Print this page
Wednesday, 18 August 2021 00:00

የኢትዮጵያ ቡና በስኒ 65 ዶላር፣ በኪሎ እስከ 330 ዶላር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   እንደ መግቢያ
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ [በግርድፉ የጥራት ሲኒ እንበለው ይሆን] የቡና የጥራት ውድድር ነው። ባለፉት 20 ዓመታት የጥራት ውድድር በዋና ዋና የቡና አብቃይ አገራት ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውድድሩ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ነው።
ዓላማው ከተመረቱት ቡናዎች መካከል የተሻለውን ቡና መርጦ፣ በዓለም አቀፍ ጨረታ ለታላላቅ ገዢዎች መሸጥ ነው። በተጨማሪም፣ ትልቁ ዓላማው፣ ገበሬዎችን ማስተዋወቅ እንዲሁም በአንድ አገር ያሉትን ልዩ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎችና አምራቾች ማስተዋወቅ ነው።
“ሲዳማ ውስጥ ያደገ ማንም ሰው ስለ ቡና በደንብ ያውቃል”
ታምሩ ታደሠ ውልደቱና ዕድገቱ በሲዳማ ክልል በምትገኘው ቀጠና ቀበሌ ነው። ከቡና ጋር የተዛመደ ሥራ የጀመረው በቅርቡ ነው። ግን ቡናን ያውቃል። በደንብ ያውቃል። “ሲዳማ ውስጥ ያደገ ማንም ሰው ስለ ቡና በደንብ ያውቃል። ይሰማል። አብዛኛው የአካባቢው ነጋዴ ቡና ነው የሚነገደው” ይላል።
ትምህርቱን በኤሌክትሪካል ምህንድስና ካጠናቀቀ በኋላ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመረ። ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‘5 ኪሎ’ ገባ። ከትምህርቱ ጎን ለጎን፣ ቡና ኤክስፖርት በሚያደርግ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ።
“ለማስተርስ  ዲግሪ 5 ኪሎ እየተማርኩ፣ ዱካለ ዋቀዮ የሚባል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ ለ6 ዓመት ሰርቻለሁ። ስለ ቡና ያወቅሁት ያኔ ነው” ብሏል፤ ለቢቢሲ።
ስለ ቡና ሥራ ዕውቀቱን ሲያገኝ ቀጣዩ ዕቅዱ ደግሞ የራሱን ድርጅት አቋቁሞ መሥራት ነበር። ከዓመት በፊት ዓላማው ተሳክቶም ድርጅቱን አቋቋመ።
“ሲዳማ መፈጠር ስለ ቡና እንድታስብ ያደርጋል። ቡናው በዕውቀት ሳይሆን በልምድ ስለነበር በፊት ቁጭት ነበረኝ። ቡና ላይ ብሠራ ስለምል ልምዱም ጠቀመኝ።”
የግድ ግን ወደ እርሻ መግባት አልነበረበትም። “የቡና እርሻ እኔ የለኝም። እርሻ ካላቸው ገበሬዎች ነው የምንሰበሰብው። የተለያየ መጠን ያለው የቡና እርሻ ካላቸው ወደ 400 ከሚጠጉ ገበሬዎች ነው ቡና የምንሰበስበው” ብሏል፤ታምሩ።
“ዓምና አንድ ኪሎ ቡና 407 ዶላር ተሸጧል”
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀመር፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ብዙ ገዢዎች ግን ተሳትፈውበታል። ውድድሩ በጣም ጥብቅና የምርጦች ምርጥ የሚወጣበት ነው። በዘንድሮው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ፣ 1864 ቡናዎች ለውድድር ቀርበው ነበር።
“ከመላው ቡና አምራች አካባቢዎች የመጡት ሁሉ ተቀምሰው የተሻሉ የተባሉት 40ዎቹን ወደ ስምንት አገር ልከናል” ይላሉ፤ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኢትዮጵያ አማካሪ ወ/ት ቅድስት ሙሉጌታ።
