Print this page
Monday, 23 August 2021 00:00

ሕይወት፣ ግሩም ናት? ከነ አደጋዋና ከነ አለኝታዋ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  ነገሩ የስራ ማስታወቂያ መሆኑ ነው። ለጋዜጣ የተዘጋጀው የማስታወቂያ ፅሁፍ እንዲህ ይላል።  ለአደገኛ የምርምር ዘመቻ፣ ሰው እንፈልጋለን።
ጉዞው የጣር እና የመከራ ነው።  በሕይወት፣ በደህና መመለሳችን ያጠራጥራል። ክፍያው፣ እዚህ ግባ የሚሉት አይደለም። ትርፍ የለውም።  ብርዱ መራራ ነው። ለረዥም ወራት በጨለማ የተዋጠ ነው። ከአደጋ እፎይታ የለም። ምናልባት ጉዞው ከተሳካ፣ ከግባችን ከደረስን ግን፣ ትልቅ ክብር ትልቅ ዝና ይሆናል።
                     
           ማስታወቂያው፣ ለአንታርክቲካ ጉዞ የተዘጋጀ ነው - በበረዶ ወደተሸፈነው ወደ ደቡብ ዋልታ። አዎ፤ ጉዞው አስቸጋሪና አደገኛ መሆኑ አይጠየቅም። የምርምር ጀብድ ለመስራት፣ እንዲሁም ከባድ ፈተናዎችን ለማሸነፍና ትልቅ ገድል ለመፈፀም የተጓዙ በርካታ ጠንካራ ሰዎች፤ ብዙ ተሰቃይተዋል። በወጡበት ቀርተዋል።
ነገር ግን፣ ከባድ ፈተናዎችን የማሸነፍና ትልቅ ገድል የመስራት ፍላጎት፤ በሰው ልጅ ውስጥ ሁሌም ይኖራል። ለጊዜው ቢዳፈንም እንኳ፣ ጨርሶ የሚጠፋ አይደለም። የጀግንነት ፍላጎት፣ ከዘላለማዊ የሰው ተፈጥሮ የሚመነጭ፣ የሰው ልጅ ውስጣዊ የመንፈስ ረሀብ ነው፡፡
ወደ ላቀ ደረጃ የመገስገስ፣ ወደ ከፍታ የመምጠቅ፣ አስፈሪ ገደሎችን የመሻገር፣ ወደ አዲስ ድንቅ ምዕራፍ የመንጠራራት መንፈሳዊ ፍላጎት፣ ከሰው ውስጥ ሊጠፋ የማይችል፣ ሊጠፋም የማይገባው ተፈጥሯዊና መንፈሳዊ ኃይል ነው - ክቡር የሰው ማንነት ጉልላት።
የኤቨረስት ተራራን አቀበት ታግለው፤ በረዶውንና ገድሉን አሸንፈው፣ የተራራው አናት፣ የሰማይ ጥግ የደረሱ ሰዎች ምን ይላሉ? ለነገሩ፣ ካሰበቡት ሳይደርሱ የቀሩና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችም፣ ምስክር ናቸው - በቃል ባይነግሩንም።
ጉዞው አደገኛ ነው። በርካታ መቶ ተጓዦች፣ በድካም አካላቸው ዝሎ፣ በቅዝቃዜ ሁለመናቸው ደንዝዞ፣ የተራራው ሰለባ ሆነዋል። በበረዶ ደርቀው፣ በበረዶ ናዳ ተቀብረው ቀርተዋል። ከገደል ተንሸራትተው ተከስክሰው ሞተዋል።
“እያንዳንዷ ደቂቃ፣ የ60 ሴኮንድ ስቃይ” ናት። ለቅጽበት ታክል ቅንጣት  ፋታ የሌለው ቆፈን፣ ናላን ያዞራል። እያንዳንዷ እርምጃ የተራራ ያህል ትከብዳለች፡፡
እልፍ ጊዜ፣ “በቃኝ” ለማለት አፋፍ ደርሰው፣ ጉዟቸውን ሳያጋምሱ የኋሊት ለመመለስ እልፍ ጊዜ አመንትተው፣ የዚያኑ ያህል እልፍ ጊዜ፣ በፅናት ለመቀጠል ይራመዳሉ። ጣር መከራቸውን አይተው፣ የዓለም ማማ ላይ ሲደርሱ፣ ሰማዩን ሲነኩ፤ ምን ይሉ ይሆን? ሆይ ሆይታና ጭፈራ፤ ሳቅና ጨዋታ አያምራቸውም። ኪስ የሚገባ ምንም ትርፍ አያገኙም። ክፍያ የለውም። የሚጨብጡት የሚዳስሱት ቅርስ፣ ለምልክት ያህል እንኳ በእጃቸው አይቀርም። የጉዞ ዱካቸውም፣ ከሴኮንዶች ያለፈ እድሜ አይኖረውም - በረዶ ይሸፍነዋል። ቢሆንም፣….
