Sunday, 15 August 2021 00:00

ኢትዮጵያችን ታማለች፤ ሁለንተናዊ ህክምናም ትሻለች

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(0 votes)

ለበርካታ አስርተ ዓመታት ተጠናውቶን የቆየው አክራሪና አግላይ የፖለቲካ አስተሳሰብ በርካታ የለውጥ አጋጣሚዎችን አምክኖና የብዙዎችን ህይወት አሳጥቶን፣ ዛሬ ላለንበት እጅግ አሳሳቢና አስጨናቂ ሃገራዊ ሁኔታ አድርሶናል። ያለፉት ሰላሳ ዓመታት የሃገራችን ፖለቲካ ዋነኛው ተዋናይ የነበረው ‘ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ’ (ህወሃት)፣ ጽንፈኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲዊነትን ከአክራሪ ብሔረተኝነት ጋር አጣምሮ የሚያራምድ በመሆኑ፣ ትግል ላይ በነበረበት ወቅትም ሆነ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በርካታ ጥፋቶችንና በደሎችን ሲያደርስ ኖሯል። ይኸው አመለካከቱ ከ2010 በኋላ በሃገራችን ከተከሰተው የለውጥ ሂደት ጋር የሚያራምደው ባለመሆኑ፣ በርካታ አፍራሽ ተግባሮችን ሲፈጽም ቆይቶ፣ የጥፋቶች ሁሉ ጥፋት የሆነውን ጥቃት በጥቅምት ወር 2013 በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ፈፀመ። ይህ ጥቃት የደቀነው ሃገራዊ አደጋ መንግሥት በወሰደው የተቀናጀ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ባጭር ጊዜ ተቀልብሶ መስመር መያዝ ጀመረ ተብሎ ብዙም ሳንቆይ ሁኔታዎች ተገለባብጠው ባሁኑ ወቅት ሃገራችን በሌላ ከፍተኛ የህልውና ህመም እየተፈተነች ትገኛለች።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት የምትገኝበትን ሁኔታ ስንመለከት በተመሳሳይ ጊዜ፣ ተስፋ ሰጪ፣ አሳዛኝና አሳሳቢ ሆኖ እናገኘዋለን። ተስፋ ሰጭነቱ፣ ህወሃት ለሃያ ሰባት ዓመታት የደከመበት ኢትዮጵያዊነትን የመሸርሸር ጥረቱ ተፍረክርኮ ወጣቱና መላው የሃገሪቱ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለሀገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ዘብ ለመቆም ተነስቶ ከመታየቱ ይመነጫል። አሳዛኝነቱ፣ በአሁኑ ወቅት በየአቅጣጫው እየተካሄደ ያለው ውጊያ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በምትባለው ቤተሰብ ውስጥ የተከሰተ በመሆኑና በየትኛውም ወገን ላይ የሚደርሰው ጉዳት በአንድ ቤተሰብ ላይ የሚደርስ ጉዳት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሚፈጥረው ህመም ነው። አሳሳቢነቱ ደግሞ፣ ያለንበትን ሁኔታ ውስብስብነት ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ቁንጽልና ስሜታዊ እይታዎች ላይ ተመርኩዘው የሚሰጡ ትንተናዎችና የሚቀርቡ የመፍትሔ ሃሳቦች ለትውልድ የሚሸጋገር ተጨማሪ ቁስሎች እንዳይፈጥሩና ሃገሪቱን የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳያስገቡ ከሚል ስጋት ይመነጫል። የዚህ ጽሁፍ ዋነኛው ትኩረት፣ የስጋት ምንጭ የሆኑትን አሳሳቢ መገለጫዎች መመርመርና ተስፋዎቻችንን ሊያጎለብቱ የሚችሉ መነሻ ሃሳቦችን ማቅረብ ነው።
