Print this page
Saturday, 14 August 2021 15:44

በኢራንና ኢትዮጵያ መካከል የዘለቀው የ70 ዓመት ወዳጅነትና መጪው ዘመን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ይህ ጽሁፍ በዓለማቀፍ የወዳጅነት ቀን ዋዜማ ላይ፣ በእህትማማች አገራቱ በኢራንና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ለማሳየትና ሁለቱ አገራት ሊጠቀሙባቸው የሚገቡ ዕምቅ እድሎችን ለመጠቆም ያለመ ነው፡፡
ጥንታዊ ፐርሺያና ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሥልጣኔዎች፤ በንግድና ባህላዊ እሴቶች አማካኝነት መደበኛ ግንኙነቶችንና ልውውጦችን ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ በርካታ የአኗኗር ልማዶችን፣ ባህላዊ እሴቶችን እንዲሁም የሥነምግባርና የሞራል መርሆችን ተጋርተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በጥንታዊ ሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነት ብቻ ሳይሆን መድብለ-ባህላዊነትንና  ብዝኃነትን በማስተናገድም ረገድ ተመሳሳይነትን ይጋራሉ፡፡ በታሪክ፣ የተለያዩ ብሔሮች አገር የሆነችው ኢራን፤ በርካታ የብሔረሰብ፣ ቋንቋና ሀይማኖት ቡድኖችን ያቀፈች መድብለ  ህብረተሰብ ሆና ቀጥላለች፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያም የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ሀይማኖቶችና ባህላዊ እሴቶች ያሏቸው ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ ሁለቱም  መድብለ ባህላዊነትን እንደ አስተዳደር ዘይቤያቸው ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ብዝኃነትን በአግባቡ በመያዝና በሰላም በጋራ መኖርን በማረጋገጥ ረገድ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው፤ያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራዊ ብሔርተኝነት ተረክ እየጎላ በመጣበት ዘመን፡፡
ሁለቱ ታላላቅ ሀገራት በረዥም ዘመን ታሪካቸው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈዋል፡፡ አገራቱ የገጠሟቸውን የውጭ ወራሪዎች በፅናት ተዋግተዋል፡፡ ነፃነታቸውን ለመቀዳጀትም ህዝባቸውን መስዋዕት አድርገዋል፡፡ ነፃነትንና ሉአላዊነትን ማስጠበቅ ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለትውልድ ላስተማሩ የሁለቱ ሀገራት ሰማዕታት ምስጋና ይግባቸውና፤ በወራሪ የውጭ ሀይሎች ላይ ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡
በዘመናዊ ዲኘሎማሲ አግባብ፣ በኢራንና በኢትዮጵያ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነት የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1960 ዓ.ም ነው፡፡ ኢራን፤ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ግንኙነት የመሰረተችበት የመጀመሪያዋ አገር ኢትዮጵያ ስትሆን ሁለቱ አገራት በአለም አቀፍና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ እይታዎችን ሲጋሩ ኖረዋል። ኢራንና ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከመሰረቱት አባል አገራት መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ፈራሚዎችም ናቸው፡፡ ከተባበሩት መንግስታትም አስቀድሞ ሁለቱ አገራት ሰላም የሰፈነባት ዓለም የመፍጠር፣ የእርስ በእርስ ዕውቅናና ክብር የመስጠት እንዲሁም ጣልቃ ያለመግባት መርሆችን ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊግ ኦፍ ኔሽንን በመቀላቀል አረጋግጠዋል፤ ምንም እንኳን ተቋሙ የተጣለበትን አደራ ሙሉ በሙሉ መወጣት ቢሳነውም፡፡ ሁለቱ አገራት የNon-Aligned movement (NAM) ደጋፊና አባላትም ናቸው፡፡ ሁለቱም የNAM ንቁ ተሳታፊ ሲሆኑ በንቅናቄው አማካኝነትም፣ ጣልቃ ገብነትን፣ ቅልበሳን፤ በሀያላን አገራት የሚደረግ የሀይል እርምጃን እንዲሁም በሌሎች አገራት የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ማናቸውም አይነት ርዕዮተ አለም ለመጫን የሚያደርጉትን ጥረት አበክረው ይቃወማሉ፡፡ ኢራንና ኢትዮጵያ፣ በNAM አማካኝነት፣ አባል አገራት ነፃነትን ፣እኩልነትንና ብሔራዊ ማንነትን እንዲሁም ውጤታማ ትብብርን እንዲያረጋግጡ አበረታተዋል፡፡  
የእህትማማች አገራቱ ጠንካራ ትብብር በሌሎች አለማቀፋዊና ክልላዊ ጉዳዮችም ተስተውለዋል፡፡ ሁለቱም የ G-77 እና ሳውዝ-ሳውዝ ትብብርና ሌሎች መድረኮችም አባላት ናቸው፡፡ ኢራንና ኢትዮጵያ፣ በእነዚህ መድረኮች አማካኝነት፣ ለአለማቀፋዊና ክልላዊ ጉዳዮች በስምምነት ላይ የተመሰረተ ህግ ለመቅረጽ እንዲሁም አለማቀፋዊና ክልላዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ዲፕሎማሲያዊ ማዕቀፍ ለማጎልበት ተግተዋል፡፡
