልድ› የሚወክሉት ወጣቶች ብዙዎቹ የተወለዱት በተቀራራቢ ግምት በ1930ዎቹ መጨረሻና በ1940ዎቹ ዓመታት ውስጥ ነበር፡፡›› ይሉናል፡፡ እውነትም ጠፍ ትውልድ!  ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግስት የነጠረ የትምህርት ሥርዓት (በአንጻራዊነት) የተቀረጸው፣ ትውልድ ተጫርሶና ተበትኖ ሌላ የትውልድ ክፍተት (Generation gap) እንዲፈጠር ሰበብ የሆነ ‹ጠፍ ትውልድ›፡፡

Read 2101 times