Sunday, 22 August 2021 11:37

የኑሮ ውድነት፣ የዶላር ምንዛሬ ማሻቀብ፣ የሸቀጥ ዋጋ መናር፣ የምርት መቀዛቀዝ…..

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የሸቀጦችና የአገልግቶች ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመናሩ በተለይ የከተማ ነዋሪዎች እጅግ ለከፋ የኑሮ ውድነት ተጋልጠዋል።
ለመሆኑ  የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንስኤው ምንድን ነው? መፍትሄውስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  ከኢኮኖሚው ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ  ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

            በአጭር ጊዜ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት መባባስን ያስከተለው  ምንድን ነው?
ለዚህ አንድ ምክንያት ብቻ አይደለም ያለው፤ መነሻ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። አንደኛ ከባለፈው ጊዜያት የቀጠሉ ችግሮች አሉ። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ የምርትና አቅርቦት መቀዛቀዝን፣ የኤክስፖርት መዳከምን፣ የስራ እድል መጥፋትን፣ የንብረት መውደምን…  አስከትሏል።
እነዚህ መፈጠራቸው ሳያንስ ደግሞ ኮሮና የበለጠ የስራ እድል መዳከምንና የምርታማነት  አለመኖርን አስከትሏል። ይህም ኢኮኖሚውን አዳክሞታል። ይህ በእርግጥ ዓለማቀፍ ሁኔታ ነው። ተፈጥሮ ያመጣው ችግር ነው። በሌላ በኩል፤ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ 23 በመቶውን አውድሟል። ጦርነቱ ያመጣው ምስቅልቅል አለ። ጦርነቱ በራሱ አዲስ ፍላጎት ፈጥሯል። ለጦርነቱ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች በገፍ አስፈልጎታል። መሳሪያ ስንቅና ትጥቅ ማቅረብ ብቻውን በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖው የበረታ ነው። ሌላው የገበያ ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር ነው። በጦርነቱ ከመንግስት በተቃራኒ የቆመው ሃይል፣ ኢኮኖሚው ላይ አሻጥር በመስራት ተንቀሳቅሷል፤ ሆን ብሎ ዶላር በመግዛት፣ እቃ በመደበቅ፣ ሃብት በመሰወር።  የገበያው ሰንሰለት ቀደም ብሎ በጥቂት ግለሰቦች የተያዘ የገበያ አቅርቦቱን ሆን ብሎ በማዛባት፣ አቅም በማሳጣት የተፈጸመም ተፅዕኖ አለ።
ከሁሉም በጣም ከባዱ ደግሞ መንግስት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ   የሚያስፈልገው ገንዘብ በህትመት ከብሔራዊ ባንክ የወጣ መሆኑ ነው። ያ ማለት የአቅርቦት ኢኮኖሚው ሳያድግ፣ የፍላጎት ኢኮኖሚው ነው ያደገው። በገበያ ዝውውሩ ብዙ ገንዘብ እንዲገባ ተደርጓል። በአንፃሩ አቅርቦት የለም። ስለዚህ ብዙ ገንዘብ፣ ያለችው ጥቂት ምርት አሳዳጅ ሆኗል። እነዚህ ተደማምረው ኢኮኖሚው ላይ ከባድ ተፅዕኖ ፈጥረዋል።
የመጨረሻው ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረገው ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ጉዳይ ነው። ብር ከዶላር አኳያ 28 በመቶ የሚደርስ ግሽበት እንዲያሳይ ተደርጓል። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች አንድን ኢኮኖሚ ወደ ወድቀት ነው የሚወስዱት። እንደውም የኛ ማህበረሰብ የፍላጎትና የአቅርቦት ጉዳይ በጣም በድህነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ኢኮኖሚው ሊቋቋመው ቻለ እንጂ ሌሎች ሃገሮች ላይ ቢሆን፣ እንደ ሃገር ከፍተኛ ምስቅልቅል ነበር የሚፈጠረው። እነዚህ ነገሮች ተደምረው ነው እንዲህ ችግሩ የተባባሰው።
የዶላር ምንዛሬ በጥቁር ገበያ  በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ በኢኮኖሚው ለይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሊያብራሩልን ይችላሉ?