በርካቶቹ እንዲህ ይላሉ። “የማላውቀው የራሴን ማንነት አወቅኩ” በማለት ይናገራሉ። አዎ፤ የሚያጨበጭብላቸውና የሚያደንቃቸው ሰው ይኖራል። የፅናትና የብርታት አርአያ ናቸው፡፡ ግን፣ አደገኛው ጉዞ፣ ለራሳቸው ለተጓዦቹም ይደንቃቸዋል። በአደገኛው ጉዞ አማካኝነት፣ አንዳች ድብቅ ሚስጥር፣ አንዳች የማይታመን ተዓምር ያዩ ያህል ይገርማቸዋል።
እያንዳንዷ የአደጋ ሴኮንድ፣ የሕይወትን ውድነት የምታሳይ ሴኮንድ ናት።
እያንዳንዷ እርምጃ፣ የሰውን ልጅ የአላማ ፅናትና የተግባር ብርታትን የምትመሰክር እርምጃ ናት - የሰው ብቃት የምታወድስ።
ይሄ ነው የአደገኛው ጉዞ ምትሃት። ለካ፣ የክብር ሁሉ ምንጭ፣ የሕይወት ውድነትና የሰው ብቃት ነው የሚያስብል ምትሃት።
ከሕይወት ውድነትና ከሰው ብቃት ውጭ፣ ለካ ሌላው ነገር ሁሉ ትርጉም ያጣል! ከዚህ እውነት ጋር፣ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር፣ በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በእውን መገናኘት፣ አዲስ ዓለም ውስጥ እንደመግባት፣ እንደገናም እንደመወለድ ሆኖ ቢሰማቸው አይገርምም።
እውነትም፣ እስከ ጫፍ ድረስ፣ ባለ በሌለ አቅም ሁሉ፣ በሙሉ ሃሳብ፣ በሙሉ አካልና በሙሉ መንፈስ፣ ከመቼም ጊዜ በላይ የመንጠራራትና የእመርታ ገድል፣ እጅግ አስደናቂ ነው። ሞክረው እስኪያዩት ድረስ፣ ጎልቶ ጠርቶ አይታይም። ተገልጦ ባይታይም ግን፤ ሁሌም የሰው ማንነት ውስጥ አለ። ከሰው ውስጥ የማይጠፋው የጀግንነት ረሃብ፣ በግላጭና በእውን፣ ገዝፎና ደምቆ፣ በገሃድ የመውጣት መንፈሳዊ ግፊት የሚፈጠረውም፤ ከዚሁ ተፈጥሯዊና መንፈሳዊ የሰው ልጅ የማንነት ምንጭ ፈልቆ ነው።
መተማመኛህ አንተ ራስህ፣ አለኝታሽ አንቺ ራስሽ!
ወደ ገደላማና ወደ ተራራማ ፓርክ የሚያስገባ መንገድ ላይ፣ ለተጓዦች የተፃፈ መልዕክት ደግሞ አለ። “ማንም አይደርስብህም፤ ማንም አይደርስልህም” የሚል ነው፤ የፅሁፉ መልዕክት። ቦታውና ጉዞው በጣም አደገኛ ነው።
ተጓዦች ይህን አደጋ አውቀውና ፈልገው፣ በራሳቸው ፈቃድ ነው የሚመጡት - ራሳቸውን ለመፈተን።
አደጋውን ሳያውቅ፣ አልያም በግዴታና በትዕዛዝ የሚመጣ ተጓዥ የለም።
“ለጉዞ የሚያስፈልግ ልብስ፤ የጉዞ ጫማና ምርኩዝ፣ ጓንትና ቆብ አሟሉ” ብሎ የሚመክር፣ የሚቆጣና የሚቆጣጠር ሰራተኛ በፓርኩ አልተቀጠረም።
“ማደሪያ ድንኳንና የእሳት መለኮሻ ክብሪት አምጡ። በረሃብና በጥም ላለመሞት በቂ ምግብና ውሃ ያዙ። የጤና ምርመራና የልምምድ ዝግጅት አድርጉ”… እንዲህ አይነት መመሪያዎችን የሚያወጣና የሚቆጣጠር ሰው በፓርኩ ውስጥ የለም።
ከራስህ በላይ ላንተ የሚያስብልህ  ሰው ከየትም አይመጣም። እንደ ወላጅ ሃላፊነት የሚወስድልሽ፣ እንደሞግዚት የሚቆጣጠርህ የፓርክ ሰራተኛ የለም።