ቀጣዩ  እነዚህን 40 ቡናዎች በጨረታ መግዛት ነው።
“እነዚህ ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች የኢትዮጵያ ቡና ናቸው። ገዢዎቹ ልዩነታቸውንና ጣዕማቸውን ስለሚፈልጉት ነው ተጫርተው የሚገዙት” ይላሉ፤ወ/ት ቅድስት፡፡
“ባለፈው ዓመት 407 ዶላር በኪሎ የተሸጠው ለኢትዮጵያ ቡና የተከፈለ ትልቁ ዋጋ ነው። ከሲዳማ ክልል ቡና አምራቹ አቶ ንጉሤ ገመዳ  ናቸው በዚህ ዋጋ የሸጡት።”
ባለፈው ዓመት አንደኛ የወጣው ሰባት ኬሻ ቡና ነው የተሸጠው። አንዱ ኬሻ 60 ኪሎ ነው። የዘንድሮ አሸናፊም ከሲዳማ ክልል አልወጣም። ተረኛው ታምሩ ታደሠ ነው።
“24 ኬሻ ነው ከፍተኛው ማቅረብ የሚቻለው”
ታምሩ ታደሠ ስለ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በአጋጣሚ ሰምቶ ነው ለውድድሩ እንዲዘጋጅ የተገፋፋው፡፡ “ባለፈው ዓመት ያሸነፈው ጓደኛዬ ነው። የማውቀው ሰው ነው። ያም አስተዋጽኦ ነበረው። በዚያው ቡና ለማዘጋጀት ወሰንኩ። ለውድድር ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት የሚሆንም ነው ያዘጋጀሁት። ማስታወቂያ ሲወጣ አቀረብኩ” ብሏል።
ታምሩ ሁለት ዓይነት ቡና ይዞ ቀረበ። ሁለቱም ቡናዎች ተሳካላቸው። አንደኛው ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ፣ ሁለተኛው ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ያዘ፡፡  
“24 ኬሻ ነው ከፍተኛው ማቅረብ የሚቻለው። እኔም አንደኛ ከወጣው ቡና 24 ኬሻ ነው ያቀረብኩት። አንድ ኬሻ በ60 ኪሎ ነው። ስለዚህ አንደኛ የወጣው 1440 ኪሎ ነው። አምስተኛ የወጣውም ብዛቱ ተመሳሳይ ነው።”
ቡናዎቹ ደረጃቸው ብቻ ሳይሆን ዋጋቸውም ጭምር ነው እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭነው።  አንደኛ የወጣው ቡና በኪሎ 330 ዶላር ነው የተሸጠው።
“ለጨረታ የቀረበው 1440 ኪሎው አይደለም። ለናሙናም ብዙ አገር ሲላክ፣ ዝግጅት ሲደረግም የሚወጣ ስላለ 1140 ኪሎ ብቻ ነው ለጨረታ የቀረበው። አንደኛ የወጣው ወደ 364 ሺህ ዶላር ነው የተሸጠው።”
አምስተኛ የወጣው ወደ 67 ሺህ ዶላር ተሸጧል።
“በአጠቃላይ ሁለቱም 431 ሺህ ዶላር ገደማ ነው የተሸጠው። አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ወደ 19 ሚሊየን ብር ማለት ነው” ታምሩ እንደገለጸው።
“ገዢዎቹ በጣም የተለየ ቡና ለመግዛት ነው የሚወዳደሩት”
ለምን ይሆን ቡናዎቹ በዚህን ያህል ዋጋ የሚሸጡት?
ይህ የቡና ግብይት መድረክ የተለየ ገበያ መሆኑን የሚገልጹት ወ/ት ቅድስት፤ “ሁሉም ቡና ግን በዚህ ዋጋ አይሸጥም” ይላሉ።
“ስፔሻሊቲም (ባለ ልዩ ጣዕም ቡና) እንደዚህ አይሸጥም። ይህ ውድድር ነው። ገዢዎቹ በጣም የተለየ ቡና ለመግዛት ነው የሚወዳደሩት። በዚያ ላይ ቡናው በአራት ደረጃ፣ በስምንት አገራት ተቀምሶ ስለተሸጠ በአንድ አምራች ሊሸጥ ሲሞከር አንድ አይደለም።” ሲሉ ያስረዳሉ፤ወ/ት ቅድስት፡፡
“ሌላው ካፕ ኦፈ ኤክሰለንስ ብዙ አባላት አሉት። እነሱ በሚያምኑት መንገድ ምንም መጭበርበር ሳይኖር የሚቀርብ ቡና ስለሆነም ነው በዚያ ዋጋ የሚሸጠው፡፡” ብለዋል።
የታምሩ ቡናስ ምን ቢሆን ነው እንደዚህ ተወዳጅና ተመራጭ የሆነው? ዋጋስ ያወጣለት?