በእርግጥ የጥቁር ገበያ ምንዛሬ በቀጥተኛ አካሄዶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እስካሁን ድረስ ያህል ከባድ የሚባል አልነበረም። ከዚህ በፊት የነበረው የጥቁር ገበያ በአመዛኙ ከባንክ የተፈቀደላቸው ዶላር ሲያንሳቸው፣ ጉዞ ሲያደርጉ በኪሳቸው የሚይዙት ዶላር ሲያስፈልጋቸውና በአብዛኛው የኮንትሮባንድ ንግዱ ነበር ተጠቃሚው። በዚህ ምክንያት ዋናውን የኢትዮጵያ የዶላር ኢኮኖሚ አልነበረም ይጎዳ የነበረው። አሁን ግን በሂደት ዋነኛው የዶላር ኢኮኖሚ መስመሩ የጥቁር ገበያው ሆነ። ዋነኛው መስመር መሆኑ ደግሞ የዶላር ፍላጎቱን አናረው፤ መንግስትም ለአቅርቦት ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ዶላር ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊ ምክንያቱ ፍላጎት ማደጉ ነው።  ይህ ሁኔታ ፍላጎትን በመጨመሩ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች  ፍላጎት ጨምሯል። ይህም የዶላር ፍላጎት መጨመር እንዲኖር አድርጓል። ያ በመሆኑ ባለችው ትንሽ ዶላር ላይ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ዋጋው መጨመሩ አይቀርም። ይሄ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ውጤት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ መንግስት ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ጋር በነበረው ግንኙነት፤ የኢትዮጵያ ብር አሁን ባለው ገበያ ተገቢው ዋጋ ላይ አይደለም፤ከዚህ በታች ዝቅ ማለት አለበት የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል።  ስለዚህም መንግስት በሂደት ቀስ በቀስ ብር ከዶላር ያለውን ምጣኔ  መቀነስ ነው የጀመረው። ይሄ ሲሆን የቅናሹ መቆሚያ ገደቡ ስለማይታወቅ፣ ሰዎች በራሳቸው ግምት እየተነሱ በየጊዜው የዶላር ፍላጎትን ተከትለው ዶላር ላይ ዋጋ መጨመር ጀመሩ ማለት ነው። አንዳንዱ በአንድ በኩል፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም አለ። በሌላ በኩል፤ መንግስት በጣም ዝግ ያለ የጭማሪ ሂደት ውስጥ በመግባቱ፣ የዶላር ገበያው በግምት ላይ ተመስርቶ፣ በግለሰቦች ፍላጎት ዋጋው እንዲወሰን ተደርጓል።
ሌላው ለዶላር ፍላጎት መጨመር መንስኤው አሻጥር ነው። በርካታ ሰዎች ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በብዙ ቦታዎች ንብረት  እየሸጡ፣ ሃብታቸውን ወደ ዶላር በመለወጥ፣ ዶላሩን አከማችተው በመያዛቸው፣ የዶላር ዝውውሩ እንዲቀንስ አድርገውታል። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው ዶላር በጥቁር ገበያ ዋጋው እንዲንር ያደረጉት።
አሁን ለተፈጠረው የኑሮ ውድነትና የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ጦርነቱ በራሱ ምን ያህል ነው ድርሻው?