“እዚህ ፓርክ ውስጥ፣ የቁጥጥር መመሪያዎች የሉም። ችግር ቢያጋጥምህ፣ ብትወድቅ፣ በአንዳች ምክንያት አደጋ ቢደርስብህ ወይም አደጋ ውስጥ ብትገባ፣ የሚደርስልኝ ይኖራል ብለህ አታስብ። ነፍስ አድን ባለሙያ፣ ፈጥኖ ደራሽ  ቡድን የለም። ለራስህ ያለኸው አንተው ራስህ ብቻ ነህ። ለራስሽ ያለሽው አንቺው ራስሽ ብቻ ነሽ።” የሚል ሃሳብ ያዘለ ነው - የማስታወቂያው መልዕክት።
“You are on your own” ለማለት ነው - ባጭሩ። “በፈቃድሽ እንደገባሽ፤ ስራሽ ያውጣሽ።” በምርጫህ እንደገባህ፤ ስራህ ያውጣህ” እንደማለት። መተማመኛህ አንተው ራስህ፤ አለኝታሽም አንቺው ራስሽ።
ተጓዦች፣ ይህን አውቀው አደገኛውን ጉዞ ሲጀምሩ፤ በውስጣቸው የነበረ አንዳች የሕይወት ኃይልና የገድል መንፈስ፣ እንደ አዲስ ሲፍለቀለቅ ይሰማቸዋል።
ከዚያ በፊት ለበርካታ ዓመታት ልብ ያላሉት የሕይወትና የኑሮ ገፅታ፤ እንደ አዲስ ቦግ ብሎ ይታያቸዋል። ደብዝዞና ተሸፋፍኖ ከቆየው፣ ከውስጣዊውና  ከድንቅ የግል ማንነታቸው ጋር በግላጭ ይገናኛሉ።
“የሕይወት ውድነትና ትርጉም”፣ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ፤ ድንገት የተገለጠላቸው ያህል ይባንናሉ። ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ሕይወትን ያጣጣሙና የግል ምሉዕ ማንነትን የተጎናፀፉ ያህል ይደነቃሉ።
የዘወትር ኑሮ ሌላ፤ አደገኛ ጉዞ ሌላ!
በእርግጥ፣ የዘወትር ኑሮ፣ ከአደገኛ ጉዞ ይለያል። እንዲያውም፤ የህልውና አላማ፣ “የኑሮ አደጋዎችን አስቀድሞ ከመከላከልና ከማስወገድ” ጎን ለጎን፣ “ኑሮን የማደላደልና የማሻሻል፤ ሕይወትን የማለምለምና የማጣጣም አላማ” ነው።
“አደጋን ፍለጋ” አይደለም - የህልውና አላማና ትርጉም።
በዚያ ላይ፣ የዘወትር ኑሮ፣ ለየብቻ የተነጣጠለ የባይተዋር ኑሮ ማለት አይደለም። መማማርና መገበያየት፣ መቅጠርና መቀጠር፣ መሸጥና መግዛት የተሰኙ ነገሮች አሉ። ኑሯችንን የምናደላድለውና የምንመራው፣ በአብዛኛው በእነዚህ የእርስ በርስ ግንኙነቶች አማካኝነት ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
አድናቆት፣ አክብሮት፣ አርአያነት፣… ከዚያም በላይ፣ ወዳጅነትና ፍቅር የተሰኙ አካላዊና መንፈሳዊ ትስስሮች አሉ። ከእነዚህ የሚፈልቁ ቅርንጫፎችም በርካታ ናቸው።
መበዳደርና መዋዋስ፣ ውለታና ልግስና፣ መተባበርና መደጋገፍ፣… ከባሰም፣ እርዳታና ምፅዋት የምንላቸው ነገሮች አሉ። በሕይወት ለመትረፍና ፈተናን አሸንፎ ለመውጣት የሚያግዙ፤ እንደገና የማንሰራራት፣ በራስ ጥረትም ሕይወትን ወደ ማለምለም የመሸጋገር እድልን የሚከፍቱ በጎ ግንኙነቶች ናቸው።
ምናለፋችሁ
የዘወትር ኑሮ፣ “አደጋን እያነፈነፉ የመፈለግ ጉዞ” አይደለም።
የዘወትር ኑሮ፣ “የተነጣጠለ የባይተዋር ኑሮ” አይደለም።
እንዲህም ሆኖ፤ የሰው መሰረታዊ ተፈጥሮ፤ የግል ሕልውና ነው።