እንደማናቸውም የዘመናችን ቀውሶችና ጦርነቶች፣ የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ወርድ (dimension) ያለው መሆኑ አያከራርክርም። ነገር ግን፣ የነኚህ ውጫዊ ሁኔታዎች ተጽእኖ የሚወሰነው በሃገሪቱ ውስጣዊ መስተጋብርና ይዞታ በመሆኑ ዋነኛው ትኩረታችን በዚሁ ላይ ይሆናል። በዚህ ረገድ፣ የመጀመሪያው ትኩረት ሊሆን የሚገባው፣ እንዴት በህዳርና ታህሳስ ወራት የተመዘገቡት አስደናቂ ወታደራዊ ድሎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ተቀልብሰው ለሰኔ ወሩ ‘የጥሞና ማፈግፈግ’ ልንበቃ ቻልን የሚለው ነው። ይህንን ባግባቡ መመርመር ካንዱ ወደ ሌላው ጣት ለመጠቋቆም ሳይሆን መሰል ስህተቶችን ላለመድገም አስፈላጊ በመሆኑ ነው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ፣ ሚያዚያ 23 ቀን አዲስ አድማስ ላይ በታተመው ‘ውጊያውን አሸንፎ በጦርነቱ መሸነፍ እንዳይሆን’ በሚል ጽሁፉ፣ ወታደራዊ ድሉን ሁለንተናዊ  በሆነ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች ማጠናከር እንደሚገባ አሳስቦ ነበር። በአሁኑ ወቅት ህወሃትን እስከነ አካቴው ለማስወገድ የሚደረጉ ወታደራዊ ዝግጅቶችም ወቅቱን በሚመጥኑ በሳል ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ካልታጀቡ፣ ለዘመናት እያመረቀዘ የሚኖር ሃገራዊ ቁስል ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
የዚህ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን የሚገባው፣ ብዙኃኑን የትግራይ ህዝብ ለዘመናት የሰላም እጦትና ማለቂያ ለሌለው ቀውስ ካጋለጠው ህወሃት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል የፖለቲካ ሥራ መስራት ነው። እዚህ ላይ፣ ህግ በማስከበር ዘመቻው ወቅት እስከ አፍንጫው ታጥቆ የነበረውን ኃይል በሶስት ሳምንታት ውስጥ ድል በማድረጉ ሂደት የትግራይ ህዝብ ያሳየው ድጋፍ እንዴት በአጭር ወራት ውስጥ ሊገለበጥ ቻለ ብሎ መመርመር ያሻል። ለዚህ፣ እላይ ከተጠቀሰው መሰረታዊ ድክመት ባሻገር፣ ሁለት ዋነኛ ምንጮች እንዳሉ መገመት ይቻላል። የመጀመሪያው፣ የመልሶ ማጥቃት ድሉን ተከትሎ፣ በትግራይ ወገኖቻችን ላይ፣ በተለይም በሴቶችና እናቶች ላይ፤ የደረሱ በደሎች በፈጠሩት የመጠቃት ስሜቶች የተጎዳ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩ ነው። ሁለተኛውና ምናልባትም አብዛኛውን የትግራይ ማህበረሰብ የሚሸፍነው፣ ከህወሃት ልዩ ባህርይ ጋር በተያያዘ በትግራይ ህዝብ መሃል ለዓመታት በተፈጠረው የፍርሃት ቆፈን የታጠረ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩ ነው። የመጀመሪያውን በተመለከተ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች አጣርቶ ለህግ የማቅረቡ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የደረሰው በደል በደላችን፣ ጥቃቱም ጥቃታችን መሆኑን በመግለጽ፣ ለህዝቡ ሃዘናችንን በይፋ መግለጽና ሲያስፈልግም ይቅርታ መጠየቅ ይገባል። ይህንን ማድረግ መንፈሳዊ ስብራት የደረሰበትን የህብረተሰብ ክፍል ከማከሙም በላይ የመንግሥትንም ሆነ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብን ሆደ ሰፊነትና ታላቅነት ያሳያል።
ሁለተኛውን በተመለከተ፣ ጭፍን ከሆነ የጅምላ ፍረጃና ውንጀላ በመቆጠብ ሁሉም ፖለቲከኞቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ ልሂቃኖቻችን፤ የሚዲያ ባለሙያዎችና ማህበራዊ አንቂዎች የትግራይ ህዝብ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ አካል መሆኑን ሳይታክቱ መግለጽና ከህዝቡ ጎን መቆማችንን ደጋግመን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የዚህ ጥረት ግቡም፣ ከህወሃት ህልፈት በኋላ የሠላም፣ ፍትህ፣ ነፃነትና ልማት አማራጭ ለትግራይ ህዝብ መኖሩን ማሳየት ሊሆን ይገባዋል። እነኚህን ሁለት እርምጃዎች ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በተለይም ብልፅግና እና የትግራይ ህዝብን እንወክላለን ብለው የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር ቀደም ድርሻ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ እጅግ አስጨናቂ በሆነው የህወሃት ድርጅታዊ ጥርነፋ እግር ከወርች የተያዘውን የትግራይ ህዝብ ነፃ በማውጣት ድርጅቱ በትግራይ ህዝብ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ መሰረት መሸርሸር ይቻላል። ይህ ቀዳሚ ተግባር በሚገባ ከተከናወነ የጥፋት ቡድኑን በወታደራዊ ዘመቻ ለማስወገድ የሚከፈለውን የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት በእጅጉ ከመቀነስም በላይ የሚገኙ ድሎችን ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ማናቸውም መሰል ሃገራዊ የፖለቲካ ቀውስ በመጨረሻ በዘላቂነት መቋጫ ሊያገኝ የሚችለው ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታች በሆነ ውይይትና ድርድር ብቻ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ይህን በተመለከተ፣ በደፈናው አንደራደርም ከማለት ይልቅ፣ መንግሥት ከህወሃት በመለስ የትግራይ ህዝብን ከሚወክሉ ማናቸውም ወገኖች ጋር በግልጽነት ለመደራደር ዝግጁነቱን በአጽንኦት ማሳወቅና ለተግባራዊነቱም መትጋት ይኖርበታል።
እነኚህ ጥረቶች ተደርገውም፣ ለዘመናት ባመኑበት ጽንፈኛ የአብዮታዊ ዲሞክራሲና አክራሪ ብሔረተኝነት ርዕዮት የተነሳና በወንጀል ድርጊቶቻቸው እንጠየቃለን በማለት እስከ ሲዖል ለመዝለቅ የተዘጋጁ የህወሃት አመራሮች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። እነኚህ ቡድኖች የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ራሳቸውን ለህግ ለማስገዛት አስካልወሰኑ ድረስ በወታደራዊ ዘመቻ የማስወገዱ አማራጭ የማይቀር ይሆናል። ነገር ግን፣ የሚወጣው ወታደራዊ ዕቅድ በህወሃት እኩይ ወጥመድ እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ አሳሳቢውና አደገኛው፣ ጦርነቱን በህዝቦች መካከል ወደሚካሄድ የዕርስ በዕርስ ጦርነት ለማሸጋገር የሚያደርጉት ተከታታይ ጥረት ነው። አንዳንድ የሃገራችን ፖለቲከኞችና የሚዲያ ተንታኞች፣ የዚህ ወጥመድ ሰለባ ሲሆኑ እና መሰል አካሄዶችን ሲያስተጋቡ መሰማቱ በጣም ያሳስባል። ከዚህ አኳያ፣ በመንግሥት ሊካሄድ የሚታሰበው የመልሶ ማጥቃት ውጊያ በተለመደው የመደበኛ ውጊያ ስልት ከመመራት ይልቅ በተቀናጀ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተመርኩዞ፣ በቅድሚያ በሽታው ወደ አጎራባች ክልሎች እንዳይዛመት ለመግታት (containment) እና በማስከተልም መርዘኛ የአመራር ማዕከሉን ነጥሎ መምታት የሚያስችል (surgical) የውጊያ ስልት ሊሆን ይገባዋል። እንዲህ ዓይነቱ የውጊያ ስልት፣ በህወሃት የተዘረጋውን ወጥመድ ከማክሸፍም በላይ በሰላማዊ ህዝብና በመከላከያ ሃይሉ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው፣ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ልዩ ቀጠናዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ክልል የተነሳ ሃገራዊው ፈተናችን ጠንካራ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ወርድ እንዲይዝ አድርጎታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ አሜሪካና ምዕራባዊያን