Saturday, 21 August 2021 00:00

በአዲስ አበባ ከ350 በላይ መንደሮች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 እናትና አባት ከእነልጅ ልጆቻቸው በጎርፍ ተወስደዋል
     - ደራሽ ውሃው የአስር ዓመቷን ታዳጊ ከአባቷ እቅፍ ነጥቆ ወስዷታል
    - ጎርፉ መንትያ ወንድማማቾችን ነጥሏል፣ የቤት ሰራተኛዋን ከእነታቀፈችው ህፃን ለሞት  ዳርጓል
                    (ሪፖርታዥ)
- ማክሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም። ዕለቱ ለመካኒሣው መካነኢየሱስ ሴሚናሪያ መንደር ነዋሪዎች ጥቁር ቀን ነበር።… ከቀናቶች ሁሉ የከፋ።
ወ/ሮ ቤዛ በዚህ መንደር ኑሮዋንም ስራዋንም ካደረገች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። በስራ ምክንያት ለጊዜው አጠገቧ ያልነበረው ባለቤቷ፣ የሷንና የልጆቿን ደህንነት እየደጋገመ በስልክ ከመጠየቅ አልቦዘነም። ነዋሪነታቸው በደቡብ ክልል ከንባታ ከተማ ውስጥ የሆኑት የቤዛ እናትና አባት፣ በዚህች መንደር በዛች ጥቁር ቀን የተገኙት፣ ከ3 ቀናት በኋላ፣ ወደ አሜሪካ  ለሚያደርጉት ጉዞ ለመዘገጃጀትና ልጃቸውን ለመሰናበት ነበር።
ቤዛ እናትና አባቷን በደስታ ተቀብላና በሚገባ አስተናግዳ እዛው ሴሚናሪያ ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው የስራ ቦታዋ ደረስ ብላ ለመመለስ ከቤት ትወጣለች። ሰዓቱ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ ይሆናል። በእነ ቤዛ ቤት አሜሪካ አገር የምትኖር ልጃቸውን ለማየት የናፈቁ እናትና አባቷ፣ የቤዛ መንትያ ልጆች፣ የአንድ እህቷ ልጅና የቤት ሰራተኛዋ ነበሩ።
መንደሩ ከትልቁ የመካኒሣ ወንዝ አጠገብ የከተመ መንደር በመሆኑ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ቀላል ጎርፎችን ያስተናገደ ቢሆንም፣ የከፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል ብሎ ያሰበም የጠረጠረም አልነበረም። ሰዓቱ ወደ 10 ሰዓት ገደማ ሆኗል። በድንገት የእነ ቤዛ መንደር ታይቶ በማይታወቅ ከባድና አስፈሪ ደራሽ ጎርፍ ተጥለቀለቀ። የመንደሩ ነዋሪዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንደ ፈረስ ከሚጋልበው የጎርፍ መዓት ለማትረፍ ተራወጡ። ጎርፉ የእነ ቤዛን ቤት ገነጣጥሎ ለመግባት የወሰደበት ጥቂት ቅፅበት ብቻ ነበር።
ያገኘውን ሁሉ እያፈነቃቀለና እያተራመሰ ወስዶ ከትልቁ የመካኒሳ ወንዝ የሚደባልቀው ደራሽ ጎርፍ እነቤዛ ቤት ላይ የጭካኔ በትሩን አሳረፈ። እንኳን ቤተኞቹን እንግዶቹንም አልማረም። ከመኖሪያ ቤቷ በጥቂት ርቀት ላይ  የነበረችው ቤዛ፤ እቤቷ ደርሳ ቤተሰቦቿን ከሞት ለመታደግ አልቻለችም። ሁሉም ነገር ቅፅበታዊና ዘግናኝ ነበር። እናቷን፣ አባቷን ከመንትያ ልጆቿ አንዱን፣ የእህቷን ልጅና የቤት ሰራተኛዋን ደራሹ ጎርፍ ነጠቃት።
ከሁለቱ መንትያ ልጆቿ አንዱን ተአምር ሊያሰኝ በሚችል ሁኔታ ያተረፉላት የነፍስ አድን ዋናተኞች ናቸው። ከጥቂት ሰዓታት በፊት የልጅ ልጆቻቸውን በስስት እያዩ በሚያጫውቱ አያቶች፣ በጣፋጭ የልጅ አንደበታቸው ቤቱን በሳቅ ጨዋታ በሚያደምቁ እምቦቀቅላዎች ደምቆ የነበረው የእነ ቤዛ ቤት አስፈሪ የሞት ጥላ አጠላበት። አምስት ነፍሶች ተነጠቁበት። በጎርፍ ፍርስርሱ ወጣ።