የጦርነት ኢኮኖሚ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ጦርነቱ ምን ያህል የወጪ ፍላጎት እንዳለውም አይታወቅም። ያ ማለት ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ለጦርነቱ የሚወጣው ወጪ መጠን ይበዛል፤ ቀለብ፣ የመሳሪያ አቅርቦት በተለይ ተተኳሾች፣ ነዳጅ ወዘተ ምን ያህል ያስወጣል የሚለው አይታወቅም። በዚህ የተነሳ ጦርነቱ የሚያስከትለውን ኪሳራ፣  አስቀድሞ በትክክል መገመት ያስቸግራል። ለእኔ ከጦርነቱ በላይ ባለፉት ሶስት አመት የተከሰተው አለመረጋጋት በተለይም የሰዎች መፈናቀልና መገደል፣ ማህበራዊ ህይወት መናጋት ወዘተ ነው።….ብዙ ችግር ያስከተለው፡፡
አሁን ላይ ላለው ችግር የበለጠውን አስተዋፅኦ እያደረገ ያለው ጦርነቱ፣ ገና መጀመሩ ስለሆነ  የጎላ ተፅዕኖ ልናይ የምንችለው፣ ምናልባት በቀጣይ በጀት ዓመት ነው። አሁን መንግስት ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በህትመት ያቀርባል። ግልፅ መሆን ያለበት መንግስት በቀላሉ  ለዚህ ጦርነት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሁለት መንገድ እንደሚያገኝ ነው። አንደኛው በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ፣ ለእነሱ የተመደበውን ወደ ጦርነቱ ማዞር ነው። ሁለተኛው መንገድ ተጨማሪ ገንዘብ ማተም ነው። እነዚህ ሁለቱም መንገዶች ለአንድ ኢኮኖሚ በጣም ጠንቅ ናቸው። ኢኮኖሚው ወይም አቅርቦቱ ከሚሸከመው በላይ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ሲገባ፣ የሸቀጦች ዋጋ ከሚገባው በላይ እንዲንር ምክንያት ይሆናል። ፕሮጀክቶች ሲታጠፉ ደግሞ በተያዘላቸው ጊዜ ባለመፈጸማቸው፣ ለስራ የተዘጋጀ ሃይል ወደ ስራ እንዳይገባ በማድረግ፣ የስራ እድልን ይቀንሳሉ፤ የስራ አጥነት ቁጥሩን ይጨምራል። በሌላ በኩል፤ አቅርቦትን ያዳክማሉ። በተያዘላቸው ጊዜ አልቀው ቢሆን ምርታቸውን ወደ ገበያ አውጥተው ገበያውን በማረጋጋት አስተዋፅ ይኖራቸው ነበር። ነገር ግን አሁን እኛ እየተጋፈጥን ያለነው ያለፉት ሶስት ዓመታት አለመረጋጋቶች ውጤትን ነው። የጦርነቱ ውጤት ገና ለወደፊት ነው በደንብ ጎልቶ የሚታየው። ከአሁን በኋላ በደንብ ግልፅ እየሆነ ይመጣል።
የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነቱ ጊዜያዊ ነው ወይስ ዘላቂነት ይኖረዋል?
አሁን ኢኮኖሚያችን ላይ የምናያቸው ችግሮች አንደኛው፣ ታቅደው ታስበው የሚፈጸሙ ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው። ለምሳሌ በዶላር መወደድ ምክንያት የጤፍ ዋጋ የሚንርበት ምክንያት አይገባኝም። የ300 እና 400 ብር የዋጋ ጭማሪ ማምጣቱ፣ የስግብግብነትና የተፈጠረውን እድል ከሚገባው በላይ የመጠቀም ባህሪ መኖሩ እንዲሁም፣ ተቆርቋሪነት ያለመኖሩ ውጤት ነው። እነዚህ ሰዎች አውቀው አቅደው የሚፈጥሯቸውን ችግሮች መፍታት ይቻላል።- ስርዓትና ህግ በማበጀት፣ አቅርቦቱን በማሻሻል። የሸማቾችና የአምራቾች ህብረት ስራ ማህበራትን እንደገና እንዲያንሰራሩ በማድረግ ብዙ ነገሮችን ማሻሻል ይቻላል።
በሌላ በኩል ማምረት የሁለትና ሶስት ወር ስራ አይደለም። በቂ ዝግጅት፣ በቂ ጥናትና አቀራረብ ይፈልጋል። ጠንካራ ስራዎች መሰራት አለባቸው።  ኤክስፖርት ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የሚያማልል ፖሊሲ መቅረፅ፣ የታክስ ሁኔታዎችን ማሻሻል፣ የተቀላጠፈ የአገልግሎት መዘርጋት፣ የሙስና ሰንሰለቱን መበጣጠስ ያስፈልጋል፤ የጉምሩክ ስርአትን ማሻሻል ያስፈልጋል። እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ደግሞ ጊዜን ይጠይቃሉ።
የሃገር ውስጥ ምርትን መጨመር፣ ኤክስፖርትን ማሳደግና ማስፋፋት ያስፈልጋል፤ እነዚህም  የረጅም ጊዜ  ሥራን ይጠይቃሉ፡፡ ሰው ሰራሽ አሻጥሮች የፈጠሩትን  ችግር ግን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ሰዎችን በማረም፣ ሃቀኞችን በማበረታታትና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የሸማቾች ማህበራትን በማጠናከር መቅረፍ ይቻላል። በሌላ በኩል፤ መንግስት የገንዘብ ህትመቱን መቀነስ አለበት።
አሁን ባለው ሁኔታ ያለ እቅድ ኢኮኖሚው ከሚሸከመው በላይ በገበያ ያለው ገንዘብ፣ ከ20 እስከ 25 በመቶ የጭማሪ ደረጃ  አሳይቷል። ይሄን ገንዘብ በአፋጣኝ ከገበያው  ሰብስቦ ግሽበትን  ጋብ ማድረግ ያስፈልጋል። አንዳንዴ አቅርቦትን ባላሳደገ ኢኮኖሚ፣ ፍላጎትን ብቻ ተከትሎ መሄድ መልካም አይሆንም።
ብሔራዊ ባንክ ንብረትን አስይዞ መበደርን መከልከሉ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
እንደውም የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ዘግቷል ማለት እንችላለን። በትክክለኛው ሰዓት ቢወሰን ኖሮ ብዙ ችግር መቅረፍ ይቻል ነበር። አሁን ቢዘገይም ውሳኔው ትክክል ነው። ባንኮች የገንዘብ ስርጭታቸውን እንዲቀንስ መደረጉ፣ በተለይ ብድር በተሰጠ ቁጥር ወደ ገበያው የሚገባውን የገንዘብ መጠን መቀነስ ያስችላል። ስለዚህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
እስቲየኑሮ ውድነቱን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የውሳኔ እርምጃዎች ይንገሩን?
የመንግስት ሰራተኛውን ደመወዝ በማሻሻል የሚቀረፍ ችግር አይኖርም። ዋናው አቅርቦትን ማሳደግ ነው። አሁን በየሰው ኪስ የሚገባው ገንዘብ መጠን ጨምሯል። ነገር ግን አቅርቦት ባለመኖሩ በየሰው ኪስ የገባው ገንዘብ ጥቂት ምርትን ነው የሚያሳድደው። ስለዚህ መንግስት ደሞዝ ከመጨመር ይልቅ አቅርቦት ማሳደግ ላይ ቢሰራ ነው የተሻለ የሚሆነው።
ሌላው የአገልግሎት ዋጋዎች ላይ ቅናሽ ማድረግ ነው። የመብራ፣ ስልክ፣ ውሃ፣ ታክስ የመሳሰሉት ላይ ቅናሽ ማድረግ ያስፈልጋል። ታክስ ሲባል የገቢ ታክስ ማለት ሳይሆን አቅርቦት ላይ የሚጣሉ እንደ ኤክሳይስ ታክስ፣ ሱር ታክስ የመሳሰሉትን ነው። እነዚህ ላይ ቅናሽ ቢደረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል። ለምሳሌ የመብራት ወጪ ለምግብ ከሚወጣው የሚተናነስ አይደለም። እዚህ ላይ ቅናሽ ማድረግ ያስፈልጋል። በዋናነት ግን በሁሉም ዘርፍ አቅርቦትን ማሳደግ ነው ወሳኙ። በእህል ምርቶች ላይ የሚጣሉ ታክሶችን ማሻሻል ተገቢ ነው። የዳቦ  አምራቾችን በተለይ በስፋት የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ማበረታታት ጠቃሚ ነው። መንግስት ትልቁ ስራው ዜጎች እንዳይራቡ ማድረግ ነው፤ የዜጎችን በልቶ ጠጥቶ የማደርን ፍላጎት  ማረጋገጥት የችሮታ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታው ነው። ይህን ካልተወጣ መንግስት ዋነኛ ሃላፊነቱን ዘንግቷል ማለት ነው።

Read 2023 times