“ቡናው ከሌላው ቡና የሚለየው፣ ከሚበቅልበት ቦታ ነው። አየሩ፣ ከአፈሩ ቡናው የሚያገኘው ሚኒራል አካባቢው ሁሉ ተደምሮ ልዩ ያደርገዋል። ከበቀለበት ቦታ እንጂ እኛ ያደረግነው ልዩ ነገር የለም። የቡናው ዝርያ ችግኙ 74158 እና 74165 የሚባል ዝርያ እኛ ጋ ብቻ አይደለም ያለው፤ ሌላም ቦታ አለ። በጣም ከፍታ ቦታ ላይ የሚበቅል ነው። ቦታው ነው ልዩ የሚያደርገው።” ብሏል፤ታምሩ፡፡
"ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በረከት ይዞ
እንደመጣ ቁጠረው"
ውድድሩ የአንድ ጊዜ ገንዘብ ማግኛ ብቻ አይደለም። ታምሩም ሁሌም ቡናውን በዚህ ዋጋ ይሸጣልም ማለት አይደለም።
“በውድድሩ መሳተፉ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ተቆጥሮም የሚያልቅ አይደለም። አንደኛውና ትልቁ ዕውቅናን ያቀዳጃል፡፡ ቡና ላይ ያለ ሰውና ገዢዎችን ለማወቅ ያግዛል። ለአገርም ለግለሰብም ትልቅ ጥቅም ነው የሚያመጣው። በዘርፉ ታዋቂ እንድትሆን ያደርጋል። ለዓለም ገበያ ኤክስፖርት እንዲኖርህ ያደርጋል። በገንዘብ ረገድም በጣም ይረዳል።”
“ጥሩ መነቃቃት ነው ለእኛ ካምፓኒ የፈጠረው። በኢትዮጵያ ደረጃም ካየነው ‘ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ’ ትልቅ ዕድል ነው ይዞ የመጣው። በረከት ይዞ እንደመጣ ቁጠረው። ለአገራችንም መነቃቃቱ ደስ የሚል ነው። ገበሬው ሁሉ ከፍ ያለ ዋጋ ነው የሚያገኘው። እንዲህ ነው ብለህ የምትጨርሰው አይደለም” ብሏል።
ጥቅሙ ታምሩ ከገለጸው ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም የሚሉት ወ/ት ቅድስት ናቸው።
“ሽልማቱም ለሁሉም ነው” ይላል፤ ታምሩ፡፡
“ውድደሩ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ ካለፈው ዓመት አሸናፊዎች እንዳየነው፣ አካባቢው በመተዋወቁ ከመደበኛው ዋጋ በላይ በሦስት እጥፍ እየሸጡ ነው። አንዱ አምራች ካሸነፈ በአካባቢው ሌሎችም ቡና አምራቾች ይጠቀማሉ።” ብለዋል፤ ወ/ት ቅድስት፡፡
ገንዘቡ ጠቀም ያለ ነውና ብሩን ምን ላይ ታውለዋለህ? ሲል ቢቢሲ ታምሩን ጠየቀ።
“ቡና ውስጥ ነው ያለሁት። 100 ፐርሰንት ኤክስፖርት አደርጋለሁ። የቡና ሥራዬን ሰፋ አድርጌ ለመሥራት ነው ዕቅዴ። በዚህ ብቻ ሳይሆን ከባንክም ጨምሬ ሰፋ አድርጌ ለመሥራት ነው የምፈልገው” ታምሩ መለሰ።
መቼም ውጤቱ የታምሩ ብቻ አይደለም። ብዙዎችም ተሳትፈዋል። “ሽልማቱም ለሁሉም ነው” የሚለውም ለዚህ ነው።
“ገበሬዎች አሉ፤ ቡና የሚያቀርቡ፡፡ እነሱ ላይ የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው እንደ ሽልማትም ለመስጠት አስበናል። እነሱንም ማበረታታት ነው። ቀጣይነት እንዲኖረው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ችግኝ በማቅረብ ምርታማነትን በመጨመር፣ ህይወታቸውን የሚያሻሽል ነገር በገንዘቡ ለመሥራት አስበናል።”
ታምሩ የአሁኑ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈበት ነው። ለዚህም ነው “በቀጣይ እወዳደራለሁ፤ ብዙ ቡና ላልሰጥ እችላለሁ ግን እወዳደራለሁ፤ በየዓመቱ ቡና እያዘጋጀሁ” ያለው፡፡  
“የቡና ሱሰኛ አይደለሁም”
ለመሆኑ ዘንድሮ ምርጥ ቡና ከኢትዮጵያ ማቅረብ የቻለው ታምሩ ቡና ይጠጣል?