ይህ አሰቃቂ መከራና ሃዘን የደረሰባት ቤዛ ደህና ግቡ ተብለው ወደ አገረ አሜሪካ ለመሄድ ከመኖሪያ መንደራቸው የተሸኙትን ወላጅ እናትና አባቷን፣ አንድ መንትያ ልጇን፣ የእህቷን ልጅና የቤት ሰራተኛዋን አስክሬን አስጭና ወደ ትውልድ መንደሯ ወደ ከምባታ ማቅናት ግዷ ሆነ። አደጋው ቤተሰቦቿን ብቻ ሳይሆን ህልውናዋን ሁሉ እንደነጠቃትና እጅግ ከባድ ሃዘን  ውስጥ እንደጣላት የቤዛ ጎረቤቶች ይናገራሉ።
ለመካኒሳ መካነኢየሱስ ሴሚናሪያ መንደር ነዋሪዎች፣ መንደሩ መኖሪያቸውም የስራ ቦታቸውም በመሆኑ አደጋው ሲከሰት አብዛኛዎቹ የመንደሯ ሰዎች እዛው እቦታው ላይ ነበሩ። አደጋው እጅግ የከፋ ጉዳት ያደረሰው በኮሌጁ መምህራንና ሰራተኞች መኖሪያ ቤት ነው፤ የስራ ቦታቸው በአደጋው ብዙም ጉዳት አልደረሰበትም።
እዛው መንደር ውስጥ አገልጋይ የሆኑት ቄስ እሴይ ጎርፉ የቅጣት በትሩን ካሳረፈባቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። አደጋው ሲከሰት ከስፍራው የነበሩት ቄስ እሴይ፤ ሁለት ልጆቻቸውን ከጎርፍ ጋር ተናንቀው ለማትረፍ ብርቱ ትግል አድርገዋል። አንደኛውን ልጃቸውን ከቤቱ ጣሪያ ላይ ለማውጣትና ህይወቱን ለመታደግ ችለዋል። የ10 ዓመት ታዳጊ ሴት ልጃቸውን ግን ከጎርፍ ለማስጣል አልቻሉም። በጎርፉ ተወሰደች። “ምነው ልጆቼን አድኜ እኔ በተወሰድኩ” ይላሉ በከባድ ሃዘን ውስጥ የወደቁት አባት ቄስ እሴይ።
በኮሌጁ ውስጥ በሙዚቃ መምህርነት የሚሰራውና  የጎርፍ አደጋ ሲከሰት በስራ ላይ ነበር። ከታች መንደር መኖሪያ አካባቢያቸው ላይ የጎርፍ አደጋ መድረሱን የተመለከተው አማረ፤ ቤት ያለችውን ህፃን ልጁን ለማዳን እየተሯሯጠ ባደረገው ሙከራ በጎርፉ ተወስዶ ከሞት ለጥቂት ነው የተረፈው። በውሃ ውስጥ የሚጓዘውን አባት ጎርፉ ሊራራለት አልፈለገም። በህይወት አድን ዋናተኞች ነው። ህፃን ልጁን ግን በጎርፍ ተነጥቋል።
በመካኒሳው መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪያ የምስራቅ ቡድን ተስፋ ለሴቶች ፕሮግራም አዘጋጇ ወ/ሮ ብርሃኔ ተፈራ ከሁለት ልጆቿና ከባለቤቷ ጋር ከአደጋው ከተረፉት የመንደሯ ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናት።
ወ/ሮ ብርሃኔ በዕለቱ ስለተከሰተው አደጋ ስትናገር ሣግ ይተናነቃታል። “ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ለእኛ መንደር ነዋሪዎች ጥቁር ቀን ነበር። ክፉ ቀን….፡፡ ወዳጆቼን፣ ጓደኞቼንና… ጎረቤቶቼን በዘግናኝ ሁኔታ ያጣሁበት ቀን ነው” ትላለች።  በቅርቡ የሚመረቀው የአምስተኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ልጇ በሳሎን ቤት ውስጥ ተቀምጦ የመመረቂያ ወረቀቱን እየሰራ ነበር። በመኝታ ክፍል ውስጥ ደግሞ የ13 ዓመት ዕድሜ ያላት ታናሽ እህቱ በእንቅልፍ ላይ ነበረች። ድንገት የሰዎች ጩኸትና ጫጫታ ይሰማና በሩን ከፍቶ ሲወጣ መንደሯ በደራሽ ጎርፍ እየተጥለቀለቀች ነው። ይኼኔ መኝታ ክፍል ውስጥ በእንቅልፍ ላይ ያለችው ታናሽ እህቱ ትዝ አለችው። እየከነፈ ሲገባ ተኝታለች። የእውር ድንበሩን እህቱን ተሸክሞ ከቤት ወጣ። መንደርተኛው ወደሚተራመስበት አቅጣጫ ሮጠ። እንቅልፍ ላይ የነበረቸው እህቱ ሩጫውን ተቀላቀለች። መንደርተኛው ውሃው ወደማይደርስበት ከፍታ ቦታ ይራወጣል። ከፍ ወዳለው ስፍራ ደርሶ ቁልቁል ሲመለከት፣ ቤታቸው በጎርፉ ስትፈራርስ አያት- ቤቱ ጣሪያው ድረስ በጎርፍ ተጥለቅልቋል። ወ/ሮ ብርሃኔ ለስራ ከነበረችበት እዛው ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የስራ ቦታዋ የተፈጠረውን ነገር ሰምታ እስክትወጣ ብዙ ነገሮች ተከናውነው ነበር። በቤት ውስጥ የነበሩት ሁለቱ ልጆቿ በህይወት መትረፋቸውን ያወቀችው እናት፤ በደራሽ ጎርፍ ለተወሰዱት ጎረቤቶቿና ጓደኞቿ እጅግ አዘነች። “እግዚአብሔር ለእኔ ምህረትን አድርጎልኛል፤ ከእነልጆቼ ተርፌአለሁ። ነገር ግን አብረን ኖረን አብረን ያረጀን ወዳጆቼን በዚህ ክፉ ቀን አጥቼአለሁ” ትላለች ወ/ሮ ብርሃኔ በሃዘን ተሞልታ።
ልጃቸውን ለመሰናበት መጥተው የጎርፍ ሰለባ ስለሆኑት የቤዛ እናትና አባት ወ/ሮ ብርሃኔ ያጫወተችኝ በከባድ ሃዘን ነበር። “እናቷ ቄስ ወጋየሁ ትባላለች። በጣም ጓደኛዬ ነበረች። ብዙ ነገር አብረን አሳልፈናል። ከልጇ ጋር በአንድ መንደር ውስጥ ስለምንኖር ልጇን አደራ ሰጥታኝ ነበር። እኔ ግን አደራዬን መጠበቅ፣ ጓደኛዬንም ከዚህ ዘግናኝ አደጋ ማዳን ቀርቶ በቀብሯ ላይ መገኘት እንኳን ሳልችል ቀረሁ። በአደጋው ቤቴ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ሁለት ልጆቼና ባለቤቴ ሸሽተን አሸዋ ሜዳ ታናሽ እህቴ ዘንድ ነው ያለነው። ሁኔታው እጅግ ዘግናኝ ነበር-ብላለች ወ/ሮ ብርሃኔ።
ከስራ ቦታቸው ልጆቻቸውን ለማዳን ወደቤታቸው የሮጡ ወላጆች ልጆቻቸው ጋር ሳይደርሱ በጎርፍ ተወስደው በህይወት አድን ሰራተኞች ነው የወጡት በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የገቡ ከ50 በላይ ሰዎች ነበሩ።
“ምን ማለት ይቻላል?! እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኛቸው። በጎርፍ አደጋ ለመስማት እንኳን የሚከብድ ከባድ ሃዘን ለወደቀባቸው ጎረቤቶቼ ለወ/ሮ ቤዛ፣ ለቄስ እሴይና ለአቶ አማረ ጌታ አፅናኝ መንፈስ ይላክላቸው የቀን ክፉ እንዲህ ያደርጋል። ወዳጆቼ ጓኞቼን ተነጥቄአለሁ ሃዘኔ እጅግ ከባድ ነው” ትላለች- ወ/ሮ ብርሃኔ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2፣ በተለምዶ ሴሚናሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የደረሰውና የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት የነጠቀው የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል  የሚጠቁሙ ፍንጮች እንደነበሩ የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በስፍራው የሚገኘው የመካኒሳ ወንዝ በአካባቢው በሚደረጉ አዳዲስ ግንባታዎች ሳቢያ የአፈር መድፊያ እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት ወንዙ ተፈጥሮአዊ የመፍሰሻ አቅጣጫውን እንዲቀይር እንዳስገደደውም ይገልፃሉ። ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውንና ምላሽ  ግን አለማግኘታቸውንም ይናገራሉ።