የእያንዳንዱን ሰው የሕይወት ውድነትና የግል ብቃትን ማክበር ነው አላማው፡፡
የጋራ አእምሮ፣ የጋራ አካል፣ የጋራ ማንነት ብሎ ነገር የለም። አዎ፤ በብዙ ሰዎች ዘንድ፣ ተማሳሳይነትን እናገኛለን። ተመሳሳይ ባሕርይ፣ ተቀራራቢ መልክ፣ የሚያስማማ ሃሳብና ንግግር ይኖራል።
ይህንን ለመግለፅም፣ “የጋራ ኑሮ፣ የጋራ ሃሳብ”… የሚሉ አባባሎችን ብንጠቀም እንኳ፣ ቃል በቃል፣ “የጋርዮሽ ሕልውና” እንደማለት መቆጠር የለበትም። የጋራ ሃሳብ ማለት፣ “አንድ ትልቅ የጋራ አንጎል” ማለት አይደለም። “የጋራ ኑሮ” ማለት፣ ትናንሽ ሰዎችን ሁሉ እየሰለቀጠ እንደተራራ የገነነ “አንድ የጋራ አካል” ማለት ሊሆን አይችልም።
የሰው ተፈጥሮ፣ በእውን እንደዚህ አይደለምና።
አንድ ሰው አወቀ ማለት፣ ሌሎች ሰዎችም ሁሉ አወቁ ማለት አይደደለም - በየግላቸው አስተውለው ወይም ተምረው፣ በየግላቸው ካልተገነዘቡ በቀር።
አንድ ሰው፣ በሙያው ጥበበኛ ቢሆንና በተግባርም ቢገነባ፤ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፤ እዚያው በዚያው፣ የጥበብና የሕንፃ ባለቤት ይሆናሉ ማለት አይደለም - በየግላቸው ካልተለማመዱ፣ ካልሰለጠኑና ካልተጣጣሩ በቀር።
ረሃብና ሕመም፤ ስቃይና ሞትም የግል ናቸው። ለተራበ መራራት፣ ለሞተም ማዘን ተገቢ ነው። መሞትና ማዘን ግን ይለያያል። ሞትንና ሃዘንን ግማሽ ግማሽ ይከፋፈሉም። የጋራ አይደለም።
የመገበያየትና የመረዳዳት ተግባር በጣም አስፈላጊና በጎ የሰዎች ግንኙነት ነው - ይህንንም “የጋራ ኑሮ” ልንለው እንችላለን። ነገር ግን፣ “ግብይትና እርዳታ” የተሰኙ ነገሮች እንዲኖሩ፤ በቅድሚያ፣ “የግል ኑሮ፣ የግል ንብረት፣ የግል ብቃት” የተባሉ ነገሮች መኖር አለባቸው፡፡ “የግል” የሚሉት ነገር ከሌላ፣ “የጋራ ግንኙነት” የሚሉት ነገር አይኖርም።
በአጭሩ፣ የሁሉም ነገር መሰረት፤ የግብይትም የትብብርም፤ የፍትህም የልግስናም፣ የአድናቆትም የፍቅርም ሁሉ ምንጭ፣ የሰዎች የግል ህልውናና የግል ብቃት ነው።
ምናለፋችሁ….
የሕይወትን ውድነትና የእያንዳንዱን ሰው ብቃት ማክበር ነው፤ የሁሉም ነገራችን የትርጉም ምንጭ።
የጀብድ ተግባሮችና የገድል ስራዎችም፤  ይህን “አውራ እውነት” በግላጭ ለማየት ይረዱናል።
በሌላ በኩል፣ ሕይወትን የሚያረክሱና የሚያጠፉ፣ የግል ብቃትን የሚያኮስሱና የሚያሰናክሉ ተግባሮች ደግሞ፤ የዚህ ተቃራኒ ናቸው፡፡ አንድም አላዋቂነትና ከንቱ ብክነት፣ አልያም መጥፎ አመልና የክፋት ወንጀል ይሆናሉ፡፡
ለዚህም ነው፤ የዘመናችን ፈር ቀዳጅ የህዋ ቢዝነስ፣ መቶ አመት ካስቆጠረው የደቡብ ዋልታ የምርምር ጉዞ ጋር እየተዛመደ የተተረከው - Space Barons በተሰኘው መፅሐፍ፡፡ ለምን? ምርምርና ቢዝነስ በጎ ናቸው፡፡ ፈር ቀዳጅ ሲሆኑ ደግሞ፣ ድንቅ ገድል ይሆናሉ፡፡

Read 8828 times