የኢራንና የኢትዮጵያ መሪዎች በ1971 ዓ.ም የኤሚቲ ትሪቲን በመፈረም አርቆ አሳቢነት የተመላበት ውሳኔን ወስነዋል፤ ይህም ሁለቱ ህዝቦች የመሰረቱትን ወዳጅነት የሚያጠናክር ወሳኝ ፖለቲካዊና ህጋዊ መሰረቶችን የጣለና ከረዥም ጊዜ አንፃርም፣ የሁለትዮሽ የወዳጅነት ትብብርን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የኤሚቲ ትሪቲ መፈረም ሁለቱ አገራት እንዲሁም የሁለቱ አገራት ህዝቦች የረዥም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ውሉ ወይም ስምምነቱ የተፈረመው የጋራ ልማትና ብልፅግናን ለማሳካት ይቻል ዘንድ ሁለቱንም በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ትብብርን ለማጠናከር ነበር፡፡
ለመጪዎቹ ረዥም ጊዜያት፣ ኢራንና ኢትዮጵያን በአንድነት የሚያስተሳስሩ እጅግ በርካታ ዕድሎች አሉ፡፡ ከአለም ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ በአንድ ክፍለ ዘመን ያልታየ ጉልህ ለውጥ እየታዘብን ባለንበት ወቅት፣ ኢራን ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር፣ በጋራ ለመስራትና ለሁለቱም ህዝቦች የበለጠ ተጠቃሚነትን ለማምጣት፣ የአገራቱን የወዳጅነት ትብብር ወደ አዲስ ደረጃ ለማሳደግ ዝግጁ ናት፡፡ ውስብስብና ተለዋዋጭ አለማቀፋዊ እውነታ በተደቀነበት ሁኔታ፣ ኢራንና ኢትዮጵያ በእጅጉ ማደጋቸውን መቀጠል ያለባቸው ሲሆን የሁለትዮሽ ግንኙነቶችንም ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡
 አገራቱ ካላቸው የቴክኒክና ኢንጅነሪንግ አቅምና ችሎታ አንፃር፣ ኢራንና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚና ንግድ ትስስራቸውን ሊያሳድጉት ይችላሉ፡፡ ሁለቱ አገራት ካላቸው የገበያ ስፋትና ቅርበት እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም አንፃር፣ የንግድ ግንኙነታቸው ሳይቋረጥ   እያደገ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በአግሮ-ፕሮሰሲንግና ኢነርጂ ዘርፍ ኢንቨስት ያደረጉ የኢራን ኩባንያዎች አሉ፤ ነገር ግን ኢራን ተጨማሪ ኩባንያዎችን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳታፊ ሆነው ማየት ትሻለች፡፡  
የአገሮቻችንን የቴክኖሎጂ እድገት አንዳንድ  አገራት ለመግታት በሚያደርጉት ማቆሚያ የለሽ የሆነ ሙከራ አውድ ውስጥ፣ በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ መስተጋብር መፍጠር ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ የሳይንስ፣ የቴክኒክና የፈጠራ ትብብርን ማጠናከር ያስፈልገናል፡፡ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በኢራን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚከታተሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ቢኖሩም፣ ያለውን አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም የበለጠ መስራት ይገባናል፡፡
ሁለቱም አገራት ለብዝኃነት መርህ ተገዥ ሲሆኑ፤ የአንድ ወገን የበላይነትንና የሀይል ፖለቲካን ይቃወማሉ። በዚህ ረገድም በስፋት ይመሳሰላሉ፡፡ ፍላጎታቸውና አጀንዳቸው ብዙ ጊዜ ይጣጣማል፤ ሁለቱም በተባበሩት መንግስታት ላይ ለተመሰረተ አለም አቀፍ የህግ ማዕቀፍ ትኩረት ይሰጣሉ፤ በተለይም በሉአላዊ አገራት ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ ያለመግባት መርህን፡፡
 ሲጠቃለል፤ ኢራንና ኢትዮጵያ ያለፈው ዘመን ታላላቅ አገራት ብቻ አይደሉም፤ የመጪውም ዘመን ታላላቅ አገራት እንጂ፡፡ በመጨረሻም፤ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንዲሁም ለሁሉም ሰላም ወዳድ ህዝቦች፤ እንኳን ለአለም አቀፍ የወዳጅነት ቀን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያና በኢራን መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበትን 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢራን የባህል ማዕከል የታዳጊዎች የስዕል ውድድር አዘጋጅቷል፡፡
የውድድሩ ጭብጥ ፡- የኢትዮ - ኢራን ወዳጅነት
ዕድሜ ፡- ከ 11 እስከ 16 ዓመት
የማስረከቢያ ቀነ-ገደብ፡-   ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ እስከ  መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም  ድረስ
የኢራን ባህል ማዕከል ለውድድሩ አሸናፊዎች  ሽልማት ይሰጣል፡፡
የውድድር ጭብጡን ወይም ደንቦችን በተመለከተ ጥያቄ ካለዎት በኢሜይል አድራሻችን፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ይጻፉልን፡፡


Read 1391 times Last modified on Saturday, 14 August 2021 15:55
Administrator

Latest from Administrator