አደጋው፤ መኖሪያቸውንም የስራ ቦታቸውንም በግቢው ውስጥ ያደረጉ የአስራ ስድስት አባወራ ቤቶችን ከእነሙሉ ዕቃቸው ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጎታል። ስድስት የውጪ አገራት ዜጎች መኖሪያ ቤቶችም ከእነሙሉ ንብረቶቻቸው ወድመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መንሸራተቶችና የወንዝ ሙላት የሚያጠቃቸው 354 ቦታዎች በጥናት ተለይተው መቀመጣቸውንና ይህ አካባቢም ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ ተብለው በጥናት ከተለዩት አንዱ መሆኑን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ጉልላት ጌታነህ፤ ስፍራው ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑ ተለይቶ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት በተደጋጋሚ  ሪፖርት መደረጉን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
ጥናቱ በየዓመቱ እየተከለሰ የጉዳዩ አሳሳቢነት የሚታይ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በዘንድሮው ዓመትም ባለፉት ግንቦትና ሰኔ ወራት በቦታው ላይ ተመሳሳይ የክለሳ ጥናት ተደርጎ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማለትም ለቤቶች ኮንስትራክሽንና ለመሬት ማኔጅመንት ቢሮዎች ሪፖርት ተደርጓል ብለዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን፣ በራሱ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ተጋላጭ ከሆኑባቸው አካባቢዎች የማንሳትና ወደ ሌላ ስፍራ የማዛወር ሥልጣን የሌለው በመሆኑ ስለ ሁኔታው አሳሳቢነት ጥናት በማድረግ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ስናደርግ ቆይተናል ብለዋል።
በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር ስምንት መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ነው ያለኝ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አደጋው ያደረሰውን ሙሉ ጉዳትና ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ቁጥር ለማወቅ እየሰራን ነው ብለዋል። ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ጊዜያዊ እርዳታ መሰጠቱንና በአደጋው በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ወገኖችን የመለየቱ ስራ እየተሰራ መሆኑንም እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ከ20 ዓመት በፊት የተቋቋመው የመካኒሳው መካነኢየሱስ ማኔጅመንትና ሊደርሺፕ ኮሌጅ፤ በአስተዳደርና ስራ አመራር ስልጠናዎቹ የሚታወቅ ሲሆን በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ከ300 በላይ ተማሪዎች በተማሪ መኖሪያ ዶርም ውስጥ ይኖራሉ። የተማሪዎቹ የመኖሪያ ህንፃ ከፍታ ቦታ ላይ የተሰራ በመሆኑ ከአደጋው መትረፉም ታውቋል።


Read 10208 times