ሃገራት በተለምዶ በሚከተሉት ቁንጽልና እብሪት የተመላበት ምልከታና ጣልቃ ገብነት የተነሳ ችግሩ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ መጥቷል። ህወሃት እና ደጋፊዎቹ ይህንን አጋጣሚ በሚገባ በመጠቀማቸውና ለነኚህ የውጭ ፍላጎቶች መሳሪያም በመሆናቸው የመረጃና ዲፕሎማሲ ጦርነቱን በቀዳሚነት ሊመሩት ችለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ እየተነቃቃ ባለው የመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የተጠናከረ አስተዋጽኦ ሁኔታዎች በመጠኑ እየተቀየሩ መጥተዋል። ነገር ግን፣ አሁንም በርካታ ፈተናዎች ያሉ በመሆናቸው ጥረቱ በይበልጥ ተጠናክሮና በዕውቀት ታግዞ መቀጠል ይኖርበታል። በዚህ ረገድ፣ ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫችን ዓለም አቀፋዊ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ፣ ሃገራዊ ሉዓላዊነታችንን የሚዳፈሩ ማንኛቸውንም ሙከራዎች በዕንጭጩ መቅጨትና ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያለንን ግንኙነት በፓን አፍሪካዊ ዲፕሎማሲ መንፈስ ማጠናከር ቢሆን ጠቃሚ ይሆናል። እንደ ምሳሌም፣ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገር መሪዎች ጋር የተደረገው ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በቅርቡ የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ያሳዩትን አጉራ ዘለል አካሄድ መንግሥት ያስተናገደበት ብስለት የተመላበት መንገድ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ተመሳሳይ ብስለትና ብልሃት የታከለበት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ዙሪያ ማካሄድ፣ ግብፅ በቀጠናው ያላትን ተጽእኖ ለመቀነስና ሃገራዊ መረጋጋቱን ለማጠናከር ያግዛል።   
በመጨረሻም፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት የተጋረጠባትን ከባድ የህልውን ፈተና መሻገሯ የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህ ፈተና ባሻገር ግን፣ መሰረታዊ ህመሟን ለመፈወስና ሌሎች መሰል ፖለቲካዊ ፈተናዎች በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች እንዳያጋጥሙን ለማድረግ፣ በወደፊቱ የሃገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባትን የሚፈጥር አካታችና አሳታፊ የሆነ ሃገራዊ ውይይት ማካሄድ ያስፈልጋል። ይህ ሂደት ውጤታማ እንዲሆንም፣ ከጦርነትና ግጭት በመለስ ማንኛውም ዐይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ በነጻነት እንዲንሸራሸር ማድረግ አስፈላጊና ተገቢም ነው። በምርጫው ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ሃገራዊ ውይይት እንደሚካሄድና የሚቋቋመውም መንግሥት ተቃዋሚዎችን የሚያካትት እንደሚሆን የገቡት ቃል ትልቅ ተስፋን የሚሰጥና ለሁለንተናዊው ፈውስም የሚረዳ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃኑ፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ መሪዎችና ዳያስፖራው በዕውቀትና አስተውሎት ላይ የተመረኮዘ ግብዓት በመስጠትና በመቀበል የሁለንተናዊ መፍትሄው አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚም አባል ናቸው።               Read 2500 times