ቡና ይጠጣል። ግን ካገኘ ነው። ሱሰኛ አይደለም። ካገኘ አራትም አምስትም ሲኒ በቀን ሊጠጣ ይችላል። ካጣ ደግሞ አንድም ላይጠጣ ይችላል። የጀበና ቡና ብዙም አይመስጠውም። ምክንያቱም ታምሩ ቡና መቅመስ ተምሯል። “በጣም ልምድ ባይኖረኝም እቀምሳለሁ” ሲል ራሱን ይገልጻል።
ቡና መቅመስ መቻሉ ደግሞ “ቡና ለመለየትም ለማድነቅም ጥሩ ነው” ይላል።
“የጀበና ቡና ብዙ ጊዜ ስለሚያር አልወደውም፡፡ በትክከል የሚፈላውን እጠጣለሁ፡፡” ብሏል።
እንደ መውጫ
ብዙዎቹ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ተጫራቾችና ገዢዎች ቡናን ከመቁላት ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ እሴት ጨምረው የሚሸጡ ናቸው። ሲሸጡም ‘ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ’ ብለው በከፍተኛ ዋጋ ነው የሚሸጡት። ሌሎች ደግሞ በጣም ትልልቅ የሆኑ ካፌዎች ውስጥ ይሸጣሉ።
“ባለፈው ዓመት አንደኛ [የሆነውን ቡና የገዛው] ለንደን ውስጥ በ65 ዶላር ነው አንድ ሲኒ የሸጠው። እሱም በማስታወቂያ ከዚህ እስከዚህ ቀን ተብሎ በግል ባሬስታ ነው የቀረበው” ብለዋል፤ ወ/ት ቅድስት።
“እነዚህ እንግዲህ ሃይ ኢንድ [ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ] ካፌዎች ናቸው። በጣም ውድ ውድድር ነው። ለብዙ ሰዎች የሚደርስ ሳይሆን የቅንጦት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም ነው ታምሩ፣ በቡና ዘርፍ የተሰማራችሁ ወገኖች፣ በውድድሩ ተሳተፉ የሚለው።
“እየተወዳደርኩ እቀጥላለሁ፡፡ መወዳደሩ ጥሩ ነው፤ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው። ሁሉም ቡና ላይ የተሠማራ ሰው መወዳደር አለበት ብዬ ነው የምመክረው” ብሏል።
ውድድሩ ለማንም ክፍት ነው፤ ቡና ላይ ለተሠማራ አምራችም ሆነ ወደ ውጪ ላኪ ለሆነ ነጋዴ።
መስፈርት ግን አለ። “ቡናው ትሬሰብል (ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ማስረጃ የሚቀርብበት) መሆን አለበት። በትክክል ቡናው የተመረተበትን ቦታ መረጃ እንፈልጋለን፤ የይዞታ ማረጋገጫ እንፈልጋለን። ይህን ማሟላት የሚችል መሳተፍ ይችላል” ብለዋል፤ ወ/ት ቅድስት።
እናም ለሚቀጥለው ዓመት ተዘጋጁ ተብላችኋል።
ምንጭ፡ (ቢቢሲ)




Read 8199 times
Administrator

Latest from Administrator