Saturday, 21 August 2021 00:00

ኢዮሃ እንቁጣጣሽ ኤክስፖ ዛሬ በመስቀል አደባባይ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኢቨንት የተዘጋጀውና ለ21 ቀናት የሚዘልቀው “እዮሃ እንቁጣጣሽ” ኤክስፖ ዛሬ በመስቀል አደባባይ በድምቀት ይከፈታል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በፕላቲኒየም ደረጃ በቴሌ ብር ስፖንስር ባደረገው በዚህ ደማቅ ኤክስፖ ላይ ከ500 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አምራቾች፣አስመጪዎች፣አከፋፋዮች ባንኮችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሳተፉ  ሲሆን በአጠቃላይ  በሃያ አንዱ ቀናትም  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንትስ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አዩ ዓለሙ፣ ሀሙስ ረፋድ ላይ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ዛሬ በመክፈቻው ዕለት መግቢያው በነፃ ሲሆን አንጋፋው ድምጻዊ ፀጋዬ እሸቱ፣ተዓምር ግዛውና መሳይ ተፈራ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ የተጠቆመ ሲሆን ነገ እሁድ የፍልሰታ ፆም ፍቺን ምክንያት በማድረግ ከታሪኩና ዋጆ ስጋ ቤቶች ጋር በመተባበር ቁርጥና ጥብስ በቅናሽ ለተጠቃሚ እንደሚቀርብ ተገልጿል።
የደህንነት ጉዳይ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የህጻናት መጫዎቻ (ጌም ዞን) እና መሰል ጉዳዮች ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገባቸው የገለፁት ስራ አስኪያጇ፤ መግቢያ በር ላይ ማስክና ሳኒታይዘር በማስቀመጥ ሁሉም እንቅስቃሴ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከነጋዴዎች ጋር በመነጋገርም የበዓሉ ዋና ግብአቶች የሆኑት ዱቄትና ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው የተባለ ሲሆን እያንዳንዱን ግብዓት ከ5 ሺ ብር ጀምሮ የመግቢያ ትኬትን ጨምሮ በቴሌ ብር ለሚከወውን ሸማች ደግሞ 10  በመቶ ገንዘቡ ተመላሽ ይደረግለታል ያሉት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ተወካዩ ሰይድ አራጋው ናቸው። ኢትዮ ቴሌኮም የ3 ዓመት ስትራቴጂ ነድፎ የቴሌኮም ገበያ መክፈቱን የገለፁት አቶ ሰይድ፤ ከነዚህም ውስጥ ቴሌ ብር አንዱ መሆኑንና በ3 ወራት ብቻ ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ደንበኛ ማፍራቱን ገልጸው፤ ይህን ኤክስፖ በፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ያረገው የቴሌ ብርን ጥቅምና አሰራር ይበልጥ በማስተዋወቅ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት  ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ አምስት ለ21 ቀናት  በሚዘልቀው በዚህ ኤክስፖ፤ ለበዓሉ የሚሆኑ አልባሳት፣ ምግብ ነክ እቃዎች፣ የልጆች የደንብ ልብሶች፣የመማሪያ ቁሳቁስና የመሳሰሉት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማች ከመቅረባቸውም በላይ በየቀኑ በታላላቅ ድምጻዊያን የሚቀርበው ኮንሰርት ኤክስፖውን ይበልጥ ደማቅና አዝናኝ ያደርገዋል የተባለ ሲሆን የመግቢያ ዋጋው 30 ብር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዛሬ በመክፈቻው ሥነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

Read 10009 times